ሄዝቦላህ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከተሳተፈ እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት እንደምትፈጸም ማስጠንቀቋ ተነገረ
ሄዝቦላህ በማንኛውም መንገድ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ፤ እስራኤል አየር ማረፊያን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በሊባኖስ ላይ እንደምትፈጽም ማስጠንቀቋን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።
ሮይተርስ ያነጋገራቸው ሁለት የሊባኖስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ እስራኤል የማስጠንቀቂያ መልዕክቷን ያደረሰችው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል ተብሏል።
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ራጂ በበኩላቸው በጄኔቫ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ሄዝቦላህ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ አገሪቱ ከእስራኤል ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በምንም ዓይነት የዋሽንግተን እና ቴህራን ውጊያ ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርግ ማሳሰባቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የሊባኖስ መንግሥት ይህን ጥሪ ያቀረበው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚል ስጋት ባየለበት በዚህ ጊዜ ነው። ሁለተኛው የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየተቃረበ ሲሆን ኢራንም ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ዓመታዊ የጦርነት ልምምድ ጀምራለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከኢራን ጋር በምታደርገው የኒውክሌር ድርድር ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ፤ ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በአውሮፓውያኑ 2024 የተካሄደውን ጨምሮ ከእስራኤል ጋር ለበርካታ ጊዜያት ተዋግቷል። አሁንም ቡድኑ በአሜሪካ እና ኢራን ጉዳይ ሊሳተፍ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው የሊባኖስ ባለሥልጣናት ሄዝቦላህ በአገሪቱ ዜጎች ላይ “መጥፎ ሁኔታን” ሊያመጣ በሚችል መልኩ ምላሽ እንዳይሰጥ ጥያቄ እንዳቀረቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራጂ ተናግረዋል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄኔቫ ውስጥ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "እስራኤላውያን የሲቪል መሠረተ ልማቶችን፤ ምናልባትም ቤሩት የሚገኘውን አየር ማረፊያ ልትመታ እንደምትችል የሚያሳዩ ምልክቶች ለሊባኖስ ደርሰዋል" ብለዋል።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ማክሰኞ ዕለት በታተመ ጋዜጣ ላይ በወጣ ቃለ መጠይቃቸው ፤ ሄዝቦላህ ሊባኖስን ወደ "ሌላ ጀብዱ" እንዳያስገባት አሳስበዋል።
አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ናኢም ቃሲም በአንጻሩ ባለፈው ወር በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ ቡድኖ በዋሽንግተን እና ቴህራን ጉዳይ “ገለልተኛ እንዳልሆነ” ተናግረዋል። በዚህ ጦርነት "ሊፈጸም የሚችል ጥቃት ዒላማ እንደሆነም" መግለጻቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።