ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ፑቲን የሩሲያ የኑክሊየር ኃይል በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዙ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው ሠራዊት የኑክሌር ኃይል ‘በተለየ ሁኔታ በተጠንቀቅ’ እንዲቆም አዘዙ። ፕሬዝዳንት ፑቲን የአገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሹይጉን ጨምሮ ለከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ተገቢ ያልሆነ” እርምጃ እና “ሕገ ወጥ ማዕቀብ” መጣላቸውን ተናግረዋል።
የቀጥታ ሽፋን
በካርኪቭ ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው- ሪፖርቶች
የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ በምትባለው የዩክሬኗ ከተማ ካርኪቭ መግባታቸውን ተከትሎ በአውራ ጎዳናዎች ላይ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል።
የሩስያ ወታደሮች ባለፈው ሰአት ከተማዋን ዘልቀው መግባታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። በማህበራዊ ትስስር ገጽ የወጡ ቪዲዮዎች በከተማ ውስጥ የሩሲያ ወታደሮችን አሳይተዋል።
በከተማው ውስጥ ቢያንስ ሁለት የሩስያ "ታይገር" የተሰኙ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በእሳት ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
ቢቢሲ የእነዚህን ምስሎች ትክለኛነት እስካሁን አላረጋገጠም። የካርኪቭ ባለስልጣናት ዛሬ ጠዋት የአካባቢው ነዋሪዎች በመጠለያዎች እንዲቆዩ እና ወደ መንገዶች እንዳይወጡ አስጠንቅቀዋል።
በዩክሬን ስላሉ አዳዲስ ክስተቶች
እንዴት አደራችሁ! ምናልባት ምሽቱን ዜና ካልተከታተላችሁና አሁን በዩክሬን ስላለው ጉዳይ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደችው ባለው ወረራ አራተኛ ቀኑ በቀጠለበት ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የተከሰቱትን ጉዳዮች ጠቅለል ስናደርጋቸው እነሆ!
- ትናንት ምሽት የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ከሩሲያ ሚሳኤሎች ጥቃት እንደሚደርስባት ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ጥቃቶቹ እስካሁን አልተከሰቱም።
- ይሁን እንጂ በከተማዋ አቅራቢያ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ በቫሲልኪቭ የሚገኘው የነዳጅ ማከማቻ መጋዘን በሚሳኤል ተመትቶ ተመትቶ በእሳት ጋይቷል ሲሉ የአከባቢው ከንቲባ ተናግረዋል። እሳቱ የመርዛማ ጭስ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን ነዋሪዎቹ መስኮቶቻቸውን እንዲዘጉ እና ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
- ደቡባዊቷ የኖቫ ካኮቭካ ከተማ በሩሲያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መዋሏን የተማዋ ከንቲባ ዛሬ ማለዳ ገልጸዋል
- ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩስያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ካርኪቭ መግባታቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ተናግረዋል። በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ተጎድቷል ተብሏል።
- የግዛቲቷ አደጋ ጊዜ እንዳስታወቀው በካርኪቭ የመኖሪያ አካባቢዎችም ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን በዚህም አንዲት ሴት መገደሏን እና ባለ ዘጠኝ ፎቅ ህንጻ ላይ የነበሩ ነዋሪዎችንም ማስወጣት ተችሏል ተብሏል።
- በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ኦክቲርካ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሲቪሎች መሞታቸውን የክልሉ ከንቲባ ገልጸዋል።
- ባለፈው ሰዓት የቢቢሲ የዩክሬን አገልግሎት በደቡብ ምስራቅ ካርኪቭ እና ኬርሶን አዳዲስ ፍንዳታዎች መድረሳቸውን ዘግቧል።
- ሩሲያን ለመቅጣት በሚወሰደው እርምጃ የአውሮፓ ህብረት ፣ አሜሪካ እና አጋሮቻቸው በርካታ የሩሲያ ባንኮች ከዋናው ዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ፣ስዊፍት እንዲታገዱ ይደረጋሉ። በተጨማሪም የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ውሳኔ ተላልፏል።
- በርካታ የምዕራባውያን አገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን አውስትራሊያ የሩሲያን ወራራ ለመቀልበስ ያስችል ዘንድ ለዩክሬን ጦር እንደምታቀርብ ያስታወቀች የመጨረሻዋ ሀገር ሆናለች። ይህ እርምጃ ጀርመን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ለማቅረብ ቅዳሜ ከወሰነች በኋላ የተከሰተ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ነው።
የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ገቡ
የሩስያ ኃይሎች የዩክሬን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ወደሆነችው ካርኪቭ መግባታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገለፁ።
የካርኪቭ ግዛት አስተዳደር ኃላፊ ኦሌግ ሲኔጉቦቭ የሩሲያ ቀላል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ "ከተማዋ ገብተዋል" ብለዋል።
ከመግለጫው በፊት፣ አንዳንድ የሩሲያ ወታደራዊ መኪኖች በሰሜናዊ ምስራቅ ከተማ ጎዳናዎች ላይ ሲዞሩ የሚያሳይ ምስል ታይቷል።
ሲኔጉቦቭ የሩሲያ ወታደሮች መሃል ከተማ ውስጥ እንዳሉ በመግለጽ ነዋሪዎቹ ከተማቸውን ለቀው እንዳይወጡ አሳስበዋል ።
"ከመጠለያዎችን አትውጡ! የዩክሬን ጦር ኃይሎች ጠላትን እያስወገዱ ነው። ሲቪሎች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ተጠይቀዋል." ብለዋል።
"ያለ ዩክሬን ሰራዊት እና ህዝብ አውሮፓ መቼም ደህና አትሆንም" የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር
የዩክሬን መንግሥት ሃገሪቱ ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ጦርነት የአውሮፓን የወደፊት እጣ ፈንታ ለማስጠበቅ ዋነኛ ትግል እንደሆነ እየተናገረ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌክሲይ ሬዝኒኮቭ በፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት ረዥም ጽሁፍ የጦር መሳሪያ ያነሱ ወታደሮችን፣ ፖሊሶችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን እና ሰላማዊ ዜጎችን አወድሰዋል።
"ዙሪያችንን እንመልከት። ብዙዎች በመጨረሻ ፍርሃትን አሸንፈው ክሬምሊንን ለመቃወም ደፍረዋል" ሲል ሬዝኒኮቭ ጽፈዋል።
አክለውም "ኪዬቭን በሁለት ሰአት ውስጥ ለመያዝ ቃል የገቡት ሁሉ የት አሉ? አላያቸውም።" ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ፈተናዎች በዩክሬን ላይ የተጋረጡ ቢሆን በዓለም ዙሪያ ያሉ ህዝቦች ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተሉ መሆናቸውን እና "ከሦስት ቀናት በፊት የማይቻል እርዳታ አሁን መንገድ ላይ ነው" ብለዋል።
"ያለዚህ ሰራዊት እና ህዝባችን አውሮፓ መቼም ደህና አትሆንም።ያለ እኛ አውሮፓ አትኖርም" ብለዋል።
የኪዬቭ ነዋሪዎች ከመርዛማ ጭስ ተጠንቀቁ ተባሉ
የሩሲያ ሚሳይሎች በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ወጣ ብላ በምትገኘው ቫሲልኪቭ የሚገኝ የነዳጅ ማከማቻ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ከንቲባው መርዛማ ጭሶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የኪየቭ ባለስልጣናት የሚቃጠለው የነዳጅ ማከማቻ (ዴፖ) መርዛማ ጭስ እያወጣ መሆኑን በመግለፅ ነዋሪዎች መስኮቶቻቸውን ጥርቅም አድርገው መዝጋትን ጨምሮ ሌሎች ማስጠንቀቂያዎች ተላልፎላቸዋል። በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤቶቻቸውን ለቅቀው ወጥተው ከቤቶች ስር በሚገኙ መጠለያዎች ይገኛሉ።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት የነዳጅ ማከማቻው ሲቀጣጠልና በአየር ላይም ከፍተኛ ጭስ እያወጣ ያሳያል።
ዩክሬን ከምዕራባውያን አገራት የጦር መሳሪያ ቃል ተገባላት
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያደረገችው ወረራ ዛሬም እንደቀጠለ ሲሆን ይህንን ጦርነት መቀልበስ ያስችል ዘንድ ምዕራባውያን አጋር ሃገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
ከነዚህም መካከል በትናንትናው ዕለት ይሰጣሉ የተባሉ መሳሪያዎችን እንመልከት
- የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጄቭሊን የተሰኙ ፀረ-ታንክ ሚሳኤሎችን ፣ ፀረ-አውሮፕላን መቃወሚያዎች፣ እና የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎችን ጨምሮ 350 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚልክ አስታውቋል።
- የጀርመን መንግስት በበኩሉ 1 ሺህ የሚሆኑ ጸረ-ታንክ የእጅ ቦምቦችን እና እንዲሁም ባስፈለገ ወቅት በአየር ላይ የሚወነጨፉ ሚሳይሎችን መሬት ላይ ሆኖ ለመቃወም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን እሰጣለሁ ብሏል።
- የኔዘርላንድስ መንግሥትም እንዲሁ 3 ፀረ-ታንክ የጦር መሳሪያዎችን እና 400 ሮኬቶችን ማሰማራቱን አስታውቋል።
- ሁለቱ ሀገራት የጋራ የአየር መከላከያን በስሎቫኪያ ለሚገኘው የኔቶ ተዋጊ ቡድን ለመላክ እያሰቡ ነው ተብሏል።
- ቀደም ሲል ኔቶ “ ድንገተኛ ምላሽ ለመስጠት” ተጨማሪ ሃይሉን ወደ ምስራቅ አውሮፓ ማሰማራት መጀመሩን አስታውቋል።
“የከፋ ከመጣ ለአባት አገር ለሩሲያ ልዘምት እችላለሁ”፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከሞስኮ
በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ምን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ?
ኪዬቭ ውስጥ በሚሳኤል የተመታው ህንጻ
ቅዳሜ ጠዋት በዩክሬን መዲና የሩሲያ ኃይሎች በአንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ በሚሳኤል ጥቃት ፈጽመዋል።
ይህ ከደኅንነት ካሜራ ላይ ከተገኘ ቪዲዮ የተወሰደ ፎቶ ሲሆን፣ ህንጻው በሚሳኤል የተመታበትን ቅጽበት ያሳያል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ሌሊት ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች 35 ሰዎች መጎዳታቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ በሚሳኤል ከተመታው ህንጻ ጋር በተያያዘ ምን ጉዳት እንደደረሰ ግን የተረጋገጠ ነገር የለም።
ሩሲያ በፌስቡክ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጣለች
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የዛሬ ዋና ዋና ክስተቶች
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ዛሬ ቅዳሜ ሦስተኛ ቀኗ ነው። ጦርነቱ የቀጠለ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተፈጸሙ ዋና ዋና ክስተቶች፡
·ሌሊቱን በዋና ከተማዋ ኪዬቭ እና በዙሪያዋ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቷል።የዩክሬን ሠራዊት በከተማዋ ውስጥ በሚገኝ ዋና መንገድ ላይ ባለ ጦር ሰፈር የሩሲያ ኃይሎችን ተከላክለው መመለሳቸውን ገልጸዋል።
·በዋና ከተማዋ ውስጥ የሚገኝ የመኖሪያ ህንጻ በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
·ጠዋት ላይ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሠራዊታቸው እጁን እንዲሰጥ አዘዋል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ አንድ ስፍራ ሆነው በቀረጹት ቪዲዮ ላይ የተወራው ሐሰት መሆኑን ገልጸዋል።
·የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮቹ በደቡብ ዩክሬን የምትገኘውን ሜሊቶፖል የተባለችውን ከተማ መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
·የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ሂፔይ እንዳሉት አገራቸውን ጨምሮ 25 አገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ለማቅረብ ተስማምተዋል።
·ሁለት ህጻናትን ጨምሮ እስከ ዛሬ 198 ዩክሬናውያን በጦርነቱ መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር የገለጹ ሲሆን ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።
·ፖላንድ በመጋቢት ወር ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሞስኮ ላይ ከሩሲያ ጋር የተያዘላትን ግጥሚያ እንደማታደርግ ገልጻለች። የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንም “እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።
·በ48 ሰዓታት ውስጥ 100,000 ያህል ሰዎች ከዩክሬን መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በሩሲያ ወረራ የተፈጸመባት ዩክሬን መሪ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ማን ናቸው?
ፈረንሳይ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መላኳ ተዘገበ
እየገሰገሰ ያለውን የሩሲያን ሠራዊት እየተፋለሙ ላሉት ዩክሬናውያን የሚሆኑ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች ምዕራባውያን እያቀረቡ ነው።
በዚህም መሠረት ከፈረንሳይ የተላኩ የጦር መሳሪያዎች ወደ ዩክሬን እያቀኑ መሆናቸው ተገለጿል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ከፈረንሳይ አቻቸው ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ዛሬ ቅዳሜ መነጋገራቸውን አመልክተው "በዲፕሎማሲው መስክ አዲስ ግንባር ተከፍቷል" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ጨምረውም "ፀረ ጦርነት ትብብሩ ሥራውን እያከናወነ ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ዛሬ ቅዳሜ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "ጦርነቱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው፤ለዚህም መዘጋጀት አለብን" ብለዋል።
ምዕራባውያን በፕሬዝዳንት ፑቲን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ላይ ማዕቀብ ጣሉ
ሜታ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን በመድረኩ ማስታወቂያ እንዳያስተላልፍ ከለከለ
የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን በመላው ዓለም ማስታወቂያ አሊያም ማንኛውንም ገቢ የሚያስገኝ ይዘት በመድረኩ ላይ እንዳታስተላልፍ እንደሚከለክል አስታወቀ።የዩክሬን ወረራ፡ ሩሲያ በፌስቡክ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጣለች
ኩባንያው ተጨማሪ የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ ልየታ ማድረጉን እንደሚቀጥል የፌስቡክ የደህንነት ፖሊሲ ኃላፊ ናታኔል ግሊቸር በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል ።
እነዚህ እርምጃዎች ቀደም ብለው ተግባራዊ እየሆኑ እንዳለ የገለጹት ኃላፊው ቅዳሜ እና እሁድም ይቀጥላሉ ብለዋል ።
ዜሌንስኪ ከአገር እንዲወጡ በአሜሪካ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ከአሜሪካ የቀረበላቸውን የድጋፍ ጥያቄ ሳይቀበሉት መቅረታቸው ተዘገበ።
ፕሬዝዳንቱ "ውጊያው ያለው እዚህ ነው። የምፈልገው የጦር መሳሪያ እንጂ የማምለጫ መንገድ አይደለም" ማለታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ጉዳዩን የሚያውቁ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካና የዩክሬን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪን ለመርዳት ተዘጋጅታ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ የሩሲያን ወረራ ተከትሎ በወሰዱት አቋም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲወደሱ ቆይተዋል።የቀድሞው ኮሜዲያንና ተዋናይ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ባደረጉት ንግግር “ጥቃት ስትፈጽሙብን ፈት ለፊት እንጋፈጣችኋለን እንጂ አንሸሽም” በማለት አገራቸውን ከወረራው ለመከላከል ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ ከኪዬቭ ለቀው ወጥተዋል የሚል ሪፖርት ከተሰራጨ በኋላ ዜሌንስኪ በሶሻል ሚዲያ ላይ ከረዳቶቻቸው ጋር ሆነው ባስተላላፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ "እዚሁ ነው ያለነው" በማለት ዋና ከተማዋ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ሩሲያ በፀጥታው ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ውድቅ አደረገች
በዩክሬን ላይ በተፈጸመው ወረራ ላይ በተወያየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበውን ወረራውን የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ ውድቅ አደረገች።
ወረራውን ለማውገዝ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ውድቅ ስታደርገው ከ15ቱ የፀጥታው ምክር ቤቱ አባላት አስራ አንዱ ደግፈውታል፤ ሕንድ፣ ቻይናና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ድምጸ ታዕቅቦ አድርገዋል።
ሩሲያ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት አገራት አንዷ በመሆኗ የውሳኔ ሐሳቡ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ከመነሻው ተቀባይነት እንደማያገኝ ይታወቅ ነበር።
በዋና ከተማ ኪዬቭ ጎዳናዎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ ሆኑ ተነገረ
በዩክሬኗ ዋና ከተማ ኪዬቭ ውስጥ የጎዳና ላይ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የዩክሬን መንግሥት አስታወቀ።
የአገሪቱ የዜና ወኪል ኢንተርፋክስ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው “በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ውጊያ እየተካሄደ ነው” ብሏል።
መንግሥት ጨምሮም የከተማዋ ነዋሪዎች በመጠለያ ቦታዎች ላይ እንዲቆዩ ወደ መስኮቶችና በረንዳዎች እንዳይቀርቡም አስጠንቅቋል።
ሌሊቱን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ውስጥ ፍንዳታዎች መሰማታቸውና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደተካሄዱ የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
በዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኘው ሜይዳን አደባባይ አቅራቢያ ከባድ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን፣ ትሮዬሽቺይና በሚባለው አካባቢ ደግሞ በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል።
የዓይን እማኞች እንዳሉት ከዋና ከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ሆነው ከፍተኛ የመድፍ ፍንዳታዎችን በቅርብ ርቀት እንደሰሙ ተናግረዋል።
አንድ ዘገባ እንዳመለከተው በከተማዋ ውስጥ ከ50 በላይ ፍንዳታዎችና ከባድ የመትረየስ ተኩስ ተሰምቷል። ኪዬቭ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሩሲያ ሠራዊት ጥቃት ተከፍቶባታል።
የዩክሬን መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ውጊያዎች እየተካሄዱ ሲሆን ከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኝበትን አካባቢ ለመቆጣጠር ውጊያ እየተደረገ እንደሆነ ተነግሯል።
ሩሲያ ኮማንዶዎቿን በቀላሉ ወደ ኪዬቭ ለማስገባት ያስችላታል የተባለውን የቫዚልኪዬቭ አየር ማረፊያን ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
የዩክሬን ኃይሎች በጥቁር ባሕር አካባቢ በምትገኘው ማይኮሌቭ ከተማ ላይ በሩሲያ ሠራዊት የተሰነዘረውን ጥቃት መክተው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የህፃናት ማሳደጊያ በሩሲያ ሚሳኤል መመታቱን የዩክሬን ባለስልጣን ተናገሩ
ከዩክሬን መዲና ኪዬቭ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቮርዜል በተሰኝው ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ የህጻናት ማሳደጊያ በሩሲያ ሚሳኤል ጥቃት ደርሶበታል ሲሉ የዩክሬን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቁ።
አይሪና ቬኔዲክቶቫ በፌስቡክ ላይ እንዳሰፈሩት የሩሲያ ሚሳኤል 50 ወላጅ አልባ ህፃናት የያዘውን ማሳደጊያ መትቷል ብለዋል።
በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰ የገለጹት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ህፃናቱን የማስወጣት ተግባሮች እየተከናወነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በምስራቃዊ ሱሚ ግዛት ኦክቲርካ ከተማ ላይ ሩሲያ ባደረገችው የከባድ መሳሪያ ድብደባ በርካታ ህጻናት መጎዳታቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የክልሉ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ዲሚትሮ ዙይቪትስኪ እንደተናገሩት የመኖሪያ አካባቢ፣ በርካታ የቦምብ መጠለያዎች እና መዋለ ህፃናት በከባድ መሳሪያ ተመትተዋል።