ደቡብ አፍሪካ ከ47 ሺህ በላይ ሰዎችን ብትመረምርም የወረርሽኙን ሙሉ ምስል ለማወቅ የበለጠ ምርመራ ያስፈልጋል አለች
በአገሪቱ ውስጥ እየተዛመተ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልግ የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር አስታወቁ።
ሚኒስትሩ ዝዌሊ ምክሂዜ እንደገለፁት ደቡብ አፍሪካ 47ሺ541 በኮሮና የተጠረጠሩ ሰዎችን የመረመረች ቢሆንም የወረርሽኙ መዛመት አለመዛመት ሙሉ ምስሉን ለማግኘት የበለጠ መሰራት አለበት ብለዋል።
"በፍጥነት ሥራዎችን ካላከናወንን ሊያጥለቀልቀን ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።
እስካሁን ባለው መረጃም በአገሪቷ ውስጥ 1ሺ462 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ሃገሪቷም ለ21 ቀናት እንቅስቃሴ በማገድ ሁሉን የመዝጋት ውሳኔ አስተላልፋለች።
በተለይም በሰኔ ወር የሚከሰተውን የጉንፋን (ኢንፍሉዌንዛ) በሽታንም ተከትሎ በርካታ ህመምተኞች ወደ ጤና ማዕከላት ሊጎርፉ እንደሚችሉ ጠቁመው ይሀም ሁኔታ የኮሮና መዛመትን እንደሚጨምረውም ፍራቻቸውን ሚኒስትሩ አጋርተዋል።
"ከጊዜ ጋር ሩጫ ነው የተያያዝነው" ያሉት ሚኒስትሩ "አገሪቱ መረጋጋት ላይ ብትሆንም ከፍተኛ ማዕበል ሊያጋጥም ይችላል" በማለት አስረድተዋል።
እስካሁን እየመረመሩ ያሉት ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ቢሆንም በቀጣይነት ወደ ተጨናነቁ መንደሮች በመሄድ ምርመራ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
ደቡብ አፍሪካ ካሏት ቋሚ መመርመሪያዎች በተጨማሪ 67 ተንቀሳቃሽ መመርመሪያ ተሽከርካሪዎችንም መድባለች።
ግለሰቦች ምልክቱ ታይቶባቸው ወይም ታመው ወደ ሆስፒታሎች ከመምጣታቸው በፊትም በየአካባቢያቸው ቢመረመሩ ወረርሽኙ የደረሰበትን ደረጃ መረዳት ያስችላል ብለዋል።