የኢራን መንግሥትን የሚደግፉ ሰልፎች እየተካሄዱ እንደሆነ ተዘገበ
የኢራን መንግሥት ያዘጋጃቸው የድጋፍ ሰልፎች በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ እየተካሄዱ እንደሆነ ከአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚወጡ ምሥሎች እያሳዩ ነው።
የኢራን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (አይቢሲ) እንዳለው ሃሚዳን እና ኢላም የተባሉትን ከተሞች ጨምሮ ሰሞኑን አገሪቱን ያናወጧትን ሰልፎች የሚቃወሙ እና መንግሥት የሚደግፉ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።
ሁለቱ ከተሞች ባለፉት ቀናት መንግሥትን የሚቃወሙ ሰልፎች በተደጋጋሚ ከተካሄደባቸው መካከል ናቸው።
ሕዝቡ በእነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ላይ እንዲሳተፍ ከጠዋት ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብ ነበር።
በተጨማሪም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት፣ የፓርላማው አፈ ጉባኤ፣ የፍትሕ አካላት እና በርካታ ታዋቂ ፖለቲከኞች ኢራናውያን በድጋፍ ሰልፉ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
ከሁለት ሳምንት በላይ የሆነው የተቃውሞ ሰልፍ እየተስፋፋ በበርካታ የኢራን ከተሞች ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ቀናትም መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን ዘግቷል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፣ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የኢራን መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ እየተቃወሙ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም፤ ወታደራዊ እርምጃን ጨምሮ በኢራን ባለሥልጣናት ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ ሌሎች እርምጃዎችን እያጤኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።