በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን አለፈ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምድራችንን ነዋሪ ጤናና ህይወት አደጋ ላይ ከመጣሉ ባሻገር የዓለምን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ አስተጓጉሏል። በበሽታው ክፉኛ የተጠቁ አገራት ውስጥ በወረርሽኙ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች አሃዝ ባለፉት ጥቂት ቀናት የመቀነስ አዝማሚያ እንደታየ ቢዘገብም አሳሳቢነቱ ግን ገና አልተወገደም። እስካሁን በኮቪድ-19 በመላው ዓለም ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተያዙ የተረጋገጠ ሲሆን ከ200 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።እኛም ከእዚህ አሃዝ ውስጥ ላለመግባት ሳንዘናጋ የመከላከያ መንገዶች ተግባራዊ እናድርግ። ስለበሽታው ትኩስ ዜናና መረጃ ለማግኘት የቀጥታ ዘገባ ገጻችንን ተከታተሉ።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኬንያዊው ዋነኛ የኮሮናቫይረስ ሳይንቲስት ከደረጃቸው ዝቅ መደረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል

    ኬንያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ኬንያ ውስጥ የኮሮናቫይረስን በመመርመር የሚታወቁት ጉምቱ ሳይንቲስት ከእርከናቸው ዝቅ መደረጋቸው የሙያ አጋሮቻቸውን እንዳስቆጣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።

    የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ጆዌል ሉቶሚያህ ከእርከናቸው ዝቅ ያሉት ቫይረሱን የምርመራ ውጤቶችን በማሳወቅ ረገድ ዝግመት በመታየቱና በአስተዳደር ጉዳዮች ነው።

    ዶክተር ጆዌል፤ የቫይረስ ምርምር ማዕከል ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነበር። አሁን ግን አጥኚ ሳይንቲስት የሚል ቦታ ተሰጥቷቸው ከኃላፊነታቸው እንዲወርዱ ሆነዋል።

    የሙያ አጋሮቻቸው ግን ዶክተሩ ከኃላፊነታቸው የተነሱት መንግሥት የኮሮናቫይረስ ምርምር ለሚደረግበት ማዕከል የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርግና ቁሣቁስ እንዲያሟላ አዘውትረው በመጠየቃቸው ምክንያት ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

    ዴይሊ ኔሽን ለተሰኘው ጋዜጣ ድምፃቸውን የሰጡ አንድ ሳይንቲስት እንደሚሉት ዶ/ር ጆዌል መንግሥት ለባለሙያዎች ግላዊ መከላከያ የማያሟላ ከሆነ ምርመራ አላደርግም ሲሉ አስፈራርተዋል።

    የምርምር ማዕከሉ ሠራተኞች በቂ የሆነ ግላዊ መከላከያ ቁሣቁስ እንዳልተሟላላቸው ይነገራል።

  2. በዓለም ላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን አለፈ

  3. በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3 ሚሊዮን እየደረሰ ነው

    ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዓለማችን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው።

    የወረርሽኙን የአገራትንና ዓለም አቀፋዊ አሃዝን የሚያጠናቅረው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ነው ይህንን መረጃ ያወጣው።

    በአሁኑ ሰዓት ከ2 ሚሊዮን 971 ሺህ በለይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ206 ሺህ በላይ ሆኗል።

    አሜሪካ በወረርሽኙ በርካታ ዜጎቿን ያጣች አገር ሆናለች። በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥርም አንደኛ ናት። እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ 965 ሺህ 910 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በሁለኛነት ስፔን ትከተላለች - በ226 ሺህ 629።

    ነገር ግን ቁጥሩ ከዚህም በላይ እንደሆነ ይገመታል። በርካታ ሰዎች በሽታውን ሳያሳውቁ ወይም ሳይመረመሩ አልቀሩም የሚል ከግምት የዘለለ እምነት አለ።

  4. ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባት የተሞከረባቸው በጎ ፈቃደኞች

  5. 'የናይጄሪያውን ሞት ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ አይደለም'

    ናይጄሪያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በሰሜን ናይጄሪያ ካኖ ግዛት በቅርቡ የተመዘገበው ሞት ኮሮናቫይረስ ከተሰኘው የመተንፈሻ አካላትን ከሚያጠቃ በሽታ ጋር ግንኙነት የለውም እያሉ ነው።

    ባለሥልጣናቱ የሞቱን ምክንያት እያጣሩ እንደሆነ አሳውቀው፤ ነገር ግን እስካሁን የተደረጉ ምርመራዎች ከኮቪድ-19 ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለ ያሳያሉ ብለዋል።

    የናይጄሪያ ጤና ሚኒስትር "ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልን ነው" ብለዋል።

    በአካባቢው ባለፈው ሳምንት ከሌላው ጊዜ በተለይ ብዛት ያላቸው ሰዎች መሞታቸውንና መቀበራቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ቁጥሩ በመቶዎች የሚቆጠር እንደሆነ ነው የተነገረው።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የለቀቀው መግለጫ ግን ለሞቶቹ ምክንያት ብሎ ያስቀመጠው ከባድ ጭንቀት፣ የስኳር በሽታ፣ ማጅራት ገትርና አጣዳፊ ወባ በሽታን ነው።

    የናይጄሪያ በሽታ መከላከል መሥሪያ ቤት ወደ ሥፍራው ጉዳዩን የሚመረምር ቡድን የላከ ሲሆን፤ ባለሥልጣናት ሰዎች ድንጋጤ ውስጥ እንዳይገቡ እየመከሩ ነው።

    ናይጄሪያ እስካሁን ከ1200 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው አረጋግጫለሁ ስትል፤ 40 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መሞታቸውን አረጋግጣለች።

  6. የኮሮናቫይረስ ክትባትን በማግኘት ህንድ የዓለምን ሕዝብ ትታደግ ይሆን?

  7. ቻይናውያን ወደ ትምህር ቤቶች እየተመለሱ ነው

    ቻይናውያን ተማሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, Sixth Tone

    የምስሉ መግለጫ, ሕፃናት ማኅበራዊ ርቀታቸውን መጠበቅ የሚያስችላው አንድ ሜትር ርዝማኔ ያለው ኮፊያ አድርገው ታይተዋል

    ሻንግሃይ እና ቤይጂንግ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መከፈት ጀምረዋል። ተማሪዎችም ከሳምንታት በኋላ ዛሬ ዕለተ ሰኞ ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው እያቀኑ ነው።

    ሻንግሃይ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ ወራት የቀራቸው ተማሪዎች ትምህርት ጀምረዋል።

    ቤይጂንግ ውስጥ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና ሊሰጥ ነው። 'ጋዎካዎ' የተሰኘ ስያሜ ያለው ይህ ፈተና በጣም ከባድ እንደሆነ ይነገርለታል። ይህን ያለፊ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ያቀናሉ።

    በሌሎችም የቻይና ግዛቶች ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው። ቫይረሱ የተጀመረባት ናት የምትባለው ዉሃን ትምህርት ቤቶቿን ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ እንደምትከፍት ተሰምቷል።

    ሃንግዙ ከተማ ውስጥ ያሉ ሕፃናት ማኅበራዊ ርቀታቸውን መጠበቅ የሚያስችላው አንድ ሜትር ርዝማኔ ያለው ኮፊያ አድርገው ታይተዋል።

  8. አሜሪካ፡ 'ትንሿ ቤተ-እምነት' እስካሁን ክፍት ናት

    Georgia

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ውስጥ 'ትንሿ ቤተ-እምነት' የሚባልላት ሥፍራ እስካሁን ለአማኞቹ ክፍት ናት።

    አሜሪካ ውስጥ ያሉ በርካታ ቤተ-እምነቶች በኮቪድ-19 ምክንያት በሮቻቸውን ዘግተዋል። ነገር ግን ጆርጂያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው 'ትንሿ ቤተ-እምነት' በሮቿን ክፍት አድርጎ አማኞችን እየጠበቀች ነው።

    'ትንሿ ቤተ-እምነት' 2.7 ሜትር ስፋት፤ 5.4 ሜትር ርዝመት አላት። ፓስተር [ሰባኪ] አልባዋ ይህች ቤተ-እምነት 12 ወንበሮች አሏት።

    ቤተ-እምነቷ የቱሪስት መናኸሪያ ስትሆን አላፊ አግዳሚዎችን ጨምሮ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቤተ-እምነቱ አቅንተው ፀሎት ያደርጉባታል። ቤተ-እምነቷ ውስጥ ማሕበራዊ ርቀትን መጠበቅ የግድ ነው።

  9. ሲንጋፖር፤ እስያ ውስጥ ከቻይናና ሕንድ ቀጥላ በህሙማን ብዛት ሦስተኛ ሆነች

    ከስደተኛ ሠራተኞች መካካል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አምስት ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ደሴቲቱ አገር ሴንጋፖር በእስያ አህጉር ውስጥ ከፍተኛ በበሽታው የተያዘ ሰው ካለባቸው አገራት አንዷ ሆነች።

    ወረርሽኙን በመቆጣጠር ረገድ እንደ ቀዳሚ ምሳሌ ስትጠቀስ የነበረችው አገር አሁን 13 ሺህ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገኝተውባታል።

    ይህም በእስያ ውስጥ እያንዳንዳቸው ከአንድ ቢሊየን ሕዝብ ካላቸው ከቻይናና ከህንድ ቀጥላ ሦስተኛ በርካታ ህሙማን ያሉባት አገር አድርጓታል።

    ለሥራ አገሯ ውስጥ ባሉ ስደተኛ ሠራተኞች መካካል ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በየቀኑ በሺህዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎችን እየመረመረች ነው።

    ከደቡብ እስያ አገራት በመምጣት በግንባታ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በተጨናነቁ አፓርታማዎች ስለሚኖሩ በሽታው በቀላሉ የመሰራጨት እድልን እንዳገኘ ይነገራል።

    ትናንት ብቻ አብዛኛዎቹ ከውጪ አገራት የመጡ ሰራተኞች የሆኑበት 931 በበሽታው የተያዙ ሰዎች በአገሪቱ ተገኝተዋል።

    ሲንጋፖር በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመለየት በስፋት ምርመራ በማድረጓ ብዙ ሰዎችን ለማግኘት እንደቻለች የተጠቀሰ ሲሆን ምናልባትም ሌሎቹ የአህጉሪቱ አገራት ተመሳሳይ ምርመራ ቢያደርጉ ከፍ ያለ የበሽታው ክስተት ላይኖራት ይችላል ተብሏል።

  10. ኒው ዚላንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መቆጣጠሯን አስታወቀች

    ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኒው ዚላንድ ከኮሮናቫይረስ ጋር የምታደርገውን ፍልሚያ በአሸናፊነት እንደተወጣችው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን አስታወቁ።

    እንደጠቅላይ ሚኒስትሯ አገላለጽ በአገራቸው በአሁኑ ወቅት በምርመራ ያልታወቀ የበሽታው ስርጭት የለም፤ ስለዚህም ኒው ዚላንድ በኮሮናቫይረስ ላይ ያካሄደችውን “ዘመቻ ድል አድርጋለች”።

    በዚህም ምክንያት አገሪቱ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ወስዳው ከነበረው የእንቅስቃሴ ገድብ እርምጃ ውስጥ የተወሰነውን ከዛሬ ዕኩለ ቀን ጀምሮ በማንሳት ወደ ቀጣዩ የጥንቃቄ ደረጃ ዝቅ ታደርገዋለች።

    የኒውዚላንድ ጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አሽሊ ብሉምፊልድ አገሪቱ በሽታውን ለማጥፋት ካስቀመጠችው ግብ ላይ ደርሳለች ብለዋል።

    ባለስልጣኑ የወረርሽኙ ክስተት ዜሮ ሆኗል ማለት ሳይሆን “በሽታው የት እንደሚከሰት ለማወቅ ችለናል” ሲሉ በቁጥጥራቸው ስር መሆኑን አመልክተዋል።

    ኒውዚላንድ ውስጥ በዛሬው ዕለት አንድ በበሽታው የተያዘ ሰው ሲገኝ አንድ ሰው ደግሞ ህይወቱ አልፏል።

    በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ 1,500 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 80 በመቶዎቹ ድነዋል። በወረርሽኙ ሳቢያም 19 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

  11. ከኮሮናቫይረስ ያገገሙት ቦሪስ ጆንሰን ዛሬ ሥራ ይጀምራሉ

    ቦሪስ ጆንሰን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ ከአንድ ወር በኋላ ዛሬ ወደ ሥራቸው ዛሬ ይመለሳሉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ ለንደን ውስጥ በሚገኘው ሴንት ቶማስ ሆስፒታል ገብተው ለአንድ ሳምንት ህክምና የተከታተሉ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ለሦስት ቀናት በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ቆይተዋል።.

    ቦሪስ ጆንሰን በታመሙበት ወቅት ተክተዋቸው ሲሰሩ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶምኒክ ራብ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥራቸው ለመመለስ ዝግጁ ናቸው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ከከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ጋር ከሚያደርጉት ስብሰባ ቀደም ብሎ የዛሬውን የሙሉ ጊዜ ሥራቸውን የሚጀምሩት በኮቪድ-19 ላይ የሚደረገውን መደበኛ ስብሰባ በመምራት ነው።

    ነገር ግን ሰኞ ሰኞ የሚሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ በመምራት ያከናውኑ እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

  12. የፊት ጭንብል፡ ሕገ ወጥነት፣ ጥራታቸው ያልጠበቁ እና እጥረት

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የፈረንሳይ ፖሊስ በጥቁር ገበያ ሊሸጡ የነበሩ 140 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን መያዙን አስታወቀ።

    ፖሊስ ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ያላውን ጭምብል የያዘው በዋና ከተማዋ ፓሪስ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ሴን ዴኒ በተባለ ስፍራ አንድ ነጋዴ ከመኪና ላይ ሲያራግፍ ነው።

    ባለፈው ወር የፈረንሳይ መንግሥት በአገሩ ውስጥ ያሉና የሚመረቱ ሁሉም የፊት መሸፈኛ ጭንብሎት ለጤና ባለሙያዎች አገልገሎት እንዲውሉ አዟል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና ባለስልጣናት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ያሏቸውን 89 ሚሊዮን የፊት ጭንብሎችን መያዛቸውን አስታወቁ። ቻይና ወደ ውጪ የምተላካቸው ጭንብሎች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም እየተባለች ስትከሰስ ቆይታለች።

    በተጨማሪም ባለስልጣናቱ 16 ሚሊዮን የሚደርሱ የንግድ ተቋማትን በመመርመር ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ጸረ-ተህዋሲያን ማጽጃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ተናግረዋል።

    ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ በመደብሮችና በሕዝብ ትራንስፖርት ውስጥ ጭምብል ማድረግ ግዴታ መሆኑን ተከትሎ ጀርመን ውስጥ የሚገኝ የህክምና መገልገያዎችን በጅምላ የሚያቀርብ አንድ ተቋም ደግሞ በክምችቱ ውስጥ ያለው የፊት መሸፈኛ ጭንብል እያለቀ መሆኑን አመልክቷል።

  13. በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተጠቁ አገራት የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ ነው

    የጣሊያን ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በስፋት ተዛምቶ በርካታ ሕዝብ ያጠቃባቸው ሁለት የአውሮፓ አገራትና አንድ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ባለፉት ጥቂት ቀናት በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ተነገረ።

    በጣሊያን፣ በስፔንና በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ባሉ በርካታ ሳምንታት ሲመዘገብ የቆየው የሟቾች መጠን በተከታታይ በነበሩ ቀናት ውስጥ እየቀነሰ ዝቅተኛ ከሚባለው አሃዝ ላይ ደርሷል።

    በዚህም መሰረት አውሮፓ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካካል አንዷ በሆነችው ጣሊያን ውስጥ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ከታየው ዝቅተኛው መመዝገቡ ተነገረ።

    ባለፉት ሦስት ቀናት የሟቾች ቁጥር በተከታታይ የቀነሰ ሲሆን ቁጥሩ እስካሁን ከተመዘገበው ዝቅተኛው እንደሆነም ተነግሯል።

    የጣሊያን የሕዝብ ጥበቃ መስሪያ ቤት እንዳለው እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 26,644 ሰዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ሌላኛዋ የኮሮናቫይረስ ሰለባ አውሮፓዊት አገር ስፔንም ከወር ለሚበልጥ ጊዜ ከመዘገበችው የሟቾች መጠን ዝቅተኛውን ባለፉት ቀናት መዝግባለች።

    የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንዳመለከተው በአንድ ወር ውስጥ ካጋጠሙት የሞት አሃዝ ዝቅተኛውን በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት ላይ መዝግቧል።

    ስፔን ከስድስት ሳምንታት በፊት ጥላው የነበረውን ከቤት ያለመውጣት እገዳን በማላላት እድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከዕሁድ ጀምሮ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ከቤታቸው ወጥተው እንዳጫወቱ ፈቅዳለች።

    የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አሃዝ እንደሚያመለክተው በወረርሽኙ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23,190 ደርሷል።

    የኒው ዮርኩ ገዢ አንድሩ ኩሞ ከአርብ ጀምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ በግዛታቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተናገሩ።

    ባለፉት ቀናት በከተማዋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ400 በታች በመሆን ቀደም ካሉት ቀናት በተለየ በተከታታይ መቀነስን በማሳየቱ በሚቀጥሉት ቀናትም ቁጥሩ እንደሚወርድ ይጠበቃል።

    አስተዳዳሪው ጨምረው እንደተናገሩት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በወረርሽኙ ምክንያት የተጣለውን የእንቅስቃሴ እገዳ ለማንሳት ከሞት ቁጥር መቀነስ በተጨማሪ የበሽታው ስርጭት መጠንም መቀነስ ይኖርበታል።

  14. የሰኞ ሚያዝያ 19/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ?

    ሰኞ ሚያዝያ 19/2012፤ የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ እነሆ ጀመረ።

    በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ከኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ በአጠቃላይ ደግሞ ከዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የሚወጡ ዜናና መረጃዎችን እናቀርባለን።

    ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ የቀጥታ ዘገባ ገጻችንን እንድትጎበኙ በአክብሮት እንጋብዛለን። መልካም ዕለት!

    ቢቢሲ አማርኛ