በሱዳን ከታሰበው ሕዝባዊ ተቃውሞ በፊት የፀጥታ ኃይሎች 'አሰሳ' እያደረጉ ነው ተብሏል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳን መንግሥት አገዛዝ ተቃዋሚ የሆነ አንድ ቡድን፤ ሊካሄድ ከታሰበው ሕዝባዊ ተቃውሞ በፊት የፀጥታ ኃይሎች አሰሳ እያደረጉ ነው ሲል ከሷል።
'ሚሊዮን ስትሮንግ ማርች' የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወታደራዊው መንግሕት ለሲቪል ሥልጣኑን አሳልፎ አለመስጠቱን ተከትሎ የሚደረግ ሰልፍ ነው ተብሏል።
'ሱዳኒዝ ፕሮፌሽናል አሶሲዬሽን' የተባለው ተቃዋሚ ማሕበር የወታደራዊው አገዛዙን 'ጨቋኝ ባህርይ' አለው ሲል ወቅሷል።
ምንም እንኳ የፀጥታ ኃይሎች አሰሳ እያደረጉ ነው ሲል ቢወቅስም ሕዝባዊ ሰልፉ ዕሁድ እንደሚካሄድ ማሕበሩ አሳውቋል።
በርካቶች የካርቱም ነዋሪዎች ከተገደሉበት የወርሃ ሰኔው ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ የሰው ማዕበል ሊታይበት ይችላል ተብሎለታል የዛሬው የሱዳን ተቃውሞ።
ተቃውሞውን የሚመሩት አሕመድ አል-ራቢ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዜና ወኪል በሰጡት ቃል የመንግሥት ወታደሮች ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳንሰጥ አድርገዋል ሲሉ ኮንነዋል።
«የነፃነት ገፈፋው ከአል-በሽር አገዛዝም የከፋ ነው» ሲሉ ለዜና ወኪሉ ሃሳባቸውን የሰጡት።
ወታደራዊው ኃይል ሕዝባዊ ተቃውሞው ላይ አንዳች የንብረት ውድመት ወይም ነፍስ መጥፋት ቢያጋጥም 'ከተቃዋሚው ማሕበር ራስ አልወርድም' ሲል አስጠንቅቋል።
ሃመቲ በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት የወታደራዊ አስተዳደሩ ገዥ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ሕዝባዊው ተቃውሞውን ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉ የሚችሉ ይኖራሉ ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ሆነ የአፍሪቃ ሕብረት ወታደራዊውን አገዛዝ እና ተቃዋሚውን ጎራ ለማስታረቅ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።













