ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአልጄሪያ ራፕ ኮንሰርት ላይ በተከሰተ መረጋገጥ አምስት ሰዎች ሞቱ
በአልጄርያ መዲና አልጄርስ ራፕ ኮንሰርት ላይ በነበረ መረጋገጥ አምስት ሰዎች ሞቱ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አብደራፍ ዴራጂ ወይም ሱልኪንግ ተብሎ የሚጠራውን ራፐር ኮንሰርት ለመታደም የተገኙ ሲሆን በአንደኛው መግቢያ ላይ በነበረ መጨናነቅ መረጋገጥ ተፈጥሮ እንደሞቱ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ 21 ሰዎችም ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ለህክምናም ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሃገሪቱ ሚዲያዎች የህክምና ምንጮችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።
ግለሰቦቹ በመሞታቸው ኮንሰርቱ ያልተቋረጠ ሲሆን በአልጀሪያ ቴሌቪዥንም በቀጥታ ተላልፏል።
የሃገሪቱ የዜና ምንጭ ቲኤስኤ እንደዘገበው ከሟቾቹ ውስጥ ሶስት ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ነው።
ከኮንሰርቱ ወጡ የተባሉ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደሚያሳዩት የህክምና ሰራተኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ታዳሚዎች በቃሬዛ ከስታዲየሙ ተሸክመዋቸው ሲወጡ ነው።
ኮንሰርቱ ላይ የነበረችው ጋዜጠኛ ሊንዳ ቸባህ ለቢቢሲ ኒውስደይ እንደተናገረችው ከጅምሩ አንስቶ የሆነ ችግር እንዳለ ያስታውቅ ነበር ብላለች።
"ስታዲየሙ ከሚችለው በላይ ህዝብ ታጭቆ ነበር፤ ታዳሚዎች መረማመጃም ሆነ መተንፈሻ አጥተው ነው። እንዲህ በነበረበት ሁኔታ እንዲህ አይነት አደጋ ማጋጠሙ አልገረመኝም" ብላለች።
አልጄሪያዊው ራፐር ሱልኪንግ ስለ ደረሰው አደጋ ምንም አስተያየት አልሰጠም።