የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግጭት ቀስቅሰዋል ሲሉ ወቀሱ

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተናገሩት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ "አንዳንዶቹ የተገደሉት ሰብአዊ ባልሆነ፣ ጭካኔ በተሞላው መንገድ ነው" ብለዋል። ለሰዎቹ ሞት አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የተቃዋሚ ሠልፈኞችን የምትገድል ከሆነ "በጣም ጠንካራ እርምጃ" እንደሚወስዱ ገለፁ

    የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች 2400 ተቃዋሚ ሠልፈኞች በኢራን ባለሥልጣናት መገደላቸውን ሲገልጹ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ “በጣም ጠንካራ እርምጃ” እንደምትወስድ ተናገሩ።

    ባለፈው ሳምንት በተቃውሞ ሠልፍ ላይ እያለ በቁጥጥር ሥር የዋለው የ26 ዓመቱ ኢርፋን ሶልታኒ ቤተሰቦች ረቡዕ ዕለት እንደሚገደል ለቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎት ተናግረዋል።

    ሄንጋው የተባለ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ተወካይ ለቢቢሲ “እንዲህ የተፋጠነ ውሳኔ አይተን አናውቅም” ሲል ተናግሯል።

    ትራምፕ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ “የሚሰቅሉት ከሆነ የሆነ ነገር ታያላችሀ. . . እንደዚያ የሚያደርጉ ከሆነ በጣም ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

    የሶልታኒ ዘመድ ለቢቢሲ ፐርዢያ አገልግሎት የኢራን ፍርድ ቤት “በሁለት ቀናት እጅግ በተፋጠነ ሂደት” የሞት ቅጣት ማስተላላፉን ተናግሯል።

    የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ 2000 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ለዚህም “ሽብርተኞቹ” ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።

  2. ኡጋንዳ ሐሙስ ዕለት ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ ኢንተርኔት አቋረጠች

    የኡጋንዳ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ሁሉም የኢንተርኔት አቅራቢዎች ከሐሙሱ ምርጫ አስቀድሞ አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ አሳሰበ።

    መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ለሕዝብ ደህንነት በሚል መሆኑን የገለፀ ሲሆን “በኦንላይን የሚሰራጩ ሐሰተኛ፣ የተዛቡ መረጃዎችን እና የምርጫ ማጭበርበር . . . እንዲሁም የአመጽ መቀስቀስን ለመከላከል” መሆኑን በመጥቀስ ውሳኔውን ተከላክሏል።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኡጋንዳ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን የኢንተርኔት መቆራረጥ ሪፖርቶችን "ተራ ወሬዎች" ሲል አጣጥሎ ነበር።

    በወቅቱ የባለሥልታኑ ሚና በመላ አገሪቱ ያልተቋረጠ ግንኙነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግሯል።

    እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን የተቃውሞ ሠልፍ ተከትሎ በአገሪቱ ኢንተርኔት ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ተቋርጧል።

    ባለሥልጣኑ የኢንተርኔት እገዳ ማክሰኞ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ መጀመር እንዳለበት ቢገልጽም፣ መቼ እንደሚያበቃ ግን አላሳወቀም።

    መደበኛ የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች ኢንተርኔት ማግኘት እንደማይችሉ ሪፖርት ቢያደርጉም፣ እንደ ትላልቅ ሆቴሎች ያሉ አንዳንድ የንግድ ተቋማት ግን ገመድ አልባ ግንኙነት መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።

    የድምጽ ጥሪዎች እና መሠረታዊ የአጭር መልዕክት አገልግሎቶች ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።

    ባለሥልጣኑ ለሞባይል ስልክ ኦፕሬተሮች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከደህንነት ኤጀንሲዎች፣ ከጦር ኃይሉ እና ከፖሊስ ጨምሮ የቀረበለትን "ጠንካራ ምክረ ሀሳብ" እየተገበረ መሆኑን ገልጿል።

    "ይህ ጊዜያዊ እገዳ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ መረጋጋትን ለመጠበቅ እና ስሱ በሆነ ብሔራዊ ጉዳይ ወቅት የመገናኛ መድረኮችን አላግባብ መጠቀምን ለመከላከል የሚደረግ የጥንቃቄ እርምጃ ነው" ሲል ደብዳቤው ላይ አብራርቷል።

    ሐሙስ ዕለት በሚደረገው ምርጫ የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እና የ44 ዓመቱ የቀድሞው ድምጻዊ ቦቢ ዋይን ይፎካከራሉ።

    ከሁለቱ ተፎካካራዎች በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ግለሰቦችም ይወዳደራሉ።

    ቦቢ ዋይን በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚቋረጥ የሚገልጸው ደብዳቤ ይፋ ከሆነ በኋላ ለደጋፊዎቹ በኤክስ ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በብሉቱዝ የሚሰራ መተግበሪያ በስልካቸው ላይ በፍጥነት እንዲጭኑ ጠይቋል።

    ይሁን አንጂ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣኑ መተግበሪያው እንዳይሰራ የማድረግ አቅም እንዳለው አስጠንቅቋል።

    ቦቢ ዋይን የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመገደብ የወሰኑ አካላትን “ፈሪዎች” ሲሉ ገልጿቸዋል።

  3. በኢራን ለሦስተኛ ሳምንት በቀጠለው የተቃውሞ ሠልፍ 2000 ሰዎች ያህል መገደላቸው ተገለፀ

    የኢራን የጸጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ከ2ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቡድን አስታወቀ።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ድጋፍ እየመጣላችሁ ነው" ሲሉ ለሠልፈኞቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የዜና ወኪል (ሃራና) እስካሁን ድረስ 1,850 ተቃዋሚ ሠልፈኞች መገደላቸውን ማረጋገጡን ዘግቧል።

    የተቃውሞ ሠልፉን ተከትሎ ኢንተርኔት በተቋረጠባት ኢራን ከተገደሉት መካከል 135 ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ዘጠኙ ደግሞ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው እንዲሁም ዘጠኙ ሕጻናት ናቸው ሲል የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ለሮይተርስ 2000 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ለዚህ ሊጠየቁ የሚገባቸው “አሸባሪዎቹ” ናቸው ሲሉ ሠልፈኞቹን ወንጅለዋል።

    ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ እንዲሁም በትክክል ምን ያህል ሰዎች በትክክል እንደተገደሉ ማክሰኞ ምሽት ገለጻ ተደርጎላቸዋል ተብሏል።

    መረጃውን ተከትሎ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

    ማክሰኞ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ የኢራን መንግሥት ሠልፈኞቹን በመግደሉ “ትልቅ ዋጋ ይከፍላል” ካሉ በኋላ የተቃውሞ ሠልፈኞቹ በድርጊታቸው እንዲቀጥሉበት ጥሪ አቅርበዋል።

    “ይህ ረብ የለሽ ግድያ እስኪቆም ድረስ ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር የነበረኝን ስብሰባ ሰርዣለሁ፤ እርዳታ እየመጣላችሁ ነው” ብለዋል።

    በስተመጨረሻም በአሜሪካ ተቀማጭነቱን ያደረገው ተቃዋሚ ቡድን የሚጠቀምበትን መፈክር “ኢራንን ዳግም ታላቅ እናደርጋታለን” ሲሉ ጽፈዋል።

  4. “ድጋፍ እየመጣላችሁ ነው” ትራምፕ ለኢራናዊያን ያስተላለፉት መልዕክት

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “ድጋፍ እየመጣላችሁ ነው” ሲሉ ለኢራናዊያን መልዕክት አስተላለፉ።

    ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው “ኢራናዊያን አርበኞች፤ ተቃውሟቸውን ቀጥሉ - ተቋማቶቻችሁን መልሳችሁ ያዙ!!! የሚገድሏችሁን እና የሚሰቃይዋችሁን ሰዎች ስም ዝርዝር ያዙ። ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ" ብለዋል።

    “ከኢራናዊያን ባለሥልጣናት ጋር ላደርገው የነበረውን ስብሰባ ይህ ስሜት የማይሰጥ የተቃዋሚዎች ግድያ እስኪቆም ድረስ ሰርዣለሁ። ድጋፍ እየመጣላችሁ ነው” ሲሉ አክለዋል።

    ትራምፕ ድጋፍ ሲሉ የገለፁት በምን መልኩ አሊያም መቼ እንዲመመጣ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚወሰደው እምርጃ ገለፃ እንደሚደርግላቸው ጽፈዋል።

    የአሜሪካ እርምጃዎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

    ኢራን ፀረ-መንግሥት ሰልፉን ያበረታቱት የአሜሪካ መንግሥት እና እስራኤል ናቸው ስትል ትከስሳለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው በአሜሪካ ለሚወሰድ “የትኛውም ዓይነት እርምጃ ዝግጁ ናት” ሲሉ ለአል ጀዚራ ተናግረዋል።

  5. የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዳይሬክተር ሬደዋን ሁሴን ሞቃዲሹን ጎበኙ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬደዋን ሁሴን ማክሰኞ ሞቃዲሾን መጎብኘታቸው ተዘገበ።

    ሬድዋን ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ጋር ዝግ ስብሰባ ማካሄዳቸውን የቢቢሲ የሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ዘግቧል።

    የሁለቱ ባለሥልጣናት ውይይት ምን እንደሆነ ባይታወቅም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት ይዘው እንደተጓዙ እና በቀጣናው እየታዩ ያሉ ለውጦች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተነግሯል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው እሑድ ወደ ጂቡቲ አቅንተው ከፕሬዝደንት ኢስማኢል ኦማር ጉሌህ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

    ዐቢይ በኤክስ ገፃቸው "ውይይታችን በጂኦፖለቲካዊ ለውጦች፣ በቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም በሁለትዮሽ ትብብር ላይ ያተኮረ ነው" ሲሉ ጽፈው ነበረ።

    እስራኤል ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ የሰጠችውን የሀገርነት እውቅና ተከትሎ ሶማሊያ ቁጣዋን የገለጸች ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት ሰፍኗል።

    የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩን ጉብኝት በተለመከተ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሊያ መንግሥት እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም።

  6. “ኢራን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለትኛውም እርምጃ ዝግጁ ናት” - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን በሚወሰደው እርምጃ ላይ እየመከሩ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው በአሜሪካ ለሚወሰድ “የትኛውም ዓይነት እርምጃ ዝግጁ ናት” አሉ።

    ሚኒስትሩ ለአል ጀዚራ እንደተናገሩት ኢራን በአሁኑ ወቅት ያለችበት የዝግጁነት ደረጃ ባለፈው ሰኔ ወር አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመችባት ጊዜ “በጣሙን የበለጠ ነው” በማለት በአሜሪካ በኩል “ብልህ ምርጫ” ላይ እንደሚደረስ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የጀርመን መራሄ መንግሥት ፍሬዴሬክ ሜርዝ በኢራን የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ የኢራን መንግሥት "የመጨረሻ ቀናት እና ሳምንታት ላይ ነን” በማለት ለሰጡት አስተያየት ቁጣ የታከለበት ምላሽ ሰጥተዋል።

    አራግቺ የሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት ጀርመን ምሳሌ ልትሆን አይገባም በማለት፤ ጀርመን ባለፉት ዓመታት ባራመደችው ሚዛናዊነት የጎደለው አቋም ተዓማኒነቷን አጥታለች ብለዋል።

    "ትንሽዬ እፍረት በማሳየት ውለታ ዋሉልን" በማለት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጀርመኑን መራሄ መንግሥት በአሽሙር ተችተዋቸዋል።

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ቡድን በኢራን ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ አማራጮች ላይ ለመወያየት ማክሰኞ በዋይት ሐውስ ይሰበሰባል።

    ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በኢራን ላይ መውሰድ ስለምትችላቸው የተለያዩ ተዘዋዋሪ እና ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃዎች ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ይህም የረጅም ርቀት የሚሳዔል እና የበይነ መረብ ጥቃትን ሊጨምር እንደሚችል የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

  7. በኢራን ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ሊሆን እንደሚችል ተነገረ

    በኢራን መንግሥት ላይ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ፐርሺያ ዘጋቢ ጂያር ጎል እና ሮይተርስ ያናገራቸው ምንጭ አመለከቱ።

    ጎል እንደሚለው “የተገደሉ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ሊሆን ይችላል” በማለት፤ መንግሥት ከዚህ ቀደም በነበሩ ተቃውሞዎች ላይ ከባድ ምላሽ ሰጥቶ ቢያውቅም “የዚህኛው ዙር ግን ጭራሽ ያልተጠበቀ ነው።"

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ደግሞ ከአንድ የኢራን የደኅንነት ባለሥልጣን ባገኘው መረጃ መሠረት የሟቾች ቁጥር 2 ሺህ ገደማ ይሆናል ሲል ዘግቧል።

    የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ ጀረሚ ሎውረንስ በጄኔቫ በተካሄደ ስብሰባ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ቃለ አቀባዩ እንደሚሉት ይህ መረጃ የመጣው እዚያው ካለ የተባበሩት መንግሥታት ምንጮች ነው።

    አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሰኞ ባወጣው ዘገባ በኢራን ተቃውሞ 650 ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ዘግቧል።

    በኢራን ተቃውሞ ምክንያት የተገደሉ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም።

    መንግሥት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንዳይገቡ የከለከለ ሲሆን ላለፉት አምስት ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎት በመላዋ ኢራን ተቋርጧል።

  8. ማንችስተር ዩናይትድ ማይክል ካሪክን ጊዜያዊ አሠልጣኝ አድርጎ ሾመ

    ማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተጫዋቹን ማይክል ካሪክን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ በሚቆይ ውል ጊዜያዊ አሠልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

    ማንችስተር ዩናይትድ ከሳምንት በፊት ፖርቹጋላዊ ዋና አሠልጣኙ የነበረውን ሩበን አሞሪምን ማሰናበቱ ይታወሳል።

    የአሞሪምን መሰናበት ተከትሎ ቡድኑን በጊዜያዊነት የተረከበው የቀድሞው የክለቡ ተጫዋች ዳረን ፍሌቸር ሁለት ጨዋታ አድርጉ ያለ ድል ኃላፊነቱን ቋጭቷል።

    ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ ወራጅ ቀጠና ከሚገኘው በርንሌ ጋር አቻ ሲለያይ፣ ከኤፍኤ ካፕ ውድድር ደግሞ በሜዳው በብራይተን ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

    ማንችስተር ዩናይትድ ከሌሎች ሁሉም ውድድሮች የተሰናበተ ሲሆን፣ በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ እየተጫወተ የውድድር ዓመቱን ይጨርሳል።

    የፕሪሚየር ሊጉ 21ኛ ሳምንቱ ላይ ማንችስተር ዩይትድ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አዲሱ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ማይክል ካሪክ ለአውሮፓ ውድድሮች ቦታ ለማግኘት ይፋለማሉል።

  9. የኢራን መንግሥት አሜሪካ እና እስራኤልን ተቃውሞውን በመደገፍ ከሰሰ

    የኢራን መንግሥት ለሳምንታት የዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጠላቶቼ በሚላቸው በአሜሪካ እና በእስራኤል የተደገፈ ነው ሲል ከሰሰ።

    የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ ፋጢማህ ሞሃጄራኒ እንደተናገሩት "በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በእስራኤል የተደገፉት ሽብርተኞች የሕዝቡን ሰላማዊ ተቃውሞ አበላሽተውታል" በማለት ለተፈጠረው ደም መፍሰስ ሁለቱ አገራት ከጀርባ እንዳሉ አመልክተዋል።

    ሰኞ ዕለት የኢራን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጎላምሆሴን ሞህሴኒ-ኤጄ በተቃውሞ ወቅት ጥቃት የተፈጸመው "የጦር መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች" ነው በማለት ተቃዋሚዎችን ከስሰዋል።

    በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ተቃዋሚዎቹ ከእስራኤል እና ከአሜሪካ "ግልጽ ድጋፍ" እንተደረገላቸው በመጥቀስ፣ የኢራን መንግሥት "ካለምንም ርህራሄ" እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

    በተቃውሞው እስካሁን ከ600 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጉዳት እንደደረሰባቸው የሆስፒታል ምንጮች እና የሰብአዊ መብት ቡድኖች እየገለጹ ነው።

  10. ቻይና የትራምፕን ታሪፍ ለመቋቋም "አስፈላጊውን እርምጃ" እንደምትወስድ ገለጸች

    ቻይና “መብቴን እና ፍላጎቶቼን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እወስዳለሁ” አለች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የንግድ ትስስር ባላቸው አገራት ላይ የ25% ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ ነው ቻይና አቋሟን የገለጸችው።

    የኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፤ ትራምፕ ከኢራን ጋር “የሚገበያዩ” አገራት ላይ “በአፋጣኝ የሚተገበር” ታሪፍ መጣላቸውን አስታውቀዋል።

    በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ “ቻይና የጅምላ ፍረጃ በሚስተዋልባቸው ታሪፎች ላይ ያላት አቋም ግልጽ እና ዘላቂነት ያለው ነው” ብሏል።

    “የታሪፍ ጦርነት እና የንግድ ጦርነት አሸናፊ የላቸውም። ጫና ማሳደር ችግርን አይቀርፍም። ታሪፍ ሁሉንም ወገን ይጎዳል” ሲልም አክሏክል።

    ቻይና የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር ስትሆን። ኢራቅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ቱርክ እና ሕንድም ከኢራን ጋር የንግድ ትስስር አላቸው።

  11. በኢራን ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 650 ደረሰ

    ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው የኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 650 መድረሱን አንድ የሰብአዊ መብቶች ተከታታይ ቡድን አስታወቀ።

    ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የኢራን መንግሥት በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ካደረገ ከአራት ቀን በላይ ሆኖታል።

    ካለፈው አርብ ጀምሮ አስከ ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ድረስ ኢራን ውስጥ ኢንተርኔት ከ108 ሰዓታት በላይ መቋረጡን በዓለም ዙሪያ የኢንተርኔት አቅርቦትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ አስታውቋል።

    አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የመብት ድርጅቶች ኢንተርኔት መቋረጡ በመንግሥት የሚካሄደውን ጭቆና እና እርምጃ የበለጠ ያባብሰዋል በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

    በተለያዩ የኢራን ግዛቶች ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት ተቃውሞዎች ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መደረጋቸውም እየተነገረ ነው።

    አሜሪካ የኢራን መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የሚያደርሰውን አፈና የሚያስቆም እርምጃ ለመውሰድ አማራጮችን እያጤነች መሆኑን ገልጻለች።

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢራን ላይ ሊወሰዱ ከሚችሉ በርካታ እርምጃዎች መካከል የአየር ጥቃት አንዱ ሆኖ ለትራምፕ ቀርቧል ብለዋል።

  12. ትራምፕ ከቬንዙዌላዊቷ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ሊገናኙ ነው

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቬንዙዌላዊቷ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ጋር እንደሚገናኙ ዋይት ሀውስ አስታወቀ።

    የቬንዝዌላው ፕሬዝዳት ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ነው ትራምፕ ከማቻዶ ጋር እንደሚገናኙ የተገለጸው።

    ትራምፕ፤ እአአ በ2024 በተካሄደው የቬንዙዌላ ምርጫ እንዳሸነፈ ለሚናገረው የማቻዶ ፓርቲ ድጋፍ አልሰጡም።

    አሜሪካ የደገፈችው የማዱሮ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ደልሲ ሮድሪጌዝን ነበር።

    ትራምፕ ማዱሮን ከሥልጣን በማስወገዳቸው ማመስገን እንደሚፈልጉ የተናገሩት ማቻዶ፤ የኖቤል ሽልማታቸውን ለትራምፕ ለመስጠት እንደሚሹም ገልጸዋል።

    ትራምፕ የኖቤል ሽልማቱ ቢተላለፍላቸው “ትልቅ ክብር” እንደሆነ ቢገልጹም፤ የኖቤል ኮሚቴ ግን ሽልማቱ ለሌላ ሰው ተላልፎ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

    ኖቤል የመሸለም ፍላጎት ያላቸው ትራምፕ ሽልማቱ ለማቻዶ በመሰጠቱ እምብዛም ደስተኛ አልነበሩም።

    ትራምፕ የያዝነው ወር መባቻ ላይ “ማቻዶ በአገሯ ደጋፊ የላትም። መልካም ሴት ናት፤ ግን የሚያከብራት የለም” ብለው ነበር።

    አሁን ግን ከማቻዶ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    አሜሪካ ቬንዙዌላ መመራት ያለባት በደልሲ ሮድሪገዝ እንደሆነ ታምናለች። ሮድሪጌዝ የአሜሪካ “አጋር” የተባሉ ሲሆን፤ በአሜሪካም ክስ አልቀረበባቸውም።

    ማቻዶ በበኩላቸው የፓለቲካ ፓርቲያቸው አገሪቱን መምራት እንዳለበት ያምናሉ። ሮድሪጌዝን “ንጹኃንን የሚጨቁነው ሥርዓት ተባባሪ” ሲሉም ገልጸዋል።

  13. ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ማብራሪያ ቀረበላቸው

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ አሜሪካ ልትወስድ በምትችላቸው ወታደራዊ እና ሌሎች እርምጃዎች ላይ ከመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ማብራሪያ ቀረበላቸው።

    ሁለት የመከላከያ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንደተናገሩት በረጅም ርቀት ሚሳዔሎች የሚፈጸም ጥቃት እንደ ዋነኛ አማራጭ ቀርቧል። ነገር ግን የበይነ መረብ ጥቃት እና የሥነ ልቦና ዘመቻም ለውይይት ቀርበዋል።

    የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ቡድን በኢራን ላይ ለሚወሰደው እርምጃ ባሉ አማራጮች ላይ ለመምከር ዛሬ ማክሰኞ ዋይት ሐውስ ውስጥ የሚሰበሰቡ ሲሆን፣ ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ተሳታፊ ስለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።

    ምንጮቹ ለሲቢኤስ እንደተናገሩት አሜሪካ በኢራን ላይ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ አየር ኃይል እንደሚሳተፍበት በመግለጽ፣ ዕቅዱን የሚያወጡት በተለይ የኢራን መንግሥት የዕዝ መዋቅርን እና የግንኙነት መስመርን ማቋረጥን እንደ አማራጭ ለመውሰድ እያሰቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹ ኢራንን ለቅቀው እንዲወጡ ወይም የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ሳያስፈልጋቸው የሚወጡበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢራን ተቃዋሚዎች የሚገደሉ ከሆነ "ከባድ እርምጃ" እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው። የኢራን ባለሥልጣናትም ጥቃት ከተፈጸመባቸው አጸፋውን እንደሚመልሱ፤ ነገር ግን ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።

  14. የኢራኑ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ “አሜሪካውያን ፖለቲከኞች ማታለላቸውን እንዲያቆሙ” አስጠነቀቁ

    መንግሥታቸው ላይ የበረታውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ እየሞከሩ ያሉት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፤ በአገሪቱ ለተካሄደው አመጽ “አሜሪካውያን ፖለቲከኞችን” ተጠያቂ አድርገዋል። ጠቅላይ መሪው ይህንን ያሉት ትናንት ሰኞ ሰልፍ ለወጡ የመንግሥት ደጋፊዎች ባደረጉት ንግግር ነው። የተደረገውን ሰልፍ “የውጭ ጠላቶች እቅድን ያከሸፈ” ሲሉ የጠሩት ኻሜኒ፤ የአሜሪካ ፖለቲከኞች “ማታለላቸውን እንዲያቆሙም” አሳስበዋል።

  15. ትራምፕ ከኢራን ጋር በሚገበያዩ አገራት ላይ 25% ታሪፍ ጣሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚገበያዩ አገራት ላይ 25% ታሪፍ መጣላቸውን አስታወቁ።

    ከኢራን ጋር የንግድ ትስስር ያላቸው አገራት ላይ የተጣለው ታሪፍ የቴህራን መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ያለመ ነው። የኢራን ተቃውሞ ሦስተኛ ሳምንቱን ይዟል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር “የሚገበያዩ” አገራት ላይ “በአፋጣኝ የሚተገበር” ታሪፍ መጣላቸውን ቢገልጹም ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።

    ቻይና የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር ስትሆን። ኢራቅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ቱርክ እና ሕንድም ከኢራን ጋር የንግድ ትስስር አላቸው።

    “ከኢራን ጋር የሚገበያይ ማንኛውም አገር ከአሜሪካ ጋር በሚያደርገው የንግድ ልውውጥ ላይ 25% ታሪፍ ይጣልበታል” ብለዋል ትራምፕ።

    ታሪፍ የተጣለባቸው አገራት የትኞቹ እንደሆኑ አልተገለጸም።

    የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ኢራን ላይ የአየር ጥቃት ማድረስን ጨምሮ ሌሎችም ወታደራዊ አማራጮች እንዳሉ ተናግረዋል።

    የኢራን መገበያያ ገንዘብ ሊያል ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ምንዛሬው መዋዠቁን በመቃወም በቴህራን የባዛር ነጋዴዎች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች ተስፋፍቷል።

    የኢራን ሪያል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ቀንሷል። የዋጋ ንረትም 40% ደርሷል።

    የአሜሪካው የመብት ተሟጋች ‘ሂውማን ራይትስ አክቲቪስት ኒውስ ኤጀንሲ’፤ 500 ተቃዋሚዎች እና 48 የፀጥታ ባልደረቦች መሞታቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል።

    ለቀናት ኢንተርኔት በመቋረጡ ከኢራን የሚወጡ መረጃዎችን ማረጋገጥ አልተቻለም።

  16. የሶማሊያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለውን ግንኙነት አቋረጠ

    የሶማሊያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳቋረጠ እና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በአጠቃላይ እንደሰረዘ አስታወቀ።

    የሶማሊያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ካደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈረሙ ስምምነቶችን መሰረዙን ይፋ አድርጓል። ይህም ከወደብ፣ ከደኅንነት እና ከመከላከያ ጋር የተያያዙ ስምምነቶችን ያካትታል።

    ከበርበራ፣ ከቦሳሶ እና ከኪስማዮ ወደቦች ጋር የሚገናኙ ስምምነቶች እንዲሁም ከሶማሊያ የፌደራል እና ክልላዊ ተቋማት ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ተሰርዘዋል።

    የበርበራ ወደብ ስምምነት እአአ በ2016 የሶማሊላንድ አስተዳደር ከዲፒ ወርልድ ጋር የተፈራረመው ሲሆን፤ ሶማሊያ ስምምነቱ ያለ ፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና የተፈረመ ነው ብላ ስትቃወመው ቆይታለች።

    የሶማሊያ መንግሥት ውሳኔውን ያሳለፈው የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ሕገ መንግሥት ለማስጠበቅ መሆኑን ገልጿል።

    የሶማሊያን መንግሥት የአገሪቱን ነጻነት፣ ብሔራዊ አንድነት እና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት የሚገዳደር ድርጊት ስለመፈጸሙ ማስረጃ በማግኘቱ የወሰደው እርምጃ መሆኑንም አስታውቋል።

    መሰል ድርጊቶች ዓለም አቀፍ መርኅን እና ሉዓላዊነትን እንደሚጥሱ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢስላሚክ ትብብር ተቋም እና አረብ ሊግ ያረቀቋቸው ጣልቃ ላለመግባት የተደረሱ ስምምነቶችን እንደሚጣረሱ የሶማሊያ መንግሥት ገልጿል።

    ውሳኔው የሶማሊያን አንድነት እና ነጻነት የሚገዳደር ድርጊትን የሚቃወሙ የሶማሊያ ዜጎችም ጭምር እንደሆነ አመልክቷል።

    የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውሳኔውን ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ለአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም ለመንግሥታቱ ድርጅት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

  17. ኢራን እና አሜሪካ ምን ዓይነት ወታደራዊ አማራጮች አሏቸው?

    አሜሪካ በኢራን ሊኖራት የሚችለውን ጣልቃ ገብነት በተመለከተ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለያዩ ወታደራዊ አማራጮች ቀርበዋል። ኢራን ጥቃት ከተፈጸመባት የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።

    ባለፈው ሰኔ ኢራን እና እስራኤል ለ12 ቀናት ተዋግተዋል። ውጊያው መጨረሻ ላይ የአሜሪካ አየር ኃይል በኢራን ሦስት የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    በኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲነሳ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደምም ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው በመንግሥት የኃይል እርምጃ ተዳፍረዋል።

    ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ትዕዛዝ ቢሰጡ ዒላማ የሚደረገው የኢራን ጠንካራ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው እስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ይሆናል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒም ዒላማ ሊደረጉ ይችላሉ።

    እርምጃ መውሰድ የአጸፋ ምላሽ ሊያስከትል ይችላል።

    የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎችን “ዶናልድ ትራምን ማስደሰት የሚፈልጉ ከዳተኞች” ብሏቸዋል።

    አሜሪካ ጥቃት ፈጽማ ንጹኃን ሰዎች የሚሞቱ ከሆነ የአሜሪካን የቦምብ ድብደባ የኢራን መንግሥት ሊጠቀምበት ይችላል።

    ኢራን የአጸፋ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አትልም።

    ኢራን ሚሳዔሎች ያሏት ሲሆን፤ የየመን ሁቲ አማጺያን ይደግፏታል። ስትራቴጂክ የሆነውን የነዳጅ መተላለፊያ የሆርሙዝ ሰርጥ ኢራን ልትዘጋው ትችላለች።

    ትራምፕ ኢራን “ሁሉም አማራጮች በእጇ አይደሉም” ብለዋል።

    ኢራን በሶሪያ አጋሯ የነበረውን የባሻር አል-አሳድ አስተዳደርን አጥታለች። እስራኤልም ክፉኛ ጥቃቶች ሰንዝራለች። ከ18 ወራት በፊት የነበራት ጥንካሬ አሁን ያለ አይመስልም።

  18. የፋኖ ከፍተኛ አመራር ከመንግሥት ጋር መስማማታቸው ተነገረ

    የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው የተነገረው ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ ከመንግሥት ጋር በመስማማት የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የተባለው ክንፍ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው የተነገረው ኮሎኔል ፈንታው ቡድኑ ቀደም ሲል ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር የደረሰውን ስምምነት በመቀበል ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸው ተገልጿል።

    በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ የፋኖ ቡድኖች አንዱ የሆነው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ባለፈው ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ከክልሉ መንግሥት ጋር የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

    የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም በማደራደር የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) መሳተፋቸውም ተነግሯል።

    በወቅቱ ስምምነቱን የተፈራረሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ እና ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በኩል ካፒቴን አቶ ማስረሻ ሰጤ ነበሩ።

    ኮሎኔል ፈንታው የትጥቅ እንቅስቃሴውን በመተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ከተመለሱ የአፋሕድ አመራሮች መካከል ሁለተኛው ናቸው።

    ኮሎኔሉ ቡድኑ ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ አማካኝነት ያደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰላም ስምምነቱን በመቀበል የተመለሱት ከታጣቂ ቡድናቸው አባላት ጋር መሆኑን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ተቋም የሆነው አሚኮ ዘግቧል።

  19. አሜሪካ በኢራን ላይ “ጠንካራ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች”- ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ቀጥሏል። እስካሁን ወደ 500 የሚደርሱ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ሲገልጹ፣ 50 የሚሆኑ የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን ደግሞ የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

    መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ያሳሰባቸው ምዕራባውያን ድርጊቱን እየተቃወሙት ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ የአጸፋ አርምጃ እንደምትወስድ እየገለጸች ነው።

    • የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በኢራን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት “በጣም ጠንካራ አማራጮችን እያጤነች ነው” ሲሉ ተናግረዋል

    • የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው ቀድማ ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ እንደሌላት፤ ነገር ግን ጥቃት ከተፈጸመባት ለጦርነት ዝግጁ መሆኗን አሳውቀዋል

    • ይህ በእንዲህ እንዳለ በመላዋ ኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በአገሪቱ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ምን እየተካሄደ እንዳለ በትክክል ለማወቅ አዳጋች ሆኗል

    • የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ እና ሌሎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከእሑድ ምሽት ጀምሮ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እያወጡ ነው

    • አንዳንድ የሰብአዊ መብት ደርጅቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ እና በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በእስር ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል

    • ከዋና ከተማዋ ቴህራን ውጪ በሚገኝ ክፍት የአስከሬን ማስቀመጫ ሥፍራ ቢያንስ 180 አስከሬኖች በነጭ ጨርቅ ተሸፍነው መመልከቷን የቢቢሲ ዘጋቢ ጽፋለች

  20. ኢራን ለድርድርም ሆነ ለጦርነት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

    ኢራን ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ ዕቅድ ባይኖራትም ጥቃት ከተሰነዘረባት ግን ለጦርነት እንዲሁም ለድርድር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ ይህን ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ጣልቃ ልትገባ እንደምትችል ጠቁመው “ወታደራዊ ኃይላችን ጠንካራ አማራጮችን እየተመለከተ ነው” በማለት ኢራን ለድርድር ጥሪ ማቅረቧን ካሳወቁ በኋላ ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በቴህራን የውጭ አገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ባደረጉት ንገግር ኢራን “ጦርነት አትሻም” በማለት የአገራቸው ጠላቶች “የተሳሳተ ስሌት ውስጥ እንዳይገቡ” አስጠንቅቀዋል።

    “ለድርድር ዝግጁ ነን፤ ነገር ግን ድርድሩ በዕኩል መብት እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” በማለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስለኢራን የድርድር ፍላጎት ያሉትን አረጋግጠዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጊ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊታከር እና በሚኒስትር አራግቺ መካከል “አስፈላጊ መልዕክት ለመለዋወጥ” የሚያስችል የግንኙነት መስመር መከፈቱን ገልጸዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት “ድንገተኛ ጥቃት” መፈጸም የኢራን ፍላጎት እንዳልሆነ፤ ጥቃት ከተፈጸመባት ግን ለጦርነት ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

    የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት የበላይ ምክር ቤት አካል የሆነው የመከላከያ ምክር ቤት ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ “በሕጋዊ እራስን የመከላከል ማዕቀፍ ውስጥ ኢራን ጥቃት ከተፈጸመባት ብቻ ምላሽ በመስጠት ላይ አትወሰንም” በማለት ስጋት በሚፈጥሩ ወገኖች ላይ ቀድሞ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆ ነበር