ቦሊቪያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቦሊቪያ በጋዛ ደረሰ ባለችው “አስከፊ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ” ጥቃት ምክንያት ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ማቋረጧን አስታወቀች።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሬዲ ማማኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ እየደረሰ ያለውን አጸያፊ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቃት ለመቃወም እና ለማውገዝ " አገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ምክንያት እንደሆናት ተናግረዋል።
በሌላ መረጃ ደግሞ ኮሎምቢያ እና ቺሊ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በእስራኤል የሚገኙ አምባሳደሮቻቸውን ጠርተዋል።
የቺሊው ፕሬዝዳንት ጋብርኤል ቦሪስ ፎንትስ በኤክስ ላይ እንዳሰፈሩት አገራቸው የእስራኤልን "ተቀባይነት የሌለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ጥሰቶችን" ታወግዛለች።
የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮም በተመሳሳይ በኤክስ ላይ “እስራኤል በፍልስጤም ላይ የምታደርሰውን እልቂት ካላቆመች ግንኙነት ሊኖረን አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል።















