ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ዋና ክስተቶች

ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ከባድ ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው። አስካሁን በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤላውያን በኩል ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱን ዋጋ እየከፈሉ ነው። ለአጭር ጊዜ በቆየው የሐማስ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ተገድለዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በጋዛ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ የደረሰውን ፍንዳታ የኦርቶዶክስ ፓትርያሪክ አወገዙ

    ፍንዳታው ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፍንዳታው ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።

    በጋዛ ከተማ የቅዱስ ፖርፊየስ ቤተ-ክርስትያን አቅራቢያ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መጎዳታቸውን ሐማስ አስታውቋል።

    የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ በበኩሉ ቢያንስ ሁለት ሴቶች መገደላቸውን ዘግቧል።

    የዓይን እማኞች ለኤኤፍፒ የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ፍንዳታው በግሪክ የኦርቶዶክስ በቤተ-ክርስቲያኗ መግቢያ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በአቅራቢያው ያለ ህንፃን አወድሟል።

    የእየሩሳሌም የኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ጥቃቱን “አጥብቆ በማውገዝ” ባወጣው መግለጫ ለፍንዳታው ምክንያት የሆነው የእስራኤል የአየር ጥቃት ነው ብሏል።

    የሠላማዊ ዜጎች መጠለያ በሆኑት በአብያተ ክርስቲያናት እና በተቋሞቻቸው ላይ የሚፈጸመው ጥቃት “ቸል ሊባል የማይችል የጦር ወንጀል ነው” ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ጉዳዩን እየተመለከተ ነው ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

  2. ዓለም 'ሰብዓዊነቷን እያጣች ነው' - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

    ከሐማስ ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን እየፈጸመች ትገኛለች።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከሐማስ ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን እየፈጸመች ትገኛለች።

    በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት መካከለኛው ምስራቅ “በገደል አፋፍ ላይ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ፊሊፕ ላዛሪኒ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የተመድ የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ ኤጀንሲ ኮሚሽነር የሆኑት ላዛሪኒ "ዓለም አሁን ሰብዓዊነቷን እያጣች ነው" ብለዋል። ግጭቱ ወደ ሌሎች ቦታዎችም ሊስፋፋ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

    በጋዛ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ ያነሱት ላዛራኒ፤ በአካባቢው የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪደሮች እንዲከፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።

    ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ያወገዙት ላዛራኒ፤ “አሰቃቂው እና አረመኔያዊው እልቂት እስራኤል ውስጥ ድንጋጤን ፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል።

    "ይህ ክስተት ግን ጦርነቱ ያለ ምንም ገደብ እንዲካሄድ ምክንያት አይሆንም። ተጨማሪ ሠላማዊ ዜጎችን መግደል ለቀጣይ ሠላም ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም" ብለዋል።

  3. እስራኤል አስካሁን ወደ ጋዛ ዘልቃ እንዳትገባ ያገዳት ምንድን ነው? አራት ቁልፍ ምክንያቶች

  4. ባይደን ሐማስ እና ፑቲን እንዲያሸንፉ አልፈቅድም አሉ

    ጆ ባይደን

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዋይት ሃውስ ሆነው ለአሜሪካውያን ባስተላለፉት የቴሌቪዥን ንግግር ሐማስ እና ፑቲን እንዲያሸንፉ አልፈቅድም ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ኮንግረስ ለእስራኤል እና ዩክሬን በቢሊዮን የሚቆጠርየእርዳታ ገንዘብ እንዲፈቅድ እንደሚጠይቁ ገልጸው ወዳጅ አገራት ላይ ፊታችንን ማዞር እንችልም ብለዋል።

    ባይደን ኮንግረሱ ለሁለቱ አገራት እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲፈቅድ ሊጠይቁ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።

    ለእስራኤል የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ የአገሪቱን የአየር ኃይል የሚያጠናክር እንደሚሆን ይጠበቃል። ባይደን አይረን ዶም የእስራኤል ሰማይን ደኅንነት ማስጠበቁን መቀጠል አለበት ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በዚህ ንግግራቸው ሐማስን "አሸባሪ" የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ደግሞ "አምባገነን" ሲሉ ገልጸዋል።

    ባይደን “አሸባሪዎች እና አምባገነኖች ዋጋ መክፈል አለባቸው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከጽሕፈት ቤታቸው ሆነው ባደረጉት ንግግር ሐማስ እና ፑቲን የተለያየ አደጋ የደቀኑ ቢሆንም የጎረቤት አገር ዴሞክራሲን ለማጥፋት መነሳታቸው ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

  5. በጋዛ 100 የእርዳታ ተሽከርካሪ መድረስ እንዳለበት ተመድ ገለጸ

    የዳቦ ሰልፍ በደቡባዊ ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእርዳታ ተቋሞች እንዳሉት፣ ጋዛ በአንድ ቀን ውስጥ ከ20 በላይ እርዳታ የያዙ የጭነት መኪናዎች መድረስ አለባቸው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእስራኤል ጉብኝታቸው ትላንት ከተመለሱ በኋላ ለጋዛ በቀን 20 መኪና እርዳታ ለማስገባት ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ እንዳሉት፣ በአንድ ቀን ውስጥ 100 የሚጠጉ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ጋዛ መድረስ አለባቸው።

    ግብጽ ወደ ጋዛ የሚያሻግር ድንበሯን መልሳ ለመክፈትና የእርዳታ መኪኖቹን ለማሳለፍ ተስማምታለች። ዝግጅትም እየተደረገ ይገኛል።

    ለፍልስጤማውያን እርዳታ እንዲደርስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደቀጠሉ ነው። የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ የዮርዳኖሱን ንጉሥ አብደላህ ዛሬ ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ግብጽ እና ዮርዳኖስ ከእስራኤል ጋር ለዓመታት ሰላም ሆነው ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች የአሸማጋይነት ሚናም ነበራቸው።

  6. ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ሰዎች አሃዝ ከ3,700 በላይ ሆነ

    የሚያለቅሱ ፍልስጥኤማዊ ሴት በጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለት ሳምንት ሊደፍን የተቃረበውን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ አስራኤል እኣካሄደችው ባለው የአየር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር ወደ 3,800 መጠጋቱን የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ገለጹ።

    ዛሬ ሐሙስ 18ኛ ቀኑን በያዘው ግጭት ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር 3,785 መድረሱን የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ አሃዝ አስታውቋል።

    መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በእስራኤል ላይ መፈጸሙን ተከትሎ እስራኤል የቡድኑ መቀመጫ በሆነችው ጋዛ ላይ ያልተቋረጠ የአየር ድብደባ እየፈጸመች ነው።

    በዚህም ሳቢያ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ከተገደሉት 3,785 ሰዎች መካከል 1,524 ሕጻናት ሲሆኑ፣ 1,000 ደግሞ ሴቶች ናቸው፤ በተጨማሪ ደግሞ 120 አረጋውያን መገደላቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

    ከተገደሉት በተጨማሪም በአጠቃላይ 12,493 ሰዎች በተለያየ ደረጃ የአካል ጉዳት ደርሶናቸዋል።

  7. ዛሬ አስከ እኩለ ቀን ድረስ የነበሩ አራት ዋና ጉዳዮች

    ሱናክ በእስራኤል፡ የዩናይትድ ኪንግድም ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤል ገብተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያ ሁ እና ከፕሩዝዳንት አይሳክ ሄርዞግ ጋር ተወያይተዋል።

    እርዳታ፡ ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት የጫኑ ተሽክርካሪዎች የራፋህ የድንበር መተላለፊያ ይከፈታል በሚል ተስፋ እየተጠባበቁ ነው። አሜሪካ በመንገዱ ላይ ያሉ ችግሮች ከተጠገኑ በኋላ የመጀመሪያዎቹ 20 የጭነት መኪኖች ነገ አርብ ከግብፅ ወዳ ጋዛ ይገባሉ ብላለች።

    የአየር ጥቃት በጋዛ፡ ሌሊቱን በሙሉ የአየር ጥቃት መፈጸሟን የቀጠለችው፣ ባለፉት 24 ሰዓታት ጋዛ ውስጥ “በመቶዎች” የሚቆጠሩ ቦታዎችን ላይ ጥቃት መፈጸሟን እስራኤል ገልጻለች።

    ቀጣይ፡ እስራኤል የነበሩት የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከሰዓት በኋላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘዋል።

  8. “እስራኤል እንድታሸንፍ እንፈልጋለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

    የዩናይትድ ኪንግድም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እስራኤል ከሐማስ ጋር የምታደርገውን ጦርነት እንድታሸንፍ አገራቸው እንደምትፈልግ እና ድጋፍ እንደምታደርግ ተናገሩ።

    “በዚህ ጨለማ ጊዜ እዚህ ከእናንተ ጋር በመቆሜ ኩራት ይሰማኛል” በማለት “ከእናንተ ጋር በአጋርነት በመቆም እንድታሸንፉ እንፈልጋለን” ብለዋል።

    ሱናክ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እስራኤል እራሷን መካለከሏን እና ሐማስ ላይ የምትወስደውን እርምጃ አገራቸው እደምትደግፍ በመግለጽ ሰላማዊ ሰዎች ከጉዳት እንዲጠበቁ ጠይቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሐመስ እስራኤል ውስጥ ከእስራኤሉ አቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት አገራቸው በዚህ አስቸጋሪ ውቅት ከእስረኤል ጋር ትቆማለች ብለዋል።

    ሱናክ ጨምረውም “ሲቪሎችን ለጉዳት ከሚያጋልጠው ሐማስ አንጻር፣ እስራኤል ሲቪሎች እንዳይጎዱ ሁሉንም አይነት ጥንቃቄዎች” እንድምታደርግ እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

    በጋዛ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንታዳ መደንገጣቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ፣ በየትኛውም ቦታ ቢሆን በንጹሃን ሰዎች ሕይወት መጥፋት እንደሚያዝኑ ተናግረዋል።

    ፍልስጥኤማውያን ሲቪሎች የሐማስ ሰለባዎች መሆናቸውን አጽንኦት በመስጠትም፣ እስራኤል ወደ ጋዛ ሰርጥ እርዳታ እንዲገባ መወሰኗን ደግፈዋል።

    ዩናይትድ ኪንግድምም ለአካባቢው የምትሰጠውን እርዳታ እንድምትጨምር እና ለሕዝቡም ተጨማሪ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲደርሰው እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

  9. እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች እንደቀጠሉ ነው

    በደቡባዊ ጋዛ የተፈጸመው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ "የሐማስ መሰረተ ልማት ናቸው" ያለቻቸውን የጋዛ ሰርጥ ስፍራዎች በአየር መደብደቧን አስታውቃለች።

    እስራኤል ላለፉት አስራ ሁለት ቀናት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ ትገኛለች። በዚህም ከ3 ሺህ ሰዎች በላይ ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል።

    ምናልባትም በቀጣይ ቀናት እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዝ ልታስገባ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።

    በባለፉት ሰዓታት የአየር ጥቃቶች ከተፈጸመባቸው የተወሰኑት በምስል፦

    በደቡባዊ ጋዛ የተፈጸመው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EFE/REX/Shutterstock

    በደቡባዊ ጋዛ የተፈጸመው የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EFE/REX/Shutterstock

  10. የሚሳኤል ጥቃት በደረሰበት ሆስፒታል ካሉ ህሙማን 40 በመቶ ህጻናት ናቸው

    በሆስፒታሉ ላይ የደረሰው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የሚሳኤል ጥቃት በተፈጸመበት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን በተገደሉበት አል አህሊ ሆስፒታል ካሉ ህሙማን አርባ በመቶ ህጻናት መሆናቸውን በጋዛ የሚገኙ የህክምና ባለሙያ ተናገሩ።

    ከለንደን የመጡት ዶክተር ጋሳን አቡ ሲታህ ማክሰኞ ዕለት በአል አህሊ ሆስፒታል ላይ የሚሳኤል ጥቃት ሲደርስም በሆስፒታሉ ውስጥ ነበሩ።

    "ሆስፒታሉ በሚሳኤል ሲመታ በቀዶ ጥገና ውስጥ ክፍል ውስጥ ነበርኩ። የቀዶ ጥገና ክፍሉ ጣሪያም በላያችን ላይ ወደቀ" ሲሉም ተናግረዋል።

    "በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖች ነበሩ። የተቆራረጡ የሰውነት ክፍሎችም አይቻለሁ" ሲሉም የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ አስረድረዋል። የህክምና ባለሙያው በሆስፒታሉ ውስጥ ካሉት ውስጥ 40 በመቶዎቹ ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

    "በርካታ ልጆች ናቸው። ሁሉም በሚባል ሁኔታ አንድ ወይም ሁለት ወላጆቻቸውን ያጡ ናቸው። ለማገገም ረጅም፣ ረጅም ጉዞ ይጠብቃቸዋል" ሲሉም አስረድተዋል።

    ዶክተር ጋሳን አቡ ሲታህ
  11. በሐማስ የፖለቲካ ቢሮ የመጀመሪያ እና ብቸኛዋ የሆኑት ሴት መገደላቸው ተነገረ

    ጀሚላ አል ሻንቲ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ውስጥ የመጀመሪያዋ እና ብቸኛዋ ሴት የሆኑት ግለሰብ በእስራኤል አየር ጥቃት መገደላቸውን የፍልስጥኤም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ዋነኛ ውሳኔ ሰጪ አካል ነው።

    ጀሚላ አል ሻንቲ በሐማስ ውስጥ የሴቶችን ንቅናቄ መስራች ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2021 በፖለቲካው ቢሮው እንዲያገለግሉ የተመረጡ የመጀመሪያ ሴት ናቸው።

    ጀሚላ የሐማስ መስራች ከሆኑት አንዱ እና በህይወት የሌሉት አብደል አዚዝ አል ራንቲሲ ባለቤት ናቸው። በዘገባዎቹ ውስጥ የአየር ጥቃቱ ስለተካሄደበት ስፍራ ዝርዝር መረጃ አልተጠቀሰም።

  12. እስራኤልን ‘የሚጻረር’ ደብዳቤ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሶስት የህግ ተማሪዎች የስራ እድላቸውን አጡ

  13. ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ዩናይትድ ኪንግደም ከእስራኤል ጎን ናት አሉ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በዛሬው ዕለት ወደ እስራኤል ያቀኑት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አገራቸው ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም ተናገሩ።

    ዛሬ ጥቅምት 8/ 2016 በቴልአቪቭ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሱበትም ወቅት ሐማስ ያደረሰውን ጥቃት "ሊነገር የማይችል አሰቃቂ የሽብር ተግባር ነው" ሲሉ አውግዘውታል።

    አገራቸው ከእስራኤል ጎንም እንደምትቆም አጽንኦት በመስጠትም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ሱናክ ከእስራኤል "ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዚዳንት የማደርጋቸውን ስብሰባዎች በጉጉት እየጠበቅኩ ነው ውጤታማ እንደሚሆኑም ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም ተደምጠዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእስራኤል ቆይታቸው ከአመራሮቹ ጋር ተገናኝተው የሚመክሩ ሲሆን በቀጣናው የሚገኙ ሌሎች ሀገራትንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  14. “እስራኤል ብቻሽን አይደለሽም፣ አሜሪካ ከጎንሽ አለች” ፕሬዝዳንት ባይደን

    ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በእሰራኤል ጉብኝታቸው ወቅት አገራቸው ለእሰራኤል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ እና አብራት እንደምትቆም ተናግረዋል።

    ባይደን መካከለኛው ምሥራቅን እንዲሁም ቀሪውን ዓለም ያሳሰበው የእስራኤል ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሳምንት በኋላ ወደ እስራኤል ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር ተነጋግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ ላይ አሜሪካ በየትኛው ጊዜ ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም “እስራኤል፣ ብቻሽን አይደለሽም” በማለት አሜሪካ “በጨለማ ቀናቶች ሁሉ አብራሽ ትራመዳለች” በማለት የአገራቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

    ጨምረውም እስራኤል ደኅንነቷ የተጠበቀ አይሁዳዊት እና ዴሞክራሲያዊ ሆና “ዛሬ፣ ነገ እና አስከ መጨረሻው” ትዘልቃለች ብለዋል።

    ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት በተመለከተም “ለጥቃቱ ምንም ይቅርታ አይኖርም፤ የተፈጸመው ጭካኔ በየትኛውም የዓለም ክፍል ከባድ ቁስልን ፈጥሯል” በማለት ጥቃቱ የተፈጸመበት ዕለት ከአይሁዳውያን እልቂት በኋላ እጅግ አስከፊው ነው ብለውታል።

    ከሐማስ ጥቃት አንጻርም “ዛሬ፣ ነገ፣ እስከ መቼውም ድረስ ቢሆን ምንም ሳናደርግ ቆመን አንመለከትም” ብለዋል ባይደን።

    በሐማስ የታገቱ ሰዎችን በሚመለከትም ከታጋች ቤተሰቦች ጎን በመሆን “ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው።”

    እስራኤል በድጋሚ ለአይሁዳውያን ሕዝቦች የደኅንነት ቦታ እንድትሆን አሜሪካ “ባላት አቅም ሁሉ የምትችለውን ታደርጋለች” በማለት ቃል ገብተዋል።

    ለዚህም በሳምንቱ ማብቂያ ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት ለእስራኤል ከዚህ በፊት “ያልተደረገ” የመከላከያ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

    በእስራኤል ላይ በሐማስ የተፈጸመውን ጥቃት ከ20 ዓመታት በፊት በአገራቸው ላይ ከተፈጸመው የመስከረም 11ዱ ጥቃት ጋር ያነጻጸሩት ባይደን፣ ጥቃቱ በብዙ እጥፍ ከዚያ የሽብር ጥቃት የላቀ ነው ብለዋል።

    ባይደን በተጨማሪም እስራኤልን ለማጥቃት የሚያስብ የትኛውም መንግሥት ወይም “ተቀናቃኝ ኃይል” ካለ እንዳይሞክረው አጽንኦት ሰጥተው አስጠንቅቀዋል።

    ጥቃቱ በእስራኤላውያን ላይ “ድንጋጤን፣ ህመምን፣ቁጣን” መፍጠሩን “እኔ እና አሜሪካውያን እንረዳዋለን” በማለት፤ ፍትሕ መስፈን እንዳለበት አመልክተው እስራኤላውያን በቁጣ እንዳይዋጡ አስጠንቅቀዋል።

    ፍልስጥኤማውያንን በተመለከተም “እነሱም በጣሙን ተጎድተዋል” ያሉት ባይደን፣ በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ ፍልስጥኤማውያን ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

    “በጋዛ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ የብዙዎች ሕይወት በመጥፋቱ ተቆጥቻለሁ፣ አዝኛለሁ። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ማስረጃዎች ጉዳቱ የደረሰው ጋዛ ውስጥ ባለ ሽብርተኛ ቡድን በተተኮሰ ሮኬት መሆኑን ያመለክታሉ” ብለዋል።

    ለጋዛ ነዋሪዎች ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት ያስፈልጋል ያሉት ባይደን “የእስራኤልን ካቢኔን ጠይቄ. . . ነፍስ አድን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ለሐማስ ሳይሆን ለጋዛ ሲቪሎች እንዲደርስ ቁጥጥር እየተደረገበት እንዲገባ ተስማምተዋል።”

    ለዚህም ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

  15. በጋዛ ሆስፒታል ፍንዳታ 471 ሰዎች ሲገደሉ 314 መቁሰላቸው ተረጋገጠ

    ጉዳት በደረሰበት ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ ምሽት ጋዛ ውስጥ በሚገኘው ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ 471 ሰዎች መገደላቸውን እና 314 መቁሰላቸውን አስታወቀ።

    ከባድ ውግዘት እና ውዝግብን ላስከተለው ፍንዳታ አስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም።

    ሐማስ አስራኤልን ሲከስ፣ እስራኤል ደግሞ የፍልስጥኤሙን ኢስላሚክ ጂሃድ ለፍንዳታው ተጠያቂ አድረጋለች።

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ማስረጃዎችን በማቅረብ በሰጡት መግለጫ ፍንዳታው ከእስራኤል በተተኮሰ መሳሪያ ሳይሆን ከጋዛ የተተኮሰ ነው ብለዋል።

    በፍንዳታው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፣ ቤተሰቦች ከፍንዳተው ስፍራ እስካሁን የሟቾችን አስከሬን እየሰበሰቡ ነው።

  16. አሜሪካ ከ60 በላይ አውሮፕላኖች የሚሸከም ሁለተኛ የጦር መርከቧን ወደ እስራኤል አንቀሳቀሰች

  17. “ቤታችንን በላያችን ላይ ቢያፈርሱትም የትውልድ ቀያችንን አንለቅም” የጋዛ ቤተሰቦች

  18. የጋዛ ሆስፒታል ጥቃት “በሌላኛው ቡድን የተደረገ ይመስላል” - ባይደን

    በ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለው በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ የደረሰወ ፍንዳታ “በሌላኛው ቡድን የተደረገ ይመስላል” ሲሉ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ረፋድ አምስት ሰዓት ገደማ ቴል አቪቭ ገብተዋል።

    ባይደን በክስተቱ “በጣም አዝኛለሁ፣ ተቆጥቻለሁ” ብለዋል።

    “ባየሁት ነገር ላይ በመመሥረት ጥቃቱ በእናንተ ሳይሆን በሌላ ቡድን የተደረገ ይመስላል። ነገር ግን እርግጠኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው ብዙ ነገሮችን ማለፍ አለብን” ሲሉ አክለዋል።

    ቢቢሲ በትናንት ምሽቱን የሆስፒታል ፍንዳታ ዙሪያ አንድ ዘገባ ለመሥራት መረጃዎችን በማጠናቀር ላይ ይገኛል። ሐማስ እና የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለጥቃቱ የእስራኤልን የአየር ጥቃትን ተጠያቂ አድርገዋል።

  19. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባልተለመደ ሁኔታ ጉብኝት ለማድረግ እስራኤል ገቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና ፕሬዝዳንት ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና ፕሬዝዳንት ባይደን

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ እስራኤል ገብተዋል።

    በእራኤል እና በጋዛ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሳምንት በኋላ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተጓዙት ፕሬዝዳንት ባይደን፣ ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊያቸውን ወደ አካባቢ ልከው ነበር።

    ግጭቱ እየተባባሰ እና የዓለም አገራትን ትኩረት መሳቡን ተከትሎ ባይደን እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንት አሁን ወደ ግጭት አካባቢ ያደረጉት ጉዞ ያልተለመደ ነው እየተባለ ነው።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ግጭቶች ወደ ሚካሄዱባቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ማስታወቂያ እምብዛም ጉብኝት ማድረጋቸው የተለመደ አይደለም።

    ፕሬዝዳንት ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የፍልስጥኤሙ መሪ ማህሙድ አባስን ጨምሮ ከዮርዳኖሱ ንጉሥ እና ከግብፅ ፕሬዝዳንት ጋር አማን ዮርዳኖስ ላይ የመወያየት ዕቅድ ነበራቸው።

    ነገር ግን ማክሰኞ ምሽት ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ከአረብ አገራት መሪዎቹ ጋር ያላቸው ስብሰባ ተሰርዟል።

    የፕሬዝዳንት ባይደን አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን
    የምስሉ መግለጫ, የፕሬዝዳንት ባይደን አውሮፕላን ኤር ፎርስ ዋን
  20. ባይደን ከአረብ መሪዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ ተሰረዘ

    በእሰራኤል ዛሬ (ረቡዕ) ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ባይደን ከዋሽንግተን ሲነሱ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, በእሰራኤል ዛሬ (ረቡዕ) ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ባይደን ከዋሽንግተን ሲነሱ

    ጋዛ ውስጥ ባለው ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከአረብ አገራት መሪዎች ጋር የነበራቸው ስብሰባ ተሰረዘ።

    ባይደን ዛሬ በእስራኤል በሚያደርጉት ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ከተወያዩ በኋላ፣ የዮርዳኖሱን ንጉሥ አብዱላህን፣ የግብፁን ፕሬዝዳንት አብደል ፋትህ አል ሲሲን እና የፍልስጥኤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስን በማግኘት ይወያያሉ ተብሎ ነበር።

    ነገር ግን ማክሰኞ ምሽት በጋዛ ሆስፒታል ላይ ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ በማድረግ ከባይደን ጋር የሚደረገው ውይይት “በፍልስጥኤማውያን ላይ የሚካሄደው ጦርነት እና ጭፍጨፋ” ሲቆም ብቻ የሚካሄድ ይሆናል ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ኃይል ግን ፍንዳታው የደረሰው በጋዛ ውስጥ ሐማስን ተከትሎ ዋነኛው ቡድን የሆነው የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ በተባለው አማካይነት መሆኑን ገልጿል።

    ወደ እስራኤል እየተጓዙ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በኤክስ (ትዊተር) ላይ “በፍንዳታው መቆጣታቸውን እና በጥልቅ ማዘናቸውን” አስፍረው፣ የብሔራዊ ደኅንነት ቡድናቸው “በትክክል ምን እንደተከሰተ ለማወቅ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን መሰብሰብ እንዲቀጥሉ” ማዘዛቸውን ገልጸዋል።