ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ኢራን መደራደር ብትፈልግም አሜሪካ ዝግጁ አይደለችም አሉ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ ሁለተኛ ሳምንቱን የደፈነውን የኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ አይደለችም አሉ። ኢራን ስምምነት መፈጸም ፈልጋለች ሲሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን “የቀረቡት የድርድር ነጥቦች ገና በቂ ስላልሆኑ” ንግግር ለማደረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ገና ምርመራ እየተደረገ ነው አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ውስጥ በሚናብ የወታደራዊ ካምፕ አቅራቢያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ።

    ትራምፕ በጥቃቱ ስለሞቱት 168 ሰዎች ኃላፊነት ይወስዱ እንደሆን ተጠይቀው ነበር። ከሞቱት መካከል 110 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው።

    ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጥቃት ጥቅም ላይ የዋለው ቶማሃውክስ የተባለው ሚሳኤል መሆኑን ገልጸዋል። ሚሳኤሉ በአሜሪካ የተሠራ ሲሆን ኢራንን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ይጠቀሙበታል ብለዋል።

    በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት የፈጸመው ሚሳኤል በአሜሪካ ተመርቶ ሌሎች አገራትም ታጥቀውታል የሚለውን ሃሳብ በመስጠት ትራምፕ ብቸኛው ባለሥልጣን ናቸው።

    ባለሙያዎች ደግሞ እስራኤልም ሆነች ኢራን ቶማውክስ ሚሳኤል አለመታጠቃቸውን ገልጸዋል።

    “ስለጉዳዩ በበቂ አላውቅም” ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ጉዳዩ በመጣራት ላይ ነው ብለዋል።

    “የሚመጣው ሪፖርት ምንም ይሁን ምን ሪፖርቱን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” በማለት አክለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።

  2. ትራምፕ ሰኞ ዕለት ስለ ኢራን ምን አሉ?

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት ከበርካታ የመገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሲሆን በተጨማሪም በሪፐብሊካን ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል። በእነዚህ ወቅቶች ትራምፕ አሜሪካ ከኢራን ጋር እያካሄደች ስላለችው ጦርነት በርካታ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

    ትራምፕ ትናንትና ባደረጓቸው ንግግሮች ላይ ስለ ኢራን ምን አሉ?

    • ለሲቢኤስ ኒውስ " ጦርነቱ በጣም እየተጠናቀቀ ይመስለኛል፤ እንደዚያ ማለት ይቻላል" ያሉ ሲሆን አክለውም "አሜሪካ ከተያዘለት ጊዜ በጣም ቀድማለች" ብለዋል።
    • ከኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ፣ የኢራንን ነዳጅ የመቆጣጠር ዕድል ክፍት እንደሆነ በመግለጽ “ሰዎች ስለእርሱ አውርተዋል” ብለዋል።
    • ከኒውዮርክ ፖስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲሁ አስተዳደሩ የአሜሪካ እግረኛ ጦር ወደ ኢራን እንዲገባ የሚያደርግ ውሳኔ ለመወሰን ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
    • ትራምፕ ለሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች ባደረጉት ንግግር ደግሞ አሜሪካ “አንዳንድ በጣም ክፉ ሰዎችን ለማስወገድ” በኢራን ውስጥ “የአጭር ጊዜ” ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ መግባቷን ተናግረዋል። በመቀጠልም "በብዙ መንገዶች አሸንፈናል፤ ግን በበቂ ድል አላደረግንም" ብለዋል።
    • ትራምፕ ለኒውዮርክ ፖስት እንደተናገሩት፣ በኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ “ደስተኛ አይደለሁም” ያሉ ሲሆን ነገር ግን በኋላ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማን እንዲተካ እንደሚፈልጉ ወይም ይህ እንዴት እንደሚሳካ ግልጽ አላደረጉም።
    • ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በኢራን የተፈፀመው ዘመቻ "እጅግ በጣም ስኬታማ" መሆኑን በድጋሚ ገልጸው፣ ነገር ግን ኢራን "ለረጅም ጊዜ" የኑክሌር ጦር መሳሪያ መገንባት አለመቻሏን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ያም በጣም ትልቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
    • ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አሜሪካ አሁንም በኢራን በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ድብደባ እየፈጸመች ነው። አክለውም ዒላማዎቹ "በአንድ ቀን" ድምጥማጣቸው ሊጠፋ ይችላል ብለዋል።
    • ያም ሆኖ ጦርነቱ "በቅርቡ ያበቃል" ብለዋል።
    • ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ ደግሞ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ውስጥ የሚደረገውን የነዳጅ ፍሰትን ካስቆመች "ሞት፣ እሳት እና ቁጣ በእነርሱ ላይ ይወርዳል" ሲሉ ዝተዋል።
  3. አውስትራሊያ የኢራን ብሔራዊ መዝሙርን አንዘምርም ላሉ የአገሪቱ እግር ኳስ ተጫዋቾች ቪዛ ሰጠች

    አውስትራሊያ ለኢራን የሴት እግር ኳስ ተጫዋች ቡድን አባላት የሰብዓዊ ቪዛ ሰጠች።

    በአውስትራሊያ በሚካሄደው የእስያ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ተሳትፈው ከውድድሩ ከተሰናበቱት የኢራን ሴት ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አምስቱ የሰብዓዊ ቪዛ ማግኘታቸውን የአውስትራሊያ መንግሥት አስታውቋል።

    ተጫዋቾቹ ወደ አገራቸው ሊመለሱ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከደቡብ ኮሪያ ጋር ሲያደርጉ የብሔራዊ መዝሙር አንዘምርም በማለታቸው ምክንያት ችግር ሊደርስባቸው ይችላል በማለት ደጋፊዎች ስጋታቸውnእ ገልጸው ነበር።

    ይህ ድርጊታቸውም ቴህራን ውስጥ ትችት ያስከተለ ሲሆን አንድ የመንግሥት አካልም “ድርጊቱ በጦርነት ወቅት የተደረገ ክህደት ነው፤ ከባድ ቅጣት ሊቀጡ ይገባል” በማለት መንግሥትን ጠይቋል። በዚህም ምክንያት የተጫዋቾቹ ጉዳይ የብዙ አካላት አጀንዳ ሆኗል።

    ተጫዋቾቹ ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ መወሰዳቸውን የአውስትራሊያ የማስታወቂያ ሚንስትር ቶኒ ቡርኬ ተናግረዋል። ሌሎቹ የቡድኑ አባላትም ግብዣ ተደርጎላቸው እንደነበር ሚንስትሩ ተናግረዋል።

    “የፖለቲካ አክቲቪስት አለመሆናቸውን በመግለጽ ከምንም ነገር ጋር የማይገናኙ ተጫዋች ብቻ መሆናቸውን” ተናግረዋል ያሉት ሚንስትሩ ለቀናት ንግግር እንዳደረጉም አስረድተዋል።

  4. ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱ በቅርቡ አንደሚጠናቀቅ ከተናገሩ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ

    የዓለም የነዳጅ ዋጋ ማክሰኞ ማለዳ በእስያ ገበያ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለፀ።

    ብሬንት በ8.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ በበርሜል 92̋ ዶላር ሲሸጥ ወደ አሜሪካ የተደረገው የነዳጅ ግብይትም እንዲሁ የ9 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በ88.60 ዶላር ተሸጧል።

    የዓለም የነዳጅ ዋጋ አሁንም የፋርስ ባሕረ ሰላጤው ጦርነት ሲጀመር ከነበረበት የ30 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ነው።

    ዛሬ ማለዳ በእስያ ገበያ ላይ የታየው ቅናሽ የተመዘገበው ዶናልድ ትራምፕ “በጣም በቅርቡ” ጦርነቱ ይጠናቀቃል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

    የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፍሎሪዳ ንግግር ሲያደርጉ ምንም እንኳን አሜሪካ በኢራን ብዙ ወታደራዊ ድሎችን ብታስመዘግብም ጦርነቱ በቅርቡ ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።

    የእስያ አብዛኛው አገራት የነዳጅ ዘይት የሚያስገቡት ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው። በዚህም የተነሳ በቀጣናው እየተካሄደ ያለው ጦርነት ገበያውን ክፉኛ ጎድቶታል።

    የእስያ የአክሲዮን ገበያም ዛሬ ማለዳ ማንሰራራት ማሳየቱ ተጠቅሷል።

  5. የኢራን አብዮታዊ ዘብ የጦርነቱን መጠናቀቅ የምትወስነው ቴህራን ናት አለ

    የኢራን አብዮታዊው ዘብ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱ በቅርብ ያበቃል ሲሉ ለሰጡት አስተያየን ምላሽ ሰጠ።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው "የጦርነቱን ፍጻሜ እንወስናለን" በማለት በመካከለኛው ምሥራቅ ከተጀመረ አስራ አንደኛ ቀኑ ላይ የሚገኘውን ጦርነት የሚያበቃበትን ሁኔታ የምትወስነው ቴህራን መሆኗን ገልጿል።

    አብዮታዊ ዘቡ የእስራኤል እና አሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ “አንድ ሊትር ነዳጅ” ከቀጠናው እንዲወጣ ቴህራን አትፈቅድም ሲል በመግለጫው ማስጠንቀቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

    በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ላይ ያለው ውጥረት ከተባባሰ ወዲህ የዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ መዋዠቅ አሳይቷል

    የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል።

  6. ትራምፕ ኢራን ዓለም ዓቀፉን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርን ብታስተጓጉል "ሞት፣ እሳት እና ቁጣ" እንደሚጠብቃት አስጠነቀቁ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ላይ የሚካሄደውን የመርከብ ጉዞ ብታስተጓጉል ከባድ ጥቃት እንደሚጠብቃት አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ በኦንላየን ባወጡት መግለጫ "ኢራን በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ የሚጓጓዘውን የነዳጅ ፍሰት የሚያስቆም ማንኛውንም ነገር ብታደርግ፣ እስካሁን ከተጎዳችው በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ሃያ እጥፍ ከባድ ጥቃት ይደርስባታል" ብለዋል።

    ወደ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ ዘይት በባህረ ሰላጤው ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን ጦርነቱም የባህር ላይ እንቅስቃሴውን በእጅጉ ቀንሶታል፤ የዓለም የነዳጅ ዋጋም ከፍ ብሏል።

    “በተጨማሪም፣ ኢራን እንደ አገር ዳግም መገንባት ፈጽሞ የማትችላቸውን እና በቀላሉ ሊጠፉ የሚችሉ ዒላማዎችን እንመታለን። ሞት፣ እሳት እና ቁጣ በላያቸው ላይ ይወርዳል። ግን ይህ እንዳይሆን ተስፋ አደርጋለሁም እጸልያለሁ!” ሲሉ ዝተዋል።

  7. ትራምፕ የኢራን ጦርነት ከታቀደለት ጊዜ በፊት "በአብዛኛው እየተጠናቀቀ” እንደሆነ ተናገሩ

    ዶናልድትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ጦርነት በቅርቡ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመው ለቢቢሲ የአሜሪካ የሚዲያ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ “ጦርነቱ በአብዛኛው፤ በጣም እየተጠናቀቀ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

    አሜሪካ "ከተያዘለት ጊዜ በጣም ቀድማለች" በማለት ኢራን "የባሕር ኃይል፣ የመገናኛ አገልግሎት፣ የአየር ኃይል የላትም" ሲሉ አክለዋል፤ ሚሳኤሎቻቸውም “ብትንትናቸው ወጥቷል” ብለዋል።

    ትራምፕ ጦርነቱ በቅርቡ ሊጠናቀቅ ይችላል ብለው ያስቡ እንደሆን ተጠይቀው “በአእምሮዬ ውስጥ ያለው ማጠናቀቅ የሚለው ነው” በማለት መልሰዋል።

    ዋይት ሐውስ ቀደም ሲል አስር ቀን የሞላው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከአንድ ወር በላይ ሊቆይ እንደሚችል አመልክቷል።

  8. ትራምፕ ወደ ኢራን እግረኛ ሠራዊት የማሰማርት ሐሳብ እንደሌላቸው ተናገሩ

    ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃት እያካሄዱ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እግረኛ ሠራዊት ወደ ኢራን የማሰማራት ዕቅድ እንደሌላቸው ጠቆሙ።

    ፕራምፕ ለኒው ዮርክ ፖስት እንደተናገሩት እስካሁን ባለው ሁኔታ የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ኢራን እንዲዘምቱ ከሚያደርስ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ያላትን የዩራኒየም ክምችት ደኅንነት ለመጠበቅ እግረኛ ወታደሮችን ለማሰማራት እያሰቡ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በዚያ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ አልደረስንም። ወደዚያ ውሳኔ ከሚያደርሰን ሁኔታ አልተቃረብንም” ሲሉ ወታደር የመላክ ሃሳብ እንደሌለ ገልጸዋል።

    የኢራን ቀጣይ መሪን በመወሰን ላይ ሚና እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ባለፉት ቀናት ሲናገሩ የነበሩት ትራምፕ የኢራን የሊቃውንት ቡድን የቀድሞውን ሟቹን ጠቅላይ መሪ ልጅ ቦታውን እንዲይዝ በመምረጣቸው “ደስተኛ እንዳልሆኑ” ተናግረዋል።

  9. የቀጠሉት ጥቃቶች፣ የነዳጅ ዋጋ ንረት እና አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ

    በኢራን ላይ የተከፈተው ጥቃት ተባብሶ አስረኛ ቀኑ ላይ በደረሰባት በዛሬው ዕለት ሰኞ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አገራት ውስጥ ፍንዳታዎች በስፋት ተሰምተዋል፤ ጉዳትም አድርሰዋል።

    • በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ስር በምትገኘው በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን እና በእስራኤል ጥቃት የሚፈጸምባት የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ከባድ ፈንዳታ ተሰምቷል።
    • ኢራን በእስራኤል ላይ እየወሰደችው ባለው የአጸፋ እርምጃ ቴል አቪቭ ውስጥ አንድ ሰው መገደሉን የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
    • ቱርክ ደግሞ በበኩሏ ወደ አየር ክልሏ የገባን የኢራን ሚሳዔል ማውደሟን ስታስታውቅ፣ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መከላከያ ሚኒስቴር በአስሮች የሚቆጠሩ ድሮኖችን መለየቱን ገልጿል።
    • ጥቃቶች በተለያዩ አገራት ውስጥ መቀጠላቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡን ቀጥሏል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ደርሷል።
    • አገራት ይህንን ለመቆጣጠር የመጠባበቂያ ነዳጃቸውን ለመጠቀም እንዲሁም የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰዱ ነው።
    • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱ የሚራዘም ከሆነ ቤተሰቦች እና የንግድ ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ ጫና እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።
    • ዶናልድ ትራምፕ ግን ከፍተኛውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለዓለም ሰላም ሲባል የሚከፈል “በጣም ትንሽዬ ዋጋ ነው” ብለዋል።
    • የኢራን ጠቅላይ መሪን በመተካት የሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ መመረጣቸውን ተከትሎ እስራኤል እና አሜሪካ ተተኪውን መሪ ዒላማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይህም ጦርነቱ በቅርቡ አይቋጭም የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
  10. አዲሱን ጠቅላይ መሪ የሚደግፍ ሰልፍ በቴህራን ተደረገ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ቦታን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ልጅ መረከባቸውን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ቴህራን የድጋፍ ሰልፍ ተደረገ።

    አደባባይ የወጡት የመንግሥት ደጋፊዎች የሟቹን ጠቅላይ መሪ እና የልጃቸውን ፎቶግራፎችን ከኢራን ባንዲራ ጋር አድርገው ይዘው ታይተዋል።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በዋና ከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ወደሚገኘው አደባባይ በመውጣት ለአዲሱ ጠቅላይ መሪ ታማኝነታቸውን ገልጸዋል።

    የአዲሱን መሪ ምርጫ በመደገፍ አደባባይ ከወጡት ኢራናውያን በተጨማሪ ሌሎች ደግሞ አዲሱ ጠቅላይ መሪ “ከአባታቸው የከፉ ናቸው” በሚል ለቢቢሲ የፋርስ ቋንቋ አገልግሎት ተናግረዋል።

    ኢራን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ወደ አገሯ ገብተው እንዳይዘግቡ ጥብቅ የቪዛ ቁጥጥር ስለምታደርግ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችሉ መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ነው።

  11. ከአራት ዓመት ወዲህ ከፍተኛው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተመዘገበ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት አንድ ሳምንት ካለፈው በኋላ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ ሲያሳይ በዚህም ምክንያት የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ ነው።

    አሁን የተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከአራት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ተነግሯል። አገራትም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት እስኪረግብ ድረስ ለመጠባበቂያ ያያዙትን የነዳጅ ክምችት ለመጠቀም እያሰቡ ነው።

    ከፍተኛው የዓለም ነዳጅ ዘይት በሚወጣበት እና በሚተላለፍበት የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የተቀሰቀሰው ጦርነት የነዳጅ ማውጫዎች፣ ማጣሪያዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል።

    ኢራን የተከፈተባትን ጥቃት ተከትሎ በሳዑዲ፣ በኤምሬትስ እና በኳታር ባሉ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማዕከላት ላይ ጥቃት በመፈጸሟ እንዲሁም፣ በርካታ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሚተላለፉበት የሆርሙዝ ሰርጥ በተከሰተው የደኅንነት ስጋት መርከቦች መንቀሳቀስ አልቻሉም።

    ከፍተኛው የነዳጅ ምርት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ባለፈው ሳምንት ከ70 ዶላር በታች የነበረው አንድ በርሜል ነዳጅ ከ100 ዶላር በላይ ተሻግሯል።

    ብሬንት የተባለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መተመኛ መድረክ ላይ እሐድ ዕለት በተደረገው ግብይት ዋጋው በ30 በመቶ ጨምሮ አስከ 119 ዶላር ደርሷል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የነዳጅ ጭማሪው ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሚቆይ በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ለአጭር ጊዜ የሚከፈል ዋጋ ነው፤ የኢራን የኒውክሌር ስጋት ሲያበቃ ዓለም ደኅንነቷ የተጠበቀ እና ሰላም ስለምትሆን ዋጋው በፍጥነት ይቀንሳል” ሲሉ ጭማሪውን አቃለውታል።

    ከአንድ ሳምንት በፊት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ በ50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

    ኢራን በተከፈተባት ጥቃት ምክንያት እየወሰደችው ባለው የአጸፋ እርምጃ በሆርሙዝ ሰርጥ የሚደረገው የነዳጅ ዝውውር ተገትቷል፤ ይህም ማለት 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ አቅርቦት እንዲቋረጥ ሆኗል።

  12. ፑቲን "የአባትዎትን ሥራ እንደሚያስቀጥሉ እተማመናሁ" ሲሉ ለአዲሱ የኢራን መሪ መልዕክት አስተላለፉ

    የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ሌሊት ለተመረጡት አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላለፉ። ፑቲን፤ ሩሲያ ለኢራን ያላትን "የማይናወጥ አጋርነትም" በድጋሚ አረጋግጠዋል።

    ፑቲን የክሬምሊን ድረ ገጽ ላይ በወጣ መልዕክታቸው፤ “እባክዎት፤ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ሆነው በመሾምዎ ከልብ የመነጨ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክቴን ይቀበሉኝ” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ፤ ሩሲያ “ለቴህራን ያላትን ድጋፍ እንዲሁም ከኢራናውያን ወዳጆቻችን ጋር ያለንን አጋርነት አረጋግጣለሁ” ብለዋል። “ታማኝ አጋር ሆኖ ለመቀጠልም” ቃል ገብተዋል።

    “ኢራን በትጥቅ የታገዘ አመጻ እየተጋፈጠች ባለችበት በዚህ ጊዜ፤ [በተረከቡት] ከፍተኛ ሥልጣን የሚወስዱት እርምጃ ያለ ምንም ጥርጥር ትልቅ ድፍረት እና ቁርጠኝነት ይጠይቃል” ሲሉ ለአዲሱ ጠቅላይ መሪ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ፑቲን መልዕክታቸው፤ “የአባትዎን ስራ እና ከፍተኛ መከራ የተደቀነበትን የኢራን ሕዝብ አንድነት በክብር እንደሚያስቀጥሉ እተማመናለሁ” ብለዋል።

  13. የኢራን ሚሳዔሎች አሜሪካ እንደማይደርሱ የቴህራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ የአገሪቱ ሚሳዔሎች አሜሪካ እንደማይደርሱ በመግለጽ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ንግግር አጣጣሉ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ኢራን ላይ ጦርነት የተከፈተበት አንዱ ምክንያት አገሪቱ በቅርቡ አሜሪካ የመድረስ አቅም ያላቸው ሚሳዔሎችን ልትታጠቅ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ትናንት ከአሜሪካው ‘ኤንቢሲ ኒውስ’ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የትራምፕን ክስ “ሐሰተኛ መረጃ” ሲሉ አጣጥለዋል።

    አራግቺ፤ “ሚሳዔሎችን የማምረት አቅም አለን፤ ነገር ግን [የሚሳኤሎቹ] ርቀት ከ2,000 ኪሎ ሜትር እንዳይበልጥ ሆነ ብለን ራሳችንን ገድበናል” ብለዋል። “ምክንያቱም በቀሪው ዓለም ባለ የትኛውም አካል እንደ ስጋት መታየት አንፈልግም” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ገልጸዋል።

    “ሚሳዔሎቻችን አሁን [የሚወነጨፉበትን] ርቀት ለመጨመር ያስጀመርነው ምንም ዕቅድ የለም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቃለ መጠይቃቸው ተኩስ አቁም ላይ የመድረስ ሀሳብንም ውድቅ አድርገዋል። አሜሪካ እና እስራኤል “ሰዎችን እየገደሉ ነው፣ ሴት ተማሪዎችን እየገደሉ ነው፣ ሆስፒታል እያጠቁ ነው” ያሉት አራግቺ፤ “ለሕዝባችን ስንል መዋጋት መቀጠል” አለብን ሲሉ ተደምጠዋል።

    አራግቺ፤ አሜሪካ ከተሳተፈችበት የባለፈው ዓመቱ የኢራን እና እስራኤል የ12 ቀናት ጦርነት በኋላ የተደረሰው የተኩስ አቁም መጣሱን ተናግረዋል። አክለውም፤ “እና አሁን በድጋሚ የተኩስ አቁም መጠየቅ ይፈለጋል? እንደዚህ አይሰራም” ብለዋል።

    “ጦርነቱ በዘላቂነት ማብቃት እንዳለበት” ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ያንን እስካላገኘን ድረስ ለሕዝባችን እና ለደኅንነታችን ስንል መዋጋት መቀጠል ያለብን ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

  14. ዛሬ በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጸሙ ጥቃቶች በምሥል

    ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አካባቢዎች የድሮን ጥቃት ስትፈጽም እስራኤል በኢራን እና ሊባኖስ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ድብደባ አካሂዳለች።

    የእስራኤል ጦር በቤይሩት ዳሂህ አካባቢ የሔዝቦላህ መሠረተ ልማት ነው ባለው ስፍራ ላይ ድብደባ ፈጽሟል።

    ቀደም ሲል የጦሩ ቃል አቀባይ አቪሻይ አድራኢ ቨቬይሩት በሚገኙ የ"አሸባሪ መሠረተ ልማቶች" ላይ "የኃይል እርምጃ እንወስዳለን" በማለት ነዋሪዎች ከአካባቢው ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበው ነበር

  15. አሥረኛ ቀኑን በያዘው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እስካሁን ያሉ ዐበይት ዜናዎች

    • ከ2022 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል 120 ዶላር ገብቷል፤ ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ሰላም "የሚከፈል በጣም ትንሽ ዋጋ" ሲሉ ጭማሪው ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
    • ዛሬ ከሰዓት በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ጨምሮ የጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ላይ ለመወያየት የቡድን ሰባት የፋይናንስ ሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄዳሉ። ደቡብ ኮሪያ በ30 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ተመን አውጥታለች።
    • የኢራን የሃይማኖት ሊቃውንት ጉባኤ ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ተክተው የአገሪቱ አዲሱ ጠቅላይ መሪ እንዲሆኑ መርጧል።
    • የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት የቀጠሉ ሲሆን በባህሬን በደረሰው ጥቃት ቢያንስ 32 ሰዎች መቁሰላቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል ።
    • የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ሌሊቱን በኢራን ላይ ተጨማሪ "የጥቃት ማዕበል" ማካሄዱን አስታውቋል። ጥቃቱ የሚሳኤል ስፍራዎችን እና ሌሎች የአገዛዙ "መሠረተ ልማቶችን" ዒላማ ያደረገ እንደነበር ጨምሮ አስታውቋል። ባለፈው ሳምንት ኢራን ላይ "ወደ 3,400 የሚጠጉ ጥቃቶችን" መፈጸሙንም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
    • የእስራኤል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት እንዳስታወቀው፣ ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንዲት ሴት በፍንጥርጣሪ ተመትታ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባታል።
    • ኢራን ከሳምንት በፊት በሳዑዲ አረቢያ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ጉዳት የደረሰበት የአሜሪካ ወታደር መሞቱ ተገልጿል። ይህ እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ የሞቱ የአሜሪካ ወታደሮችን ቁጥር ሰባት ያደርሰዋል።
  16. የቡድን ሰባት አገራት የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ነዳጅን ስለመልቀቅ ሊወያዩ መሆኑ ተገለጸ

    የቡድን ሰባት አገራት፤ ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም ከመጠባበቂያ የነዳጅ ክምችታቸው ውስጥ የተወሰነውን በጋራ የመልቀቅ ሀሳብ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ጉባኤ ሊያካሂዱ ነው።

    የነዳጅ ክምችቱን የሚያስተባብረው ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ነው። 32 የኤጀንሲው አባላት በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሚፈጠርን ቀውስ ለማስተዳደር በተዘረጋ የጋራ የአደጋ ጊዜ ስርዓት አማካኝነት ስትራቴጂክ የነዳጅ ክምችት ይዘዋል።

    አሜሪካን ጨምሮ ዋነኛዎቹ ሦስቱ የቡድን ሰባት አገራት በጋራ ነዳጅ የመልቀቅን ሀሳብ እንደደገፉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መናገራቸውን የአሜሪካው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ ያለው የነዳጅ ክምችት 1.2 ቢሊዮን በርሜል ነው። አሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ከዚህ ውስጥ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን በርሜል ያህሉ በጋራ ቢለቀቅ ተገቢ ነው የሚል ሀሳብ እንዳላቸው አንድ ምንጭ ተናግሯል ተብሏል።

    የቡድን ሰባት አገራት ይህንን ስብሰባ የሚያካሂዱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጦርነቱ መጀመር ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ የጨመረውን የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ እንዲያስቆሙ ጫና እየተደረጋቸው ባለበት ጊዜ ነው።

    ከአውሮፓውያኑ 2022 በኋላ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተስተዋለበት ነዳጅ በበርሜል 110 ዶላር ገብቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ኢራን ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛ የሚሆነው የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች። በተጨማሪም በዚህ ጦርነት የነዳጅ ማከማቻ እና ማምረቻዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

  17. የቻይና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ የኢራን ጦርነትን ለማሸማገል ሳዑዲ አረቢያ ገቡ

    የቻይና መንግሥት የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ዣይ ጁን አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያካሄዱት ያለውን ጦርነት ለማሸማገል ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል።

    ቤይጂንግ "በባህረ ሰላጤው አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የማያቋርጥ ጥረት" ለማድረግ ከሪያድ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን የቻይና መንግሥት አስታውቋል።

    ቻይናን "የሳዑዲ አረቢያ ጥሩ ወዳጅ እና አጋር" ሲሉ የገለጹት ዣይ፣ ከሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳዑድ እና ከባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት (ጂሲሲ) ዋና ፀሐፊ ጃሴም አል ቡዳይዊ ጋር ውይይት ያደርጋሉ።

    ዣይ ከልዑል ፋሲል ጋር በተወያዩበት ወቅት "በቀጣናው ስላለው ውጥረት ትልቅ ስጋት" እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን የባህረ ሰላጤው አገራት ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት እና የግዛት አንድነት መጣስ እንደሌለበት ተናግረዋል።

    "በንጹኃን ዜጎች እና ወታደራዊ ባልሆኑ ዒላማዎች ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት ሊወገዝ እንደሚገባም" ገልጸዋል።

    ዣይ ቤይጂንግ ከዚህ በፊት "ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ" ስትል ያቀረበችውን ጥሪም በድጋሚ አቅርበዋል።

  18. አሜሪካ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞቿን አስወጣች

    አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ተቀጣሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው በደኅንነት ስጋት ምክንያት ሳዑዲ አረቢያን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘ።

    ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሜሪካውያን ዜጎች ወደ ሳዑዲ ጉዞ የማድረግ ሀሳባቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑትም አሳስቧል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው “የኢራን ድሮን እና ሚሳዔል የአሜሪካ ፍላጎቶችን ዒላማ” ያደርጋሉ የሚል ስጋት በመኖሩ እንደሆነ ገልጿል።

    “የትጥቅ ግጭት፣ ሽብር፣ ከአገር የመውጣት ክልከላ እና የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴን በተመለከተ የአገር ውስጥ ሕግ” የመውጣት እርምጃዎችም በስጋት ምንጭነት ተጠቅሰዋል።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር የምትፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች በቀጠሉበት በዚህ ጦርነት የተነሳ አሜሪካ የኤምባሲ ሠራተኞቿን ስታስወጣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ሳምንት በኩዌት ኤምባሲ የነበሩ ሠራተኞቿን በሙሉ በሙሉ አስወጥታለች።

    በተጨማሪም ሳዑዲ የአየር ኃይል ሰፈሯን ዒላማ ያደረገ ባለስቲክ ሚሳዔል ከኢራን እንደተተኮሰባት ገልጻለች። የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው “ወደ ልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል ሰፈር የተተኮሰውን” ባለስቲክ ሚሳዔል መክሸፉ እና መውደሙን አስታውቋል።

    ከዚህ አስቀድሞም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ሪያድ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል የተተኮሱ ሁለት የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታውቆ ነበር።

  19. ትራምፕ እና የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ከተወቃቀሱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነጋገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ዩናይትድ ኪግደም ከኢራን ጋር ለሚያደርጉት ጦርነት የሰጠችውን ምላሽ ተከትሎ መራር ትችት ከሰነዘሩ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ጋር ተነጋገሩ።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስለመሪዎቹ ንግግር ባወጣው መረጃ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአገራቱ መካከል ስላለው ወታደራዊ ትብብር ተወያይተዋል ብሏል።

    ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ዩኬ የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመላክ እያሰበች እንደሆነ በማንሳት "ካሸነፍን በኋላ ጦርነቱን የሚቀላቀሉ ሰዎች አያስፈልጉንም!" ሲሉ ጽፈዋል።

    ብሪታንያንም "በአንድ ወቅት ታላቅ አጋራችን" ነበረች ሲሉ ጠርተዋታል።

    ኪር ስታርመር ቀደም ሲል ዩኬ በኢራን በሚካሄደው ጦርነት ላይ እንደማትሳተፍ ገልጸው ነገር ግን አሜሪካ በኢራን የሚሳዔል ተቋማት ላይ ለምትፈጽማቸው የመከላከል ጥቃቶች የብሪታኒያ ጦር ሰፈሮችን እንድትጠቀም ተስማምተዋል።

    ትራምፕ በኢራን ላይ ለፈጸሙት የመጀመርያ ዙር ጥቃት የዩኬ ጦር ሰፈርን ለመጠቀም ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ከሆነ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ላይ የተሰማቸውን ብስጭት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ "በዩኬ ደስተኛ አይደለሁም" ካሉ በኋላ ስታርመር "ዊንስተን ቸርችልን አይደሉም" ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቬት ኩፐር እሁድ ዕለት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኪር ስታርመር "ለብሪታንያ ጥቅም የመቆም መብት አላቸው" በማለት የዩኬ መንግሥት ከፕሬዚዳንቱ ጋር "በእያንዳንዱ ጉዳይ" እንደማይስማሙ ተናግረዋል።

    “የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ምን እንደሚያስብ የመወሰን ኃላፊነት አለበት፤ እናም ይህን ማድረግ ያለበት እርሱ ነው” ብለዋል።

    አክለውም “ነገር ግን እንደ ዩኬ መንግሥት የዩኬ ብሔራዊ ጥቅምን የመወሰን ሥራ የእኛ ነው፤ ይህ ማለት ከሌሎች አገሮች ጋር መስማማት ወይም የውጭ ፖሊሲያችንን ለሌሎች አገሮች ጥቅም ማዋል ማለት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

  20. የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዲስ ለተሾሙት ጠቅላይ መሪ "ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ ዝግጁ" ነኝ አለ

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከአዲሱ ጠቅላይ መሪ የሚመጡ ትዕዛዞችን ያለምንም ማመንታት ለመቀበል እና ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ።

    የኢራን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ኢሪብ እና የታስኒም የዜና ወኪል አዲስ ስለተሾሙት ሞጅታባ ከአብዮታዊ ዘብ የተሰጠውን መግለጫ አጋርተዋል።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው ሞጅታባ ኻሜኒ “ሁሉን አቀፍ የሕግ ባለሙያ፣ ወጣት አሳቢ እና በፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጣም እውቀት ያላቸው” ሲል ገልጿቸዋል።

    የአብዮታዊ ዘብ አባላቱ ከበላይ መሪው የሚሰጡ ትዕዛዞችን ያለምንም ማመንታት እንደሚቀበሉ “ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ እና ራስን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ" ናቸው በማለት ለኻሜኒ ያለውን "አክብሮት፣ ታማኝነት እና ታዛዥነት" ገልጿል።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ በከፈቱት የጋራ ጥቃት ከተገደሉ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት መካከል የአብዮታዊው ዘብ ዋና ጽህፈት ቤት አዛዦች ይገኙበታል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከ190 ሺህ በላይ ወታደሮች እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን፤ የራሱን የምድር፣ የባሕር እና የአየር ኃይል አጠናክሯል። ወሳኝ የሚባሉትን የኢራንን ስልታዊ የጦር መሣሪያዎችንም የሚቆጣጠረው ይኸው ኃይል ነው።