የማዳበሪያ ፋብሪካው ፍንዳታ በርካቶችን ገደለ

በአደጋው የተጎዱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በምሥራቃዊ ቻይና በአንድ የኬሚካል ፋብሪካ ላይ በደረሰ ከባድ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 44 ሲደርስ የቆሰሉት ደግሞ 640 መድረሱን መንግሥታዊው የዜና ወኪል ዠንዋ ዘገበ።

ከባዱ ፍንዳታ ማዳበሪያ በሚያመርተው ፋብሪካ ላይ የተነሳውን እሳት ተከትሎ ነው የተከሰተው።

በቻይና የሚከሰቱ ርዕደ መሬቶችን የሚከታተለው ተቋም እንዳለው በፍንዳተው ወቅት 2.2 መጠን ያለው መንቀጥቀጥ እንደተመዘገበ አመልክቷል።

ቲያንጂያይ ኬሚካል በተባለ ድርጅት በሚተዳደረው ያንቼንግ የማዳበሪያ ፋብሪካ ውስጥ የተከሰተው አደጋ፤ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በቻይና በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት የከፋው እንደሚያደርገውም ተነግሯል።

የዜና ወኪሉ እንደዘገበው ከሞቱት ባሻገር በአጠቃላይ 640 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ከመካከላቸውም 32ቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ 58ቱ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከአደጋው ከባድነት የተነሳ ፍንዳታው ከፋብሪካው በርቀት ላይ የሚገኙ የሌሎች ፋብሪካዎች ሕንፃዎች ላይ የመደርመስ ጉዳት ማድረሱን ሠራተኞችን መውጫ እንዳሳጣ ቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አደጋው ከደረሰበት ሦስት ኪሎ ሜትሮች እርቆ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራ ሰው እንደተናገረው በፍንዳታው ሳቢያ የሕንፃው ጣራ ሲደረመስ በሮችና መስኮቶች ተሰባብረዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት እንደተናገሩት እሳቱን ለማጥፋት ከሌሎች አካባቢዎች ተጫማሪ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንዲመጡ ተደርጓል።

አስፈላጊ የደህንነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ ስለማይደረጉ ቻይና ውስጥ በማዕድን ማውጫዎችና በፋብሪካዎች ላይ ተደጋጋሚ አደጋዎች ያጋጥማሉ።

በዚህ ፋብሪካ ላይ ላጋጠመው ቃጠሎና ፍንዳታ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል። አንድ የሃገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው ከ12 ዓመታት በፊት የተቋቋመው ይህ ፋብሪካ በቆሻሻ አያያዙ እና ባስከተለው የአየር ብክለት ምክንያት ስድስት ጊዜ በመንግሥት ቅጣት ተጥሎበታል።