የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ። ይህ የተባለው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር አየተደረገ ባለው ግጭት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየቀረቡ ያሉትን ጥሪዎች ውድቀ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኔታንያሁ ሐማስ የለቀቀውን የታጋቾች ቪድዮ “ጭካኔ የተሞላ የሥነ ልቦና ፕሮፓጋንዳ” አሉት

    ቤንያሚን ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሐማስ የተለቀቀው ታጋቾችን የሚያሳይ ቪድዮ “ጭካኔ የተሞላበት ሥነ ልቦና ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ነው” በማለት አወገዙ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጣቸውን የገለጹት ጋዛ ውስጥ ተይዘው የሚገኙ ሦስት ታጋቾችን የሚያሳይ ቪድዮ በሐማስ መለቀቁን ተከትሎ ነው።

    ኔታኒያሁ የታጋቾቹን ስም በመጥራትም መልዕክት አስተላልፈዋል። “የጦር ወንጀል በሚፈጽመው ሐማስ የታገታችሁት ኤሌና ትሩፓኖቭ፣ ዳንኤል አሎኒ እና ሪሞን ኪርሽት አቅፌያችኋለሁ” ብለዋል።

    ከአንድ ደቂቃ ትንሽ በሚረዝመው እና ቢቢሲ በማያጋራው ቪድዮ ላይ፣ ሦስቱ ታጋቾች ግድግዳ ጥግ ተቀምጠው ወደ ካሜራ እያዩ ሲናገሩ ይታያል።

    ሐማስ ከሦስት ሳምንት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ጊዜ ከ230 በላይ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱን የእስራኤል መንግሥት አስታውቋል።

    ባለፈው ሳምንት የተወሰኑ ሰዎችን በቀይ መስቀል በኩል የለቀቀ ሲሆን፣ የቀሩትን ለመልቀቅ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ዘመቻ እንድታቆም ጠይቋል።

  2. የእስራኤል እግረኛ ጦር ጥቃት ወደ ጋዛ ማዕከላዊ ክፍል እየገፋ መሆኑ ተነገረ

    የእስራኤል ታንክ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ሠራዊት የሚፈጽመው ጥቃት ወደ ጋዛ ማዕከላዊ ክፍል ዘልቆ እየገባ ሲሆን፣ ታንኮቹም በጋዛ ቁልፍ መንገዶች ላይ መታየታቸው ተዘገበ።

    በጋዛ ሰርጥ ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚወስደው ዋና አውራ ጎዳና ላይ የእስራኤል ታንኮች ታይተዋል።

    ይህም ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ወደ ጋዛ ዘልቀው የገቡት የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች በአሁኑ ጊዜ የበለጠ ወደ ጋዛ ከተማ መጠጋት መጀመራቸውን ያሳያል።

    ወደ ጋዛ እየተጓዘ የነበረ መኪና ላይ የእስራኤል ታንክ እንደተኮሰበት የተዘገበ ሲሆን፣ በዋዲ ጋዛ ደቡብ በኩል የእስራኤል ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ጎዳና ላይ መታየቱ ነው።

    ይህ ዋዲ ጋዛ የሚባለው ቦታ የእስራኤል መከላከያ ኃይል የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ እንዲወጡ ካስጠነቀቀ በኋላ የሚጓጓዙበት መስመር ነው።

    የእስራኤል ኃይሎች ጋዛ ከተማ ላይ አነጣጥረው ዘመቻቸውን አጠናክረው እየቀጠሉ ነው።

    አሁንም ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በፍርሃት እና ቤታቸውን ለቀው ላለመውጣት በመወሰን በሰሜናዊ የጋዛ ክፍል ለመቆየት መርጠዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ግን መስመሩን ሙሉ በሙሉ ሊቆርጠው ይችላል።

    ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚወስዱት ሁለት መንገዶች ብቻ ናቸው። አንደኛው ዛሬ ታንክ የታየበት ሳላህ-አል-ዲን የሚባለው ዋነኛ መንገድ ነው።

    ሁለተኛው አነስተኛ መንገድ በባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ያለ ሲሆን የእስራኤል የጦር መርከብ ዒላማ ያደረገው ነው።

    ዋዲ ጋዛ ከጋዛ ያነሰ ሰው ነው የሚኖርበት። እስራኤል የጋዛ ሰርጥን ለሁለት ለመክፈል የምትጠቀመው ይህንን ቦታ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

  3. በመቶዎች የሚቆጠሩ ህሙማን በሆስፒታል ውስጥ ናቸው፤ መውጣትም አይችሉም- ተመድ

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በአል ቁድስ ሆስፒታል የተገኘ በሚል ይህንን ፎቶ አጋርቷል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በአል ቁድስ ሆስፒታል የተገኘ በሚል ይህንን ፎቶ አጋርቷል

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች በሰሜን ጋዛ በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ በመሆናቸው ወደ ደቡብ ጋዛ መሸሽ አልቻሉም ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ተናግሩ።

    የድርጅቱ ባልደረባ የሆኑት ቶም ዋይት በሰሜን ጋዛ ከሚገኙት እንደ አል ቁድስ ካሉ ሆስፒታሎች፤ ህሙማንን ማንቀሳቀስ አይቻልም ሲሉ ዶክተሮች እና ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች የተናገሩትን ስጋት አስተጋብተዋል።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ እንደገለፀው እስራኤል ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ አዛለች። የሆስፒታሉ አካባቢ የአየር ደብደባ ዒላማ መሆኑም ተጠቅሷል።

    "በሰሜን ጋዛ ያሉ ብዙ ሰዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች መጠለል ይፈልጋሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ህመምተኞች እና መንቀሳቀስ የማይችሉ ህሙማን በአንዱ ሆስፒታል ይገኛሉ" ሲሉ ዋይት ተናግረዋል።

    በሰሜን ጋዛ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችም "አቅም ስለሌላቸው መንቀሳቀስ አይችሉም" ብለዋል።

    ሰዎቹ "በጣም ተርበዋል፣ በጣም ተጠምተዋል እንዲሁም በጣም ፈርተዋል" ብዙዎች በዳቦ እና "እኛ ስንችል በምንሰጠቻው የታሸጉ ምግቦች እየኖሩ ነው” ብለዋል።

  4. የእስራኤል ጦር ከሰሜን ወደ ደቡብ ጋዛ የሚወስደውን ቁልፍ መንገድ መዝጋቱን የዐይን እማኞች ተናገሩ

    እስራኤል ጦር ወደ ጋዛ በመግባት በታንክ እና በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከሰሜን ወደ ደቡብ የጋዛ ሰርጥ የሚወስደውን ቁልፍ መንገድ መዝጋታቸውን ፍልስጤማዊያን የዐይን እማኞች ተናገሩ።

    ታንኮቹ በካርኒ-ኔትዛሪም አቅራቢያ በሚገኘው ሳላ-አል-ዲን መንገድ ላይ መሆናቸው ተነግሯል። ይህም በግዛቲቱ ትልቁ ከተማ ላይ የሚደረገው ዘመቻ አካል ሊሆን ይችላል የሚል ግምትን ፈጥሯል።

    በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አንድ ቪዲዮ እየተሰራጨ ይገኛል። በቪዲዮው አንድ መኪና ወደ ታንክ ተጠግቶ ለመታጠፍ ሲሞክር ተኩስ ተከፍቶበት ተሽከርካሪው ሲወድም ያሳያል።

    አንድ ግለሰብ “እሱም፣ መላው ቤተሰቡም አልቀዋል” እያለ በፍጥነት ሌሎች መኪኖች ዞረው እንዲመለሱ ሲነገር ይደመጣል።

    የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት በጋዛ የእግረኛ ጦር ዘመቻውን ማስፋፋቱን አስታውቋል። ጦሩ “በደርዘን የሚቆጠሩ አሸባሪዎችን በተሳካ ሁኔታ ማጥፋት ችያለሁ” ብሏል።

    ጦሩ በጋዛ የትኛው ክፍል እንደሚገኝ ከማሳወቅ ተቆጥቧል።

    በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ “ለፀጥታ ኃይሎቻችን ቅድሚያ እንሰጣል” ብለዋል።

    "በጋዛ ሰርጥ የትጥቅ እና የእግረኛ ክፍላችንን በማሳተፍ ዘመቻችንን አስፋፍተናል" ብለዋል።

    ሃጋሪ ስለ ዘመቻው አጠቃላይ ሁኔታ ሲናገሩም፤ የምድር እና የአየር ጥቃት ለመሰንዘር ወደ ጋዛ ተጨማሪ “እግረኛ ወታደሮችን፣ ታንኮችን እና የመድፍ ኃይልን” እንደሚልኩ ተናግረዋል።

  5. እስራኤል ሌሊቱን ባካሄደችው ጥቃት በርካታ የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሏን ገለጸች

    በአየር ጥቃት የወደመ የጋዛ ሰርጥ አካባቢ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በአየር ጥቃት የወደመ የጋዛ ሰርጥ አካባቢ

    ካለፈው አርብ ጀምራ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የምታካሂደውን ዘመቻ በማስፋት እግረኛ ሠራዊቷን ያሰማራችው እስራኤል በርካታ የሐማስ ተዋጊዎችን መግደሏን ገልጻለች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል “ሠራዊቱ ጋዛ ውስጥ በሕንጻዎች እና በዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ ወታደሮቻችንን ለማጥቃት ከሞከሩ አሸባሪዎች ጋር በተካሄደ ግጭት ብዙዎቹ ተገድለዋል” ብሏል።

    የጦር ሠራዊቱ በመግለጫው ላይ በአንድ ጥቃት መሬት ላይ ባሉ የእስራኤል ወታደሮች ጠቋሚነት “ከ20 በላይ የሐማስ አሸባሪ ተዋጊዎች በውስጡ ነበሩበት” ባለው ሕንጻ ላይ በጦር አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    በተጨማሪም አል-አህዛር ከተባለው ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ ፀረ ታንክ ሚሳኤል የሚወነጨፍበት ወታደራዊ ኬላ በጦር አውሮፕላን መመታቱን አመልክቷል።

    እሁድ ሌሊት ጋዛ ውስጥ ከባድ የአየር ድብደባ ሲያካሂድ ያደረገው የእስራኤል አየር ኃይል ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 600 ኢላማዎችን ጋዛ ውስጥ መምታቱን ሰኞ ጠዋት ገልጿል።

    እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ጋዛ አስገብታ ጥቃት እያካሄደች በላበት በአሁኑ ወቅት የአየር ድብደባውም ቀጥሏል። በዚህም ሠራዊቱ ሐኪሞች ለቀው እንዲወጡ ካዘዘበት የአል-ቁዱስ ሆስፒታል አቅራቢያ የአየር ድብደባ እየተካሄደ መሆኑን የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር አስታውቋል።

  6. ሒዝቦላህ የእስራኤልን ድሮን መትቶ መጣሉን አስታወቀ

    በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአስራኤል ጥቃት የተገደለ የሒዝቦላህ አዛዥ ቀበር ላይ የተገኙ የቡድኑ ተዋጊዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአስራኤል ጥቃት የተገደለ የሒዝቦላህ አዛዥ ቀበር ላይ የተገኙ የቡድኑ ተዋጊዎች

    በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኘው ታጣቂ ቡድን ሒዝቦላህ አንድ የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መትቶ መጣሉን አስታወቀ።

    ይህም በአካባቢው ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሒዝቦላህ እንዲህ አይነቱን እርምጃ መውሰዱን ሲገልጽ የመጀመሪያው ነው።

    ሒዝቦላህ እንዳለው ድሮኑ የተመታው ሊባኖስ ከእስራኤል ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አካባቢ ኻይም በተባለ ስፍራ እሁድ ዕለት ነው። የተመታው ድሮንም በእስራኤል ግዛት ውስጥ ሲወድቅ መታየቱን ገልጿል።

    በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም በሽብርተኛ ቡድንነት የተፈረጀው ሒዝቦላህ፣ ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለፉት ሦስት ሳምንታት 46 ተዋጊዎቹ እንደተገደሉበት እና 43 መቁሰላቸውን ገልጿል።

    ባለፉት ሳምንታት ሒዝቦላህ ከሊባኖስ በኩል ወደ እስራኤል የሮኬት ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ እስራኤልም በአየር እና በከባድ መሳሪያዎች አጸፋ ስትመለስ ቆይታለች።

  7. የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል

    የጋዛ ነዋሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ተኩስ ቆሞ በችግር ላይ ላሉት የጋዛ ነዋሪዎች እርዳታ እንደቀርብ የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ቢሰበሰብም ውጤት አልተገኘም

    እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደው ጥቃት ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጋዛ ውስጥ ባለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቀውስ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ሊያደርግ ነው።

    እስራኤል ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ እየተነገረ ነው።

    በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ጥያቄ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም. በሚካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ለፍልስጤማውያን ስደተኞች እርዳታ የሚያቀርበው የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ስላለሁ ሁኔታ ማብራሪያ ይሰጣል ተብሏል።

    ባለፈው ቅዳሜ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ተኩስ እንዲቆም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበውን ጥያቄ ከመፍቀድ ይልቅ እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታካሂደው ዘመቻ መጠናከሩ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

    ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተኩስ እንዲቆም ለማድረግ በሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ ላይ አራት ጊዜ ቢሰበሰብም ውጤት ሳያስገኝ ቀርቷል።

    ለዚህም ምክንያቱ አሜሪካ ወይም ሩሲያ በቀረቡት ሃሳቦች ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ውድቅ በማድረጋቸው ነው።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሳያ የሚሆን ማስጃን በመጥቀስ እንዳለው፣ በሰሜን ጋዛ የሚካሄደው የአየር ጥቃት የመኖሪያ አካባቢዎችን በማውደም ላይ ያነጣጠረ ይመስላል ብሏል።

  8. እስራኤል ሐማስን ማስወገድ ከቻለች በጋዛ ላይ ምን የያዘችው ዕቅድ አለ?

  9. አሜሪካ ወደ እስራኤልም ሆነ ወደ ጋዛ ወታደር የመላክ ፍላጎት የላትም፡ ካማላ ሐሪስ

    ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/EFE

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ

    መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ አሜሪካ ወደ እስራኤል ወይም ወደ ጋዛ ወታደሮቿን ለመላክ ፍላጎት እንደሌላት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ ገለጹ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቷ ‘60 ሚነትስ’ ከተባለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “ወደ አስራኤልም ሆነ ጋዛ ሰርጥ ወታደሮቻችንን የማሰማራት ፍላጎት ወይም ዕቅድ ፈጽሞ የለንም” በማለት ፈርጠም ብለው ተናግረዋል።

    ነገር ግን አሜሪካ ለእስራኤል የምክር፣ የቁሳቁስ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ እየሰጠች መሆኑን ገልጸዋል።

    “ጥያቄ በማይቀርብበት ሁኔታ እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት አላት። ይህ ተብሎ ግን ሐማስን እና ፍልስጤማውያንን አንድ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖር የለበትም” ብለዋል ሐሪስ።

    “የፍልስጤማውያንን ደኅንነት የሚያስጠብቁ፣ የእራሳቸውን ዕድል የመወሰን እና ክብራቸውን የሚያስጠብቁ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንፈልጋለን፤ በተጨማሪም የጦርነት መመሪያዎች መከበር እንዳለባቸው ግልጽ አድርገናል፤ እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባም መደረግ አለበት።”

    ምክትል ፕሬዝዳንት ሐሪስ አክለውም፣ አሜሪካ ግጭቱ እንዳይባባስ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት በማመልከት ኢራን እጇን እንዳታስገባ አስጠንቅቀዋል።

  10. እስራኤል ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ጋዛ ማሰማራቷን አስታወቀች

    የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ

    ከተቀሰቀሰ ሦስተኛ ሳምነቱን ያሳለፈው የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ወደሌላ ደረጃ ተሸጋግሯል። ለሦስት ሳምንታት ያህል እስራኤል በጋዛ ላይ ስታካሂደው የቆየው የአየር ድብደባ የቀጠለ ሲሆን፣ እግረኛ ወታደሮች እና ከባድ መሳሪያዎች ወደ ጋዛ ዘልቀው ገብተዋል። የዛሬ እሁድ ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም. ዋና ዋና ክስተቶች. . .

    • የቅዳሜ ሌሊት የእስራኤል ጥቃት

    ከቅዳሜ ሌሊት ጀምሮ ተጨማሪ እስራኤል ወታደሮች ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባታቸውን ቁጥሩን ሳይገልጹ የጦሩ ቃል አቀባይ ሬር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ አስታውቀዋል።

    በተጨማሪም ቅዳሜ ሌሊቱን የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ጋዛ ውስጥ የሚገኙ 450 የሐማስ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

    • የጋዛ የእርዳታ ማዕከላት ሁኔታ

    በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የእርዳታ አቅርቦት የተቀመጠባቸውን መጋዘኖች ሰብረው በመግባት ዱቄት እና የንጽህና መገልገያዎችን መውሰዳቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።

    ድርጅቱም ጨምሮ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ መደበኛው የሕዝብ ሥርዓት መጣስ እየጀመረ መሆኑን አመልክቷል።

    ጋዛ ውስጥ ከአንድ ቀን በላይ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠው የነበሩት የግንኙነት መስመሮች ወደ አገልግሎት እየተመሱ ሲሆን፣ ስልክ እና ኢንተርኔት መሥራት እየጀመሩ ነው።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር ሰሜናዊ የጋዛ ክፍል የውጊያ ቀጠና በመሆኑ ከአል-ቁዱስ ሆስፒታል ለቆ እንዲወጣ በእስራኤል ባለሥልጣናት እንደተነገረው ገልጿል።

    • እስራኤላውያን ታጋቾች

    ጋዛ ውስጥ እስራኤል የጀመረችው የእግረኛ ሠራዊት ዘመቻ ያሳሰባቸው የታገቱ ሰዎች ቤተሰቦች ስጋታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ፣ ታጋቾችን ወደ ቤተሰባቸው መመለስ የጦሩ ቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

    በሐማስ ከእስራኤል ተወስደው ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ታጋቾች ቤተሰቦች፣ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ዛሬ እሁድ ለመገናኘት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

  11. ፍልስጥኤማውያን በፍርስራሽ ክምሮች ውስጥ ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ነው

    በኻን ዮኒስ የደረሰው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፍልስጥኤማውያን በአየር ጥቃት ከፈራረሱ ክምሮች ስር ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ነው። የኻን ዮኒስ ከተማ ህንጻዎች በአየር ጥቃት ወድመዋል።

    ኻን ዮኒስ እስራኤል ከሰሜን ጋዛ እንዲወጡ የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ በርካቶች የተሰዱዳባት ከተማ ናት። አንዳንድ ፎቶዎች በጣም አሰቃቂ ናቸው።

    በኻን ዮኒስ የሚገኘው የናስር ሆስፒታል የተገደሉ ሰዎችን አስክሬን መሬት ላይ ተደርድረው የሚያሳይ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ ሶስቱ ህጻናት ናቸው።

    በጋዛ ፍርስራሽ ስር በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተቀብረው እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ አስታውቋል።

    በትናንትናው ዕለትም የእስራኤል ጦር የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ደቡብ እንዲሸሹ ያስጠነቀቀ ሲሆን ሰብዓዊ ጥረቶችም ይጨምራሉ ብሏል።

    እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገቻት የጋዛ ሰርጥ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች። በዚህም ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

    በኻን ዮኒስ የደረሰው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኻን ዮኒስ የደረሰው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኻን ዮኒስ የደረሰው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  12. የጋዛ ነዋሪዎች የእርዳታ መጋዘኖችን ሰብረው በመግባት ዱቄት እና ሌሎች ፍጆታዎችን መውሰዳቸውን ተመድ አስታወቀ

    ፍልስጥኤማውያን እርዳታ ሲወስዱ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    በሙሉ ከበባ ላይ ባለችው የጋዛ ሰርጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መጋዘኖችን እና ማከፋፈያ ማዕከሎችን ሰብረው በመግባት ዱቄት እና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን መውሰዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

    "ከሶስት ሳምንታት ጦርነት እና በሙሉ ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ ህዝባዊ ስርዓቱ መፍረስ መጀመሩን የሚያሳይ አሳሳቢ ምልክት ነው" ሲል የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም ስደተኞች የእርዳታ ኤጀንሲ በመግለጫው አስፍሯል።

    "ነዋሪዎች ፈርተዋል፣ ተበሳጭተዋል እንዲሁም ተስፋ ቆርጠዋል። ውጥረቱ እና ፍርሃቱ በስልክ እና ኢንተርኔት መቋረጡ ተባብሷል" ብሏል።

    በዛሬው ዕለት የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶቹ የትኞቹ መጋዘኖቹ እንደተሰበሩም ግልጽ አላደረገም።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊዝ ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳታ ጠብታ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

    እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን ነዳጅ፣ መብራት እና ውሃ የተቋረጠ ሲሆን የማያባራ የአየር ጥቃትም እያስተናገደች ትገኛለች።

  13. ሐማስ በጋዛ ካሉ የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያዎች ማካሄዱን አስታወቀ

    የእስራኤል እግረኛ ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces

    የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው ኢዘዲን አል ቃሳም ብርጌድ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር በስተሰሜን ምዕራብ ጋዛ የትጥቅ ግጭቶች ማካሄዱን በቴሌግራም ገጹ አስፍሯል።

    የእስራኤል መከላከያ ወታደሮቹ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንደገቡ ያስታወቀ ሲሆን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጦር አዛዦችም በመላው ጋዛ መሰማራታቸውንም አክለዋል።

    በትናንትናው ዕለትም በሰሜን ምዕራብ ጋዛ ውጊያዎች እንደነበረ ይሄው ቴሌግራም ገጽ አስፍሯል። የእስራኤል መከላከያ ያወጣው ቪዲዮ ላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሰሜን ምዕራብ ጋዛ አቅራቢያ የሚታዩ ሲሆን ስፍራው በእስራኤል ውስጥ መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል።

    ይኸው የአል ቃሳም ቴሌግራም ከጋዛ ከተማ በስተምስራቅ ከሰፈሩ የእስራኤል ወታደሮች ጋር የትጥቅ ግጭት መኖሩን ዘግቧል።

  14. የእስራኤል እግረኛ ጦር የታጋቾችን የመለቀቅ ጥረት ያወሳስበዋል- ኳታር

    የእስራኤል ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Israel Defence Force

    እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ማስገባቷን ተከትሎ በሐማስ የተወሰዱ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ጥረት እንዳወሳሰበው የኳታር መንግሥት አስታወቀ።

    "ሁኔታዎች መባባሳቸው ጉዳዩን የበለጠ ፈታኝ ያደርገዋል" ሲሉም የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ማጅድ አል አንሳሪ ተናግረዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ሐማስን ድል መንሳት እና ታጋቾቹን ማስለቀቅ "ምንም ተቃርኖ" የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉም ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።

    እስራኤል 229 ሰዎች በሐማስ ታግተው መወሰዳቸውን ገልጻለች።

  15. እስራኤል የጋዛ ሰርጥ ወረራን ጀምራለች?

  16. የፍልስጥኤም ድጋፍ በዓለም ዙሪያ

    በተለያዩ አገራት የፍልስጥኤም የአጋርነት ሰልፎች ተደርገዋል።

    በለንደን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፋቸውን በአደባባይ በመውጣት ያሳዪ ሲሆን የፍልስጥኤም ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ ፍልስጥኤም ነጻ እንድትሆንም ጠይቀዋል።

    በቱርኳ ኢስታንቡል በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የተገኙ ሲሆን እስራኤልንም ወራሪ ሲሉ የጠሯት ሲሆን በጋዛ ላይ እየደረሰ ላለው ግድያም ምዕራባውያንን ተጠያቂ አድርገዋል።

    የፕሬዚዳንቱንም ንግግር ተከትሎ እስራኤል ዲፕሎማቶቿን ከቱርክ በመጥራት ምላሽ ሰጥታለች።

    በለንደን ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, በለንደን ለፍልስጥኤም የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ
    በቱርክ በተደረገው የፍልስጥኤም የድጋፍ ሰልፍ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እስራኤልን በጦር ወንጀል ከሰዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በቱርክ በተደረገው የፍልስጥኤም የድጋፍ ሰልፍ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እስራኤልን በጦር ወንጀል ከሰዋል
    በዌስት ባንክ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ቤተሰቦቻቸው በእስራኤል የታሰሩባቸው ፍልስጥኤማውያን እንዲፈቱ እንዲሁም ለጋዛ ያላቸውንም አጋርነት ገልጸዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በዌስት ባንክ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ቤተሰቦቻቸው በእስራኤል የታሰሩባቸው ፍልስጥኤማውያን እንዲፈቱ እንዲሁም ለጋዛ ያላቸውንም አጋርነት ገልጸዋል
    የፍልስጥኤም ደጋፊዎች በማሌዥያዋ ኳዋላላምፑር በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የፍልስጥኤምን ሰንደቅ አላማ አውለብልበዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የፍልስጥኤም ደጋፊዎች በማሌዥያዋ ኳዋላላምፑር በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የፍልስጥኤምን ሰንደቅ አላማ አውለብልበዋል
    በአውስትራሊያዋ ፐርዝ በርካታ የፍልስጥኤም አጋሮች ድጋፋቸውን በአደባባይ ገልጸዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በአውስትራሊያዋ ፐርዝ በርካታ የፍልስጥኤም አጋሮች ድጋፋቸውን በአደባባይ ገልጸዋል
  17. እስራኤል "እርምጃ እንድንወስድ ልታስገድደን ትችላለች " የኢራን ፕሬዚዳንት

    የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ራይሲ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል እያደረገችው ያለው ተግባር ቀይ መስር አልፏል፤ እርምጃ እንድንወስድ የሚያስገድደን" ሁኔታ ውስጥ እያስገባችን ነው ሲሉም የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ራይሲ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ሰርጥ ባስገባችበት እና የጦር አዛዦችም በመላው ጋዛ ሰርጥ ተሰማርተዋል ባሉበት ወቅት ነው።

    "አሜሪካ ምንም እንዳናደርግ እየጠየቀችን ነው። ነገር ግን በተቃራኒው ለእስራኤል ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠች ነው። አሜሪካ ለአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ መልዕክት የላከች ሲሆን ነገር ግን በጦር ሜዳውም ግልጽ ምላሽ አግኝታለች" ብለዋል።

    አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ በመካከለኛው ምስራቅ ሐማስን ጨምሮ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖችን የሚያመለክት ነው።

    አሜሪካ ሰፋ ያለ ቀጠናዊ ግጭት እንዳይከሰት በሚል ኢራን በእሰራኤል እና ሐማስ ጦርነት ተሳታፊ እንዳትሆንም የአሜሪካ ባለስልጣናት እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

    በሊባኖስ የሚገኘው እና በኢራን የሚደገፈው የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ባለፉት ሳምንታት ከእስራኤል ጋር ተኩስ ተለዋውጧል።

  18. በእስራኤል- ጋዛ የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    የፈራረሰችው ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ሶስት ሳምንት አለፈው። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገው የእግረኛ ጦር የዘመቻው ቀጣይ ደረጃ መሆኑን ገልጸው ረዥም እና ፈታኝ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

    በቅርቡ የተከሰቱ ጉዳዮችን እንዳስ፦

    • በጋዛ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት እየተመለሰ ነው። አርብ አመሻሽ ላይ የስልክ እና ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ጋዛም ከአለም ተቆራርጣም ነበር። በዚህም ወቅት በጦርነቱ የከፋውን የአየር ጥቃትም አስተናግዳለች።
    • ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባቱን ለማመላከት "የጥፋት ምሽግ" ገብቷል ያሉ ሲሆን የጦር አዛዦችም በመላው ጋዛ ሰርጥ መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ታጋቾቹን ማስመለስ የጦሩ አላማ ቢሆንም ዋናው ተቀዳሚ ጉዳይ ሐማስን "ማጥፋት" ነው ብለዋል።
    • የእስራኤል መከላከያ ኃይል ግብጽ እና አሜሪካ ወደ ጋዛ የሚደረገውን ዕርዳታ እንደሚያስተባብሩ ቢጠቅስም ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል። የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲረግብ ጥሪ አቅርቧል። የሰው ህይወት እየረገፈ እንደሆነ እና ህዝቡም ለከፋ ስቃይ መጋለጡንም ገልጿል።
    • የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን እስራኤልን በጦር ወንጀሎች ከሰዋል። ኔንታንያሁ ዲፕሎማቶቻቸውን ከቱርክ በማስወጣት ምላሽ ሰጥተዋል።
    • ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 400 እስራኤላውያን ተገድለዋል፤ 229 ሰዎች ታግተዋል። እስራኤል የማያባራ ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ላይ እየፈጸመች ሲሆን ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች ናቸው። እስራኤል ጋዛ ሰርጥን በሙሉ ከበባ በማስገባት ነዳጅ፣ ውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጋለች።
  19. እስራኤል ዲፕሎማቶቿን ከቱርክ ጠራች