ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የእስራኤል ጋዛ ጦርነት ዋና ክስተቶች

ልክ የዛሬ ሁለት ሳምንት ሐማስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ከባድ ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት እንደቀጠለ ነው። አስካሁን በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤላውያን በኩል ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱን ዋጋ እየከፈሉ ነው። ለአጭር ጊዜ በቆየው የሐማስ ጥቃት ከ1400 በላይ እስራኤላውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎች ተገድለዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ብሊንከን ወደ እስራኤል ተመለሱ

    ከአራት ቀናት በፊት እስራኤልን ጎብኝተው የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በዛሬው ዕለት ተመልሰው መጥተዋል።

    ብሊንከን በጋዛ ላይ ስላለው ግጭት ከእስራኤል አመራሮች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ይጠበቃል።

    ብሊንከን አሜሪካ ለእስራኤል ያላትን ድጋፍ ለማሳየት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እለት ወደ ቴልአቪቭ አቅንተው የነበረ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ስድስት የአረብ አገራት በማቅናት ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን አድርገዋል።

    ፕሬዚዳንት ባይደንም ከእስራኤል በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት በሚቀጥሉት ቀናት አገሪቱን ይጎበኛሉ የሚል ግምት አለ።

  2. 500 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙት እና ወደ እስራኤል የሚያሻግሩት የሐማስ ዋሻዎች

  3. የእስራኤል ጦር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ገለጸ

    የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ምንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ገለጸ። በግብጽ እና ጋዛ ያለው የድንበር ማቋረጫ መከፈቱ ጋር በተያያዘ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚኖር የግብጽ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ መዘገቡን ተከትሎም ነው ጦሩ ይህንን አስተያየት የሰጠው።

    "እኔ የማውቀው ምንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነት የለም። የሚወጡ ዘገባዎችን እያየሁ ነው። ምንም የማረጋግጠው ነገር የለም" ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃለ አቀባይ ኮሎኔል ሪቻርድ ሄክት ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትም እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ ውድቅ አድርጓል።

    "በአሁኑ ወቅት ከጋዛ የውጭ አገር ዜጎችን በግብጽ ድንበር በኩል ለማስወጣት የተደረገ የተኩስ አቁም እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ ስምምነት የለም" ሲልም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በመግለጫው አትቷል።

    የሐማስ ሚዲያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በደቡባዊ ጋዛ ተደረሰ ስለተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሳላማ ማሩፍ በጋዛ እና ግብጽ መካከል ያለው የድንበር ማቋረጫን መከፈቱን በተመለከተ ከግብጽ በኩል ምንም ማረጋገጫ እንዳላገኙ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

    ሮይተርስ አሜሪካ፣ እስራኤል እና ግብጽ በደቡባዊ ጋዛ በኩል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሁለት የግብጽ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቦ ነበር።

    ስምምነቱ የሚደረገው በጋዛ እና ግብጽ መካከል ያለው የራፋህ ድንበር ማቋረጫ መከፈት ጋር በተያያዘም እንደሆነ አስነብቧል።

  4. ለጋዛ የሚሆን እርዳታ በግብጽ ድንበር በኩል ሊገባ ይችላል ተባለ

    በጋዛ ሰርጥ እና ግብጽ መካከል ያለው የድንበር ማቋረጫ ለአጭር ጊዜ ሊከፈት እንደሚችል የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እሁድ ዕለት ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በግብጽ ቁጥጥር ስር ያለው ድንበር ወደ ጋዛ ዕርዳታ ለማድረስ እንደሚከፈት ተናግረዋል። ሆኖም መቼ እንደሚከፈት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

    የእስራኤልን ሰሜናዊ ጋዛ ለቃችሁ ውጡ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጥኤማውያን ወደ ደቡብ መሰደዳቸውን የመከላከያ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

    ቢቢሲ ይህንን አኃዝ ማረጋገጥ አይችልም።

    በሙሉ ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ ሁኔታዎች እየከፉ ነው። ውሃ፣ ምግብ፣ ኃይል እና መድኃኒቶች አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመነ ነው።

    በጋዛ ሆስፒታሎች ያለው መጠባበቂያ ነዳጅ በ24 ሰዓታት ውስጥ ተሟጦ ሊያልቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቆ በሺዎች የሚቆጠሩ ህሙማንንም ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅም አሳስቧል።

  5. ኻን ዩኒስ፡ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነባት የጋዛ ከተማ

  6. የ6 ዓመቱ ታዳጊ በጸረ ሙስሊም ጥቃት መገደሉን የአሜሪካ ፖሊስ አስታወቀ

  7. የጋዛ ሆስፒታሎች መጠባበቂያ ነዳጃቸው በ24 ሰዓታት ተሟጦ ያልቃል- ተመድ

    በጋዛ ሆስፒታሎች ያለው መጠባበቂያ ነዳጅ በ24 ሰዓታት ውስጥ ተሟጦ ሊያልቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠነቀቀ።

    “የመጠባባቂያ ጄነሬተሮችን ማቋረጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህሙማንን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል” ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በድረገጹ አስፍሯል።

    በሙሉ ከበባ ላይ ባለችው ጋዛ ውሃ፣ ምግብ፣ ሃይል እና መድኃኒት አቅርቦት እየተመናመነ የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶችም ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ መዳረሻዎች እንዲከፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    በጋዛ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የህክምና ባለሙያ ዶክተር አቡ ሲታ በሆስፒታላቸው ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ህሙማንን ለመርዳት በቂ መሳሪያ እንደሌላቸው አስጠንቅቀዋል።

    የድንገተኛ ህሙማን ቁጥር በማሻቀቡም “በየቀኑ ለአንድ ወር ወይም ከአንድ ወር ተኩል በላይ ሊያገለግሉ የሚችሉ የሚችሉ የህክምና ቁሳቁሶችን እየተጠቀምን እንገኛለን” ብለዋል።

  8. እስራኤል በጋዛ ላይ በምታካሂደው የእግረኛ ጦር ዘመቻ ምን ማድረግ ትፈልጋለች?

  9. የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሰላማዊ ሰዎች ስቃይ ተጠያቂው ሐማስ ነው አሉ

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊይ ሰላማዊ ሰዎች ለስቃይ ለመዳረጋቸው ተጠያቂው ሐማስ ነው አሉ።

    ሚኒስትሩ ይህ ያሉት ዛሬ ጠዋት ዩኬ የእስራኤል መንግሥት ጥቃቱን እንዲቀጥል ደግፋ እንደሆነ በተጠየቁበት ወቅት ነው።

    ሚኒስትሩም ሲመልሱ “ለፍልስጥኤማውያን ስቃይ ተጠያቂው ሐማስ ነው” ብለዋል።

    ሆኖም በተለይ እስራኤል የምድር ጥቃት ከመጀመሯ ቀደም ብሎ በጋዛ እየደረሰ ያለው ሞት እንዳሳሰባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደችው ባለው የቦምብ ዘመቻ ከ2 ሺህ 300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፍልጥኤም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    ክሌቨርሊይ “ እስራኤል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የመቀነስ ግዴታ አለባት።በዚህ ጉዳይ ላይም ከእስራኤል መንግሥት ጋር በነበረኝ ውይይት ይህንኑ አንስቻለሁ” ብለዋል።

    የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሰላማዊ ሰዎች ከሰሜናዊ ጋዛ ወደ ደቡብ እንዲሄዱ መገደዳቸው እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል ማለታቸውን ተከትሎም ዩኬ በእስራኤል ላይ የጦር ወንጀል ክስ አንስታ እንደሆነም ሚኒስትሩ ተጠይቀው ነበር።

    “የዩኬ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ሕግ መከበር ቁርጠኛ አቋም ነው ያለው” ሲሉ የእንግሊዝ መንግሥት እስራኤል የምትፈፅመውን ጥሰትም ዝም ብሎ እንደማያልፍ ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ በመጨረሻም የዩኬ መንግሥት በግብፅ እና በጋዛ ሰርጥ መካከል ያለውን የራፋህ መሻገሪያን ለመክፈት ከግብፅ እና ከእስራኤል ጋር እየተነጋገረ መሆኑን፤ ነገር ግን እስካሁን አለመሳካቱን ተናግረዋል።

  10. የእስራኤል መከላከያ ኃይል የኪቡትዝን ጥቃት የመራውን የሐማስ አዛዥ ገድያለሁ አለ

    የእስራኤል ጦር በደቡባዊ የጋዛ ከተማ ካን ዮኒስ የሚገኙ የሐማስ ኃይሎች አዛዥ የሆነውን ቢላል አል ከድራን መግደሉን አስታወቀ።

    ጦሩ ይህን ያለው እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የአየር ድብደባ በቀጠለችበት ወቅት ነው።

    እስራኤላውያን ባለፈው ቅዳሜ የሐማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በመግባት ድንገተኛ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ በደቡብ እስራኤል ኪቡትዝ ኒሪም ለተፈፀመው የጅምላ ግድያ ቢላል አል ከድራ ተጠያቂ ነው ብለዋል።

  11. 126 እስራኤላውያን በጋዛ ታግተው እንዳሉ ጦሩ አስታወቀ

    ሐማስ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት 279 ወታደሮቿ መገደላቸውን ያስታወቀው የእስራኤል ጦር 126 ታጋቾች ተወስደዋል ብሏል።

    በጥቃቱ ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች እየፈጸመች ሲሆን በነዚህ ጥቃቶች 13 እስራኤላውያን ታጋቾች መገደላቸውን ሐማስ ከዚህ ቀደም አስታውቋል።

    እስራኤል በዚህ ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።

    ቀደም ሲል ወደ 150 የሚጠጉ ሰዎች ታግተው እንደነበር አስታውቃ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል የታጋቾች ቁጥር 126 መሆኑን ገልጿል።

  12. በሰሜን እስራኤል ከሊባኖስ በተተኮሰ ሚሳኤል አንድ ሰው ተገደለ

    በሰሜን እስራኤል ከሊባኖስ በተወነጨፈ ሚሳኤል አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አስታውቋል።

    በሊባኖስ እና በእሰራኤል ድንበር ላይ ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱም ተነግሯል። እስራኤል የተገደለው እንዲሁም የቆሰሉት ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን አስታውቃለች።

    የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ሽቱላ በተሰኝው የድንበር ከተማ ላይ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፉን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ በከባድ መሳሪያ የታገዘ የጥቃት ምላሽ እንደሰጠም አስታውቋል። ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እስራኤል እና ሄዝቦላህ የሮኬቶች እና የከባድ መሳሪያ ልውውጥ አድርገዋል።

  13. ሰበር, እስራኤል ከሰሜን ጋዛ ለሚሸሹ አንደኛውን መንገድ ለሶስት ሰዓታት ከኢላማ ውጭ እንደምታደርገው አስታወቀች

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የምታደርገውን የምድር ላይ ጥቃት ከመጀመሯ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከሰሜን ጋዛ እየሸሹ ይገኛሉ።

    በሰሜን ጋዛ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ድረስ ወጥተው ወደ ደቡባዊ ጋዛ ማምራት እንዳለባቸው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አዲስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ነዋሪዎች ከቤይት ሃኑን ወደ ክሃን ዩንስ የሚወስደውን መስመር ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሶ በእነዚያ ሰዓታት ውስጥ መንገዱ ከኢላማ ውጭም እንደሚሆንም አስፍሯል።

    እስራኤል በሰሜን ጋዛ ለሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሄዱ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅትም ሁለት መንገዶችን መጠቀም አለባቸው ብላ ነበር።

    በሰሜን ጋዛ ያሉ ሆስፒታሎችም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት የእስራኤልን ውጡ ማስጠንቀቂያ በሆስፒታል ያሉ ህሙማንን አስገድዶ ማስወጣት "የሞት ፍርድ ነው" ሲል አውግዞታል

  14. ጋዛን ለቀው እየወጡ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት የምናውቀው

  15. በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ከ2 ሺህ 300 በላይ ሆነ

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እየፈጸመችው ባለችው የአየር ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ከ2 ሺህ 300 በላይ መሆኑን የፍልስጥኤም ጤና ኃላፊዎች ተናግረዋል።

    በአየር ጥቃቶች 2 ሺህ 329 ፍልስኤማውያን ሲገደሉ 9 ሺህ 714 ሰዎች ደግሞ እንደቆሰሉ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ሐማስ በሰነዘረው ጥቃት ስምንት ቀናትን አስቆጥሯል።

    በዚህ ጥቃት 1 ሺህ 300 እስራኤላውያን ተገድለዋል። እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ነው በሚል በጋዛ ሰርጥ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እየፈጸመችው ካለችው የአየር ጥቃት በተጨማሪ እግረኛ ጦሯን ለማስገባት ዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጻለች።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግንባር ላሉ ወታደሮቻቸው "ቀጣዩ ሂደት እየመጣ ነው" ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር ጋዛ ሰርጥን በሙሉ ከበባ ውስጥ እንድትገባ በማድረግም ውሃ፣ ምግብ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መቋረጡንም ከቀናት በፊት አስታውቋል።

  16. በእስራኤል- ጋዛ የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

    የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት ከተከሰተ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል። በሳምንቱ የተከሰቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንቃኝ

    • የእስራኤል ጦር በጋዛ በአየር፣ በባህር እና በመሬት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመፈጸም ወታደራዊ ዝግጅት ማድረጉን የገለጸ ሲሆን እግረኛ ጦሩም ወደ ጋዛ ዘልቆ እንደሚገባም እየተጠበቀ ነው።
    • እስራኤል በሰሜን ጋዛ የሚኖሩ 1.1 ሚሊዮን ፍልስጥኤማውያን ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲወጡ ማስጠንቀቋን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተሽከርካሪዎች እና በእግራቸው እየሸሹ ይገኛሉ።
    • በሰሜን ጋዛ ያሉ ሆስፒታሎችም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።የዓለም ጤና ድርጅት የእስራኤልን ውጡ ማስጠንቀቂያ በሆስፒታል ያሉ ህሙማንን አስገድዶ ማስወጣት "የሞት ፍርድ ነው" ሲል አውግዞታል
    • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዲሁም የፍልስጥኤም መሪ ማህሙድ አባስን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረዋል።
    • ሐማስ ከሳምንት በፊት በከፈተው ጥቃት 1 ሺህ 300 ሰዎች ተገድለዋል፤ 150 ሰዎች ታግተዋል።
    • እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ እያካሄደችው ባለው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጥኤም ባለስልጣናት ተናግረዋል።
  17. በዩኬ ለፍልስጥኤም ድጋፋቸውን ለመግለጽ በሺዎች የሚቆጠሩ አደባባይ ወጡ