ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ የኑክሊየር ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዙ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው ሠራዊት የኑክሌር ኃይል ‘በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ’ እንዲቆም አዘዙ። ፕሬዝዳንት ፑቲን የአገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉን ጨምሮ ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ተገቢ ያልሆነ” እርምጃ እና “ሕገ ወጥ ማዕቀብ” መጣላቸውን ተናግረዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የዩክሬን ባለሥልጣን ሩሲያ በኪዬቭ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን ገለጹ

    የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደማይሮ ኩሌባ ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ላይ ‘አስከፊ’ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን አስታወቁ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመን በዩክሬን ላይ ካደረገው ጥቃት ጋር አነጻጽረውታል።

    በኪዬቭ ያለው የቢቢሲ ዘጋቢ ፖል አደምስ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል እና ቢያንስ አንድ የፍንዳታ ድምጽ በከተማዋ መስማቱን ተናግሯል።

    አንድ የዩክሬን ጋዜጣ የሩሲያ ታንኮች ወደ መዲናዋ እንዳይገቡ የዩክሬን ወታደሮች በኪዬቭ አቅራቢያ የሚገኝ ድልድይ ማፍረሳቸውን ዘግቧል።

  2. በዩክሬን ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት በአፍሪካ ላይ ምን አይነት ጫና ይኖረዋል?

  3. የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ሩሲያ ተኩስ እንድታቆም ጠየቁ

    የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚየር ዜሌኒስኪ ጦርነቱ እንዲቆም ሩሲያ ልታነጋግረን ይገባል አሉ።

    ፕሬዝደንቱ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት 1፡30 ላይ በቴሌቪዥን ቀርበው በዩክሬን እና በሩሲያ ቋንቋዎች ንግግር አድርገዋል።

    ዜሌኒስኪ በንግግራቸው ዛሬ ዓርብ ንጋት ላይም ሩሲያ የጦር እና ሲቪል ተቋማትን በሚሳኤል ደብድባለች ካሉ በኋላ ሞስኮ ተኩስ እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።

    “ይህን ወረራ እና ግጭት ለማቆም ይዘግይ እንጂ ሩሲያ እኛን ማነጋገሯ አይቀርም” ያሉት ዜሌኒስኪ፤ “ንግግሩን በፍጥነት መጀመር፤ ሩሲያ የሚደርስባትን ውድመት አነስተኛ ያደርገዋል” ብለዋል።

    ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ ያቀረቡት የተኩስ አቁም ንግግር ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ “አገራችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

    ዜሌኒስኪ "ምዕራባውያኑ ሁኔታውን ከሩቅ ሆነው መመልከትን መርጠዋል" ካሉ በኋላ "እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም አገራችንን ለብቻችን እየተከላከልን ነን" በማለት ምዕራባውያን ለዩክሬን ድጋፍ እንዲሰጡ ዳግም ጠይቀዋል።

  4. 'ሩሲያ ወደ ኃያልነቷ መልሰዋል' የሚባልላቸው ቭላድሚር ፑቲን ማን ናቸው?

  5. በጦርቱ አስካሁን 137 ሰዎች መገደላቸውን ዩክሬን አስታወቀች

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች በኋላ እስካሁን137 ሰዎች መገደላቸውን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አስታወቁ።

    ቪዲዮ ተቀርጾ ለሕዝብ በተላለፈው መልዕክት ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ በሩሲያ ወረራ 137 ዜጎቻቸው መገደላቸውንና ዩክሬናውያን አገራቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    ጨምረውም አቅሙ ያለው ዩክሬናዊ የቻለውን እንዲያደረግ እንዲሁም ዕድሚያቸው ከ18 አስከ 60 ያሉ ዜጎች አገራቸውን ጥለው እንዳይወጡ አሳስበዋል።

    "ሩሲያ የዩክሬንን መሪ በማስወገድ አገሪቱን ከፖለቲካው መድረክ ማስወገድ ትፈልጋለች” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የወረራው ዋነኛ ኢላማ እሳቸውና ቤተሰባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

    ነገር ግን እሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው እዚያው ዩክሬን ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

  6. የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሩሲያ አምባሳደሮችን ሊያባርሩ ነው

    የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርድነር በአገሪቱ ያሉ የሩሲያ አምባሳደሮችን ማባረርን እንደ አማራጭ እየተመለከትኩ ነው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ አምባሳደሮች ከዌሊንግተን ማሰናበት ቀላል ውሳኔ ባይሆንም በጠረጴዛ ላይ ያለ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል።

    ሐሙስ ዕለት የኒው ዚላንድ መንግሥት በሩሲያ ወረራ ተሳትፎ አላቸው ባለቻቸው ሩሲያውያን ግለሶቦች ላይ የጉዞ እገዳ አስተላልፋለች።

    ከዚህ በተጨማሪም ኒው ላንድ ከሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የውጭ ጉዳይ ምክክርን አቋርጣለች እንዲሁም ለሩሲያ ጦር ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ከመላክ ተቆጥባለች።

    የሩሲያን ወረራ “ሕገ-ወጥ” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ፤ የንጹሃንን ሕይወት ለመታደግ እና አላስፈላጊ ውድመት ከመድረሱ በፊት የሩሲያ ወታደሮች ወታደራዊ ዘመቻቸውን አቁመው ከዩክሬን ግዛቶች እንዲወጡ ጠይቀዋል።

  7. ሌሊት ምን ተከሰተ?

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት ከከፈተች ሁለተኛ ቀን ሆኖታል። አስካሁን የተከሰቱ ዋና ዋና ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

    • አርብ ማለዳ ዋና ከተማዋ ኪዬቭ ውስጥ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን አንድ አውሮፕላን ተመቶ መውደቁ ተነግሯል።
    • የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ‘ተላላኪዎች’ ወደ ዋና ከተማዋ መግባታቸውን ተናገሩ።
    • ጦርነቱ በመላዋ ዩክሬን በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄደ ነው። በተለይ በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ከባድ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
    • በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው የኑክሌር ማዕከል ቼርኖቤል በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ገብቷል።
    • በሺዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ከተሞች እየለቀቁ ወጥተዋል። ወደ ምዕራባዊ ዩክሬን ከሄዱት በተጨማሪ ወደ አጎራባች ፖላንድና ሮማኒያም የተሰደዱ አሉ።
    • የአውሮፓ ሕብረት፣ አውስትራሊያ እና ጃፓን የሩሲያ ባንኮችን፣ ኩባንያዎችንና ባለሃብቶችን ኢላማ የሚያደርጉ አዳዲስ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
    • ሞስኮና ሴንት ፒተርስበርግን ጨምሮ በተለያዩ የሩሲያ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ጦርነቱን ተቃውመዋል። በመቶወች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸው ተነግሯል።
  8. እንዴት አደራችሁ?

    ዓለምን እያነጋገረ ያለው የሩሲያ ወረራ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

    ዛሬ ላይ የሩሲያ ኃይሎች ከዩክሬን መዲና አቅራቢያ ደርሰው በሁለቱ አገራት ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ስለመሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው።

    ዩክሬናውያን ከከባድ መሳሪያ ጥቃት እራሳቸውን ለመከላከል ከምድር በታች በሚገኙ የባቡር ጣቢያዎች ተጠልለዋል።

    ዛሬ የሚኖሩ ዋና ዋና ክስተቶችን በቀጥታ ዘገባ ገጻችን በፍጥነት እናቀርባለን።

    ትናንት የነበሩትን ዋና ዋና ክስተቶችን ማንበብ ከፈለጉ ከታች ይመልከቱ።

  9. የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዋና ከተማ ኪዬቭ ተቃርበዋል

    የሩሲያ አየር ወለዶች ከዩክሬን መዲና ኪዬቭ በ30 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛሉ።

    ከረፋድ ጀምሮ የሩሲያ አየር ወለዶቹ የዩክሬንን አንቶኖቭ ጦር ካምፕን በቁጥጥራቸው ስር አስገብተዋል።

    በሌላ በኩል ደግሞ የዩክሬን ብሔራዊ ዘብ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

    በምድር፣ በአየርና በባሕር ሐሙስ ጠዋት በዩክሬን ላይ ጥቃት የከፈተችው ሩሲያ ከፍተኛ ውግዘት እየገጠማት ቢሆንም ዘመቻዋን ቀጥላለች።

    የሩሲያ ጦር በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት የከፈተ ሲሆን ብረተ ለበስ ሜካናይዝድ ጦር ፈጣን ግስጋሴ እያደረገ ነው። በዚህም ከደቡብ አቅጣጫ በቤላሩስ ድንበር በኩል እንዲሁም በሰሜን ከክሬሚያ አቅጣጫ ወደ ዩክሬን አምርቷል።

    በኪዬቭ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ፖል አደምስ ሩሲያ በቀጣይ ምን ልታደርግ እንደምትችል ግልጽ አይደለም ብሏል።

    ምናልባት የአየር ኃይሉን ጦር ካምፕ የተቆጣጠሩት አየር ወለዶች ባሉበት ሆነው ሜካናይዝድ ጦሩን ሊጠብቁ እንደሚችሉ አመልክቷል።

    አልያም አየር ወለዶቹ የያዙትን የአየር ኃይል ካምፕ በኪዬቭ ላይ የአየር ጥቃት ለመክፈት ይጠቀሙበት ይሆናል ብሏል።

  10. በምስል: ፍርሃት እና ድንጋጤ በዩክሬን ጎዳናዎች ላይ

    የሩሲያ ጦር በዩክሬን ወታደራዊ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ዩክሬናውያን ድጋጤ ውስጥ ገብተዋል።

    ከዚህ በታች የሚታዩት ምስሎች በዩክሬን ጎዳናዎች ላይ ያለውን ሁኔታ ያሳያሉ።

  11. የሩሲያ እና የዩክሬን ፍጥጫ አሁን ካለበት እንዴት ደረሰ?

  12. ሩሲያ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ከሞስኮ ጥቃት ጋር የሚስተካከል ይሆናል- ማክሮን

    የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩሲያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስታወቁ።

    ማክሮን ሞስኮ ላይ የሚጣለው ማዕቀብ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከከፈተችው ጥቃት ጋር የሚስተካከል ይሆናል ብለዋል።

    ፕሬዝደንቱ የሩሲያን ጦር፣ ምጣኔ ሃብት እና የኢነርጂ ዘርፍ የሚያሽመደምዱ ማዕቀቦች ይጣላሉ ብለዋል። “ያለ ማቅማማት ዩክሬንን እንደግፋለን፤ የአውሮፓ አጋሮቻችንን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን” ሲሉ ለፈረንሳይ ሕዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ተናግረዋል።

    ማክሮን የፈረንሳይ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማዎችን ከጀርባቸው አድርገው የሩሲያ ጥቃት “የአውሮፓን ታሪክ የቀየረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ለዚህ የጦርነት ቅስቀሳ እርምጃ በአንድነት፣ በቁርጠኝነ እና በእርጋት ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል።

  13. ዩክሬን የሩሲያን ሄሊኮፕተር መትታ ጣለች

    ዩክሬን የሩሲያን ተዋጊ ሄሊኮፕተር ዋና ከተማዋ ኪዬቭ አቅራቢያ መትታ ጣለች።

    ቢቢሲ የተከሰከሰ የሩሲያ ሄሊኮፕተርን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ምንጭን ማወቅ ባይችልም ትክክለኛነቱን ግን አረጋግጧል።

    ሄሊኮፕተሩ ተመትቶ የወደቀው ሆስፖሜል በተሰኘ የዬክሬን አየር ማረፊያ አቅራቢያ ነው።

    ኪዬቭ አቅራቢያ የሚገኘውን ይህን የአየር ማረፊያ ለመቆጣጠር ሩሲያ ጥቃት ስለመክፈቷ የዩክሬን ከፍተኛ ጦር አባል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ሆስፖሜል አየር ማረፊያ የዩክሬን ግዙፉ የእቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ማረፊያ እና የጦር ካምፕ ነው።

  14. ጎረቤት አገራት በዩክሬናውያን ስደተኞች ሊጥለቀለቁ ይችላሉ ተባለ

    የተባበሩት መንግሥት በዩክሬን ያለው ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ ስለሆነ ጎረቤት አገራት ለስደተኞች በሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጠየቀ።

    የተመድ የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፤ “ገና ከአሁኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እየተመለከትን ነው። በርካታ ሰዎችም ከጥቃት ለመዳን ቤቶቻቸውን ጥለው እየሸሹ ነው” ብለዋል።

    በርካታ የዩክሬን ጎረቤት አገራት የሩሲያን ወረራ ተከትሎ መኖሪያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሰዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

    የፖላንድ ጤና ሚኒስትር በአገሪቱ ድንበር አቅራቢያ የስደተኞች መቀበያ ስፍራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

    ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ በተመሳሳይ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ለማስተናገድ ጦራቸውን ወደ ድንበር እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

    ጀርመን በበኩሏ ስደተኞችን ለሚቀበሉ አገራት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻለች።

  15. ቤላሩስ በዚህ ጦርነት ተሳትፎ እንዳታደርግ የአውሮፓ ሕብረት አሳሰበ

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምትደርገው ጥቃት ቤላሩስ ተሳትፎ እንዳይኖራት የአውሮፓ ሕብረት አሳሰበ።

    የአውሮፓ ሕብረት ካውንስል ፕሬዝደንት ቻርልስ ሚሼል ለቤላሩስ መንግሥት እና ሕዝብ፤ “የሩሲያን የአጥፊነት መንገድ መከተል የለባችሁም” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    “በጎረቤታችሁ ላይ በተፈጸመ በዚህ አላስፈላጊ አፍራሽ ተግባር ላይ ያለመሳተፍ ምርጫ አላችሁ” ብለዋል የካውንስሉ ፕሬዝደንት።

    የአውሮፓ ሕብረት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

    በቀጠናው የሩሲያ የቅርብ አጋር እና ከዩክሬን ጋር በድንበር የምትዋሰነው ቤላሩስ፤ ወታደሮቿን ከሩሲያ ጎን ስለማሰለፏ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም የሩሲያ ወታደሮች በቤላሩስ በኩል ወደ ዩክሬን ዘልቀው እንዲገቡ ቤላሩስ ፈቅዳለች በማለት የኪዬቭ ባለሥልጣናት ቅሬታ አቅርበዋል።

  16. በዩክሬን ተማሪ የሆነችው ኢትዮጵያዊት፡ "የሚሳኤል ፍንዳታው ርችት መስሎኝ ነበር"

  17. ኢስቶኒያ ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ ገለጸች

    የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካጃ ካላስ በተቻለን መጠን ዩክሬንን እንደግፋለን ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ከሩሲያ ጋር ድንበር የምትጋራው ኢስቶኒያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር ነች።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ በአውሮፓ ሕብረት እና በኔቶ ደረጃ ይህ የሩሲያ ጥቃት እንዳይስፋፋ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን ብለዋል።

    ቀደም ሲል የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶለተንበርግ በሰጡት መግለጫ፤ “በአንድ አባል አገር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም አባል አገራት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ተደርጎ ይወሳዳል” ብለው ነበር።

    ይህ የኢስቶኒያ መንግሥት አቋም የተሰማው ቤላሩስ ከሩሲያ ጎን በመሰለፍ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ልካለች የሚል መረጃ ከወጣ በኋላ ነው።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው ጦርነት ወደተቀሩት የአውሮፓ አገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊቱዌኒያ ፕሬዝደንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል።

    ከሩሲያ ጋር ድንበር የምትጋራው ሊቱዌኒያ የሩሲያ እና የቤላሩስ ወታደሮች በስፋት በመሰማራታቸው ድንበር ለመጠበቅ ወታደሮቻቸው እስፈላጊውን እንደሚያደርጉ ፕሬዝደንት ጊታናስ ናኤሱዳ ገልጸዋል።

    በተመሳሳይ ሊቱዌኒያም የኔቶ አባል አገር ናት።

  18. ኔቶ የአባል አገራት ደኅንነትን አረጋግጣለሁ አለ

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአባል አገራትን ደኅንነት አረጋግጣለሁ አለ።

    የኔቶ ዋና ጸሓፊ የንስ ስቶለተንበርግ የኔቶ ዋነኛ ዓላማ አባል አገራትን መከላከል ነው ብለዋል።

    ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከደቂቃዎች በፊት በሰጡት መግለጫ፤ “በአንድ አባል አገር ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም አባል አገራት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ተደርጎ ይወሳዳል” ብለዋል።

    ኔቶ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ቱርክን ጨምሮ በርካታ አውሮፓውያን አገራት የተካተቱበት 30 አባል አገራት አሉት።

    ዩክሬን የኔቶ አባል አገር አይደለችም። ይሁን እንጂ ዩክሬን የኔቶ አባል አገር የመሆን ፍላጎት እንዳላት ፕሬዝደንት ዜሌኒስኪ ከዚህ ቀደም በይፋ ተናግረው ነበር።

    ሞስኮ ዩክሬን በየትኛውም መንገድ የኔቶ አባል አገር መሆን የለባትም በማለት ስትቃወም ቆይታለች።

    ኔቶ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት መክፈቷ በተቀሩት ጎረቤት አባል አገራት ላይ የደኅንነት ስጋት ነው ብሎ ያምናል።

    ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑት ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ የኔቶ አባል አገራት ናቸው።

    የኔቶ ዋና ፀሐፊ በመግለጫቸው ሩሲያ ከኃይል ይልቅ ዲፕሎማሲን መምረጥ አለባት ብለዋል።

  19. ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ምን አይነት ማዕቀቦችን ሊጥሉ ይችላሉ?

    ፑቲን ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመራቸውን ተከትሎ ምዕራባውያኑ በሞስኮ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየዛቱ ነው።

    ቀደም ሲል አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ሞስኮ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማዕቀብ የፑቲን አስተዳደርን ለመቅጣት በቂ አይደለም የሚሉ መከራከሪያዎች እየተሰሙ ነው።

    ለዚህም ይመስላል ምዕራባውያኑ በሞስኮ ላይ ተጨማሪ ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየገለጹ የሚገኙት።

    ለመሆኑ ምዕራባውያኑ በሩሲያ እና ፑቲን ላይ ምን አይነት ማዕቀቦችን ሊጥሉ ይችላሉ?

    ዘገባውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ። https://bbc.com.im/amharic/news-60158165%3C/p%3E%3C/div%3E%3C/div%3E%3C/article%3E%3C/li%3E%3Cli class="css-xxlek1">

    የዩክሬን ወታደራዊ እና ደኅንነት ተቋማት ጥቃት ተፈጸመባቸው

    የዩክሬን ወታደራዊ እና የደኅንነት ተቋማት በሩሲያ የሚሳኤል ጥቃቶች ዒላማ መደረጋቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት እና የዓይን እማኞች ተናገሩ።

    ከደቂቃዎች በፊት ሮይተርስ የዜና ወኪል በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ከሚገኘው የአገሪቱ ጦር ደኅንነት ዋና መሥሪያ ቤት ጥቁር ጭስ ሲወጣ ታይቷል ሲል ዘግቧል።