ለሰላምታ እጃቸውን ከዘረጉ 10 ዓመታት ያስቆጠሩት መምህር
መምህር ብርሃኔ አቻሜ ለሰላምታ እጃቸውን ከዘረጉ 10 ዓመታትን አስቆጥረዋል።
መምህር ብርሃኔ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፉት 10 ዓመታት "በእጀ ተጨባብጨ አላውቅም" ይላሉ።
በዘመኑ ቋንቋ፤ “እጅ ይነሳሉ እንጅ፤ እጅ አይሰጡም።” በዚህም ልማዳቸውም ወዳጅ ዘመዶቻቸው አኩርፈዋቸው ያውቃሉ።
በእርግጥ መምህሩ ይህን ልማድ የጀመሩት ሰው በመጥላት አሊያም በመናቅ አይደለም። ለጋራ ጤንነት ሲሉ እንጂ።
መምህር ብርሃኔ የዚህን ልማዳቸውን መነሻ ሲያስረዱ፤ ከአስር ዓመታት በፊት በየዓመቱ የዓለም የቆሻሻ ነገር ውድድር እንደነበር ያስታውሳሉ።
ታዲያ በዚያን ወቅት በነበረው ውድድር ላይ በቆሻሻነቱ አንደኛ ሆኖ የተገኘው የኮምፒዩተር ኪቦርድ ነበር ይላሉ። እንደ እርሳቸው መረጃ ከሆነ፤ በኮምፒዩተር ኪቦርድ ላይ በአንድ ስኩየር ኢንች 44 ሺህ ጀርሞች ይገኛሉ።
በዚህም ምክንያት “የእኔን ቆሻሻ ለሰው አላሳልፍም፤ የሌላም አልቀበልም” ብዬ በእጅ ሰላምታ መለዋወጡን እርግፍ አድርጌ ተውኩ ሲሉ ያስረዳሉ።
በዚህ ልማዳቸውም በርካታ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ስላኮረፏቸው፤ “ለሰላምታ እጀን አለመዘርጋቴ እናንተ ቆሻሻ ናችሁ ማለት ብቻ ሳይሆን፤ እኔም ቆሻሻ ነኝ ማለቴ ነው” ሲሉ አበክረው አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ በርካቶች በውል እየተረዷቸው የመጡት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አለምን እያስጨነቀ ከመጣ ወዲህ መሆኑን መምህሩ ይናገራሉ።
አሁን የኮሮና ቫይረስ መተላለፊያ መንገድ አንዱ እጅ በመሆኑ የእጃችንን ንጽህና መጠበቅ አለብን ሲሉም ይመክራሉ።
በግል ንጽህና ላይ የግል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል የሚሉት መምህር ብርሃኔ፤ ስለ ጤናችን መንግስት ይህን አድርጉ፤ አታድርጉ ሳይለን ራሳችን ተገቢውን ማድረግ እንችላለን ይላሉ።
መምህሩ "በእጅ በመጨባበጥ የሚደረግ ሰላምታ ይቅር፤ የቃል ሰላምታዎችን መለዋወጡ በቂ ነው፤ እኔም ስከተለው የኖርኩት ይህንኑ ነው" ሲሉም ይመክራሉ።