አንድ ሺህ ዶላር በየወሩ ለእያንዳንዱ ዜጋ፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ተፎካካሪ

ታትሟል

አንድሪው ያንግ ይባል፤ በመጪው ኣመት ለሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቧል። ሰውዬው በቴክኖሎጂ ምርምሮች ላይ ገንዘቡን ፈሰስ የሚያደርግ የ44 ዓመት ሚሊየነር ነው።

የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተፎካካሪው አንድሪው ያንግ ለዶናልድ ትራምፕ ትክክለኛው ማርከሻ ''በሂሳብ ጎበዝ የሆነ ከእስያ የመጣ ሰው ነው'' በሚለው ንግግሩ ታዋቂነትን ማትረፍ ችሏል።

ከዚህ ባለፈም ምንም ግዳጅ በማይኖረው መልኩ ለእያንዳንዱ ከ18 ዓመት በላይ ለሆነ አሜሪካዊ በየወሩ 1000 ዶላር እቆርጥለታለሁ የሚለው አንድሪው፤ ገና ካሁኑ ብዙ ተከታዮችን እያገኘ ነው።

በፖለቲካው ዓለም ብዙም እውቅና የሌለው ይህ ሰው በበይነ መረብ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን የሚከታተሉና ከልባቸው የሚደግፉት ብዙ ሺህ ተከታዮች አሉት።

አንድሪው እንደሚለው አሁን ባለው የቴክኖሎጂ እድገት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብዙ አሜሪካዊያን ሥራቸውን በሰው ሰራሽ ማሽኖች አልያም ሮቦቶች ሊነጠቁ ስለሚችሉ በየወሩ የሚቆረጥላቸው አንድ ሺህ ዶላር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግሯል።

ምንም እንኳን በቅስቀሳ ንግግሮቹ ወቅት ሌሎች ተፎካካሪዎች በሃሳቡ ላይ ቢሳለቁም "ሂሳቡን ቀድሜ በደንብ ሰርቼዋለው፤ ከልባችን ከሠራን ይህንን ማሳካት አይከብደንም" ብሏል አንድሪው።

እስካሁን ባደረጋቸው ቅስቀሳ ዝግጅቶች ከአጠቃላይ መራጮች 3 በመቶ የሚሆኑትን ድጋፍ ያገኘው አንድሪው ከፊቱ ያሉት ፖለቲከኞች ጋር ለመድረስ እጅግ በጣም ብዙ ይቀረዋል።

ነገር ግን ብዙ ልምድ አላቸው ከሚባሉት ሴናተሮች ኮሪ ቡከር እና ኤሚ ክሎቡቻር የተሻለ ድጋፍ ማግኘቱ ደግሞ ተስፋ ሊኖረው እንደሚችል ብዙዎች እንዲገምቱ አስገድዷል።

አንድሪው የምረጡኝ ቅስቀሳውን ሲያደርግ ዝግጅቱን ለመታደም ከ3 ሰዓታት በላይ ተጉዛ የመጣችው የ18 ዓመቷ ኤሚሊ ሲይኖስኪ እንደምትለው፤ ከዚህ በኋላ ትኩረት መሆን ያለበት ወደፊቱ ላይ ነው።

እሷ እና በበእሷ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በሙሉ ድጋፋቸውን ለአንድሪው የሚያደርጉት እርሱ ቴክኖሎጂና ሥራ ፈጠራ ወደፊት ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ቀድሞ ስለተረዳ ነው ስትል አስተያየቷን ለቢቢሲ ሰጥታለች።

ከቅስቀሳ ንግግሩ በኋላ አንድሪው ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተፎካከሩ ከሚገኙት መካከል ከፍተኛውን የትዊተር ተከታይ ማግነት ችሏል።

አንድሪው ከወጣቶች በተጨማሪ ብዙም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ሆን ውክልና የሌላቸው የእስያ ተወላጆችን ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘት ችሏል።

ከታይዋን ስደተኛ ቤተሰቦች የተገኘው አንድሪው ያንግ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከምሥራቅ እስያ መጥቶ የተፎካከረ የመጀመሪያው ተወዳዳሪ ነው።