ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ፣ ኤምሬትስ እና ኳታር የነዳጅ ማውጫ ላይ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሆነ አስጠነቀቀ

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ውስጥ በሚገኙ የነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሆነ አስጠነቀቀ።

    በዚህም ምክንያት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ባሉ የነዳጅ ማምረቻ ተቋማት ውስጥ እና በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

    ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል በቴሌግራም ገጹ ላይ “አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ” በሚል ባወጣው መልዕክት፤ ዜጎች እና ነዋሪዎች በዝርዝር ካስቀመጣቸው የነዳጅ ማዕከላት አቅራቢያ እንዲርቁ አዝዟል። እነዚህም፡-

    • ሳምሬፍ የነዳጅ ማጣሪያ - ሳዑዲ አረቢያ
    • አል-ጁቤይል ፔትሮኬሚካል ማምረቻ እና ማሳኢድ ኩባንያ - ሳዑዲ አረቢያ
    • አል-ሆሳን የጋዝ ማውጫ ቦታ - የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ
    • ራስ ላፋን የነዳጅ ማጣሪያ - ኳታር

    መግለጫው “እነዚህ የነዳጅ ማዕከላት ቀጥተኛ እና ተገቢ ዒላማዎች በመሆናቸው በሚቀጥሉት ሰዓታት ውስጥ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።

    "ስለዚህም ሁሉም ዜጎች፣ ነዋሪዎች እና ሠራተኞች በአስቸኳይ ከእነዚህ አካባቢዎች ለቅቀው በመውጣት ሳይዘገዩ ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ ርቀት እንዲሄዱ ተጠይቀዋል” ብሏል።

  2. ለተገደሉት ባለሥልጣናት የሽኝት ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢራናውያን አደባባይ ወጡ

    ማክሰኞ ዕለት በእስራኤል ጥቃት በተገደሉት የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መገኘቱን ከቴህራን የሚወጡ መረጃዎች አመለከቱ።

    በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ከነበራቸው ላሪጃኒ በተጨማሪ በተመሳሳይ በእስራኤል የተገደሉት የአብዮታዊ ዘቡ የሚሊሻ ክንፍ የሆነው የባሲጅ ታጣቂ ኃይል አዛዥ ለጎላምሬዛ ሶሌማኒም እና በአሜሪካ ጥቃት በተፈጸመበት የኢራን የጦር መርከብ ላይ ለተገደሉ 84 ባሕረተኞችም በአንድ ላይ ሽኝት ተደርጓል።

  3. የኢራን የሚሳዔል ጥቃት በአሜሪካ ኤምባሲ ላይ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመሩ በኋላ በአጸፋው ኢራን የተለያዩ ዒላማዎችን በሚሳዔሎች እና በድሮኖች እየመታች ነው።

    ከእነዚህም መካከል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚገኑ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ሌሎች ተቋማት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

    ይህ ቪዲዮ ማክሰኞ ዕለት ኢራቅ ውስጥ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲን ዒላማ ያደረጉ የሚሳዔል ጥቃትን ያሳያል።

  4. ሰበር, እስራኤል የኢራን የደኅንነት ሚኒስትርን መግደሏን አስታወቀች

    የኢራን የደህንነት ሚኒስትር ኢስማኤል ካሪብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ኢዝራኤል ካትዝ የኢራኑ የደኅንነት ሚኒስትር ኢስማኤል ኻቲብ መገደላቸውን ተናገሩ።

    ካትዝ በመግለጫቸው ላይ “ትናንት ሌሊት የኢራን ደኅንነት ሚኒስትር ኻቲብ ተወግደዋል" ብለዋል።

    ኢራን ስለሚኒስትሩ መገደል እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

    ኢስማኤል ኻቲብ የኢራን የደኅንነት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር።

    ከሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ እና ከሌሎችም የኢራን ከፍተኛ መሪዎች ጋር እስላማዊ ሕግን ያጠኑ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ውስጥ እንዲሁም በጠቅላይ መሪው ጽህፈት ቤት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርተዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2022 የደኅንነት ሚኒስትሩ “በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ላይ የበይነ መረብ ጥቃት እንዲፈጽም” አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል በሚል በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

    ኻቲብ በኢራን አብዮት ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ ከ45 ዓመታት በፊት የእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ አባል በመሆን ነው በመንግሥት ውስጥ ማገለግል የጀመሩት።

    በተመሳሳይ ትናንት በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው የአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ ተገድለዋል።

  5. እስራኤል በቤይሩት የሄዝቦላህ 'የፋይናንስ ክንፍን' ማጥቃቷን ገለጸች

    እስራኤል በቤይሩት የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል ሌሊቱን በቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህን ጦር በገንዘብ የሚደግፈው የአል ቋርድ አል ሃሳን ንብረቶችን ዒላማ ማድረጓን አስታወቀች።

    እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ አስር ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 27 ሰዎች መጎዳታቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    እስራኤል የሄዝቦላህ የፋይናንስ ክንፍ ነው ካለችው አል ቋርድ አል ሃሳን በተጨማሪ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝ “የማዘዣ ጣቢያ” መደብደቧንም ገልጻለች።

    ማክሰኞ ዕለት እስራኤል “ሆን ተብሎ” ሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ውስጥ የተቀመጠ የጦር መሣሪያ ማከማቻን መደብደቧን ገልጻለች።

  6. ከሰባቱ ቁልፍ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስድስቱ ተገድለዋል

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጥቃት ከጀመሩበት ደቂቃ አንስቶ እስካሁን ድረስ ዋነኛ ዒላማ እያደረጓቸው ያሉት የአገሪቱን ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎችን ነው።

    በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ የሆኑት አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ባለሥልጣናት በጽህፈት ቤታቸው እና በመኖሪያቸው ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።

    በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ባለፉት ዓመታት ጭምር ተገድለዋል። አሁን የተከፈተው ጦርነት ደግሞ ሌሎቹንም የጥቃት ዒላማ አድርጓቸዋል።

    ለመሆኑ ወሳኝ ከሚባሉት ሰባት የኢራን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መሪዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ከጥቃት ተርፈው በሕይወት የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ መሱድ ፔዜሽኪያን ብቻ ናቸው። ኢራን መሪዎቿን ባጣች ጊዜ እንዴት ሳትንኮታኮት ጸንታ መቀጠል ቻለች?

    ባለሥልጣናት
  7. አሜሪካ ለምን በአሁኑ ወቅት በኢራን ላይ ከባዱን ቦምብ ተጠቀመች?

    2270 ኪሎ ግራም የሚመዝነው መሽግ ደርማሽ ቦምብ

    የፎቶው ባለመብት, USAF

    የምስሉ መግለጫ, 2270 ኪሎ ግራም የሚመዝነው መሽግ ደርማሽ ቦምብ

    ጦርነቱ ሦስተኛ ሳምንቱን ባገባደደበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ 2270 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ምሽግ ደርማሽ ቦምብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደ ጀመረች እየተዘገበ ነው።

    ይህ ቦምብ ከመሬት በታች በተገነቡ ጠንካራ ምሽጎች ውስጥ ያሉ ዒላማዎችን በጥልቀት በመግባት የማውደም ከፍተኛ አቅም ያለው ሲሆን፣ አሁን ጥቅም ላይ መዋሉ ኢራን የደበቀችው ጦር መሳሪያ እንዳለ ጥርጣሬ መኖሩን ያሳያል።

    የአሜሪካ ጦር በኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢ ባሉ የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች ላይ ጥቃቱን መፈጸሙን ያስታወቀ ቢሆንም የትኛውን ዓይነት ቦምብ ጥቅም ላይ እንደዋለ ዝርዝር አልሰጠም።

    ነገር ግን ሁለት ዓይነት ቦምቦች እንዳሉ ይታወቃል እነሱም፤ በጨረር የሚመራው ጁቢዩ-28 እና አዲሱ ዘመናዊ ጂቢዩ-72 የተባሉት ናቸው። በአሁኑ ጥቃት አዲሱ ቦምብ ጥቅም ላይ ሳይውል እንዳልቀረ ይታመናል።

    ለሦስት ሳምንት ያህል አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያልተቋረጠ የሚሳዔል እና የአየር ድብደባዎችን እየፈጸሙ ቢሆንም፤ ኢራንም በበኩሏ ያልተቋረጠ የአጸፋ ጥቃት በእስራኤል እና በአሜሪካ አጋሮች ላይ እየፈጸመች ነው።

    ባለፉት ቀናት የኢራን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ተዳክመው ሊቆሙ ይችላሉ ተብሎ ቢታሰብም አሁንም ከኢራን በኩል የሚሰነዘሩት ጥቃቶች በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ዋነኛ ስጋት ሆነው እንደቀጠሉ ናቸው።

    ለዚህም ሊሆን ይችላል አሜሪካ ከመሬት በታች ዘልቀው በመግባት የሚያወድሙትን ከባዶቹን ቦምቦች በመጠቀም የኢራንን የሚሳዔል እና የድሮን ክምችቶችን እንዲሁም ማስወንጨፊያዎችን ለመጠቀም የተገደደችው።

    ቦምቡን የሚጥለው ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኢግል የጦር ጄት

    የፎቶው ባለመብት, USAF

    የምስሉ መግለጫ, ቦምቡን የሚጥለው ኤፍ-15ኢ ስትራይክ ኢግል የጦር ጄት
  8. በኢራን ጥቃት ተጎድተው 192 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን እስራኤል አስታወቀች

    ቴል አቪቭ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ኢራን በፈጸመችው ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው ቢያንስ 192 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ከተጎጅዎቹ መካከል አራቱ መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።

    177 የሚሆኑት ደግሞ ቀላል ጉዳት ያስተናገዱ ሲሆን በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየወሰዱ ነው ብሏል። ቀሪዎቹ 11 ሰዎች ግን በምን ሁኔታ እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።

    ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን 3 ሺህ 727 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና ክትትል ማድረጋቸውን ገልጿል።

  9. ኢራን ‘ለእስራኤል በመሰለል’ የተከሰሰን ግለሰብ በሞት ቀጣች

    ኢራን ለእስራኤሉ የስለላ ድርጅት “ሞሳድ ሲሰልል” ነበር የሚል ክስ የቀረበበትን ግለሰብ በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪሎች አስታወቁ።

    ኩሮሽ ኬይቫኒ የተባለው ግለሰብ በሞት መቀጣቱን በተመለከተ ዜናው ይፋ ሲሆን፣ የቀረበበት ክስ እና ቅጣቱ የተላለፈበትን ሂደት በተመለከተ ምንም ዝርዝር መረጃ አልቀረበም።

    ነገር ግን ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ቅርበት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል ባወጣው ዘገባ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው አሁን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ሳይሆን፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ እስራኤል እና ኢራን ለ12 ቀናት የቆየ ጦርነት ባካሄዱበት ጊዜ ነው።

    የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የስለላ ክስ የሚቀርብባቸው ሰዎች ራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን ኢራን እንደማታከብርላቸው እና ነጻ የሆነ የፍርድ ሂደት እንደማይካሄድ ይከሳሉ።

    በተጨማሪም የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሞት ቅጣቶችን በስፋት የሚፈጽመው በተቃዋሚዎቹ እና በሕዝቡ ዘንድ ጭቆናን እና ፍርሃትን ለማንገስ ነው ይላሉ።

  10. አሜሪካ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ አቅራቢያ የሚገኙ የኢራን የሚሳዔል ጣቢያዎችን ደበደበች

    የሆረሙዝ የባሕር ወሽመጥን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የመተላለፍበት የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ

    የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጥቃት የሚውሉ የኢራን የሚሳዔል ጣቢያዎችን መደብደቡን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገፁ ላይ ባወጣው ጽሑፍ ጦሩ በኢራን የባሕር ዳርቻ በሚገኙት "ጠንካራ የኢራን የሚሳዔል ጣቢያዎች ላይ 5,000 ፓውንድ የሚመዝኑ ሰረስረው የሚገቡ ቦምቦችን ተጠቅሞ በተሳካ ሁኔታ ድብደባ ፈጽሟል" ሲል አስታውቋል።

    "በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተተከሉት የኢራን ፀረ-መርከብ ክሩዝ ሚሳዔሎች በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ላሉ ዓለም አቀፍ መርከቦች አደጋ ፈጥረዋል" ሲል የአሜሪካ ጦር ተናግሯል።

    ኢራን 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚጓጓዝበትን የባሕር ወሽመጥ በመዝጋቷ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ግዙፎቹ ቦምቦች አሜሪካ ባለፈው ዓመት በኢራን ውስጥ የሚገኙ ሦስት የኒውክሌር ጣቢያዎችን ስትደበድብ ከተጠቀመችባቸው ቦምቦች ጋር ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ።

    እነዚህ ቦምቦች በአየር ወይም በመሬት ላይ በሚገኙ ዒላማዎችን መትተው አይፈነዱም። ከዚያ ይልቅ በጥልቀት የተቀበሩ እና የተጠናከሩ ጉድጓዶችን እና ዋሻዎችን ሰርስሮ በመግባት የማጥቃት አቅም አላቸው።

    ስድስት ሜትሮች ርዝመት ያለው ይህ ቦምብ ከመፈንዳቱ በፊት በግምት 61 ሜትሮች ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት ይችላል ተብሎ ይታመናል።

  11. እስራኤል ሌሊቱን በቤይሩት የፈጸመችው ድብደባ ያደረሰው ውድመት በምሥል

    እስራኤል ሌሊቱን በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ላይ የፈጸመችው ጥቃትን ተከትሎ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 24 ደግሞ ቆስለዋል።

    ሊባኖስ ወደዚህ ግጭት ተስባ የገባችው ሄዝቦላህ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒን መገደል ተከትሎ የአጸፋ እርምጃ በሚል ሮኬቶችን እና ድሮኖችን መተኮሱን ተከትሎ ነው።

    እስራኤል በሄዝቦላህ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድበደባዎችን እየፈጸመች ሲሆን፣ ውስን የእግረኛ ጦርም ማሰማራቷን አስታውቃለች።

    በቤይሩት በሚገኝ ሕንጻ ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ ጥቁር ጭስ ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በቤይሩት ባቾራ በሚባል አካባቢ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የደረሰውን ውድመት ተከትሎ በሕይወት የተረፉትን ለማዳን ሲረባረቡ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በቤይሩት ባቾራ በሚባል አካባቢ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የደረሰውን ውድመት ተከትሎ በሕይወት የተረፉት ሰዎችን ለማዳን ሲረባረቡ ታይተዋል
    በቤይሩት ዙቃቅ አል-ብላት ዲስትሪክት የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ የደረሰውን ውድመት አንድ ሰው በረንዳ ላይ ቆሞ ሲመለከት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በማዕከላዊ ቤይሩት ዙቃቅ አል-ብላት በተባለ ስፍራ
    በማዕከላዊ ቤይሩት ዙቃቅ አል-ብላት ዲስትሪክት በጥቃት የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በማዕከላዊ ቤይሩት ዙቃቅ አል-ብላት አካባቢ በጥቃት የወደመ ሕንጻ
  12. ኢራን ቴል አቪቭ ላይ የፈጸመችው ጥቃት በምሥል

    ኢራን በእስራኤል ላይ ሌሊቱን በፈጸመችው የሚሳዔል ትቃት አንድ የ70 ዓመት ወንድ እና ሴት መሞታቸው ተሰምቷል። የደረሰውን ጥቃት የሚያሳዩ ምሥሎች ይፋ ሆነዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የዐይን እማኝን ጠቅሶ እንደዘገበው ዛሬ ማለዳ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ባቹራ በሚባል አካባቢ እስራኤል ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል።

    የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቴል አቪቭ ራማት ጋን ሰፈር የደረሰ የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ በቦታው ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Alexi J Rosenfeld via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቴል አቪቭ ራማት ጋን ሰፈር የደረሰ የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ በቦታው ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል
    የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቴል አቪቭ ራማት ጋን ሰፈር የደረሰ የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ በቦታው ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Ilia Yefimovich via Getty Images

    ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎች በቴል አቪቭ ሰማይ ላይ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎች በቴል አቪቭ ሰማይ ላይ ታይተዋል
  13. ኢራን የበቀል ጥቃት ለመፈጸም ስትዝት በእስራኤል የሚሳዔል ጥቃት ሁለት ሰዎችን ገድሏል

    በቴል አቪቭ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የደረሰ የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ ምላሽ ለመስጠት ተገኝተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ በሚገኘው እና አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ቀጥለዋል። በኢራን እና በአጋሮቿ የሚሊሻ ቡድኖች የሚሰነዘሩ የአጸፋ ጥቃቶች ሌሊቱን ሙሉ የቀጠሉ ሲሆን፣ የሰዎች ሞትም ተመዝግቧል።

    • የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ፈጣሪው የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጠዋል ። ላሪጃኒ ከጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሞት ወዲህ ከተገደሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
    • የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ውስጥ የሔዝቦላህ ዒላማዎችን መደብደቡን ቀጥሏል። የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር በማዕከላዊ ቤይሩት በተፈጸሙ የእስራኤል ሁለት ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 24 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
    • የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ተተኳሽ የኢራንን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ቢመታም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት አስታውቋል።
    • የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አቅራቢያ የሚገኙ የኢራን የሚሳኤል ጣቢያዎችን መምታቱን አስታውቋል።
    • ዶናልድ ትራምፕ የኔቶን እና ሌሎች አጋሮችን ተችተዋል፤ ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል ድጋፍ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም አሜሪካ በኢራን ጦርነት ላይ "ከእንግዲህ ወዲህ እርዳታ አትሻም ወይም አትፈልግም" ብለዋል።
    • በቴል አቪቭ የኢራን የሚሳዔል ጥቃትን ተከትሎ በ 70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተገድለዋል።
    • የኢራን የጦር አዛዥ የላሪጃኒን ግድያ በመበቀል "ወሳኝ፣ የሚያሽመደምድ እና ጸጸት ላይ የሚጥል" ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል። ከጦሩ የተለየ ወታደራዊ አካል የሆነው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የላሪጃኒን ሞት “ለመበቀል” ወደ ማዕከላዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፉን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
  14. በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ዳግም ጥቃቶች ተፈጸሙ

    በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ዳግም ጥቃቶች ተፈጸሙ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ አዲስ ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቷል።

    ኤኤፍፒ እና የሮይተርስ የዜና ኤጀንሲዎች ረቡዕ ማለዳ በኤምባሲው አካባቢ ፍንዳታ እንደደረሰ ዘግበዋል።

    ኤጀንሲዎቹ የጸጥታ ምንጮችን እና በከተማው የሚገኙ የኤፍፒ ጋዜጠኞችን ጠቅሰው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መገኛ በሆነው አካባቢ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ ፍንዳታ መስማታቸውን ገልጸዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ ኤምባሲ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥቃት ደርሶበታል።

  15. የኢራን ጦር አዛዥ እስራኤል የደኅንነት ኃላፊው ላሪጃኒን መገደሏን ተከትሎ 'ወሳኝ' የአጸፋ እርምጃ እንደሚወሰዱ ዛቱ

    የኢራን ጦር አዛዥ አሚር ሃታሚ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጦር አዛዥ አሚር ሃታሚ

    የኢራን ጦር አዛዥ አሚር ሃታሚ በእስራኤል የአየር ጥቃት የደኅንነት ኃላፊው አሊ ላሪጃኒን መገደላቸውን ተከትሎ "ወሳኝ" የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዛቱ።

    "ለወንጀለኛዋ አሜሪካ እና ደም የተጠማው የጽዮናውያን አገዛዝ በተገቢው ጊዜ እና ቦታ ወሳኝ፣ የሚያሽመደምድ፣ ጸጸት ውስጥ የሚጥል ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ ሃታሚ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

    የላሪጃኒ እና የሌሎች "ሰማዕታት ሞት እንበቀላለን” በማለት አክለዋል።

    ከኢራን ጦር ኃይል የተለየ ወታደራዊ ክፍል የሆነው እስላማዊው አብዮታዊ ዘብ የላሪጃኒ ሞትን "ለመበቀል" ወደ ማዕከላዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን መተኮሱን የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ ሰኞ ለማክሰኞ ሌሊት በእስራኤል በተፈጸመባቸው ጥቃት ከልጃቸው ጋር መገደላቸው ተነግሯል።

    ላሪጃኒ በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት እና ከሟቹ ጠቅላይ መሪ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ካላቸው የአገሪቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች መካከል ቀዳሚው ናቸው።

    እስራኤል የላሪጃኒን መገደል ቀድማ ያሳወቀች ሲሆን፣ የመከላከያ ሚኒስትሯም ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናትን እያደኑ ማጥፋታቸወን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

  16. የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በኢራን የሚካሄደውን ጦርነት ተቃውመው ሥልጣን ለቀቁ

    ጆ ኬንት

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ጆ ኬንት

    የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የፀረ ሽብርተኝነት ማዕከል ዳይሬክተር “በኢራን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በበጎ ህሊና መደገፍ አልችልም” በማለት ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት መልዕክት አስታወቁ።

    ጆ ኬንት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ባሳወቁበት ደብዳቤ "ኢራን በአገራችን ላይ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ስጋት አልደቀነችም፣ ይህንን ጦርነት የጀመርነው በእስራኤል እና በአሜሪካ ባሏት ኃያል ደጋፊዎቿ ግፊት መሆኑ ግልጽ ነው” ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ሦስት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ይዘው የተነሷቸውን ፖሊዎች ደግፈው ከጎናቸው እንደቆሙ ያስታወሱት ጆ፣ አስከ 2025 በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የተካሄዱት ጦርነቶች የአሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፉ እና የአገሪቱን ሃብት ያሟጠጡ መሆናቸውን ትራምፕ ይረዱ እንደነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

    “በ11 ውጊያዎች ላይ እንደተሳተፈ የቀድሞ ወታደር እና በእስራኤል በተፈበረከ ጦርነት ውድ ሚስቱን እንዳጣ ባል፣ ቀጣዩ ትውልድ ለአሜሪካ ጥቅም በማያስገኝ እና የሚከፈለው ዋጋ አሳማኝ ወዳልሆነ ጦርነት መሄዱን መደገፍ አልችልም” በማለት ጦርነቱን ተቃውመዋል።

    አሁን ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት ጆ ኬንት በትራምፕ ተመርጠው በአሜሪካ ሴኔት ለቦታው ብቁ ናቸው ተብለው ተቀባይነት ያገኙት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ነበር። የኢራንን ጦርነት ተቃውመው ሥልጣን የለቀቁት የአሜሪካው ከፍተኛ ባለሥልጣን ማን ናቸው?

  17. በሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይ አውሮፓውያን ፊታቸውን ያዞሩባቸው ትራምፕ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው የሆርሙዝ ሰርጥ የሚተላለፉ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለመጠበቅ አጋሮቻቸው እንዲተባበሩ ያቀረቡት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ተቆጥተዋል።

    ምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ይህ የትራምፕ ጥሪ አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ ወደ ከፈተችው ጦርነት የሚያስገባቸው ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የባሕር ኃይላቸውን ወደ ጦርነት ቀጣናው ለመላክ አልፈቀዱም።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ የነዳጅ ምርት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ በመዘጋቱ የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል በአገራት ምጣኔ ሀብት ላይም ተጽእኖው እየተንጸባረቀ ነው።

    የአሜሪካ የቅርብ አጋሮች የሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመንን ጨምሮ ግሪክ፣ አውስትራሊያ፣ ስፔን፣ ጃፓን እና ሌሎችም በሆርሙዝ ሰርጥ የሚተላለፉ መርከቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ትራምፕ ባዘጋጁት ዕቅድ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ መልስ ሰጥተዋል።

    በአውሮፓ ታላላቅ ወታደራዊ ኃይል ያላቸው አገራቱ ምንም እንኳን የነዳጅ እንቅስቃሴው መስተጓጎል ቢጎዳቸውም በዚህ ምክንያት ግን ከኢራን ጋር ወደ ቀጥታ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው አሳውቀዋል። ይህም ሦስት ሳምንት ያስቆጠረው ጦርነት የአሜሪካ እና የእስራኤል ጉዳይ መሆኑን በተዘዋዋሪ መልዕክት ያስተላለፉበት ነው።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው ሆርሙዝን በመጠበቅ ሰበብ ወደ ጦርነት ተስባ እንደማትገባ ሲጠቅሱ፣ የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ደግሞ ትራምፕ አጋሮቻቸው ካልተባበሯቸው ለኔቶ መጥፎ ሁኔታ ይፈጠራል በማለት ለሰጡት ማስጠንቀቂያ “ኔቶ የመከላከያ ስምምነት እንጂ የጣልቃ ገብነት ትብብር አይደለም” ሲሉ መከላከያ ሚኒስትራቸው ደግሞ “የእኛ ጦርነቱ አይደለም፤ እኛም አልጀመርነውም” በማለት እራሳቸውን አርቀዋል።

    ነገር ግን ትራምፕ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት “በርካታ አገራት” ጥሪያቸውን ተቀብለው ከጎናቸው እንደሚቆሙ እንደገለጹላቸው ጠቁመው፤ አሜሪካ ስትከላከላቸው የቀዩ አገራት ለቀረበላቸው ጥሪ ምላሽ ካልሰጡ “ምስጋና ቢስነት ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ ሆርሙዝ ሰርጥን በመጠበቅ ከጎኔ ይቆማሉ ብላ የምትጠብቃቸው የአውሮፓ ባለሥልጣናት የኔቶ አባል አገራት ትብብር እራስን የመከላከል ዓላማ መሆኑን አጽንኦት እየሰጡ ነው።

    ኢራንን እና የኒውክሌር ፕሮግራሟን ዒላማ ማድረግ ግን አሜሪካ እና እስራኤል “በምርጫ የገቡበት ጦርነት ነው” በማለት አገራት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ግልጽ አድርገዋል።

    በኔቶ በኩል ዩክሬንን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት እየደገፏት የሚገኙት የአውሮፓ አገራት በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ለመሸፈን በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ትራምፕ በማንሳታቸው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

  18. እስራኤል የኢራን መሪዎችን “ማደን እቀጥላለሁ” አለች

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ ጦር ኢራን መሪዎችን ማደኑን እንዲቀጥል ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናገሩ።

    እስራኤል ሰኞ ሌሊት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከፍተኛ የኢራን የደኅንነት ኃላፊ የሆኑትን አሊ ላሪጃኒን መግደሏን ገልጻለች። ባለሥልጣኑ የተገደሉት ከልጃቸው ጋር በተደበቁበት አፓርትመንት ውስጥ እንደሆነ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    በተጨማሪም የእስራኤል ጦር ‘ባሲጅ’ የተባለው የኢራን ታጣቂ ኃይል አዛዥ የሆኑትን ጎላምሬዛ ሶሊማኑን መግደሏን አስታውቃለች። የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለውን ታጣቂ ቡድን ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲመሩ ቆዩትን ወታደራዊ አዛዥ ተገድለዋል ብሏል።

    አዛዡ የሚመሩት ታጣቂ ቡድን ታኅሣሥ ላይ የነበረውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ለማፈን በተወሰደው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ዘመቻ ውስጥ ተሳትፎ ነበረው።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ፤ የኢራኑ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን መገደላቸውን ባስታወቁበት መግለጫ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና እኔ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የኢራንን የሽብር እና የጭቆና አገዛዝ አመራሮች ማደኑን እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥተናል” ብለዋል።

    “የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራን አመራሮች በከፍተኛ መጠን ስለ መለዋወጣቸውን ሲናገሩ ነበር ... ከቀሩት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ሁለቱ ስለተገደሉ የአመራሮች መለዋወጡ እንደቀጠለ መረጃ እናደርሳቸዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    እስራኤል ይሄንን ብትልም እስካሁን ድረስ ላሪጃኒ እና ሶሎማኒ ስለመገደላቸው ከኢራን በኩል ማረጋገጫ አልተሰጠም።

    የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቢገደሉም መንግሥቱ ባለበት እንዲቀጥል እንዴት ቻለ የሚለውን ለመረዳር ተጨማሪ እዚህ ያንብቡ ➤ ኢራን መሪዎቿን ባጣች ጊዜ እንዴት ሳትንኮታኮት ጸንታ መቀጠል ቻለች?

  19. የባሕረ ሰላጤው አገራት የኢራን የመሣሪያ አቅም ሳይዳከም አሜሪካ ጥቃቷን እንዳታቆም እየገፉ ነው ተባለ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የመካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራት፤ አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው የነዳጅ መተላlፊያ መስመር እና በዚሁ ላይ በተመሠረተው ኢኮኖሚ ላይ አደጋ የደቀነችው ኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት እንዳታቋርጥ እየወተወቱ መሆኑ ተዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስ የባሕረ ሰላጤውን እና ምዕራባውያን ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው አሜሪካ የቀጣናው አገራት ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ ግፊት ስታደርግ ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት እና በአገር ውስጥ ያላቸውን ድጋፍ ለማጠናከር ሲሉ የቀጣናው አገራት ዘመቻውን እንዲደግፉ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሦስት ምንጮች ተናግረዋል ተብሏል።

    የባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ጥያቄ ባያቀርቡም በቴህራን ከደረሰባቸው ጥቃት በኋላ ዋሽንግተን ወደ ኋላ እንዳትል ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።

    ኢራን በፈጸመቻቸው ጥቃቶች በስድስት የቀጣናው አገራት ውስጥ የሚገኙ አየር ማረፊያዎች፣ ወደቦች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የንግድ ማዕከላት ተመትተዋል። በአገራቱ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ኤምባሲዎችም የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

    ኢራን በእነዚህ ጥቃት አቅሟ ምን ያህል እንደሆነ አሳይታለች። የባሕረ ሰላጤው አገራት በአንጻሩ ኢራን ከፍተኛ የጦር መሣሪያ የማምረት አቅሟን ይዛ ከቀጠለች ውጥረት በተነሳ ቁጥር የቀጣናውን የኢነርጂ መስመር አደጋ ላይ ትጥላለች የሚል ስጋት እንደገባቸው የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

  20. እስራኤል የኢራን ቁልፍ የደኅንነት ባለሥልጣን የሆኑት አሊ ላሪጃኒን መግደሏን ተናገረች

    የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ አስታወቁ።

    ሌሊቱን በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው የተነገረው ላሪጃኒ በኢራን መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ከነበራቸው መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

    የባለሥልጣኑ በእስራኤል ዒላማ መሆን እየተነገረ በነበረበት ጊዜ ቢያንስ ሁለት የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናትን ጠቅሰው ግለሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ መግለጫ ይሰጣሉ ብለው ነበር።

    አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን አሊ ላሪጃኒ በእስራኤል መከላከያ ዒላማ መደረጋቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

    አሊ ላሪጃኒ በኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት የሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ተወካይ እና ዋና ፀሐፊ ሆነው የተሾሙት ባለፈው ዓመት ነሐሴ በፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ነበር።

    ለ12 ዓመታት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ የነበሩት ላሪጃኒ “ለዘብተኛ ወግ አጥባቂ” እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፤ በተጨማሪም በኢራን መገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ መሪው አማካሪ እንደሆኑ ይጠቀሱ ነበር።

    እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት መገደላቸው የተነገረው ታዋቂው ኢራናዊ ፖለቲከኛ የፓርላማው አፈ ጉባዔ ከመሆናቸው በፊት ኢራንን ከምዕራባውያን ጋር እያወዛገበ በሚገኘው የኒውክሌር ድርድር ላይ አገራቸውን ወክለው ተደራዳሪ ነበሩ።

    በኢራን ፖለቲካ ውስጥ አሊ ላሪጃኒ ብቻ ሳይሆኑ ወንድማቸውም ከፍተኛ ተሰሚነት አላቸው። ወንድማቸው ሴዴጌ ላሪጃኒ በኢራን ሁለት ኃያል ምክር ቤቶች የበላይ አካል የሆነው ጉባዔ ሊቀ መንበር ናቸው።