ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በደረሰ ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠሩ
ፍልስጥኤማውያን ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ተነገረ።
ለጥቃቱ ሐማስ የእስራኤል የአየር ጥቃት ምክንያት ነው ሲል፣ እስራኤል ደግሞ
የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለው ቡድን የተኮሰው ሮኬት ኢላማውን ስቶ ሆስፒታሉ ላይ በመውደቁ ነው ብላለች።
ነገር ግን እስራኤልም ሆነች ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ከቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ ቡድን
የሆነው እስላማዊ ጂሃድ ለጥቃቱ ተጠያቂ አለመሆናቸውን አስተባብለዋል።
በሐማስ በምትተዳደረው ጋዛ ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት እንዳሉት ሆስፒታሉ ላይ በደረሰው
የፍንዳታ ጥቃት 500 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።
ሐማስ ድርጊቱን በእስራኤል የተፈጸመ “የጦር ወንጅል” ያለው ሲሆን፣ የተለያዩ
አገራት መሪዎች በሆስፒታሉ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ለጠፋው ሕይወት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የዮርዳኖስ፣ የግብፅ እና የፍልስጥኤም መሪዎች ዛሬ ረቡዕ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ
ባይደን ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባም ተሰርዟል።
ጆ ባይደን ለእስራኤል አጋርነታቸውን ለማሳየት እና ግጭቱ እንዲያበቃ ለማገዝ ዛሬ
በእስራኤል ጉብኝት በማድረግ ከአገሪቱ መሪዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሐማስ እና የሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ በሆስፒታሉ ላይ ለተፈጸመው የፍንዳታ
ጥቃት አሜሪካ ከአስራኤል ጋር የጥፋቱ ተጋሪ ናት ሲሉ ከሰዋል።
ሌሊቱን ቤይሩት ውስጥ ከአሜሪካ ኤምባሲ ውጪ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈበት የተቃውሞ
ሰልፍ ተካሂዷል።