ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ የኑክሊየር ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዙ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው ሠራዊት የኑክሌር ኃይል ‘በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ’ እንዲቆም አዘዙ። ፕሬዝዳንት ፑቲን የአገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉን ጨምሮ ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ተገቢ ያልሆነ” እርምጃ እና “ሕገ ወጥ ማዕቀብ” መጣላቸውን ተናግረዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ አቋረጠች

    የሩሲያን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ኪዬቭ ከሞስኮ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ ማቋረጧን አስታወቀች።

    ይህ የተገለጸው የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎደሚየር ዜሌኒስኪ በሰጡት መግለጫ ነው።

    ፕሬዝደንቱ በዚህ መግለጫቸው ፍላጎት ያላቸውን የዩክሬን ዜጎች በሙሉ መንግሥታቸው እንደሚያስታጥቅ ተናግረዋል።

    ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ለሲቪል ዜጎቿ መሠረታዊ ወታደራዊ ስልጠና ስትሰጥ ቆይታለች።

  2. አየር መንገዶች የዩክሬንን የአየር ክልል መጠቀም አቆሙ

    የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ አየር መንገዶች የዩክሬንን የአየር ክልል ከመጠቀም ተቆጥበዋል።

    የሩሲያ ጥቃት መጀመርን ተከትሎ ዩክሬን ለሲቪል በረራዎች የአየር ክልሏ ዝግ መሆኑን አስታውቃለች።

    ቀደም ሲል ዩክሬን በረራዎችን አቋርጣ ነበር። የአገሪቱ የቪዬሽን ባለስልጣን “አየርክልሉየሲቪልበረራንለአደጋሊያጋልጥስለሚችልበረራእንዲቋረጥተደርጓል” ሲልመግለጫአውጥቶ ነበር።

    የዩናይትድ ኪንግደም የትራንፖርት ሚኒስትር የአገሪቱ አየር መንገዶች የዩክሬንን የአየር ክልል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

  3. ስለ ወረራው እስካሁን ድረስ የምናውቀው

    ሩሲያ ዩክሬንን ወራለች የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ የተፈጠረው ምንድን ነው?

    • በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ሲነጋጋ 11፡ 55 ላይ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ምሥራቃዊ ዶንባስ ግዛት “ወታደራዊ ዘመቻ “ እንደሚካሄድ አስታወቁ።
    • ሩሲያ ራሷን ለመከላከል ይህንን ወታደራዊ ዘመቻ እንደከፈተች ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬን ወታደሮች መሣሪያቸውን እንዲያስቀምጡ አሳስበዋል። በሩሲያ ላይ በማንኛውም የውጭ ኃይሎች የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች “ፈጣን” ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።
    • ሩሲያ የዩክሬንን መሠረተ ልማቶችን በሚሳኤል መምታቷን ዩክሬን አስታውቃለች። ዩክሬን በምላሹ የሩሲያ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ብትገልጽም የሞስኮ ባለሥልጣናት ይህንን አልተቀበሉትም።
    • ወታደሮች የጫኑ መኪኖች እና ታንኮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዩክሬን ገብተዋል። ወታደሮችን የጫነ መኪና በአጎራባቿ ቤላሩስ አልፎ በዋና መዲናዋ ኪየቭ በስተሰሜን በኩል ተሻግሯል። ሌላኛው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ ከዩክሬን በወሰደቻች ክሬሚያ ግዛት በኩል በደቡብ ገብቷል።
    • እስካሁን በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
    • የፈሩ ነዋሪዎች ከዋና ከተማዋን ኪየቭ ለመሸሽ ሲሞክሩም ረዥም የትራፊክ መጨናነቅ አጋጥሟል። ሌሎች ነዋሪዎች በየባቡር ጣቢያዎች ጊዜያዊ መጠለያዎችን በመሻት ላይ ናቸው። የቢቢሲ ዘጋቢዎች እንደተናገሩት ነዋሪዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ቢጠብቁም የወረራው መጠን ግን አስገርሟቸዋል።
    • ዩክሬን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (ወታደራዊ ሕግን) አውጃለች። የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያን ከዓለም አቀፍ የስዊፍት የገንዘብ ማስተላለፊያ ሥርዓት ማገድን ጨምሮ ጥብቅ ማዕቀቦች እንዲጣልባት ጠይቀዋል ።
    • ወረራውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በሰባት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ደርሷል። የሩስያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል በዶላር፣ በዩሮ እና በፓውንድ ያለው ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆል አሳይቷል።
    • ወራራውን የዓለም መሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያወገዙት ይገኛሉ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱ “አሰቃቂ የሕይወት ጥፋት” ያስከትላል ብለዋል። የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የደረሰው ያልተጠበቀ ጥቃት በጣም እንዳስደነግጣቸው ተናግረዋል።
  4. ዩክሬን የሲቪል በረራዎችን አቋረጠች

    የዩክሬን በረራ ቁጥጥር የሲቪል በረራዎች እንደቆሙ አስታወቀ።

    የአገሪቱ የአየር ክልል ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ ነው ውሳኔው የተላለፈው።

    “የአየር ክልሉ የሲቪል በረራን ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በረራ እንዲቋረጥ ተደርጓል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

    በሌላ በኩል ጡረታ ለወጡ የቀድሞ የዩክሬን ወታደሮች መሣሪያ እየታደለ እንደሚገኝ ዘገባዎች እየወጡ ነው።

    ዩክሬን ዜጎቿ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪም አቅርባለች።

  5. በበርካታ ስፍራዎች ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው

    በዩክሬን በተከፈተው ጦርነት በበርካታ ስፍራዎች ላይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆናቸው ተገልጿል።

    ኪየቭ እና ካርኪቭን ጨምሮ በተለያዩ የዩክሬን ግዛቶች የሚሳኤል ጥቃቶች እና ፍንዳታዎች ተዘግበዋል።

    ፑቲን ከረፋዱ በሰጡት የቴሌቭዥን መግለጫ ሩሲያ ዩክሬንን ወራ የመቆጣጠር እቅድ እንደሌላት በመግለጽ ወታደሮቿ መሳሪያ እንዲያስረክቡ ጠይቀዋል።

    ሆኖም ከትንሽ ቆይታ በኋላ በዩክሬን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል።

    ዩክሬን በበኩሏ በሩሲያ ላይ "ሙሉ ወረራ" ፈፅማለች ብላለች።

  6. “ሩሲያ እጅግ ጥብቅ ማዕቀብ ይጠብቃታል”

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ኃላፊ ጄምስ ከልቭሊ “ሩሲያ ያልጠበቀችው እጅግ ጥብቅ ማዕቀብ ይጠብቃታል” አሉ።

    እነዚህ ማዕቀቦች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚተገበሩ ተገልጿል።

    ከዚህ ቀደም ሩሲያ ላይ ከተጣሉ ማዕቀቦች ባጠቃላይ ይህኛው እጅግ የከበደ ነው ተብሏል።

    “ዩክሬናውያን ዩኬ ከእናንተ ጎን መቆሟን እወቁ” ብለዋል ኃላፊው።

    የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሴላ ቮን ደር ሌይን “ቭላድሚር ፑቲን ጦርነትን ወደ አውሮፓ መልሰው አምጥተዋል” ሲሉ ኮንነዋል።

    በአውሮፓ ኅብረት የሚጣሉት ጠንካራ ማዕቀቦች የሩሲያን ምጣኔ ሀብት እንደሚያሽመደምዱም ተናግረዋል።

  7. በሩሲያ የቦምብ ጥቃት የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዩክሬን አስታወቀች

    በሩሲያ ኃይሎች በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዩክሬን ፖሊስ አስታወቀ።

    እስካሁን ድረስ ሰባት ሰዎች መሞታቸውና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸው የተገለጸ ቢሆንም ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል።

    ጥቃቱ የደረሰው ከኦዴሳ ግዛት ውጭ በሚገኘው በፖዲልስክ በሚገኝ ወታደራዊ ክፍል መሆኑንም ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

    በዚህም ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲሞቱ በማሪፖል ከተማ ደግሞ አንድ ሰው መሞቱን ጨምረው ገልጸዋል።

    ከሞቱትና ከቆሰሉት በተጨማሪ 19 ሰዎችም ጠፍተዋል።

  8. ሩሲያ ስለምን ጦሯን ወደ ዩክሬን ለማዝመት ፈለገች? ፑቲንስ ፍላጎታቸው ምንድነው?

    ለወራት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር ስለማቀዳቸው ሲያስተባብሉ ነበር። አሁን ግን የሠላም ስምምነትን አፍርሰው ጦራቸውን በአማፂያን ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሁለት የምስራቃዊ ዩክሬን ክልሎችን እንዲዘምቱ አዘዋል።

    ምክንያታቸው ደግሞ "ሠላምን ለማስፈን" የሚል ነው።

    ሩሲያ ባለፉት ጥቂት ወራት ቢያንስ 150 ሺህ ወታደሮቿን በዩክሬን የድንበር አካባቢዎች አሰማርታለች። የአሁኑ እርምጃ ለአዲሱ ወረራ የመጀመሪያ ምልክት ነው ተብሎም ተሰግቷል። ቀጥሎ የሚሆነው ነገር የአውሮፓን የደህንነት መዋቅር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።

    የሩሲያ ወታደሮች ወደ የት ነው ተላኩ? ለምን? ዝርዝሩን ያንብቡሩሲያ ስለምን ጦሯን ወደ ዩክሬን ለማዝመት ፈለገች? ፑቲንስ ፍላጎታቸው ምንድነው?

  9. አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ተመድና ኔቶ ሩሲያን ኮነኑ

    የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አመራሮች ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት መክፈቷን አወገዙ።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ኦፕሬሽኑ የዩክሬንን የታጠቀ ኃይል ለማርገብ ያለመ ነው” ብለዋል።

    ኪየቭ እና ካሃሪክቭን ጨምሮ ወደተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ሚሳኤል ተተኩሷል።

    የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተባበሩት መንግሥታት የሩሲያን ወረራ ለመግታት “የቻለውን ሁሉ ማድረግ ይገባዋል” ሲሉ ተማጽነዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን አውግዘው ሩሲያ የእጇን እንደምታገኝ ዝተዋል።

  10. የሩሲያን ጥቃት መክፈት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቀበ

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምሥራቃዊ ዩክሬን ላይ “ወታደራዊ ዘመቻ” መጀመሩን መግለጻቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

    በዚህም ሳቢያ በሰባት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ አሻቅቧል።

    ውጥረትና ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን እንደሚቀጥል ተነግሯል።

    የነዳጅ ዘይት ዋጋ ውዝግቡ በተባባሰባቸው ባለፉት ቀናት ውስጥ በየዕለቱ እየጨመረ ሄዶ ነው አሁን ከአንድ መቶ ዶላር በላይ የደረሰው።

    ከነዳጅ በተጨማሪ የወርቅ ዋጋም ባለፉት ዓመታት ከታየው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    ከሳዑዲ አረቢያ በመቀጠል በዓለም ሁለተኛዋ የነዳጅ ዘይት አምራች የሆነችው ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት ምዕራባውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

  11. ዩክሬን የሩሲያን አውሮፕላኖች መታ መጣሏን አስታወቀች

    ዩክሬን አምስት የሩሲያ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች መታ እንደጣለች አስታወቀች።

    የዩክሬን መከላከያ “ተረጋጉና በዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ተማመኑ” ሲል መገለጫ አውጥቷል።

    የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ አውሮፕላንም ይሁን ሄሊኮፕተር በዬክሬን ተጥሏል መባሉን አጣጥሏል።

    የሩሲያን የሚሳኤል ጥቃት ተከትሎ የዩክሬን መዲና ኪየቭ ነዋሪዎች እየሸሹ ይገኛሉ።

    ዩክሬንም ሩሲያ ላይ ‘ከባድ ማዕቀብ’ እንዲጣል መጠየቋን ቀጥላለች።

  12. ሩሲያ ላይ ‘ከባድ ማዕቀብ’ እንዲጣል ዩክሬን ጠየቀች

    የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደሚይቶ ኩሌባ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሩሲያ ላይ ‘ከባድ ማዕቀብ’ እንዲጥል አሳሰቡ።

    ሩሲያ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ “ለአውሮፓ እና ለዓለም ደኅንነት ሲል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት” ብለዋል።

    ስዊፍት የተባለውን የገንዘብ መለዋወጫ ሥርዓት ሩሲያ እንዳትጠቀም ማገድን ጨምሮ የተለያዩ ማዕቀቦች በአፋጣኝ እንዲጣሉም ጠይቀዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዓለም ለዩክሬን ሰብአዊ እርዳታ እና መሣሪያ በማቅረብ ሩሲያን እንዲቃወምም አሳስበዋል።

  13. የኪየቭ ነዋሪዎች እየሸሹ ነው

    ሩሲያ የመጀመሪያዎቹን ሚሳዔሎች ወደ ዩክሬን መተኮሷን ተከትሎ የመዲናዋ ኪየቭ ነዋሪዎች እየሸሹ ይገኛሉ።

    ኪየቭ ውስጥ የአደጋ ጊዜ ጠቋሚ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ መዲናዋን ለቀው ለመውጣት በቸኮሉ ነዋሪዎች ዋና አውራ ጎዳናዎች ተጨናንቀዋል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በወጡ መረጃዎች መሠረት ነዋሪዎች እጅግ ተደናግጠዋል።

    ከፍንዳታ ራስን ለመከላከል ወደተሠሩ የመሬት በታች መጠለያዎች የገቡ እንዳሉም ተገልጿል።

    አንዳንድ ነዋሪዎች በየመንገዱ ፀሎት ሲያደርሱ በቴሌቭዥን ታይቷል።

    ጋርዲያን እንደዘገበው ገንዘብ ከኤቲኤም የሚያወጡ ነዋሪዎችም ታይተዋል።

  14. ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጡ

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምስራቃዊ ዩክሬን ዶንባስ ክልል ወታደሮቻቸው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያካሂዱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልእክት በሩሲያ የሚደገፉ አማጺያኖች ጋር እየተዋጉ የሚገኙ የየክሬን ወታደሮች መሳሪያቸውን አስቀምጠው ወደቤታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

    ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዩክሬንን የመቆጣጠር እቅድ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ማንኛውም አካል ሩሲያ ላይ አደጋ የሚጭር ነገር ካደረገ ምላሻችን ፈጣን ነው ብለዋል።

    ዩክሬን ደግሞ ፕሬዝዳንት ፑቲን አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ለመውረር እንቅስቃሴው ተጀምሯል ብላለች።

    የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ''ሰላማዊ የሆኑ የዩክሬን ከተሞች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ይህ ጦርነት መጎሰም ነው። ዩክሬን እራሷን ትከላከላለች፤ ስትከላከልም ቆይታለች። ዓለም ፑቲንን ሊያስቆመው ይገባል። እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው'' ብዋል።

    እየወጡ ባሉ ሪፖርቶች መሰረት አንዳንድ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ ተኩስና ፍንዳታ የሚሰማ ሲሆን በዋና ከተማዋ ኪዬቭ በሚገኘው ቦሪስፒል አየር ማረፊያ አካባቢም ተኩስ እየተሰማ ስለመሆኑ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጡ

  15. የዩክሬን ፕሬዝዳንት ራሳችንን እንከላከላለን ሲሉ ሩሲያን አስጠነቀቁ

    ሩሲያ በማንኛውም ቀን "አውሮፓ ውስጥ ትልቅ ጦርነት" ልትጀምር እንደምትችል የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አስጠንቅቀው ሩሲያውያን እርምጃውን እንዲቃወሙት ጠይቀዋል።

    ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቀዋል።

    "ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጋር የስልክ ንግግር ለማድረግ ሞከርኩ። ውጤቱ ዝምታ ሆነ" ብለዋል ዜለንስኪ።

    ሩሲያ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የውጊያ መኪናዎች በዩክሬን ድንበር እንዳሏት ተናግረዋል።

    ዜለንስኪ ንግግራቸውን ከዩክሬን ቋንቋ ወደ ሩስኪ በመቀየር ሩሲያውያን በዩክሬን ጉዳይ እየተዋሹ መሆኑን ጠቅሰው ጥቃትን እንዲቃወሙ በስሜት ተሞልተው ተማፅነዋል።

    "(ጦርነቱን) ማን ሊያቆመው ይችላል? ሰዎች። እርግጠኛ ነኝ እነዚህ ሰዎች ከእናንተ መካከል ናቸው" ብለዋልየዩክሬን ፕሬዝዳንት ራሳችንን እንከላከላለን ሲሉ ሩሲያን አስጠነቀቁ

  16. ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት ከፈተች

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ዜለንስኪ ሩሲያ በአገራቸው ላጥ ጥቃት መክፈቷን አስታወቁ። ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ፕሬዚዳንቱ የሚሳአኤል ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ሩሲያ ዛሬ ማለዳ ላይ የከፈተችው ጥቃት ኢላማ ያደረጉት የዩክሬን መሰረተ ልማቶችና የድንበር ጥበቃዎች ላይ ነው ብለዋል።

    የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሰራዊቱ ጥቃት መሰንዘሩን አረጋግጦ ኢላማዎቹ ከተሞች ላይ ሳይሆኑ የዩክሬን ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች፣ የአየር መከላከያ እና የአየር ኃይል ተቋማት መሆናቸውን ገልጿል።