የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ግድያ ተከትሎ ኢራን እና እስራኤል እንደ አዲስ ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት እንደተገደሉ ከተረጋገጠ በኋላ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና በእስራኤል ላይ “አስከፊ ጥቃት” እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል። ይህንንም ተከትሎ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢራቅ እና ኦማን ውስጥ ጥቃት ተፈጽሟል። የእስራኤል ጦርም የኢራን ዋና ከተማ ቴህራንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኤፕስቲን ከመታሰሩ አንድ ቀን ቀደሞ ሞሮኮ ውስጥ ውድ ቤተመንግሥት ሊገዛ እንደነበር ተገለጸ

    ባለፈው ወር የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች መሠረት ጄፍሪ ኤፕስቲን እአአ በ2019 ከመታሰሩ አንድ ቀን በፊት በሞሮኮ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ቤተ መንግሥት ለመግዛት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር ተባለ።

    ኤፕስቲን እአአ ከ2011 ጀምሮ ቢን ኤናኪልን የተባለውን በሞሮኮ የሚገኝ ቤተ መንግሥት ለመግዛት ሲጥር የነበረ ቢሆንም፣ በዋጋው እና በግዢ ውል ዙሪያ ከሻጩ ጋር ባለመግባባቱ ለዓመታት ተጓትቷል።

    ቅንጡው ፓልሜሬይ ማራኬሽ አካባቢ የሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥት በ1,300 የእጅ ባለሞያዎች የተገነባ እና በተጌጡ ቅርጻ ቅርጾችን እና ሞዛይኮችን የተዋበ ድንቅ የሕንጻ ሥራ እንደሆነ ተገልጿል።

    ኤፕስቲን ከመያዙ አንድ ቀን በፊት እአአ ሐምሌ 5/2019 14.95 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንዲፈጸም ፈርሟል።

    ይህም ንብረቱን ከሚያስተዳድረው ኩባንያ ጋር በ18 ሚሊዮን ዩሮ ለመግዛት ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላ ነው።

    ይፋ በሆኑት ሰነዶች መሠረት ኢፕስቲን በአሜሪካ ባለሥልጣናት ከወሲብ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት የፈጸመው የመጨረሻው የግዢ ውል ነው።

    በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ ሦስት ቀናት አስቀድሞ የኢፕስቲን የሒሳብ ባለሙያ ሪቻርድ ኻሃን ገንዘቡ እንዳይከፈል በማድረጉ ግዢው ሳይፈጸም ቀርቷል።

    የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት የወሲብ ንግድ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን የተለያዩ ሰነዶች ይፋ አድርጓል።

    ኤፕስቲን በ2019 ነሐሴ ላይ በወሲብ ንግድ ዝውውር ተከስሶ፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ፣ በኒው ዮርክ በሚገኝ እስር ቤት ብይን እየተጠባበቀ ሳለ ነበር የሞተው።

    ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ በማቅረብ 'የወሲብ ወንጀል' በሚል ከተፈረጀ በኋላ ታዳጊዎችን ለወሲብ ንግድ የሚያቀርበው "መጠነ ሰፊ በሆነ የወንጀል መረብ ነው" በሚል ተከስሷል። ኤፕስቲን "ጥፋተኛ አይደለሁም" ሲል ተከራክሯል።

  2. ሕንድ እና እስራኤል በመከላከያ እና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ተስማሙ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በእስራኤል ለሁለት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ሕንድ እና እስራኤል በመከላከያ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ተናገሩ።

    ሞዲ እና የእስራኤል አቻቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ አገራቱ ነፃ የንግድ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

    ሞዲ በኤክስ ገጻቸው ላይ "በጊዜው የተፈተነ አጋርነታችንን ወደ ልዩ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ለማሳደግ ታሪካዊ ውሳኔ ወስነናል" ብለዋል።

    ሞዲ ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ በእስራኤል ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ጉዞ ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ካላት ግንኙነት አንጻር የሕንድ የውጭ ፖሊሲ ፈተና ተድርጎ ተቆጥሯል።

    በጉብኝቱ ወቅት ሞዲ የእስራኤልን የአይሁዳውያን ፍጅት መታሰቢያ የሆነውን ያድ ቫሼምን የጎበኙ ሲሆን፣ በአገሪቱ ምክር ቤት ተገኝተውም ንግግር አድርገዋል።

    በዚህ ንግግራቸው ላይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዘዋል።

    "ሕመማችሁ ይሰማናል። ሐዘናችሁን እንጋራለን። ሕንድ በዚህ ወቅት እና ከዚያም በኋላ . . . ከእስራኤል ጋር በፅኑ ትቆማለች" ብለዋል።

    ቀደም ሲል ሕንድ የሐማስን ጥቃት አውግዛ ለእስራኤል ያላትን አጋርነቷን በመግለጽ በጋዛ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በተመለከተም ስጋቷን አስታውቃ ነበር።

    ሁለቱ አገራት በመረጃ መረብ ደኅንነት፣ በንግድ፣ በኅዋ ምርምር፣ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና እና በኢኮኖሚ ትብብር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

    በተጨማሪም እስራኤል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 50,000 ሠራተኞችን ከሕንድ ወደ አገሯ ለማስገባት ቃል ገብታለች።

  3. በአከራካሪ ቦታዎች ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን የሚቃወም ሠልፍ በትግራይ ከተሞች ተካሄደ

    ምርጫ ቦርድ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ በሆኑ አምስት የምርጫ ክልሎች ከሁለቱም ክልል ውጭ ሆነው በቀጥታ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች ምርጫ እንዲካሄድባቸው ውሳኔ ማስተላለፉን የሚቃወም ሰልፍ ትበትግራይ የተለያዩ ከተሞች ተካሄደ።

    የሁመራ፣ የአዲ ረመጽ፣ የጠለምት፣ የኮረም ኦፍላ እና የራያ አላማጣ የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንዲካሄድባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ የካቲት 16/2018 ዓ.ም ነው።

    በትግራይ የክልል ከተሞች ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ የተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍን የተጠራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ንግግር አድርገዋል።

    በክልሉ ይህንን የተቃውሞ ሠልፍ ለማካሄድ በሚል የመንግሥት እና የግል ተቋማት እንዲሁም ትምሀርት ቤቶች ተዘግተዋል።

    የምርጫ ቦርድ አምስቱ አከራካሪ ቦታዎች ከሁለቱ ክልሎች ውጭ ሆነው ምርጫ እንዲካሄድባቸው ውሳኔ ያሳወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ ነው።

    በአምስቱ የምርጫ ክልሎች የሚደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በቀጥታ እንዲሆን እና ለክልል ምክር ቤት ምርጫ አመቺ ጊዜ ተመርጦ ወደፊት እንዲካሄድ በመጀመሪያ የወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ቦርዱ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው በአማራ እና በትግራይ ክልል ያለው የይገባኛል ጥያቄ በሕገ መንግሥት ውሳኔ እስከሚፈታ ድረስ መሆኑም ተገልጿል።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ምርጫ ቦርድ ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ በምርጫ እንደማይሳተፍ ያስጠነቀቀው ስምረት ፓርቲ፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ “በጊዜያዊነት” እንዲታገድ አድርጓል።

    የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህወሓት፣ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና ሌሎችም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ውሳኔውን ሲቃወሙ፤ በአማራ ክልል በኩል ያሉ ፖለቲከኞች የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ደግፈውታል።

  4. በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን መካከል ግጭት ሲጀመር፣ ካቡል ላይ የአየር ጥቃት ተፈጸመ

    ፓኪስታን የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

    ፓኪስታን አርብ ዕለት ጥቃት መፈጸም የጀመረችው ታሊባን ሁለቱን አገራት በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተጋጋለ የመጣ ሲሆን፣ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼባዝ ሻሪፍ አገራቸው “ማንኛውም ጠብ አጫሪነትን የመስበር ሙሉ አቅም አላት” ሲሉ ተናግረዋል።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በታሊባን ላይ “ግልጽ ጦርነት” አውጀዋል።

    የታሊባን ወታደራዊ ቃል አቀባይ “ጥቃት ከተፈጸመብን ምላሽ እንሰጣለን፤ ነገረ ግን ግጭት በአሁኑ ሰዓት አልጀመርንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢኡላህ ሙጃሂድ በኤክስ ገጻቸው ላይ በፓኪስታን ወታደሮች ላይ እንደ አዲስ ጥቃት መከፈቱን ጽፈው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ አጥፍተውታል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣናት በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲረግብ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ኢራን ለማደራደር ጠይቃለች።

    የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፓኪስታን አቻቸውን የሁለቱ አገራት ውጥረት እንዲረግብ ማነጋገራቸው ተገልጿል።

    የታሊባን ባለሥልጣናት ፓኪስታን ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸው ከ50 በላይ ወታደሮችን መግደላቸውን እንዲሁም 19 የፓኪስታን የድንበር ኬላዎችን ማውደማቸውን እና በርካታ ወታደሮችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል።

    ፓኪስታን በበኩሏ ታሊባን የሚቆጣጠራቸው 27 የድንበር ኬላዎችን ማውደሟን ገልጻ፣ በታሊባን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል ብላለች።

  5. አሜሪካዊ ዲፕሎማት በቡርኪና ፋሶ ሁለት ታዳጊ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

    ቡርኪናፋሶ በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ ይሠራ የነበረ አሜሪካዊ ሁለት ታዳጊ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም ወንጀል ተከስሶ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

    ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ዳኞች ግለሰቡን ታዳጊዎች ላይ ፆታዊ ጥቃት በመፈጸም፣ በማታለል እና በማስገደድ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማደናቀፍ ሙከራ በማድረግ ወንጀሎች ጥፋተኛ ብለውታል።

    የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ ግለሰቡ የ41 ዓመቱ ፎዴ ሲታፋ መሆኑን እና ከጥቅምት ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰጠቱን አስታውቋል።

    ዐቃቤ ሕጎች ወንጀሉ የተፈጸመው ከአውሮፓውያኑ 2022 እስከ 2023 በቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ዋጋዱጉ ግለሰቡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተቀጣሪ በነበረበት ወቅት ነው ብለዋል።

    ለፍርድ ቤት የቀረበው ማስረጃ ወንጀሉ የተፈጸመው በአሜሪካ ዲፕሎማት መኖሪያ ቤት መሆኑን ያሳያል።

    ሁለቱ ጥቃት የደረሰባቸው ታዳጊዎች በወቅቱ የ13 እና የ15 ዓመት ልጆች ነበሩ።

    ግለሰቡ ለአንዲቷ ታዳጊ ግልጽ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በመላክ እንዲሁም የቤቱን ሠራተኛ ለመርማሪዎችን ሐሰተኛ ቃል እንድትሰጥ በማግባባት ጥፋተኛ ተብሏል።

  6. የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በእስራኤል አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ታዩ

    የውጊያ ጄቶችን አየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችሉ በርካታ የአሜሪካ አየር ኃይል ቦይንግ ኬሲ-135 አውሮፕላኖች ቴል አቪቭ አቅራቢያ በሚገኘው ቤን ጎሪያን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ታዩ።

    አውሮፕላኖቹ ከሁለት ቀናት በፊት በስፍራው መድረሳቸው ተገለጿል።

    እነዚህ ኬሲ-135 አውሮፕላኖች ረጅም ርቀት ተጉዘው ጥቃት የሚፈጽሙ ተዋጊ ጄቶችን በረራ ላይ ሳሉ ነዳጅ መሙላት የሚችሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የአሜሪካ ጦር በቀጠናው ያለውን ዝግጅት የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

    አውሮፕላኖቹ እስራኤል የደረሱት በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል የሚደረገው የኒውክሌር ፕሮግራም ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ቀጠናውን ወደ ተራዘመ ጦርነት አይመራውም ሲሉ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ቀጠናውን ወደ ተራዘመ ጦርነት እንደማይመራ ገልጸው “በመካከለኛው ምሥራቅ ማብቂያው የማይታወቅ ጦርነት እንደምንጀምር የሚነገረው መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።

    ቫንስ “ዲፐሎማሲያዊ መንገድን ነው የምንመርጠው” ካሉ በኋላ “ያ ግን የሚመሠረተው ኢራን በምትወስደው እርምጃ ላይ ነው “ ብለዋል።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል በስዊትዘርላንድ የተደረገው ሦስተኛው ዙር ድርድር ሐሙስ ዕለት ተጠናቅቋል።

    የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት በጄኔቫ ባካሄዱት ድርድር "ከፍተኛ ለውጦች" መታየታቸውን የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገረዋል።

  7. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ ጉብኝት አዘርባጃን ገቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ ጉብኝት አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ መግባታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የአዘርባጀን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው 'አዛርታክ'፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 19/2018 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በአህጉረ እስያ እና አውሮፓ ወደ ምትገኘው አገር መድረሳቸውን ዘግቧል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት ምሽት ላይ ጉብኝቱን በማስመልከት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት እና ምሥል አስታውቋል።

    በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከከፍተኛ የልዑካን ቡድናቸው ጋር ሐሙስ ረፋድ ላይ አዘርባጃን መግባታቸውን አመለክቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባኩ ውስጥ በሚገኘው ሃይደር አሊየቭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሚር ሻሪፎቭ እና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊየቭ እንዲሁም ሌሎች ባለሥልጣናት ተገኝተው አቀባበል እንዳደረጉላቸው ዘካስፒያን ፖስት እና ሪፖርት የተባሉት የአገሪቱ የዜና ድረገጾች ዘግበዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይፋዊ ጉብኝት ለምን ያህል ቀናት እንደሚደረግ፣ ከየትኞቹ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚገናኙ እና በምን ጉዳይ እንደሚነጋገሩ በይፋ አልተገለጸም።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል ያለው ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጠነከረ መምጣቱን እና ለዚህም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው መሳያ መሆነት ጠቅሷል።

    በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የልዑካቸው ጉብኝት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ወደ ላቀ እና ትርጉም ወዳለው ደረጃ እንደሚያደርስ ይጠበቃል ብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በካስፒያን ባሕር እና በካውካሰስ ተራሮች መካከል በአውሮፓን እና በእስያ አዋሳኝ ቦታ ላይ ወደምትገኘው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካል አዘርባጃን፤ ያደረጉት ጉዞን በተመለከተ በራሳቸውም ሆነ በጽህፈት ቤታቸው በኩል እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

  8. ሂላሪ ክሊንተን እና ባለቤታቸው የወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲንን በተመለከተ ምስክርነት ሊሰጡ ነው

    የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፤ የሟቹን የወሲብ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስቲንን ወንጀሎች በሚመረምረው የተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ ፊት ሊቀርቡ ነው።

    ከዚህ ቀደም ዴሞክራቲክ ፓርቲን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ሂላሪ፤ ከባለቤታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ጋር በመሆን በምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ፊት ለመመስከር የተስማሙት በቅርቡ ነበር።

    ሁለቱ ጥንዶች ከዚህ ቀደም ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ የቀረበላቸውን ጥሪ ፖለቲካዊ ዓላማ እንዳለው በመግለጽ ውድቅ አድገው ነበር።

    አሁን ለመመስከርመስማማታቸው በምክር ቤቱ ሊከፈትባቸው ይችል የነበረውን ኮንግረስን መዳፈርን የተመለከተ ሂደት ያስቀርላቸዋል።

    ሂላሪ ክሊንተን ከኤፕስቲን ጋር ስለ መገናኘታቸውም ሆነ ስለ ማውራታቸው እንደማያስታውሱ ተናግረዋል።

    ከኤፕስቲን ጋር የሚተዋወቁት ባለቤታቸው ቢል ክሊንተን ደግሞ ምንም ጥፋት እንዳልፈጸሙ እና ስለ ግለሰቡ ሌሎች ወንጀሎች እንደማያውቁ ገልጸዋል።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከኤፕስቲን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን የሚናገሩት ቢል ክሊንተን፤ ስማቸው ከግለሰቡ ጋር እንዲነሳ የሚያደርግ ነገር በመኖሩ እንደሚጸጸቱ ተናግረዋል።

    ሂላሪ ዛሬ ሐሙስ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ሲሆን፣ ቢል ክሊንተን ደሞ አርብ ዕለት ኮሚቴው ፊት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

    የጥንዶቹ ምስክርነት የሚደመጠው በኒው ዮርክ ግዛት ቻፓኳ ውስጥ ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ነው። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ምስክርነት የሚሰጠው በዝግ ነው።

    ይሁን እንጂ ክሊንተኖች ከሚቀርበው ማስረጃ ውስጥ የተወሰነው ክፍል ለመገናኛ ብዙኃን ሾልኮ ይወጣል የሚል ስጋት ስላደረባቸው፤ ምስክርነታቸው ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን መሟገታቸው ተዘግቧል።

    የሂላሪ ክሊንተን ምስክርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የኮሚቴው አባል ሆኑ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

    ምስክርነታቸው በከፍኛ ሁኔታ እየተጠበቀ ያለው ቢል ክሊንተን ከአውሮፓውያኑ 1983 በኋላ በምክር ቤት ኮሚቴ ፊት ቀርበው የመሰከሩ የመጀመሪያው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

  9. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሙስሊሞቹን የኮንግረስ አባላት “ወደ መጡበት መልሰን መላክ አለብን” አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ለኮንግረስ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ተቃውሞ ያሰሙትን የምክር ቤት አባላት ኢልሃን ኦማር እና ራሺዳ ትላቢን “ወደ መጡበት መልሰን መላክ አለብን” አሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር ያደረጉበት 'ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን' የተባለው የምክር ቤት ንግግራቸው ሲካሄድ ዴሞክራቶች በተለያየ መልኩ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።

    ትራምፕ ስለ ስደተኞች እና ሚኒሶታ ውስጥ በሚገኙ የሶማሊ አሜሪካ ማኅበረሰብ አባላት ይፈጸማል ስላሉት የማጭበርበር ተግባር በሚናገሩበት ወቅት የግዛቱ ተወካይ የሆኑት ኢልሃን ኦማር በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንቱ ላይ ሲጮኹ ታይተዋል።

    የኮንግረስ አባሏ “ይሄ ውሸት ነው፣ ውሸታም ነዎት” ሲሉ እርሳቸውን በተመለከተ ሲናገሩ ለነበሩት ትራምፕ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ከኢልሃን አጠገብ ተቀምጠው የነበሩት የሚቺጋን ግዛት ተወካይዋ ራሺዳም ኢልሃንን ተቀላቅለው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ሁለቱን የምክር ቤት አባላትን “ዝቅተኛ የማገናዘብ ብቃት ያላቸው” ሲሉ ዘልፈዋል። በስብሰባው ላይ “ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ሲጮሁ” ነበርም ብለዋል።

    ሁለቱ ፖለቲከኞች “ልክ እንደ እብዶች፣ አእምሮአቸው እንደተቃወሰ እና የታመሙ ሰዎች የፈጠጠ እና የደፈረሰ ዐይን ነበራቸው፤ በእውነቱ ከሆነ የሕክምና ተቋም ውስጥ መገባት ያለባቸው ነው የሚመስሉት” ብለዋል።

    አክለውም “በተቻለ ፍጥነት ወደ መጡበት መልሰን መላክ አለብን” በማለት ጽፈዋል። “አሜሪካን ለመጉዳት እንጂ ለመርዳት ማድረግ የሚችሉት ነገር የለም” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ቢሉም ሁለቱም የምክር ቤት አባላት ዜግነታቸው አሜሪካዊ ነው።

  10. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ “ጊዜያዊ ዕገዳ“ አሳለፈ

    የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ አምስት የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንዲያካሄድ ያሳለፈው ውሳኔ ላይ ጊዜያዊ ዕግድ ጣለ።

    ምርጫ ቦርድ በሁለቱ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ በሆኑ አምስት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ እና ከአማራ ክልል ውጭ ሆነው በቀጥታ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች ምርጫ እንዲካሄድባቸው ውሳኔ ያስተላለፈው ሰኞ የካቲት 16/2018 ዓ.ም. ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐሙስ የካቲት 19/2018 ዓ.ም. በውሳኔው ላይ ዕግድ ጥሏል።

    በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ስምረት ፓርቲ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሲያደርግ በይፋ ተቃውሞውን በመግለጫ ያሳወቀ ሲሆን፣ ጉዳዩንም በፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ በኩል ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባጋሩት በዚህ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ መልሱን የካቲት 25/2018 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዝዟል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካካል አከራካሪ ሆነው የቆዩ የተባሉትን አምስት የምርጫ ክልሎች በተመለከተ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ደርሶኛል ያለውን ውሳኔ ይፋ ካደረገ በኋላ የሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞች ድጋፍ እና ተቃውሟቸውን ግልጸዋል።

    የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና ሌሎችም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ውሳኔውን ሲቃወሙ፤ በአማራ ክልል በኩል ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተላለፈውን ውሳኔ ደግፈውታል።

  11. ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ወዳጅ ልትሆን እንደምትችል መሪዋ ተናገሩ

    የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የአገራቸውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አቅምን ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸው እና ይህንንም አሜሪካ እንድታከበር ጥሪ አቀረቡ።

    አሜሪካ እና ሰሜን ኮሪያ “ወዳጅ መሆን” እንደሚችሉ የተናገሩት ኪም ነገር ግን ይህ የሚሆነው አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗን ስትቀበል ነው ብለዋል።

    ይህ በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ የተደረገው የመሪው ንግግር ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጪው ሚያዝያ ቻይናን በሚጎበኙበት ወቅት ድርድር ለማድረግ የሚያስችል ዕድል ለመክፈት የታሰበ ነው ተብሏል።

    ነገር ግን ኪም ደቡብ ኮሪያን “ዋነኛዋ ጠላት” በማለት ከጎረቤታቸው ጋር ሊኖር የሚችልን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተስፋን አጨልመውታል።

    አሜሪካ "ያለንን የኒውክሌር ይዞታ የምታከበር ከሆነ እና የጠላትነት ፖሊሲዋን የምታነሳ ከሆነ...የማንስማማበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም” ሲሉ ኪም በኮሪያ ሠራተኞች ፓርቲ ጉባኤ ላይ መናገራቸውን የአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    መሪው ጨምረውም የአሜሪካ እና የሰሜን ኮሪያ የወደፊት ግንኙነት “ሙሉ ለሙሉ በአሜሪካ አመለካከት ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት “ሰላማዊም ሆነ ዘላቂ ፍጥጫ ለሁለቱም ዝግጁ ነን፤ ምርጫውም የእኛ ሳይሆን የእነሱ ነው” ብለዋል።

    ጎረቤት ደቡብ ኮሪያን በተመለከተም የአገራቸው ወዳጅ ካልሆኑት መካከል መሆኗን እና "ከእኛ ጋር ድንበር አስከተጋራች ድረስ፣ በሰላም ለመኖር ያላት ብቸኛ አማራጭ እኛን በሚመለከቱ ጉዳዮች ውስጥ መግባት የለባትም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  12. ሶማሊላንድ ከፍተኛ ዲፕሎማቷን በእስራኤል የመጀመሪያ አምባሳደሯ አድርጋ ሾመች

    ሶማሊላንድ ባለፈው ታኅሣሥ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና በሰጠቻት እስራኤል ውስጥ አምባሳደር ሆነው የሚወክሏትን ከፍተኛ ዲፕሎማት ሾመች።

    የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሞሐመድ ኦማር ሃጊ ሞሐሙድ በእስራኤል ውስጥ የአገሪቱ አምባሳደር እና ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሆኑ መሾማቸውን ባወጣው የሹመት ደብዳቤ አሳውቋል።

    በአምባሳደርነት የተሾሙት ከፍተኛ ዲፕሎማቱ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ ላይ የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ አማካሪ እንዲሁም በታይዋን ውስጥ የሶማሊላንድ ተወካይ ነበሩ።

    የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሹመቱ በሶማሊላንድ እና በእስራኤል መካከል በተደረሰው ስምምነት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር የሶማሊላንድ ጉብኝት መሠረት የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ እንደተቀበለው አሳውቋል።

    ጨምሮም እስራኤል በቅርቡ በሶማሊላንድ አምባሳደሯን እንደምትሾም እና በሁለቱ ወገኖች መካከል በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ግንኙነቶችን እንደምታጠናክር አሳውቋል።

    ነጻ አገርነቷን አውጃ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተነጥላ ለቆየችው ሶማሊላንድ እስራኤል የአገርነት ዕውቅናን የሰጠችው ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም. ነው።

    ይህን የእስራኤል ውሳኔ ሶማሊያ “በሉዓላዊነቷ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው” በማለት ያወገዘች ሲሆን፤ አገራት፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም ዕውቅናውን ተቃውመው ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

  13. የኩባ ባሕር ጠባቂዎች በአሜሪካ ፈጣን ጀልባ ላይ ተኩሰው አራት ኩባውያንን ገደሉ

    የኩባ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች በከፈቱት ተኩስ በአሜሪካ በተመዘገበች ፈጣን ጀልባ ላይ ሲጓዙ የነበሩ አራት ኩባውያን ሲገደሉ ስድስቱ ደግሞ ቆሰሉ።

    የኩባ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በፈጣን ጀልባዋ ላይ ሲጓዙ የነበሩት ኩባውያን በተጠጓቸው የኩባ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ላይ ረቡዕ ዕለት ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ነው ጉዳቱ የደረሰባቸው።

    የኩባ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በጀልባዋ ላይ የነበሩት 10 ሰዎች ሲሆኑ ከመካከላቸውም የቀደመ የወንጀል ክስ ያለባቸው እና የታጠቁ እንደነበር እና “የሽብር ዓላማ ይዘው ሰርገው ለመግባት” ዓላማ ነበራቸው ብሏል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አገራቸው “ፈጽሞ ያልተለመደ” ያሉትን ክስተት እየመረመረች መሆኑን ገልጸዋል።

    በፈጣን ጀልባዋ ላይ ሽጉጦች፣ ጠመንጃዎች፣ ፈንጂዎች እና ሌሎች ወታደራዊ ቁሶች መገኘታቸውን እና በተከፈተው ተኩስ አንድ የጠረፍ ጥበቃ አዛዥ ጉዳት እንደደረሰበት የኩባ መንግሥት አስታውቋል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኩባ ባወጣችው መረጃ ላይ እንደማይተማመኑ በመግለጽ ክስተቱን በተመለከተ የራሳቸውን ምርመራ በማድረግ እንደሚያረጋግጡ አሳውቀዋል።

    ይህ ሁኔታ የተከሰተው ኩባ ወዳጇ ከሆነችው ቬንዙዌላ የሚቀርብላትን ነዳጅ አሜሪካ ማገዷን ተከትሎ በአገሪቱ ያለው የነዳጅ እጥረት በመባባሱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ከፍ ባለበት ጊዜ ነው።

    አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ፈጽማ የኩባ ወዳጅ የሆኑትን ፕሬዝዳንት ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ከቬንዙዌላ ወደ ኩባ የሚላከው ነዳጅ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

  14. ዚምባብዌ የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ ጋር የደረሱትን የጤና ስምምነት ውድቅ አደረገች

    አሜሪካ እንዲሰጣት በምትጠይቀው ጥበቃ የሚፈልጉ መረጃዎች ምክንያት ዚምባብዌ ከአሜሪካ 376 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝላትን የጤና ስምምነት ውድቅ አደረገች።

    ይህ የዚምባብዌ ውሳኔ ይፋ የሆነው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስምምነቱ ለአሜሪካ ያደላ ነው ያሉበት የመንግሥት ማስታወሻ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነው።

    የመንግሥት ቃል አቀባይ ኒክ ምናንግዋ በስምምነቱ አሜሪካ የጤና ናሙናዎችን ለምርምር እና ለንግድ አገለግሎት መጠየቋን እና ነገር ግን ወደ ፊት ለሚሰሩ ክትባቶች እና መድኃኒቶች ለማጋራት ፈቃደኛ አይደለችም ብለዋል።

    በዚህም ሳቢያ አሜሪካ ለዚምባብዌ የምትሰጠውን የጤና ድጋፍ ለማቋረጥ እንደምትገደድ በአገሪቱ የአሜሪካ አምባሳደር ፓሜላ ትሬሞንት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

    ባለፉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ ለዚምባብዌ ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የጤና ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ኤምባሲዋ ገልጿል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአሜሪካ የእርዳታ አቅርቦት ላይ ባደረጉት ለውጥ የተዋወቀው አዲሱ አሠራር አገራት ጠቃሚ የጤና መረጃዎችን ለአሜሪካ በማጋራት የተለያየ መጠን ያለው ድጋፍን እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።

    እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 የአፍሪካ አገራት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን፣ ነገር ግን በሚተላለፈው መረጃ እና አገራት በሚያገኙት ጥቅም ላይ ጥያቄ እየተነሳ ነው።

    ስምምነቱን ቀድማ የፈረመችው ኬንያ ውስጥ ያሉ የመብት ተሟጋች ቡድኖች የዜጎች ግላዊ የጤና መረጃ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱን እንደ ስጋት በመጥቀስ ባቀረቡት ክስ ስምምነቱ በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ መታገዱ ይታወሳል።

  15. የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለጉብኝት እስራኤል ገቡ

    የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እስራኤል ገቡ።

    ሞዲ በእስራኤል ፓርላማ፣ ክኔሴት ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

    ነገር ግን ከፍልስጤም መሪዎች ጋር ለመናኘት ምንም ዓይነት ፕሮግራም እንዳልተያዘላቸው ተገልጿል።

    ጉብኝቱ የመጣው ሁለቱም አገራት በመከላከያ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ ረገድ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

    የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ከአስር ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው።

    ይሁን እንጂ ተንታኞች እንደሚሉት ጉብኝቱ ሕንድ ከእስራኤል እና ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነው ተብሏል።

    በአውሮፓውያኑ 2017 ሞዲ እስራኤልን የጎበኙ የመጀመሪያው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል። ጉዞው በሁለቱ አገራት ወዳጅነት መካከል ትልቅ ለውጥ ማምጣቱ ይገለጻል።

    ሁለቱ አገራት በፀረ-ሽብር እና በመከላከያ ዘርፍ በቅርበት ይሠራሉ። ሕንድ ከእስራኤል የጦር መሳሪያ ገዢዎች መካከልም ዋነኛዋ ናት።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የናሬንድራ ሞዲን ጉብኝት "ታሪካዊ" ሲሉ ጠርተውታል።

    “በእስራኤል እና በሕንድ መካከል ያለው ትስስር በሁለት ዓለም አቀፍ መሪዎች መካከል ያለ ጠንካራ ጥምረት ነው። በፈጠራ፣ በደኅንነት እና በጋራ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አጋሮች ነን። አብረን ለመረጋጋት እና ለዕድገት ቁርጠኛ የሆኑ አገሮቻችንን በጥምረት እየገነባን ነው” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

  16. የመንግሥታቱ ድርጅት ጄነራል ዳጋሎን ጨምሮ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጣለ

    የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎን ጨምሮ አራት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ መሪዎች ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለ።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ማዕቀቡን የጣለው ወታደራዊ መሪዎቹ በኤል ፋሽር በፈጸሙት ወንጀል ነው ተብሏል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤል ፋሸርን የተቆጣጠረው በጥቅምት ወር ሲሆን፣ በከተማዋ የተፈጸመው ለሦስት ዓመት ያህል በተካሄደው የሱዳን እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከታየው ሁሉ አስከፊው ነበር ተብሏል።

    ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት እውነት አፈላላጊ ቡድን በከተማዋ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት እርምጃ ለመካሄዱ አስረጅ ነው ብሏል።

    በኤል ፋሽር የጅምላ ግድያን ጨምሮ ማንነት ተኮር ግድያ መካሄዳቸውን በመጥቀስ ሐምዳን ዳጋሎን ጨምሮ አራት የፈጥኖ ደራሽ አባላት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

    ከዳጋሎ በተጨማሪ 'የኤል ፋሽር ነፍሰ በላ' በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው አቡ ሉሉ ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል ይገኛል።

    ጄነራል ዳጋሎ ማዕቀብ ሲጣልባቸው ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀድም አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ጥለውባቸዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ እና ብሪታኒያ በሦስቱ አዛዦች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

  17. ሴኔጋል በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ የሚጣለውን የእስር ቅጣት በእጥፍ ልታሳድግ ነው

    የሴኔጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማኔ ሳንኮ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ የሚፈረደውን ከፍተኛውን የእስር ቅጣት በእጥፍ ሊጨምር የሚችል ረቂቅ ሕግ አቀረቡ። በአዲሱ ረቂቅ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ።

    የሴኔጋል ካቢኔ ባለፈው ሳምንት ያጸደቀው ይህ ረቂቅ ሕግ ማክሰኞ ዕለት ለአገሪቱ ፓርላማ ቀርቧል። ቀድሞውኑ በሕግ ክልከላ በጣለችው ሴኔጋል ይህ ረቂቅ የተዘጋጀው፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ተገኝተዋል የተባሉ ሰዎች ላይ ተከታታይ እስሮች ከተፈጸሙ በኋላ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንኮ በፓርላማ ለሕግ አውጪዎች ባደረጉት ንግግር፤ አዲሱ ሕግ “ከተፈጥሮ የተቃረነ ድርጊት” ሲሉ የጠሩትን ተግባር ከአምስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስር የሚቀጣ እንደሆነ ገልጸዋል። በነባሩ ሕግ ግን የሚያስቀጣው ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስር ነበር።

    “ድርጊቱ በዕድሜ ካልደረሱ ልጆች ጋር የተፈጸመ ከሆነ ከፍተኛውን ቅጣት ያስወስናል” ሲሉ ተናግረዋል። የመብቶች ተሟጋቾች በበኩላቸው ረቂቅ ሕጉን ተችተዋል።

    የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተሟጋች መሆን እንደ የውጭ ጣልቃ ገብነት በሚቆጠርባት ወግ አጥባቂዋ ሴኔጋል ውስጥ፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብትን በተመለከተ የሚደረግ ክርክር ውጥረት የሚፈጥር ጉዳይ ነው።

    በቅርብ ዓመታት የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣል የሚጠይቁ ሰልፎችን አካሂደዋል።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ደግሞ የአገሪቱ ፖሊስ በፀረ ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ሕግ አማካኝነት ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች እና አንድ ስመ ጥር ጋዜጠኛን በቁጥጥር ሥር አውሏል። በአጠቃላይ በዚህ ወር 30 ገደማ ሰዎች ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  18. ትራምፕ ስለ ኢራን ኒውክሌር የተናገሩት “ትልቅ ውሸት ነው” ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣን ተቹ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስለ ኢራን ኒውክሌር እና ባለስቲክ ሚሳዔል የሰጠው አስተያየት “በተደጋጋሚ የተባለ ትልቅ ውሸት ነው” ሲሉ አጣጣሉ።

    ትራምፕ ለኮንግረስ አባላት ባደረጉት ንግግር ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት “በፍጹም አልፈቅድም” ብለዋል።

    የትራምፕን ንግግር ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማዔል ባቄይ “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ኢራን ቢያንስ 20,000 ተቃዋሚዎችን ገድላለች ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል። በተጨማሪም “አውሮፓን የሚያሰጋ ሚሳዔል ገንብታለች። አሜሪካ የሚደርስ ሚሳዔልም እየገነባች ነው” ብለዋል።

    ኢራን “መሰሪ የሆነ የኒውክሌር ዕቅዷን” ለመተግበር እየሠራች ነው ሲሉም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከስሰዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ “ማንም ሰው በዚህ ነጭ ውሸት መታለል የለበትም” ብለዋል።

  19. የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለመነጋገር አዲስ አበባ ገቡ

    የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና በምክትላቸው አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት አስመልክቶ ባሰራጨው መረጃ፤ ሄርዞግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደሚገናኙ አስታውቋል። ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋርም እንደሚነጋገሩ ጠቅሷል።

    እንደ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ‘ቤተ እስራኤላውያን’ ተብለው የሚጠሩት የኢትዮጵያ የአይሑድ ማኅበረሰብ አባላት መሪም ከፕሬዝዳንት ሄርዞግ ጋር ይገናኛሉ።

    “ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ወሳኝ አገር” እንደሆነች የገለጸው የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ጉብኝቱ "በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር፤ በአጠቃላይም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ብሏል።

    የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በሳምንቱ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የቱርኩ ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የአገርነት ዕውቅና መተቸታቸው ይታወሳል።

    ኤርዶዋን፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና "ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም" አይኖረውም ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ንግግራቸው ሶማሊላንድን አስቆጥቷል።

    "የመላው ዓለም ዐይን ወደ የአፍሪካ ቀንድ” የዞረበት ጊዜ እንደሆነ የገለጹት ኤርዶዋን፤ ቱርክ በቀጣናው አዲስ ግጭት እንዲነሳ እንደማትፈልግ ተናግረው ነበር። "የዚህ ቀጣና ችግሮች በራሳቸው በቀጣናው አገራት ሊፈቱ እንደሚገባ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን እንደሌለበት እናምናለን" ብለውም ነበር።

    ከትናንት በስቲያ ሰኞ ደግሞ የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጋር ተነጋግረዋል።

    ስለ ቀጠናዊ ሰላም እና ሁለቱን አገራት በሚመለከቱ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል የተባሉት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አንድ ሳምንት አስቀድሞ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተነጋግረው ነበር።

    ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

  20. ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት “አልፈቅድም” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በመግለጽ አገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመግታት እንድትስማማ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ለኮንግረስ አባላት ባደረጉት ንግግር “የእኔ ምርጫ ችግሩን በዲፕሎማሲ መፍታት ነው። አንድ ጉዳይ ግን እርግጥ ነው። እሱም፤ የዓለም ቁጥር አንድ የሽብር ደጋፊ የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት አልፈቅድም” ብለዋል።

    ሁለት ሰዓት ገደማ በቆየው የ ‘ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን’ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት፤ ኢራን በአሜሪካ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይሰነዘርባት በሚል ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች።

    ሆኖም ግን ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ግንባታን በተመለከተ ምንም ስምምነት እንዳላደረገች አክለዋል።

    አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ የጦር መርከቦቿን ማሰማራቷን ተከትሎ ከኢራን ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት አንዣቧል።

    ትራምፕ በዛሬው ንግግራቸው ኢራን ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ እንዲሁም ተቃዋሚዎችን እንደገደለች ገልጸዋል።

    በተጨማሪም “የኢራን መንግሥት እና ገዳይ የሆኑት አጋሮቹ ሽብር፣ ሞት እና ጥላቻን ነዝተዋል” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኢራን ላይ ሊወሰድ ስለሚችል እርምጃ ቢገልጹም ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጡም።