የሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ
እስራኤል ሐሙስ ዕለት በጋዛ ሰርጥ ዴይር አል ባላህ በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መገደላቸውን ሐማስ አስታወቀ።
ሐማስ አክሎም እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን እየጣሰች ነው ሲል ወንጅሏል።
በእስራኤል ጥቃት ተጨማሪ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
እስራኤል ስለ አየር ጥቃቱ እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።
መቀመጫቸውን በሊባኖስ ያደረጉ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የአልቃሰም ብርጌዶች አዛዥ ሙሐመድ አል ሐዋሊ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ተናግረዋል።
አክለውም “እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጣስ ያላትን ፍላጎት ያሳያል’ ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።
በተጨማሪም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ልየ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እስራኤል ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
“ኳሱ ያለው በትራምፐ እና በዊትኮፍ ሜዳ ነው፤ ዋሽንግተን እስራኤል ለተኩስ አቁሙ ስምምነት ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው” ብለዋል።
የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የጋዛ ጦርነትን ለመቋጨት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ግዛቱን የሚያስተዳድር በባለሙያዎች የሚመራ መንግሥት ወደሚቋቋምበት ሁለተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩ ከተገለፀ በኋላ ነው።
የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ምሽት በሐዋሊ ቤተሰብ መኖሪያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአልቃሰም ብርጌዶች ኮማንደር አል ሐዋሊ ባለቤት እና ሴት ልጅ እንዲሁም ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የሕክምና ባለሙያዎች ከተገደሉት ሰዎች መካከል የ16 ዓመት ልጅ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።