የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በእሰራኤል ጉብኝታቸው ወቅት አገራቸው
ለእሰራኤል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ እና አብራት እንደምትቆም ተናግረዋል።
ባይደን መካከለኛው ምሥራቅን እንዲሁም ቀሪውን ዓለም ያሳሰበው የእስራኤል
ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሳምንት በኋላ ወደ እስራኤል ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር ተነጋግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ ላይ አሜሪካ በየትኛው ጊዜ ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም
“እስራኤል፣ ብቻሽን አይደለሽም” በማለት አሜሪካ “በጨለማ ቀናቶች ሁሉ አብራሽ ትራመዳለች” በማለት የአገራቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
ጨምረውም እስራኤል ደኅንነቷ የተጠበቀ አይሁዳዊት እና ዴሞክራሲያዊ ሆና “ዛሬ፣
ነገ እና አስከ መጨረሻው” ትዘልቃለች ብለዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት በተመለከተም “ለጥቃቱ ምንም ይቅርታ
አይኖርም፤ የተፈጸመው ጭካኔ በየትኛውም የዓለም ክፍል ከባድ ቁስልን ፈጥሯል” በማለት ጥቃቱ የተፈጸመበት ዕለት ከአይሁዳውያን እልቂት
በኋላ እጅግ አስከፊው ነው ብለውታል።
ከሐማስ ጥቃት አንጻርም “ዛሬ፣ ነገ፣ እስከ መቼውም ድረስ ቢሆን ምንም ሳናደርግ
ቆመን አንመለከትም” ብለዋል ባይደን።
በሐማስ የታገቱ ሰዎችን በሚመለከትም ከታጋች ቤተሰቦች ጎን በመሆን “ታጋቾቹ
ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው።”
እስራኤል በድጋሚ ለአይሁዳውያን ሕዝቦች የደኅንነት ቦታ እንድትሆን አሜሪካ
“ባላት አቅም ሁሉ የምትችለውን ታደርጋለች” በማለት ቃል ገብተዋል።
ለዚህም በሳምንቱ ማብቂያ ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት ለእስራኤል ከዚህ በፊት
“ያልተደረገ” የመከላከያ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
በእስራኤል ላይ በሐማስ የተፈጸመውን ጥቃት ከ20 ዓመታት በፊት በአገራቸው
ላይ ከተፈጸመው የመስከረም 11ዱ ጥቃት ጋር ያነጻጸሩት ባይደን፣ ጥቃቱ በብዙ እጥፍ ከዚያ የሽብር ጥቃት የላቀ ነው ብለዋል።
ባይደን በተጨማሪም እስራኤልን ለማጥቃት የሚያስብ የትኛውም መንግሥት ወይም
“ተቀናቃኝ ኃይል” ካለ እንዳይሞክረው አጽንኦት ሰጥተው አስጠንቅቀዋል።
ጥቃቱ በእስራኤላውያን ላይ “ድንጋጤን፣ ህመምን፣ቁጣን” መፍጠሩን “እኔ እና
አሜሪካውያን እንረዳዋለን” በማለት፤ ፍትሕ መስፈን እንዳለበት አመልክተው እስራኤላውያን በቁጣ እንዳይዋጡ አስጠንቅቀዋል።
ፍልስጥኤማውያንን በተመለከተም “እነሱም በጣሙን ተጎድተዋል” ያሉት ባይደን፣
በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ ፍልስጥኤማውያን ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
“በጋዛ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ የብዙዎች ሕይወት በመጥፋቱ ተቆጥቻለሁ፣
አዝኛለሁ። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ማስረጃዎች ጉዳቱ የደረሰው ጋዛ ውስጥ ባለ ሽብርተኛ ቡድን በተተኮሰ ሮኬት መሆኑን ያመለክታሉ” ብለዋል።
ለጋዛ ነዋሪዎች ምግብ፣ ውሃ እና መድኃኒት ያስፈልጋል ያሉት ባይደን “የእስራኤልን ካቢኔን ጠይቄ. . . ነፍስ አድን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ለሐማስ ሳይሆን ለጋዛ ሲቪሎች እንዲደርስ
ቁጥጥር እየተደረገበት እንዲገባ ተስማምተዋል።”
ለዚህም ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እየሰሩ
መሆናቸውንም አመልክተዋል።