ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ዋና ክስተቶች

ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ከባድ ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው። አስካሁን በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤላውያን በኩል ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱን ዋጋ እየከፈሉ ነው። ለአጭር ጊዜ በቆየው የሐማስ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ተገድለዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ሆስፒታል በምስል

    ማክሰኞ ማታ ጋዛ ውስጥ በሚገኘው አል አህሊ በተባለው ሆስፒታል ላይ በተደሰ ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ሳይገደሉ እንዳልቀረ ተሰግቷል።

    ሐማስ ለአደጋው የእስራኤል የአየር ጥቃት ምክንያት ነው ያለ ሲሆን፣ እስራኤል ግን ፍንዳተው የተከሰተው ሌላኛው የፍልስጥኤም ቡድን ኢስላሚክ ጂሃድ በስህት በተኮሰው ሮኬት የደረሰ ነው ስትል እጇ እንደሌለበት ገልጻለች።

    በሆስፒታሉ ላይ የደረሰው ከባድ ፍንዳታ ያስከተለውን ጉዳት በጥቂቱ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እነሆ፡

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ሆስፒታል በምስል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ሆስፒታል በምስል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ሆስፒታል በምስል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ሆስፒታል በምስል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  2. እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው የአየር ጥቃት ዛሬም ቀጥሏል

    እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ዛሬ ጠዋት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተነሳ ጪስ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ዛሬ ጠዋት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተነሳ ጪስ

    ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ማከሰኞ ምሽት የተፈጸመውን ጥቃት እንዳላደረሰች የገለጸችው እስራኤል ረቡዕ ጠዋት በተለያዩ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

    በሆስፒታሉ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፤ ሐማስ እስራኤልን፣ አስራኤል ደግሞ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለውን ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ እያደረጉ ነው።

    የእስራኤል አየር ኃይል ዛሬ ጠዋት በተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች ባሉ ወታደራዊ ያላቸውን ዒላማዎች የመታ መሆኑን ገልጾ፣ በዚህም የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን ሁለት አባላትን “መደምሰሷን” አሳውቃለች።

    የእስራኤል ሠራዊት በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ገደልኩ ያላቸውን ሁለት ሰዎችን ስም እና ሚናቸውን ይፋ አድርጓል። አንደኛው ሙሐመድ አልዋዲ የተባለ እና በጋዛ ውስጥ የሐማስ ፀረ ታንክ ቡድን መሪ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ አክራም ሂጃዝ የሚባል የጦር መሳሪያ ነጋዴ ነው ብሏል።

    የእስራኤል አየር ኃይል ባለፉት ቀናት በካሄዳቸው የአየር ጥቃቶች የሐማስ ጽህፈት ቤቶችን፣ የሮኬት እና ፀረ ታንክ መሳሪያዎች ማስወንጨፊያዎችን እና ሌሎች የቡድኑ ተቋማትን በዋናነት ዒላማ ማድረጉን አመልክቷል።

  3. ጥቃት በደረሰበት ሆስፒታል ውስጥ ያለው 'አስጨናቂው' ሁኔታ

    መሬት ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉ ሰዎችን የሚያክም ዶክተር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, መሬት ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉ ሰዎችን የሚያክም ዶክተር

    ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በተፈጸመበት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው በተነገረለት የጋዛው አል አህሊ ሆስፒታል ውስጥ ያለው ሁኔታ “ወደር የሌለው እና ለመገልጽ አስቸጋሪ” መሆኑን በጋዛ ያለው የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

    “ዶክተሮች መሬት ላይ እና በመተላለፊያ ኮሪደሮች ላይ ቀዶ ሕክምና እያደረጉ ነው፣ አንዳንዶቹ ታካሚዎችም ካለማደንዘዣ ነው ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው” በማለት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዶክተር አሽራፍ አል-ቁድራ በፌስቡክረ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    “በርካታ ሰዎች ቀዶ ሕክምና ለማግኘት እየተጠባበቁ ሲሆን፣ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ያሉትን ሰዎች ሕይወትን ለማትረፍ የሕክምና ባለሙያዎች ጥረት እያደረጉ ነው።”

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም ከጥቃቱ ሰለባዎች አብዛኞቹ “የወደፊት ተስፋቸውን የተነጠቁ” ሕጻናት ናቸው በማለት፣ አብዛኞቹ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለማከም በሆስፒታሉ “ካሉት ሐኪሞች አቅም በላይ ነው” ብለዋል።

    በሆስፒታሉ ላይ ማን እንደፈጸመው አስካሁን ባልታወቀው የፍንዳታ ጥቃት አምስት መቶ የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    ሐማስ ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ ሲያደርግ፣ የእስራኤል መንግሥት ደግሞ ሌላኛውን የፍልስጥኤም ቡድን ኢስላሚክ ጂሃድን ጥቃቱን ፈጽሟል ብሎ እየከሰሰ ነው።

  4. ተቃውሞ ሊባኖስ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ

    የተቃውሞ ሰለፍ ቤይሩት ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት የተቆጡ ተቃዋሚዎች ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ውጪ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች በኤምባሲው ዙሪያ እሳት በማንደድ እና የፍልስጥኤም ሰንደቅ አላማን በኤምባሲው አጥር ላይ በመስቀል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

    ሮይትርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተኩሷል።

    በተመሳሳይ እዚያው ቤይሩት ውስጥ በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ትንሽ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተሰብስበው የነበረ ሲሆን፣ በሕንጻው ላይ ድንጋይ መወርወራቸው ተዘግቧል።

    ሐማስ እና የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋዛ ውስጥ በሚገኘው አል አህሊ ሆስፒታል ላይ ለተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን እና አሜሪካንን ተያየቂ አድርገዋል፤ እሰራኤል ግን ለጥቃቱ እስላማዊ ጂሃድ የተባለውን የፍልስጥኤም ቡድንን ከሳለች።

    ሄዝቦላህ ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ “ታይቶ የማይታወቅ ሕዝባዊ ቁጣ የሚገለጽበት” በማለት ለረቡዕ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል።

    በተጨማሪም ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በተለያዩ ስፍራዎች ተቃውሞዎች እየተቀሰቀሱ ነው።

    • ዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ ፍልስጥኤማውያን ማክሰኞ ምሽት በበርካታ ከተሞች ውስጥ ወደ አደባባይ በመውጣት ድንጋይ እየወረወሩ በፍልስጥኤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የፀጥታ ኃይሎችም ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተኩሰዋል።
    • በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ገድሞ በዋና ከተማ ትሪፖሊ እና በሌሎች የሊቢያ ከተሞች ውስጥ የፍልስጥኤም ሰንደቅ ዓላማን በመያዝ የጋዛ ነዋሪዎችን የሚደግፉ መፈክሮችን እያሰሙ አደባባይ ወጥተዋል።
    • ተቃዋሚዎች ኢራን ዋና ከተማቴህራን ውስጥ ከሚገኙ የብሪታኒያ እና የፈረንሳይ ኤምባሲዎች ውጪ የተሰበሰቡ ሲሆን፣ በቱርክ እና በዮርዳኖስ ከሚገኙት የእስራኤል ኤምባሲዎች ደጃፍ ሰዎች ለተቃውሞ መሰብሰባቸው ተዘግቧል።
    ተቃዋሚ ሰልፈኞች በትሪፖሊ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ተቃዋሚ ሰልፈኞች በትሪፖሊ
  5. በጋዛ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ተባለ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በደረሰ ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ተነገረ።

    ለጥቃቱ ሐማስ የእስራኤል የአየር ጥቃት ምክንያት ነው ሲል፣ እስራኤል ደግሞ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለው ቡድን የተኮሰው ሮኬት ኢላማውን ስቶ ሆስፒታሉ ላይ በመውደቁ ነው ብላለች።

    ነገር ግን እስራኤልም ሆነች ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ከቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ ቡድን የሆነው እስላማዊ ጂሃድ ለጥቃቱ ተጠያቂ አለመሆናቸውን አስተባብለዋል።

    በሐማስ በምትተዳደረው ጋዛ ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት እንዳሉት ሆስፒታሉ ላይ በደረሰው የፍንዳታ ጥቃት 500 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

    ሐማስ ድርጊቱን በእስራኤል የተፈጸመ “የጦር ወንጅል” ያለው ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት መሪዎች በሆስፒታሉ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ለጠፋው ሕይወት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

    የዮርዳኖስ፣ የግብፅ እና የፍልስጥኤም መሪዎች ዛሬ ረቡዕ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባም ተሰርዟል።

    ጆ ባይደን ለእስራኤል አጋርነታቸውን ለማሳየት እና ግጭቱ እንዲያበቃ ለማገዝ ዛሬ በእስራኤል ጉብኝት በማድረግ ከአገሪቱ መሪዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ሐማስ እና የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ በሆስፒታሉ ላይ ለተፈጸመው የፍንዳታ ጥቃት አሜሪካ ከአስራኤል ጋር የጥፋቱ ተጋሪ ናት ሲሉ ከሰዋል።

    ሌሊቱን ቤይሩት ውስጥ ከአሜሪካ ኤምባሲ ውጪ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።

  6. እስካሁን ጋዛ ውስጥ 3,000 ሰዎች ሲገደሉ ከ12,000 በላይ ተጎድተዋል

    የፍንዳታ ጭስ በጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ጋዛ

    የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር አዲስ ያወጣው መረጃ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት 3,000 የሚደርሱ ሰዎች ጋዛ ሰርጥ ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ምክንያት መገደላቸውን አመለከተ።

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ድንበር ተሻግሮ በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ፣ በጋዛ ላይ የእስራኤል አየር ኃይል ያለማቋረጥ በፈጸመው የአየር ድብደባ ነው ሰዎቹ የተገደሉት።

    ከተገደሉት ፍልስጥኤማውያን በተጨማሪ 12,500 የሚሆኑት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    በሌላ በኩል ደግሞ ከጋዛ በስተምሥራቅ ተነጥሎ በሚገኘው የፍልስጥኤም ግዛት ዌስት ባንክ ውስጥ 61 ፍልስጥኤማውያን የተገደሉ ሲሆን፣ ከ1,250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።

    በጋዛ ላይ የእስራኤል ጦር ኃይል ሙሉ ከበባ በመጣሉ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ችግር የተፈጠረ ሲሆን፤ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ አቅርቦት በመቋረጡ በነዋሪው ላይ የበለጠ ችግር ይፈጠራል ተብሎ ተሰግቷል።

    የፍልስጥኤም የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ጋዛ ውስጥ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ እና የነዳጅ እጥረት በመፈጠሩ ሆስፒታሎች “ሥራቸውን ወደማቆም ተቃርበዋል።”

  7. የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሐማስ መሪ ጋር ተወያዩ

    የሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ እና የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር

    የፎቶው ባለመብት, AFP/REUTERS

    የምስሉ መግለጫ, የሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ እና የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር

    የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሐማስ መሪ ጋር “ወደ ፍልስጥኤም ግዛቶች ሰብአዊ እርዳታ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን” ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ናሌዲ ፓንዶር የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን በመወከል ከሐማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ ጋር መወያየታቸውን ዛሬ ማክሰኞ አረጋግጠዋል።

    ነገር ግን ውይይቱ የተደረገው በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጥያቄ ሳይሆን በሐማስ ፍላጎት መሆኑም ተነግሯል።

    በስልክ በተደረገው ውይይት ወቅት “ሚኒስትር ፓንዶር ደቡብ አፍሪካ ለፍልስጥኤም ሕዝብ ያላትን ድጋፍ በመግለጽ፣ በፍልስጥኤም እና በእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች ላይ በደረሰው የሕይወት መጥፋት ማዘናቸውን ተናግረዋል” ብሏል የወጣው መግለጫ።

    በተጨማሪም “ሚኒስትሯ እና የሐማሱ መሪ አስፈላጊ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ጋዛ እና ወደ ሌሎች የፍልስጥኤም ግዛቶች እንዴት ሊደረስ እንደሚችል” መወያየታቸው ተገልጿል።

    ከሳምንት በፊት ሐማስ በእስራኤል ላይ ከባድ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የእስራኤል ሠራዊት በጋዛ ላይ ከበባ በመጣሉ ሐማስ በሚያስተዳድራት በጋዛ ውስጥ የመሠረታዊ አቅርቦት ቀውስ ተፈጥሯል።

    የሚኒስትሯ ጽህፈት ቤት በአንድ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ሐማስ በእስራኤል ላይ ለፈጸመውን ጥቃት ሚኒስትሯ ድጋፋቸውን ገልጸዋል መባሉን አስተባብሏል።

    በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር መወያየታቸውን በይፋ ከተናገሩ ጥቂት አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ናት።

  8. ጋዛ ውስጥ ያሉ 11 ሺህ ቁስለኞችን ለመርዳት እንድገባ ይፈቀድልኝ፡ የዓለም ጤና ድርጅት

    ራፋህ ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰበትን ሰው የተሸከሙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ራፋህ ውስጥ በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰበትን ሰው የተሸከሙ ሰዎች

    የዓለም ጤና ድርጅት አስራ አንድ ሺህ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ወደደረሰባቸው ጋዛ እርዳታ እና የሕክምና አቅርቦት ለማድረስ አስቸኳይ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠየቀ።

    ድርጅቱ ጨምሮም ጋዛ ውስጥ አሁን ያለው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰብአዊ ቀውስጥ ሊከሰት ይችላል በማለት አስጠንቅቋል።

    የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ የአጸፋ የአየር ድብደባ መፈጸም ከጀመረች ሳምንት ያለፋት ሲሆን፣ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ፍልስጥኤማውያን አስካሁን ተገድለዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅትን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገባው ጋዛ ውስጥ ከተገደሉት 2,800 ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። በተጨማሪም አስካሁን 11,000 ሺህ ሰዎች በጥቃቱ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    ድርጅቱ ምንም አይነት ነገር ለማስገባት እና ለማስወጣት ወደማይቻልባት ጋዛ አስፈላጊው የሕክምና እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለማድረስ የሚያስችል በር በአስቸኳይ እንዲከፈት ለማስቻል “ከውሳኔ ሰጪ አካላት” ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።

    ባለሥልጣናት ጨምረውም በጋዛ ውስጥ ባሉ በ115 የጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የጋዛ ሆስፒታሎች የውሃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ስላለባቸው ሥራቸውን እያከናወኑ አይደለም።

    የውሃ እና የንጽህን አቅርቦቶች በመቋረጣቸው “የተቅማጥ እና የውሃ ወለድ በሽታዎች ስጋት ከፍተኛ ነው” የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጥኤም ስደተኞች ተቋም “ካለውሃ ሰዎች መሞት ይጀምራሉ” በማለት ስጋቱን ገልጿል።

  9. የተባበሩት መንግሥታት ጋዛ ውስጥ የጦር ወንጀል ሊፈጸም ይችላል ሲል አስጠነቀቀ

    ከጋዛ የሚወጡ ፍልስጥኤማውያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤልን ጥቃት በመፍራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከሰሜን ጋዛ እየወጡ ነው

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ድርጅቶች ወደ ጋዛ መግባት እንዲፈቀድላቸው በድጋሚ በመጠየቅ፣ ጋዛ ውስጥ የጦር ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

    የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ራቪና ሳምዳሳኒ እንዳሉት፣ የእስራኤል ሠራዊት በሰሜን ጋዛ ያሉ ፍልስጥኤማውያን ወደ ደቡብ እንዲወጡ ማዘዙ “ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ሲቪሎችን በኃይል ከመኖሪያቸው ማስወጣት ነው” በማለት ሁኔታው የተባበሩት መንግሥታት “እንዳሳሰበው” ገልጸዋል።

    አንድ አገር በግጭት ወቅት የጦር ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ከታመነ ጉዳዩ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል። ፍልስጥኤም የፍርድ ቤቱ አባል ስትሆን እስራኤል ግን አይደለችም።

    ቃል አቀባይዋ በሰጡት መግለጫ ከሰሜናዊ ጋዛ ለመውጣት በሚሞክሩ ሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ ወገን መመርመር አለባቸውም ብለዋል።

    በተጨማሪም ቁጥራቸው ወደ 199 የደረሰው በሐማስ የታገቱ እስራኤላውያን “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ” እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

  10. የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ምንድን ነው? እንዴትስ የጋዛ ነዋሪዎች ተስፋ ለመሆን በቃ?

  11. በደቡባዊ ጋዛ አየር ጥቃት የተገደሉት በርካቶቹ በእስራኤል ትዕዛዝ ከሰሜን የተፈናቀሉ ናቸው

    በአየር ጥቃቶቹ የተጎዱ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተገደሉት በርካቶች በእስራኤል አስገዳጅ ትዕዛዝ ከሰሜን የተፈናቀሉ ናቸው።

    እስራኤል 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የደቡባዊ ጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሰሜን እንዲሄዱ 24 ሰዓታት ሰጥታቸዋለች።

    የቢቢሲ ዘጋቢ በርካታ ተፈናቃዮችን እያስተናገደች ባለችው ኻን ዩኒስ ይገኛል። ቀያቸውን ለቀው ወደ ደቡባዊ ጋዛ ለተሰደዱ በርካቶች የሆነው ነገር አሳሳቢ ነው።

    እስራኤል በምሽቱ በፈጸመቻቸው ሶስት የአየር ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰዎችን እንደገደለች የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

    አብዛኛዎቹም በእስራኤል ትዕዛዝ ከሰሜን የተፈናቀሉ ናቸው። በርካታ የተፈናቀሉ ፍልስጥኤማውያንን እቃቸውን ሸክፈው ወደ ቤታቸው ለመመለስ እንዳሰቡ በጋዛ ለሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ተናግረዋል።

    ለባለፉት ቀናት ጎዳና ለማደር እንደተገደደ የሚናገረው አንድ ግለስብም በውሃ ጥም ከመሞት በክብር መሞትን እንደሚመርጥም ተናግሯል።

    ቀድሞም በከፍተኛ ህዝብ ተጨናንቃ በነበረችው ኻን ዩኒስ ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት ከሰሜን ጋዛ የተፈናቀሉ 600 ሺህ የሚገመቱ ተጨማሪ ፍልስጥኤማውያንን ማስተናገድ ይጠበቅባታል።

    እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ 'ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ባለፈው ሳምንት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።

  12. ኢራን ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጠች

    የእስራኤል መድፍ በድንበር ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት ዝም ብላ እንደማትመለከት ኢራን አስታወቀች።

    እስራኤል በጋዛ ባሉ "ፍልስጥኤማውያንን ላይ እየፈጸመችው ያለችውን የጦር ወንጀሎች" ካላቆመች ኢራን የመከላከል እርምጃም እንደምትወስድም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች።

    እስራኤል ለሐማስ ጥቃት ምላሽ ነው በሚል እየፈጸመችው ያለውን የአየር ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር ላይ ውጥረት ነግሷል።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በጦርነቱ ተሳታፊ ሊሆን ይችላል የሚልም ስጋት አጭሯል። አሜሪካ ኢራን ግጭቱን ከማባባስ እንድትቆጠብ ማስጠንቀቂያ የሰጠች ሲሆን እስራኤል በበኩሏ ሄዝቦላህ ተሳታፊ ከሆነ የከፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብላለች።

    ባለፈው ሳምንት ሄዝቦላህ እና የእስራኤል ጦር በድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ቢያደርጉም ከቁጥጥር ስር የወጣ አይደለም ተብሏል።

    የእስራኤል ጦር ትናንት ምሽት ከሄዝቦላህ ጋር የተገናኙ መሰረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረጉን ገልጿል። በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ምንም አይነት መረጃ የለም።

  13. በጋዛ- እስራኤል የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    የጋዛ ህጻናት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አስር ቀናት ባስቆጠረው የሐማስ እስራኤል ግጭት የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንቃኝ

    • የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ረቡዕ ወደ እስራኤል ያቀናሉ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እንደተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የሚያደርጉት ጉብኝት ለእስራኤል፣ ለአካባቢው እና ለመላው ዓለም ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው።
    • የእስራኤልን ከሰሜናዊ ጋዛ ውጡ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ቤታቸውን ለቀው የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች አስቸኳይ ምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
    • ሩሲያ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለጋዛ ሰብዓዊ መፍትሄ እንዲበጅ ያቀረበችው ረቂቅ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ሐማስን ማውገዝ ባለመቻሉ ውድቅ አድርገውታል።
    • አሜሪካ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ ለማድረግ ከእስራኤል ዋስትና እንዳገኘች የተናገሩት ብሊንከን መቼ እና እንዴት እንደሆነ ዝርዝር ጉዳዮችን አልሰጡም።
    • በግብጽ እና በጋዛ መካከል ያለው ራፋህ የተሰኘው የድንበር ማቋረጫንም ለማስከፈት የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች አሁንም ቀጥለዋል።
    • የአሜሪካ ከፍተኛ ጄነራል ሚካኤል ኩሪላ በይፋ ባይነገርም በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ይገኛሉ። ጄነራሉ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎችን እንዲሁም የጦሩ ማዕከላዊ እዝ መሪ ናቸው።
    • የእስራኤል አየር ኃይል በኢራን የሚደገፈውን የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ታጣቂ ቡድንን ኢላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
    • ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት በሰነዘረበት ወቅት ካገታቸው ሰዎች መካከል አንዷን የሚያሳይ ቪዲዮ ለቋል። የ21 ዓመቷ ግለሰብ ስሟ ማያ ሼም መሆኑንም በዕብራይስጥ ቋንቋ ስትናገር ይሰማል።
    • ባለፉት አስር ቀናት ውስጥ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ እስራኤላውያን እንደተፈናቀሉ ጦሩ አስታውቋል።
  14. ታዋቂው ካርቱኒስት ኔታንያሁን በጋዛ ላይ በሚያሳየው ካርቱን ምክንያት ከሥራው ተባረረ

  15. በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጋዛ-ግብፅ የድንበር ማቋረጫ በኩል ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው

  16. ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ለእስራኤል ያላቸውን ጥልቅ አጋርነት በድጋሚ አረጋገጡ

  17. ከሁለት ሚሊየን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ‘ክፍቷ እስር ቤት’ ጋዛ

  18. ግጭቱ ወደ ሌሎች ግንባሮች እየተስፋፋ ነው ስትል ኢራን አስጠነቀቀች

    የእስራኤል ወታደሮች ከሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ታንኮች ከሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴይን አሚራብዶላሃይም በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የሚካሄደው ግጭት ወደ ሌሎች ግንባሮች እየተስፋፋ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ግጭቱ ወደ ሌሎች ግንባሮች በመስፋፋት “ለማስቆም ከማይቻልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው” ብለዋል።

    በኤክስ (ትዊተር) የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ በተሰራጨው መግለጫ ላይ ሚኒስትሩ ለተፈጠረው ችግር “ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማግኘት የሚቻልበት ጊዜ እያለፈ ነው” በማለት እስራኤልን ጋዛ ውስጥ “ወንጀል እና ግድያ” እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰዋል።

    ጨምረውም “ከማሌዢያ፣ ከፓኪስታን እና ከቱኒዚያ አቻዎቼ ጋር ተወያይቻለሁ። በአስቸኳይ ጽዮናውያን ጋዛ ውስጥ የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች እና ግድያዎች እንዲቆሙ እንዲሁም ሰብአቂ እርዳታ እንዲገባ አጽንኦት ሰጥተናል” በማለት አስፍረዋል።

    “ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማግኘት ጊዜው እያበቃ መሆኑን አበክሬ ተናግሪያለሁ፣ ጦርነቱ ወደ ሌሎች ግንባሮች የመዛመቱ ዕድል ለማስቀረት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር።

    ኢራን እስራኤል ቀዳሚ ባላንጣዎቼ ከምትላቸው አገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን፣ ሐማስን ጨምሮ በአካባቢው አሉ የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖችን በማስታጠቅና በመደገፍ ትታወቃለች።

  19. ጋዛ ውስጥ ከ1,000 በላይ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረዋል፡ ባለሥልጣናት

    ፍልስጥኤማውያን በኻን ዩኑስ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ካለ ፍርስራሽ ሰዎችን ሲፈልጉ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ፍልስጥኤማውያን በኻን ዩኑስ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ካለ ፍርስራሽ ሰዎችን ሲፈልጉ

    እስራኤል በጋዛ ላይ ባለፉት ቀናት በፈጸመችው የአየር ድብደባ ምክንያት በፈራረሱ ሕንጻዎች እና ቤቶች ስር ተቀብረው ያልተገኙ ሰዎች ከአንድ ሺህ በላይ መሆናቸውን የፍልስጥኤም የአደጋ ጊዜ ነፍስ አድን ተቋም አስታወቀ።

    በጋዛ ውስጥ ያለው በሐማስ የሚመራው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ አያድ አል-ቦዞም፣ ያልተገኙት ሰዎችን በተመለከተ የተጠቀሰው ቁጥሩ ትክክል እንደሆነ አረጋግጠዋል።

    ከአንድ ሳምንት በፊት ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የተፈጸመውን የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደች ባለው የአየር ድብደባ ምክንያት ቢያንስ 2,750 ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ፣ 9,700 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በተጨማሪም ሌላኛው የፍልስጥኤም ክፍል በሆነው ዌስት ባንክ ውስጥ አስካሁን 58 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ1,250 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መጎዳታቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

  20. የእስራኤል የአየር ድብደባ እና የሚያደርሰው ጉዳት

    እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባን ቀጥላለች። የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ባለፉት 24 ሰዓታት ከ100 በላይ ወታደራዊ ናቸው የተባሉ የተለያዩ ኢላማዎች ላይ ድብደባ ተፈጽሟል።

    ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀው ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያሉ ሕንጻዎች፣ መሠረተ ልማቶች እና የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ከባድ ውድመት ደርሷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ለሞት እና ለጉዳት ተዳርገዋል።

    ኻን ዩኒስ ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከወደመ ሕንጻ አቅራቢያ የተሰበሰቡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ኻን ዩኒስ ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከወደመ ሕንጻ አቅራቢያ የተሰበሰቡ ሰዎች
    ኻን ዩኒስ ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከወደመ ሕንጻ ፍርስራሽ ውስጥ የተጎዱ ሰዎችን ሲፈልጉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ኻን ዩኒስ ውስጥ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከወደመ ሕንጻ ፍርስራሽ ውስጥ የተጎዱ ሰዎችን ሲፈልጉ
    ጋዛ ውስጥ መሠረታዊ አቅርቦቶች እየተሟጠጡ በመሆናቸው ሰብአዊ ቀውስ ይከሰታል በማለት የእርዳታ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጋዛ ውስጥ መሠረታዊ አቅርቦቶች እየተሟጠጡ በመሆናቸው ሰብአዊ ቀውስ ይከሰታል በማለት የእርዳታ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው