በስፔን «በሬ ሰዶ የማሳደድ ፌስቲቫል» የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታትሟል
በመካከለኛ ስፔን የበሬ ፌስቲቫል የ62 ዓመት ሰው በቀንድ ተወግቶ ሕይወቱ አልፋለች።
የከተማዋ ከንቲባ ካርሎስ ፍሬይል ለአገሬው ጋዜጠኞች እንደተናገሩት ግለሰቡ ደረቱ ላይ እንደገናም ደግሞ አንገቱ ሥር የተቆጣ በሬ ክፉኛ ስለወጋው ማዳን አልተቻለም።
ዜናውን ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገው ሟች በሬ ሰዶ በማሳደዱ ፌስቲቫል ላይ ተመልካች እንጂ ተሳታፊ አልነበረም።
በሬው መጀመርያ ለመውጋት አስቦ ሲያሳድደው የነበረው ሰው ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ ማምለጥ ሲችል በሬው ቁጣው አልበርድ ስላለ ይህን ግለሰብ ወግቶታል። ግለሰቡ ለማምለጥ ምን ዓይነት መፈናፈኛ በማጣቱ ነው ለሞት የተዳረገው።
በስፔን የበጋ ወራት «በሬን ሰዶ የማሳደድ» ጨዋታ እጅግ የሚወደድ ሲሆን በየዓመቱ ተመሳሳይ አደጋ ማጋጠሙ የተለመደ ነው።
በዚህ ዓመት ብቻ ፓፕፕሎና ውስጥ በፈርሚን ፌስቲቫል 35 ሰዎች በሬ ወግቷቸው አንዳች ጉዳት ደርሶባቸዋል።












