ኢራን በባህረ ሰላጤ 'ህገወጥ' የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ መያዟ ተገለፀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን የእንግሊዝን ባንዲራ የምታውለበልብ የነዳጅ መርከብ ማገቷ "ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ገልፀውታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ኢራን በባህረ ሰላጤ ህገወጥ ነው ያለችውን የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ መያዟን የኃገሪቱ ሚዲያ አስታውቋል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ኮማንደር በባህረሰላጤው በኩል ለአረብ ኃገራት በህገወጥ መንገድ ነዳጅ ዘይት ሊያስገባ ሲል መያዛቸውን መግለፃቸውን የኃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

መርከቧ ከ700 ሺ በላይ ሊትር ነዳጅ ዘይት ስትንቀሳቀስ እንደነበርና ሰባት የመርከቧ ሰራተኞች አብረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ኢራን በህገወጥ መንገድ የነዳጅ ዘይት ይዣለሁ ስትል ይህ ሁለተኛው ነው፤ ከሳምንታት በፊትም የኢራን የባህር ጠረፍ ጠባቂ የፓናማ ሰንደቅ አላማ የነበራትን መርከብ አግተው ነበር።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ በድረገፁ እንዳሳወቀው በወቅቱ መርከቧ የተያዘችው የባህር ኃይሉ የተደራጀ ህገወጥ የነዳጅ ዘይት ዝውውርን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ነው።

ባለፈው ወርም የእንግሊዝ ባንዲራን ታውለበልብ የነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሃርሙዝ ስርጥ የውሃ ክልል ላይ እንደታገተች ነው።

አሜሪካ እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2015 በሁለቱ ኃገራት የተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት ራሷን ካገለለች በኋላ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ በባህረ ሰላጤው አካባቢ ውጥረት መንገሱ ተገልጿል።

በአማን ባህረ ሰላጤ ለተፈፀሙ ሁለት የተለያዩ የነዳጅ መርከብ ጥቃቶች አሜሪካ ኢራንን መወንጀሏ የሚታወስ ነው።

በሃርሙዝ የቀጠና የበረራ ቅኝት ላይ የነበረ ሰው አልባ የአሜሪካ አውሮፕላን መትታ የጣለችው ኢራን በበኩሏ ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።

እስካሁን ድረስ ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ባለቤትነት ያልታወቀ ሲሆን የፋርስ ዜና ወኪል እንደዘገበው መርከቧን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ የተከናወነው ባለፈው ረቡዕ እለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የመርከቧ ሰራተኞች ዜግነታቸው ግልፅ አልተደረገም።

ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ቡሸህር የሚባል ቦታ የተወሰደች ሲሆን ነዳጁም ለባለስልጣናቱ እንደተላለፈም ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል።

ከየትኛውም ኃገርም መርከቤ ጠፍቶብኛል ወይም ታግቶብኛል የሚል መግለጫም እንዳልወጣም ተገልጿል።

የቢቢሲ አረብኛው ኤዲተር ሰባስቲያን የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ምንም እንኳን ትልቅ ባትሆንም በቀጠናው ያለውን ውጥረት ሊያባብሰው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።