አፍሪካውያን በቻይና “በዘፈቀደ እየታሰሩ ነው” ተባለ

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ በቻይናዋ ጉዋንዡ ግዛት አፍሪካውያን በግዴታ ለይቶ ማቆያ መግባታቸው “የዘፈቀደ እስር” ነው አሉ።
በኮሮናቫይረስ ፍርሀት ሳቢያ አፍሪካውያን መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን መግለጽ ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
አፍሪካውያን ኮሮናቫይረስ እንደሌለባቸው ቢረጋገጥም በሆቴሎች፣ በሆስፒታሎች፣ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸው እንዲራዘም እየተደረገ መሆኑም ለቢቢሲ ተገልጿል።
የሂውማን ራይትስ ዋቹ፤ ያኩዩ ዋንግ እንደሚሉት፤ ኮሮናቫይረስ የሌለባቸው አፍሪካውያን በግድ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው።
የቻይና መንግሥት እነዚህን ክሶች ቢያጣጥልም፤ የጤና ባለሙያዎች በጉዋንዡ የሚኖሩ አፍሪካውያን እንደተመረመሩ ተናግረዋል።
የአምንስቲ ኢንተርናሽናሉ ጆሽዋ ሮዘንዝዊግ፤ “ሰዎች ከጤና ጋር የተያያዘ ምክንያት ሳይኖር በቆዳ ቀለማቸው ብቻ በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚገደዱ ከሆነ የዘፈቀደ እስር ነው። ዓለም አቀፍ ሕግንም ይጻረራል” ብለዋል።
በርካታ አፍሪካውያን ከመኖሪያ ቤታቸውና ከሆቴላቸው እንዲወጡና በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መገደዳቸውን የማኅበረሰብ ወኪሎች ተናግረዋል።
ወደ ቤታቸው መመለስ ወይም ሆቴል መግባት እንደተከለከሉም ተገልጿል።

















