ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በፓኪስታን ቤት መቀመጥን ህግ ጥሰው ቤተሰባቸውን ሲቀብሩ የተገኙ ሃዘንተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ፓኪስታን ያወጀችውን ከቤት ያለመውጣት አስገዳጅ ሕግን ተላልፈው ቤተሰባቸውን ሲቀብሩ የተገኙ ሃዘንተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የዶክተር አንጁም ማህሙድ ቤተሰቦች ናቸው።
ዶክተሩ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱትን እናቱን ሊቀብሩ በሄዱበት ወቅት ቀብር ላይ መላ ቤተሰቡ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አንዳንድ ዘመዶቹም ከቤት ውጭ በር ተቆልፎባቸው በፖሊስ እየተጠበቁ እንደሚገኙ ዶክተሩ ለቢቢሲ አስረድቷል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ሃያ የሚሆኑ የቤተሰቡ አባላት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
ቤተሰቦቹም ሆነ እሱ ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ ሲሆን ወደ ፓኪስታን ያቀኑትም ለሠርጉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመሸመት በሚል ነበር።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባይከሰት የሠርጉ ቀን የተቆረጠው መጋቢት ወር ላይ ነበር።
በፓኪስታንም ቆይታቸው እናቱ በቫይረሱ ሞቱ፤ በነገታው ለቀብር በወጡበት ጊዜ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
"የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ፀሎት እየተጠናቀቀ በነበረበት ወቅት በርካታ የፖሊስ መኪኖች መጥተው ሃያ አምስት የሚሆኑ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል" ብሏል ዶክተሩ።
በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩት አባቱ ለኮሮናቫይረስ ህመምተኞች በተዘጋጀ የለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።
"አባቴ የ74 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ነው፤ በሃዘን ልቡ ተሰብሮ ባለበት ወቅት እንዲህ የሚያስጨንቅ ቦታ ውስጥ ማስገባት ትክክል አይደለም" ብሏል።
አክሎም "ከኮሮናቫይረስ ነፃ ነህ ቢባልም እስካሁንም ከለይቶ ማቆያው ሊለቁት አልቻሉም"
"ዘመዶቼም ለባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ተቆልፋባቸው ያለ ምግብና ውሃ ይገኛሉ" ብሏል።
የአካባቢው ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ሰይፍ አንዋር ጃፓ በበኩላቸው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወቅት መመሪያዎቹ ተግባራዊ አልሆኑም ብለዋል።
ነገር ግን ዶክተር አንጁም በኮሚሽነሩ ሃሳብ አይስማም በመመሪያው መሰረት አካላዊ ርቀትን እንደጠበቁና በቀብሩ ላይ የተገኙትም ሰዎች ቁጥር ጥቂት እንደሆነ ነው።