ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ጦርነት ምክንያት የቻይናው ጉዟቸውን አራዘሙ

    ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በኢራን ጦርነት ምክንያት ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊያደርጉት የነበረውን ተጠባቂውን የቻይና ጉዟቸውን ለአንድ ወር በሚጠጋ ጊዜ ለማራዘም ማቀዳቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሐውስ በጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጉዞውን “በአንድ ወር ወይም እንዲያ አካባቢ ለማዘግየት ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል።

    ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ ይገናኙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጉብኝት ከመጋቢት 22 እስከ 24/2018 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።

    እንደ ትራምፕ ገለጻ ጉዞውን ማራዘም ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነቱን ለመምራት አገር ውስጥ መሆን አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

    “በጣም ቀላል ነው። ጦርነት እያካሄድን ነው። እዚህ መሆኔ አስፈላጊ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል። ትራምፕ እዚህ ውሳኔያቸው ውስጥ “ምንም ማታለል” እንደሌለበት አጽንኦት የሰጡ ሲሆን የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉም አክለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት ከብሪታኒያው ጋዜጣ ፋይናንሻል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ቻይና ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የማታግዝ ከሆነ ጉብኝታቸው ሊያራዝሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    በሁለቱ ግዙፍ የዓለም ኢኮኖሚዎች መካከል ያለው ፍትጊያ በኢራን ጦርነት ምክንያት ተባብሷል። የኢራን የኢነርጂ ኤክስፖርት ዋነኛ ገዢ የሆነችው ቻይና አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ከፈቱትን ጥቃት ተቃውማለች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው “ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና ጉብኝት ቀን እና ተያያዥ ጉዳዮችን” በተመለከተ ቤይጂንግ እና ዋሽንግተን እየተነጋገሩ መሆኑን ማክሰኞ ዕለት ገልጸዋል።

  2. የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአገሪቱ ቡድን ጨዋታዎች ሜክሲኮ ውስጥ እንዲካሄዱ እየተደራደረ መሆኑን ገለጸ

    የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደኅንነት ስጋት ምክንያት የአገሩ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወሩ ለማድረግ ከፊፋ ጋር እየተደራደረ መሆኑን አስታወቀ።

    የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት መህዲ ታጅ በኤክ ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ “ትራምፕ የኢራን ብሔራዊ ቡድንን ደኅንነት ማስጠበቅ እንደማይችሉ በግልጽ በተናገሩበት ሁኔታ በእርግጠኝነት ወደ አሜሪካ አንጓዝም” ብለዋል።

    አክለውም “በአሁኑ ሰዓት የኢራንን የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሜክሲኮ ውስጥ ለማድረግ ከፊፋ ጋር እየተደራደርን ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን ቴህራን ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ፤ ባለፈው ሳምንት የኢራን ስፖርት ሚኒስትር የአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው መሳተፍ እንደማይችል ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የዓለም ዋንጫውን ለመሳተፍ እንደምትችል ጠቁመው፤ ነገር ግን “ለራሳቸው ሕይወት እና ደኅንነት ሲባል እዚህ መምጣታቸው ተገቢ አይደለም” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

    በምድብ ሁለት ውስጥ ያለው የኢራን ብሔራዊ ቡድን ሎስ አንጀለስ ውስጥ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን፣ አንድ ጨዋታ ደግሞ ሲያትል ውስጥ እንዲያደርግ ድልድል ወጥቷል።

  3. እስራኤል የዜጎቼ ደኅንነት ሳይረጋገጥ የሊባኖስ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው አይመለሱም አለች

    ቤይሩት ውስጥ በተከፈተው ጥቃት ተፈናቅለው የፕላስቲን መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ አዛውንት

    የፎቶው ባለመብት, WAEL HAMZEH/EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, ቤይሩት ውስጥ በተከፈተው ጥቃት ተፈናቅለው የፕላስቲን መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ አዛውንት

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የድንበር አካባቢዎች ያሉ ዜጎቿ ደኅንነት እስከሚረጋገጥ ድረስ ሊባኖስ ውስጥ በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እንደማይመለሱ ተናገረች።

    ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣልያን በበኩላቸው በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ሊባኖስ ውስጥ የተከፈተው የእረኛ ጦር ጥቃት “አስከፊ ሰብአዊ መዘዝ” እንደሚኖረው አስጠንቅቀዋል።

    የዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ እንደሚያሳየው በሄዝቦላህ ጥቃት የተሰነዘረባት እስራኤል የከፈተችውን ዘመቻ ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተጠግቷል።

    የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ሌተናንት ኮሎኔል ናዳቭ ሾሻኒ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ "አዲስ ስፍራዎች” ላይ የእግረኛ ጦር ጥቃት መፈጸም መጀመራቸውን እንደተናገሩ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል። አዲሱን ጥቃት “ውሱን እና ዒላማዎች ላይ ያተኮረ” ሲሉ ገልጸውታል።

    “ባለፉት ሁለት ሳምንታት በደቡባዊ ሊባኖስ ውስን ዒላማ ያለው የእግረኛ ጦር ዘመቻ ከፍተናል፤ [ዘመቻው] ስጋቱን ከድንበር የመግፋት እና የሰሜናዊ እስራኤል ነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ ደኅንነት የማረጋገጥ ዓላማ አለው” ብለዋል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር እንደሚገልጸው፤ በእስራኤል ጥቃቶች 880 ሰዎች ተገድለዋል። ሚኒስቴሩ ይህ ቁጥር በንጹኃን ላይ ብቻ የደረሰ ጉዳት ስለመሆኑ አላብራራም።

    ምዕራባውያን አገራት በበኩላቸው ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ እስራኤል እና ሊባኖስ ድርድር በማድረግ “ተጨባጭ የፖለቲካ መፍትሔ” ላይ እንዲደርሱ አሳስበዋል። ሊባኖስ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ሁኔታም “እጅግ አሳሳቢ” እንደሆነ ገልጸዋል።

    “ከፍተኛ የሆነው የእስራኤል የእግረኛ ጦር ጥቃት አስከፊ ሰብአዊ መዘዝ ይኖረዋል፤ ወደ ተራዘመ ጦርነትም ሊያመራ ይችላል። መቀልበስ አለበት” ብለዋል።

    የእስራኤል ጥቃት ከተጀመረ አንስቶ የተፈናቀሉ ነዋወዎች ብዛት አንድ ሚሊዮን ተጠግቷል

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጥቃት ከተጀመረ አንስቶ የተፈናቀሉ ነዋወዎች ብዛት አንድ ሚሊዮን ተጠግቷል
    ከእስራኤል ጋር በሚጎራበተው ኪያም የተባለ የደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከእስራኤል ጋር በሚጎራበተው ኪያም የተባለ የደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የተፈጸመ ጥቃት
    በደቡባዊ ቤይሩት የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በደቡባዊ ቤይሩት የተፈጸመ ጥቃት
    የእስራኤል ወታደሮች በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደሮች በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ
  4. የእስያ አገራት ነዳጅ ለመቆጠብ የሥራ ቀናትን ከመቀነስ አንስቶ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው

    ነዳጅ ማደያ አካባቢ የተሰለፉ ሞተር ሳይክሎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስያዊቷ አገር ሲሪ ላንካ፤ በኢራን ጦርነት ምክንያት ሊፈጠር የሚችል የነዳጅ እጥረትን ለመቋቋም በየሳምንቱ ረቡዕ ዕለት እንደ የሕዝብ በዓል ተቆጥሮ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ወሰነች። ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎችም ምን ያህል ነዳጅ መግዛት እንደሚችሉ የሚወስን የራሽን ካርድ እንዲይዙ ተደርጓል።

    የሲሪ ላንካ ፕሬዝዳንት አኑራ ኩማራ ዲሳናያኬ ሰኞ ዕለት በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ “ለከፋው ነገር መዘጋጀት አለብን፤ ነገር ግን ጥሩ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    ሲሪ ላንካ ይህንን እርምጃ የወሰደችው በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ ሌሎች የእስያ አገራት የቁጠባ ውሳኔዎችን ካሳለፉ በኋላ ነው።

    ባለፈው ዓመት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ካለፈው ነዳጅ እና ጋዝ ውስጥ 90 በመቶ የሚጠጋው የደረሰው ወደ እስያ ነው።

    ሌሎችም የእስያ አገራት በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር በመስጋት እርምጃዎችን ወስደዋል።

    ምያንማር - የግል ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቀድላቸው አንድ ቀን እያለፉ ነው። በየትኛው ቀን የቱ ተሽከርካሪ ይንቀሳቀሳል የሚለው የሚወሰነው በሰሌዳ ቁጥር ነው።

    ባንግላዴሽ - ነዳጅ እና ኤሌክትሪክ ለመቆጠብ ሲባል እስከ ኢድ አልፈጥር ድረስ ዩኒቨርሲቲዎች ተዘግተዋል። በመላ አገሪቱ መብራት የሚጠፋባቸው ቀናት እንደሚኖሩም ተገልጿል።

    ፊሊፒንስ - የመንግሥት ሠራተኞች ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ከቤት እንዲሰሩ ታዝዘዋል። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማክሮስ ጁኒየር የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ወሳኝ ያልሆኑ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ ከልክለዋል።

    ታይላንድ - የዜጎች የአየር ማቀዝቀዣ አጠቃቀም እንዲቀንስ ሲባል ነዋሪዎች ከሱፍ ይልቅ እጅጌ ጉርድ ልብሶችን እንዲያደርጉ አሳስባለች።

    ቬትናም - ነዳጅ መቆጠብ እንዲቻል ዜጎች ይበልጥ ቤታቸው መዋልን እንዲያዘወትሩ በአጽንኦት አሳስባለች። ሕዝቡ “አላስፈላጊ ሲሆን የግል መኪና ጠቀምን እንዲገድብ” እንዲሁም “ሳይክል እንዲነዱ፣ ጋሪ እንዲጠቀሙ እንዲሁም በሕዝብ ትራንስፖርት እንዲገለገሉ” ጥሪ ቀርቧል።

  5. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይ ለማገዝ ጉጉት አልታየባቸውም ያሏቸውን አገራት ወቀሱ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚያልፈውን ነዳጅ ለማጀብ የጦር መርከቦቻቸውን እንዲልኩ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉን ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን በምስጋና ቢስነት ወቀሱ።

    ትራምፕ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና የኔቶ አባላት ያሉ አጋሮች በጦርነቱ ከአሜሪካ ጋር ለመሰለፍ አንገራግረዋል ሲሉ ተችተዋል። በተለይም ዩናይትድ ኪንግደም ጦርነቱን በተመለከተ ባሳየችው አቋም “እጅግ መገረማቸውን” ተናግረዋል።

    ትራምፕ፤ “ከሁለት ሳምንት በፊት ‘ለምን ተጨማሪ መርከቦችን አትልኩም’ አልኩ። [የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር] እውነትም ማድረግ አልፈለገም ነበር” ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደሙን መሪ ኪር ስታርመር ወቅሰዋል።

    “አካባቢው ላይ ፈንጂ የሚቀርብ መርከብ እንዳላቸው ይነግሩናል፤ ማድረግ ግን አይፈልጉም፤ ይሄ መጥፎ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዩናይትድ ኪንግደም “ደስተኛ አይደለሁም” ሲሉም ተደምጠዋል። “ሊሳተፉ እንደሚችሉ አስባለሁ፤ ነገር ግን በጉጉት መሳተፍ አለባቸው” ብለዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ 20 በመቶ ገደማው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥን ዘግታለች። ሊያልፉ የሞከሩ መርከቦች ላይም ጥቃት ተፈጽሟል።

    ወሳኙ መተላለፊያ እንዲከፈት የሚደረገውን ጥረት ቢያንስ አምስት አገራት ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ትራምፕ ተናግረው ነበር። ጀርመን፣ ስፔን እና ጣልያንን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ አጋር አገራት አሁን ወደ ሰርጡ የጦር መርከብ የመላክ እቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    ትራምፕ ትናንት በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር አገራት እገዛ ለማድረግ መንገድ ላይ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። የትኛዎቹ አገራት ድጋፍ እንደሚደርጉ ባይጠቅሱም፤ በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይገልጻል ብለዋል።

    “የተወሰኑ አገራት [እገዛ ለማድረግ] ጉጉት አላቸው፤ የተወሰኑት ደግሞ የላቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። “አንዳንድ አገራትን ለብዙ፣ ብዙ ዓመታት አግዘናቸዋል፤ ከመጥፎ የውጪ አካል ጠብቀናቸዋል፤ እናም ግን [እኛን ለማገዝ] ጉጉት አልነበራቸውም። ምን ያህል ጓጉተዋል የሚለው ለእኔ ዋጋ አለው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

  6. ኢራቅ ውስጥ "ከባድ" የሮኬት እና የድሮን ጥቃት ተፈጽሞ የአሜሪካ ኤምባሲ ተመታ

    ህንጻዎች ከሚገኙበት አከባቢ ወደላይ የሚወጣ እሳት እና ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, reu

    በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሮኬቶች እና አምስት ድሮኖች እንደተወነጨፉበት ገለጸ። የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኢራቅ ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ከባዱ ነው የተባለው ሮኬት እና ድሮን የተወነጨፈው በባግዳድ ከተማ ዙሪያ ካሉ አከባቢዎች እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ቢያንስ ሦስት ድሮኖች ወደ ኤምባሲው አቅጣጫ ሲያመሩ መመልከታቸውን ገልጸዋል። ‘ሲ-ራም’ የተሰኘው የአየር መከላከያ ስርዓት ሁለቱን ድሮኖች መትቶ ሲጥላቸው ሦስተኛው የኤምባሲውን ግቢ እንደመታ ገልጸዋል።

    ቀጥሎም ከኤምባሲው ግቢ እሳት እና ጭስ ሲወጣ ይታይ ነበር ተብሏል። ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ በኢራቅ ዋና ከተማ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን እንደተናገሩ ተዘግቧል።

    ሌላኛው የዜና ወኪል አሶሺየትድ ፕሬስ በበኩሉ ኤምባሲውን ዒላማ ያደረጉት አራቱም ድሮኖች በአየር መከላከያ ስርዓቱ ተተመትተው መውደቃቸውን ሁለት የኢራቅ ባለሥልጣናት እንደነገሩት ዘግቧል። ይሁን እንጂ ድሮኖቹ ሲመቱ የነበረው ስብርባሪ ኤምባሲውን እንደመታው ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ባግዳድ ውስጥ በሚገኘው አል ጃድሪያ አካባቢ ውስጥ የሚገኘው እና ከፍተኛ የጥቃት መከላከያ የተደረገለት ፕሬዝዳንታዊ ግቢ ውስጥ ያለን ቤት ዒላማ ያደረገ የአየር ጥቃት እንደተፈጸመ የኤፒ ዘገባ ያመለክታል።

    የመንግሥት ህንጻዎች እና የውጭ ኤምባሲዎች በሚገኙበት የባግዳዱ ‘ግሪን ዞን’ አካባቢ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በእሳት የተያያዘው ቅንጡ ሆቴል እንደሆነ ተነግሯል።

    ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው እንደማይታወቅም ዘገባው አክሏል። ሮይተርስ በበኩሉ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን ገልጿል።

    ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው ሄዝቦላህ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ እና ቃል አቀባዩ መገደላቸውን አስታውቋል። ሌላኛው ታጣቂ ቡድን ‘ፖፑላር ሞቢላይዜሽን ፎርስስ’ ደግሞ ከሶሪያ አቅራቢያ በምትገኘው የኢራቋ አል ቃኢም ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ስምንት ተዋጊዎቹ መገደሉን ገልጿል።

  7. የኢራን ጦር እስራኤል ውስጥ የሚገኙ የጦር መሣሪያ ማምረቻዎችን መትቻለሁ አለ

    የኢራን ሜሳዔል እና ባንዲራ

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    የኢራን ጦር፤ በዛሬው ዕለት እስራኤል ውስጥ የሚገኙ የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ ማዕከላትን በድሮን ጥቃት መደብደቡን ገለጸ።

    የኢራን ጦር የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በዛሬው ዕለት እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ወሳኝ እና ስትራቴጂክ የጦር መሣሪያ ማዕከላትን ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

    ራፋኤል በተሰኘው ኩባንያው እንዲሁም ‘ኢዝራኤል ኤሮስፔስ ኢንደስትሪስ’ የተባለው ተቋምን መምታቱንም ተናግሯል።

    ራፋኤል የተባለው ኩባንያ እንደ አይረን ዶም እና ዴቪድስ ስሊንግ ያሉ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን የሚሠራ ተቋም ነው። ስፓይክ ሚሳዔሎች እና ወታደራዊ የኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂዎችም ኩባንያው ውስጥ ይሠራሉ።

    ‘ኢዝራኤል ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪስ’ ደግሞ የውጊያ አውሮፕላኖች፣ ድሮኖች፣ ሚሳዔሎች እና የመከላከያ ሥርዓቶችን ያመርታል። እንደ አሮው ሚሳኤል መከላከያ ያሉ ወሳኝ ሥርዓቶችንም እንደሚያመርት የፋርስ ዜና ወኪል ዘገባ ያመለክታል።

  8. ኔቶ በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ይሳተፋል ብለው እንደማያስቡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

    የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሃን ዋድፉል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የሰሜን አትላንቲን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በኢራን የተዘጋውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የማስከፈት ሂደት ውስጥ ሚና ይኖረዋል ብለው እንደማያስቡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሃን ዋድፉል ተናገሩ።

    ኢራን ወሳኝ የነዳጅ ምርቶች መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ መዝጋቷን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራት የባሕር መስመሩን ለማስከፈት እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

    ትራምፕ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አጋር አገራት ወሽመጡን ለመቆጣጠር እገዛ የማያደርጉ ከሆነ “ለኔቶ መጻኢ እጅግ መጥፎ” እንደሚሆን ተናግረዋል።

    የአወሮፓ ኅብረት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሊያደርግ ካቀደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በፊት ንግግር ያደረጉት የጀርመኑ ሚኒስትር፤ የኔቶ ተሳትፎን ጉዳይ አንስተዋል።

    “ኔቶ በዚህ አቅጣጫ ውሳኔ ማሳለፉ ወይም የሆርሙዝ ወሽመጥን በተመለከተ ኃላፊነት መውሰዱ አይታየኝም። ጉዳዩ ይህ ቢሆን ኖሮ የኔቶ አካላት በዚሁ አኳዃን መፍትሔ ይሰጡት ነበር” ብለዋል።

    ያልተረጋጋው የመካለኛው ምሥራቅ ሁኔታ ቢኖርም፤ አውሮፓ ደኅንነትን በተመለከተ ቅድሚያ የምትሰጠው የዩክሬንን ጉዳይ እንደሆነ ዋድፉል ተናግረዋል። የነዳጅ እና ጋዝ ዋጋ ሲጨምር የሩሲያ የጦርነት አቅም እንደሚጨምር ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ማዕቀቡን ማላላት የተሳሳተ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት ዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርም የሆርሙዝ ወሽመጥን የማስከፈት ጉዳይ የኔቶ ተልዕኮ እንደማይሆን ተናግረዋል።

  9. ዩኬ ከኢራን ጋር በተያያዘ ወደ “ሰፊ ጦርነት” ተስባ እንደማገትባ አስታወቀች

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር አገራቸው ከኢራን ጋር በተያያዘ ወደ “ሠፊ ጦርነት” ተስባ እንደማትገባ፤ ነገር ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ለማድረግ “ከአጋሮች ጋር እንደምትሠራ” ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ በፈጸሙት የመጀመሪያ ጥቃት ዩናይትድ ኪንግደም አለመሳተፏን አንስተው አብራርተዋል።

    ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትችት አስነስቶባቸው እንደነበር ይታወሳል። ኋላ ላይ ግን የአሜሪካ ሠራዊት የዩናይትድ ኪንግደምን ጦር ሠፈሮች እንዲጠቀም ተፈቅዶለታል።

    ስታርመር በጋዜጣዊ መግለጫው፤ የአሜሪካ ዘመቻ “ኢራን ውስጥ የሚገኘው አጸያፊ አገዛዝ’ ወታደራዊ አቅም “በከፍተኛ ሁኔታ አዳክሞታል” ብለዋል።

    ከጦርነቱ በኋላ ግን ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን መልሳ የመገንባት አቅሟን የሚገድብ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞን ደኅንነት የሚያስጠብቅ የሆነ ዓይነት “በድርድር የሚደረስ ስምምነት” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

    የዓለም አቀፍ “ገበያዎችን መረጋጋት ለማረጋገጥ” እንዲቻል ኢራን የዘጋችው የሆርሙዝ ወሽመጥ በድጋሚ መከፈት እንዳለበትም ገልጸዋል። ነገር ግን ይህንን ማድረግ “ቀላል ሥራ እንዳልሆነ” አክለዋል።

    ለዚህም ሲባል ዩናይትድ ኪንግደም በቀጣናው የባሕር ጉዞ የማድረግ ነጻነትን ለመመለስ የሚያስችል “ተጨባጭ ዕቅድ” ለማዘጋጀት “ከሁሉም አጋሮቿ ጋር” እየሠራች መሆኑን አስታውቀዋል።

    በዚህ ጦርነት የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር፤ በዚህ ምክንያት የመጣውን የኑሮ ውድነት የሚያበርደው ውጤታማ መንገድ ግጭቱን ማርገብ መሆኑንም አክለዋል።

  10. የኢራን አብዮታዊ ዘብ 55 ዙር የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ

    የኢራን ሚሳዔል ሲተኮስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ ‘ኦፕሬሽን ትሩ ፕሮሚስ 4’ በተሰኘው ዘመቻ “ቴል አቪቭ እና ቤን ጉሪኦን” አየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ማዕከላትን ዒላማ ያደረጉ “55 ዙር” የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን መፈጸሙን ገለጸ።

    በእነዚህ ጥቃቶች ዒላማ ከተደረጉት ተቋማት መካከል “የኤሮስፔስ መሣሪያዎች ማምረቻ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ መቅጃ የእገዛ ማዕከላት” እንደሚገኙበት አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    በዚህ ዘመቻ “ፈታህ፣ ኤማድ፣ ቋድር ሃይፐርሶኒን ሚሳዔሎች እንዲሁም አውዳሚ ድሮኖች” ጥቅም ላይ እንደዋሉም ተነግሯል።

    አብዮታዊ ዘቡ አክሎም፤ “አል ድሃፍራ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር፣ ጁፍኤር ባሕር ኃይል ጦር ሰፈር እንዲሁም ሼክ ኢሳ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር” ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

    በጦር ሰፈሮቹ የሚገኙት የአሜሪካ ይዞታዎች ከተመቱባቸው መሣሪያዎች መካከል “ፋተህ፣ ዙልፊቃር፣ ደዝፉል የመካከለኛ ርቀት ሚሳዔል“ ተጠቅሰዋል። “ስማርት እና አውዳሚ ድሮኖችን” ጥቅም ላይ ውለዋል ተብሏል።

    ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ አቡ ዳቢ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አል ድሃፍራ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር፤ የኤምሬቶች አየር ኃይል የውጊያ ዕዝ እና የአሜሪካ አየር ኃይል ዋና መስሪያ ቤቶችን ይዟል።

    ባህሬን ውስጥ የሚገኘው ጁፍኤር የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ደግሞ ‘ዩኤስ ፊፍዝ ፍሊት’ የተሰኘው የአሜሪካ ጦር መርከብ ማረፊያ ነው። ሼክ ኢሳ አየር ኃይል ጦር ሰፈርም ባህሬን ውስጥ የሚገኝ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ነው።

    በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት የአሜሪካ እና የእስራኤል ተዋጊ ጄቶቸ በምሥራቃዊ ቴህራን በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የኢራኑ ፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  11. የእስራኤል ጦር የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪን የግል አውሮፕላን ማውደሙን ተናገረ

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ፎቶ እና የኢራን ባንዲራን የያዘ እጅ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ጦር ቴህራን በሚገኘው መህራባድ አየር ማረፊያ ላይ በፈጸመው ጥቃት የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ይጠቀሙበት የነበረን አውሮፕላን ማውደሙን ተናገረ።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በፋርስ ቋንቋ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ አውሮፕላኑ “በሽብርተኛው የኢራን አገዛዝ መሪ አሊ ኻሜኒ እና በሌሎች የአገዛዙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም የኢራን ጦር አባላት” ጥቅም ላይ ይውል ነበር ብሏል።

    ባለሥልጣናቱ “ወታደራዊ ግዢዎችን ለመፈጸም እንዲሁም በአገር ውስጥ እና የውጭ በረራዎች ከተጣማሪ አገራት ጋር የሚደረግ ግንኙነትን ለመምራት” ይጠቀሙበት እንደነበርም ገልጿል።

    ሰኞ ጠዋት ላይ ቴህራን ውስጥ በርካታ የአየር ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ተገልጿል። ነዋሪዎች መህራባድ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በርካታ ፍንዳታዎችን እንዲሁም ጥቁር ጭስ ወደላይ ሲጎን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

    በርካታ ተጓዦችን በማስተናገድ ከኢራን አየር ማረፊያዎች ቀዳሚ የሆነው መህራባድ በርካታ የአየር ጥቃቶች ዒላማ ሆኗል።

  12. የአውሮፓ ኅብረት ሆርሙዝን ለማስከፈት ምን ማድረግ እንደሚቻል ሊነጋገር ነው

    ግዙፍ የጭነት መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት ምክንያት የተዘጋውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለማስከፈት ምን ማድረግ እንደሚቻል ለመነጋገር አንደሚሰበሰቡ የውጭ ፖሊሲ ኃላፊው ተናገሩ።

    ካያ ካላስ በብራሰልስ ከሚካሄደው የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ስብሰባ አስቀድመው “የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ መቀጠሉ ለእኛም ጥቅም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    በዚህ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ በሚያልፍበት የውሃ አካል ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለማለፍ የሞከሩ በርካታ መርከቦች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ አጋሮች የመተላለፊያውን ደኅንነት ለማረጋገጥ ድጋፍ ካላደረጉ "ለኔቶ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም መጥፎ ይሆናል" ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ትራምፕ ከሰር ኪር ስታርመር ጋር “በዓለም አቀፍ የመርከብ ጭነት ላይ የሚደርሰውን መስተጓጎል ለማስቆም” የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና መከፈት አስፈላጊ መሆኑን መነጋገራቸውን አስታውቋል።

  13. ኢራን ቀይ ባሕር ላይ የሚገኘውን የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብን ዒላማ አደርጋለሁ አለች

    ጄራርድ አር. ፎርድ የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጄራርድ አር. ፎርድ የጦር መርከብ

    የኢራን ጦር በቀይ ባሕር አካባቢ የሚገኘው የአሜሪካ ግዙፉ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ለአገሩ ስጋት በመሆኑ ተገቢ የጥቃት ዒላማ እንደሚሆን አስታወቀ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አንድ አካል የሆነው ኻታም አል-አንቢያ ባወጣው መግለጫ “የአሜሪካ ጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ጄራርድ ፎርድ በቀይ ባሕር መገኘቱ” ለኢራን “ስጋት” ስለሚሆን የመርከቡ የአቅርቦት እና የአገለግሎት ማዕከላት በሙሉ “የኢራን ጦር ኃይሎች ዒላማ” ተደርገው ይቆጠራሉ ብሏል።

    ሦስት መቶ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ጄራርድ አር. ፎርድ የተባለው የጦር ጄቶች ተሸካሚ የጦር መርከብ በዓለም ላይ ትልቁ የጦር መርከብ ነው።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ባለፈው ሐሙስ በዚህ የጦር መርከብ አንድ ክፍል ላይ እሳት ተነስቶ እንደነበር አስታውቋል።

    ነገር ግን እሳቱ በቁጥጥር ስር እንደዋለ እና “በመርከቧ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል የሚያስከትል ጉዳት እንዳልደረሰ እና ሙሉ ለሙሉ ሥራውን እያከናወነ” መሆኑን ገልጿል።

    ማዕከላዊ ዕዙ ጨምሮም በመርከቡ ላይ የተነሳው እሳት “ከጦርነት ጋር በተያያዘ አይደለም” ሲሉ በወታደራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት እንዳልሆነ አመልክቷል።

    የጦር አውሮፕላን ተሸካሚው ዩኤስኤስ ጄራርድ አር. ፎርድ በቬንዙዌላ ከተፈጸውን የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በኋላ በኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ ነው በቀይ ባሕር ላይ የሚገኘው።

  14. የድሮን ጥቃት በዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ

    ሌሊቱን በዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ምክንያት በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረው በረራ መልሶ እንደሚጀመር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    በረራዎች እንዲቋረጡ የተደረገው በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት በነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ በተነሳ እሳት መሆኑን እና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተዘግቧል።

    የዱባይ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ለጥንቃቄ ሲባል ተቋርጦ የነበረውን የአየር ትራንስፖርት “ከዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደተወሰኑ መዳረሻዎች የሚደረጉ በረራዎች ቀስ በቀስ መልሰው እንደሚጀምሩ” አስታውቋል።

    መንገደኞችም ስለበረራዎቻቸው መረጃዎችን ከሚጠቀሟቸው አየር መንገዶች እንዲያጣሩ ተነግሯቸዋል።

  15. ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ “ነዳጅን በቁጠባ እና ለመሠረታዊ ነገሮች” እንዲውል አሳሰቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

    የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahimed

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት አስራ ስድስተኛ ቀኑን በያዘበት በዛሬው ዕለት “ነዳጅን በቁጠባ” መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋዊ የማኅበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት አጭር መልዕክት ነዳጅን ገዝተው የሚጠቀሙ አገራት መቸገራቸውን ገልጸው፤ “በቁጠባ እና ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት መጠቀም" አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንቱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ ሕብረተሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን "በከፍተኛ ቁጠባ" እንዲጠቀሙ አሳስበው ነበር።

    በጦርነቱ ምክንያት የታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ "አስፈሪ" ሲሉ የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት "በቅርቡ ተጨማሪ የነዳጅ ቁጠባ እርምጃዎችን" ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ የነዳጅ አከፋፋዮችም ሆኑ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ማደያዎች ለመሠረታዊ አገልግሎት ቅድሚያ እንዲሠጡ እና በቁጠባ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

    የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የተነሳ በተጨማሪም በጦርነቱ የኢራን እና የሌሎች የመካለኛው ምሥራቅ አገራት የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ጥቃት ስለተፈጸመባቸው የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት በበርሜል 120 ዶላር ገብቶ ነበር።

    ይህንንም ተከትሎ የዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከፍተኛ መጠን ያለውን ነዳጅ ከክምችቱ በማውጣት ለእስያ እንዲሁም ኦሺኒያ አገራት በዛሬው ዕለት እንደሚያከፋፍል ይፋ አድርጓል።

    የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ አቅርቦት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ መዘጋትን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ዛሬም እንደቀጠለ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

    እሁድ ዕለት በዓለም አቀፍ ገበያ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ እስከ 3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በበርሚል 106 ዶላር ተሸጧል።

    በዛሬው ዕለት ደግሞ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል 104.63 እየተሸጠ ነው።

  16. እስራኤል “ለውስን ዘመቻ” ወታደሮቿን ወደ ሊባኖስ ማስገባቷን አስታወቀች

    የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ወደ ሊባኖስ በመግባት “ቁልፍ የሔዝቦላህ ይዞታዎችን ዒላማ ያደረጉ ውስን ዘመቻዎችን” ማካሄድ መጀመሩን በቴሌግራም ገጹ ላይ አስታውቋል።

    ሠራዊቱ ወታደሮቹ ወደ ደቡባዊ የሊባኖስ አካባቢዎች ከመግባታች ቀደም ብሎ “በበርካታ የሽብርተኞች ዒላማዎች” ላይ ድብደባ መፈጸሙን እና ዘመቻው “የፊት መስመር የመከላከያ ይዞታን” በማጠናከር ዓላማው በአካባቢው ያሉትን “የሽብርተኞች መሠረተ ልማቶችን ማፈራረስ ነው” ብሏል።

    የእስራኤል ጦር ጨምሮም ሊባኖስ ውስጥ በሔዝቦላህ ላይ የሚያካሂደውን “ዘመቻ በቁርጠኝነት” እንደሚቀጥል አስታውቋል።

  17. የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያሳሰባቸው ትራምፕ ኔቶ እና ሌሎች አገራት እንዲደግፏቸው ጥሪ አቀረቡ

    የቆሙ መርከቦች እና የተቀመጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት የመርከቦች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል

    ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት የሚወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ኔቶ እና ሌሎች አገራት እንዲተባበሩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥረት እያደረጉ ነው።

    ግዙፍ መርከቦችን ከኢራን ጥቃት ለመጠበቅ የአገራት ጥምረት ለመፍጠር የአሜሪካ መንግሥት ከሰባት አገራት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የጠቀሱት ትራምፕ ከእነዚህም መካከል ቻይና እንደምትገኝበት ገልጸዋል።

    ትራምፕ የሌሎች አገራትን ስም ባይጠቅሱም የኔቶ አባል አገራት “ግዛታቸውን ይከላከላሉ” ብለው እንደሚያምኑ እና አሁን በሆርሙዝ ወሽመጥ የተከሰተው ሁኔታን እንደ ግዛታቸው መመልከት ያለባቸው አገራቱ “ነዳጅ የሚያገኙበት” አካባቢ በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ደግሞ ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለመጠበቅ አጋሮቻቸው ድጋፍ የማያደርጉ ከሆነ “የኔቶ የወደፊት ዕጣ በጣም መጥፎ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    በተጨማሪም ቻይና ተሳታፊ እንደምትሆን እንደሚጠብቁ፤ ነገር ግን ድጋፍ የማታደርግ ከሆነ ግን በምላሹ ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ካር በቅርቡ ሊካሄድ የታቀደውን ስብሰባ ሊያዘገዩት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

    ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም የምትሳተፍበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጋር መነጋገራቸው ተዘግቧል።

    ጃፓን በበኩሏ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወታደራዊ መርከቦቿን በመላክ የመሳተፍ “ፍላጎት እንደሌላት” የገለጸች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዚህ ሳምንት ወደ አሜሪካ በመሄድ ከትራምፕ ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    በተመሳሳይም አውስትራሊያ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በጭነት መርከቦች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ለመከላከል የጦር መርከቦቿን ወደ አካባቢው እንደማታሰማራ በትራንስፖርት ሚኒስትሯ በኩል አሳውቃለች።

    አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ከተሾሙ በኋላ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ኢራናውያንን ደግሞ ሆርሙዝን በመዝጋት እንደሚበቀሉ አመልክተው ነበር።

    የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ምርት የሚተላለፍበት ሆርሙዝ ወሽመጥ በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረ ስጋት በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ የመርከቦች ቁጥር ከጦርነቱ በፊት ከነበረው የ90 በመቶ ቅናሽ ማሳያቱን የቢቢሲ ቬሪፋይ ዘገባ አመለክቷል።

    ከጦርነቱ መጀመር በኋላ አስካሁን ቢያንስ 19 ከባድ መርከቦች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ወድመዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በአካባቢው በተፈጠረው ስጋት ምክንያትም 20 ሺህ የሚጠጉ መርከበኞችን እና የመርከብ ሠራተኞችን የያዙ ግዙፍ መርከቦች ለመንቀሳቀስ ተቸግረው ውቅያኖስ ላይ ቆመው የሚገኙ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የምግብ እና የውሃ እጥረት እያጋጠማቸው ነው።

  18. የባሕረ ሰላጤው አገራት ሌሊቱን ከኢራን ተጨማሪ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው አስታወቁ

    የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ

    የባሕረ ሰላጤው አገራት ከኢራን በኩል ሌሊቱን ተጨማሪ ጥቃቶች እንደተፈጸመባቸው አሳወቁ።

    የዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው መካከል አንዱ ነው። በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት እሳት ተያይዞ የነበረ ሲሆን፣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል።

    ኢራን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ 2 ሺህ የሚጠጉ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ተኩሳለች። የኤምሬትስ የመከላከያ ሥርዓት አብዛኞቹን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች አምክኗል።

    ሳዑዲ አረቢያም ሌሊቱን በርከት ያሉ የኢራን ድሮኖችን መምታቷን አስታውቃለች። በተመሳሳይ ኢራቅ እና ኩዌትም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት የቀጠሉ ሲሆን፣ በመዲናዋ ቴህራን ከባድ ድብደባ እንደነበር ተገልጿል።

    በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ከፍተኛ ፍንዳታ ያስከተለ ጥቃት ተፈጽሟል። እስራኤል ጥቃቱን የፈጸመችው የሄዝቦላህን መሠረተ ልማት ለማውደም መሆኑን ገልጻለች።

    በእስራኤል ከሰሜን የሄዝቦላህ ከደቡብ ደግሞ የኢራን ሚሳዔሎች ይመጣሉ በሚል የአደጋ ጊዜ ደወል መጮሁ ተነግሯል።

  19. አሜሪካ “ኢራን ድርድር ትፈልጋለች”፤ ኢራን “ፈጽሞ አልጠየቅንም”

    የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሁለቱ ወገኖች መካከል ሊደረግ ስለሚችለው ድርድር የሚቃረን አስተያየት እየሰጡ ነው።

    ሌሊት ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ከአሜሪካ ጋር መደራደር አጥብቃ እንደምትፈልግ እና ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ ተናግረዋል። ዲፕሎማሲያዊ ንግግርን በተመለከተም "እየተነጋገርን ቢሆንም እነሱ ግን ዝግጁ የሆኑ አይመስለኝም፣ ነገር ግን ወደዚያው እየቀረቡ ነው” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ዋነኛ ተደራዳሪ አባስ አራግቺ ግን የትራምፕን ንግግር ተቃርነዋል። ሚኒስትሩ አገራቸው “የተኩስ አቁም እንዲደረግ ፈጽሞ አልጠየቀችም፣ ለመደራደር እንኳን ፈጽሞ አልጠየቅንም” በማለት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    እየተካሄደ ባለው ጦርነት በኢራን ላይ ድል መቀዳጀታቸውን ለማወጅ እየተዘጋጁ እንደሆነ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ያንን እንደማያደርጉ ነገር ግን አስካሁን ባለው ሁኔታ አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ ውድመት ማድረሷን እና “አሁን ብንተዋቸው እንኳን መልሰው ለመገንባት 10 ዓመት ይፈጅባቸዋል” ብለዋል።

    ትራምፕ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ባለፈው ሳምንት በቴህራን ውስጥ አዲሱን ጠቅላይ መሪ በመደገፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ መውጣታቸውን እንዲሁም ኢራን በአሜሪካ የጦር መርከብ አብርሃም ሊንከን ላይ ፈጸመችው ስለተባለው “የአጥፍቶ ጠፊ ጀልባ” ጥቃት ተጠይቀው ሁሉም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተፈበረኩ ምሥሎች ናቸው ብለው ቢያጣጥሉም ማስረጃ ግን አልሰጡም።

  20. 16ኛ ቀኑን በያዘው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምን እየሆነ ነው?

    በቴህራን ቤርያናክ አካባቢ የሚገኝ መኖሪያ ቤት እሁድ ዕለት በሚሳዔል ጥቃት ከወደመ በኋላ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን ቤርያናክ አካባቢ የሚገኝ መኖሪያ ቤት እሁድ ዕለት በሚሳዔል ጥቃት ከወደመ በኋላ

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ሊያስቆም ይችላል በሚባል ድርድር ዙሪያ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ እየሰጡ ነው። ዛሬ አስራ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሰላም በቅርብ የሚመጣ አይመስልም። ሌሊቱን የተከናወኑ ዋናዋና ነገሮች እነሆ፡

    • የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን ለድርድር ዝግጁ ናት ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ውድቅ አድርገዋል። ቴህራን “የተኩስ አቁም በጭራሽ አልጠየቀችም፤ ድርድር እንኳ አልጠየቅንም” ሲሉ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።
    • ኢራናውያን አገራቸው ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ትቀየራለች ሲሉ ያላቸውን ስጋት ለቢቢሲ ተናግረዋል። እስራኤል በቴህራን የምትፈጽመውን ጥቃት አስፈታ የቀጠለች ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ የተከመረው ፍርስራሽ መንገዶችን ለመጠቀም አስቸጋሪ ማድረጉ ተገልጿል። በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት አሁንም የተቋረጠ ሲሆን፣ ቁልፍ የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመር ከጥቅም ውጭ ሆኗል።
    • በእስራኤል የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በኢራን ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 15 መድረሱን ገለጿል። በቴል አቪቭ ክላስተር ቦምብ ጉዳት አድርሷል። የእስራኤል ጦር በኢራን የሚፈጽመውን ጥቃት እያሰፋ መሆኑን በመግለጽ አሁንም “በሺህዎች የሚቆጠሩ” ዒላማዎች እንደሚቀሩት ተናግሯል።
    • በሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 850 መድረሱን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል በደቡባዊ ቤይሩት ድብደባ ከመፈጸሙ በፊት ከአካባቢው ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቋል። የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ሊኖር የሚችልን የሰላም ንግግር ውድቅ አድርገዋል።
    • ዶናልድ ትራምፕ እና የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የሆርሙዝን ወሽመጥ ዳግም ስለማስከፈት በስልክ ተወያይተዋል። ሰኞ ዕለት የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የካናዳው አቻቸው ተገናኝተው በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ዙሪያ ይነጋገራሉ ተብሏል።
    • ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በእስያ እና ኦሺኒያ ከአስቸኳይ ጊዜ ክምችት ነዳጅ በፍጥነት እንደሚለቀቅ ይፋ አድርጓል። የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ ከአገራት ጋር በተናጠል ለመነጋገር መንግሥታቸው “ክፍት” መሆኑን ተናግረዋል።