ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ኢራን መደራደር ብትፈልግም አሜሪካ ዝግጁ አይደለችም አሉ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አሜሪካ ሁለተኛ ሳምንቱን የደፈነውን የኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ አይደለችም አሉ። ኢራን ስምምነት መፈጸም ፈልጋለች ሲሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን “የቀረቡት የድርድር ነጥቦች ገና በቂ ስላልሆኑ” ንግግር ለማደረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መርከቦችን ለማጀብ “ዝግጁ እንዳልሆነ” ተገለጸ

    የአሜሪካ ኢነርጂ መሥሪያ ቤት ሚኒስትር የሆኑት ክሪስ ራይት፤ የአገሪቱ ባሕር ኃይል ኢራን በምትቆጣጠረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጀብ ዝግጁ አለመሆኑን ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ግን የአሜሪካ ባሕር ኃይል በወሽመጡ በኩል ያለፈን ነዳጅ ጫኝ በተሳካ ሁኔታ ማጀቡን ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከዚህ ቀደም “አስፈላጊ ከሆነ” አገራቸው በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦችን እንደምታጅብ መግለጻቸው ይታወሳል።

    የኢነርጂ ሚኒስትሩ ዛሬ ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ሲኤንቢሲ’ ጋር በነበራቸው ቆይታ እጀባው “በአንጻራዊነት በቅርቡ ይሆናል፤ አሁን ግን ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

    “በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ወታደራዊ ኃይሎቻችን ትኩረታቸው የኢራንን የማጥቃት አቅሞችን እንዲሁም ለማጥቃት የሚሆን ግብዓት የሚያቀርበውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ማጥፋት ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ከዓለም ነዳጅ አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች። “ትዕዛዙን ተላልፈው” በአካባቢው የሚያልፉ መርከቦች ላይም ጥቃት እየፈጸመች ነው።

    በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ አሳይቷል። የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ 120 ዶላር ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይ ግን ቀንሷል።

    ዋይት ሐውስ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብን እያጀበ አለመሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ግን ዋጋው ተመልሶ ጭማሪ አሳይቷል።

  2. ኢራን ባለቤትነቱ የአሜሪካ በሆነው መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሟን አረጋገጠች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማክሰኞ ዕለት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ባለቤትነቱ የአሜሪካ የሆነው መርከብ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነት መውሰዱን ከፊል ይፋዊ የሆነው ፋርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው በባሕረ ሰላጤው ሰሜናዊ ክፍል ላይ የአሜሪካ መርከብ ተመትቷል።

    በኢራቅ የውሃ ክፍል ላይ ባስራ በተባለው ስፍራ አቅራቢያ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ናቸው።

    ከእነዚህ አንዱ የሆነው ‘ሴፍሲ ቪሽኑ’ የተባለው የአሜሪካ መርከብ ሲጓዝ የነበረው የማርሻል ደሴት ባንዲራን እያውለበለበ ነው።

    የዜና ወኪሉ ባወጣው ዘገባ በአሜሪካው መርከብ ላይ ጥቃት የተፈጸመበትን ቅጽበት የሚያሳይ ቪዲዮ አካትቷል። ቪዲዮው፤ በእኩለ ሌሊት በውሃ ክፍሉ ላይ እየተጓዘ የነበረው መርከብ ላይ ተፈጠረውን ከፍተኛ ፍንዳታ ያሳያል።

    የህንድ ባለሥልጣናት ‘ሴፍሲ ቪሽኑ’ ጥቃት የተፈጸመበት “ነጭ ቀለም ባለው፣ ፈንጂ የጫነ ፈጣን ሰው አልባ ጀልባ” እንደሆነ ተናግረው ነበር። ጀልባው “ከመርከቡ ጋር ተጋጭቶ፤ ከፍተኛ እሳት መያያዙንም” ገልጸዋል።

    በዚህ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ቀሪዎቹ የመርከቡ ሠራተኞችን ማዳን ተችሏል።

    ፋርስ የዜና ወኪል በዘገባው፤ መርከቡ ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ “ማክበር አለመቻሉን” ጠቅሷል።

  3. አሜሪካ ዒላማዋን በትክክል ለመምታት ምን ዓይነት መሣሪያ እየተጠቀመች ነው?

    የአሜሪካ እና የእስራኤል ኃይሎች 13ተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት በኢራን ወታደራዊ ይዞታዎች እንዲሁም ተቋማት ላይ እየፈጸሙ ያሏቸውን ጥቃቶች የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎችን ለቅቀዋል።

    ጥቃት ለመፈጸም ከዋሉት መሣሪያዎች መካከል ‘GBU-31 JDAMs’ ወይም ‘ባንከር በስተርስ’ በሚለው ስያሜ ይበልጥ የሚታወቀው ተተኳሽ ይገኝበታል። ከ907 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝነው ይህ መሣሪያ፤ ጠንካራ ስፍራዎችን ሰብሮ መግባት ይችላል።

    ብዙውን ጊዜ በእነዚህ መሣሪያዎች ጥቃት የሚፈጸመው በሳተላይት አቅጣጫ ጠቋሚነት በመታገዝ ነው። ረቡዕ ምሽት ግን የአሜሪካ ጦር ቦንቦችን በዒላማው ላይ ለመጣል የጨረር መለያን እየተጠቀመ መሆኑን የሚያመለክት ማስረጃ ታይቷል።

    በዛሬው ዕለት የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ውስጥ አርፎ የነበረ አውሮፕላን የፈጸማቸውን ጥቃቶች የሚያሳይ ቪዲዮ ለቅቋል።

    ቪዲዮው ዒላማው ላይ ጨረር ሲያርፍ በግልጽ ያሳያል። ጨረሩ ጥቃት በሚፈጽመው አውሮፕላን የነዳጅ መያዣ (ፖድ) ላይ የሚቀመጥ ሲሆን፣ አብራሪውም ዒላማው ላይ እንዲያነጣጠር ያደርገዋል።

    ተተኳሹ ከጄቱ ከወጣ በኋላ በተገጠመለት መቆጣጠሪያ አማካኝነት እየተመራ ጨረሩ ያረፈበት ስፍራ ላይ ያርፋል። ቦምቡ ከብዙ ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ቢጣልም እንኳ ከዒላማው ፈቀቅ የሚለው በአንድ ወይም ሁለት ሜትር ልዩነት ነው።

    ይህ የጨረር መከታተያ መሣሪያ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዒላማዎችን ለመምታትም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ሁሌም ምርጥ ነው ማለት ግን አይደለም።

    ደመና እና ሌሎች የከባቢ አየር ሁኔታዎች ዒላማውን በትክክል የመምታት አቅሙን በከፍተኛ መጠን ሊቀንሱት ይችላሉ። በጂፒኤስ የሚታገዝ መሣሪያ ጥቅም ላይ የሚለው እንግዲህ በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ነው።

    ጨረርም፣ ጂፒኤስም በመጠቀል ዒላማ የሚያደርጉ መሣሪያዎች በመኖራቸው እንደ ሁኔታው አመቺነት ተገቢው አማራጭ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

  4. የእስራኤል ጦር የኢራን “የኒውክሌር መሣሪያ ማምረቻ ግቢን” መትቻለሁ አለ

    የእስራኤል ጦር “ባለፉት ቀናት” በፈጸማቸው ጥቃቶች ቴህራን ውስጥ የሚገኝ የኢራን “ኒውክሌር ማምረቻ ግቢን” መምታቱን ገለጸ።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ጥቃት የደረሰበት ስፍራ ኢራን “ወሳኝ” የኒውክሌር መሣሪያ “አቅሞቿን ለማሳደግ” ለማሳደግ ትጠቀምበት ነበር ብሏል።

    ‘ታሌግሃን’ የተባለው ይህ ግቢ የተመታው ባለፉት ቀናት ውስጥ አካባቢው ላይ በተፈጸመው ተከታታይ ጥቃት እንደሆነ ተገልጿል።

    የእስራኤል ጦር በቴሌግራም ገጹ ባወጣው መግለጫ “የ‘ታሌግሃን’ ግቢ የኒውክሌር መሣሪያዎችን ለማልማት የሚያስችሉ ወሳኝ አቅሞችን ለማሳደግ በአገዛዙ ጥቅም ላይ ውሏል” ብሏል።

    እንደ እስራኤል ጦር ገለጻ፤ ስፍራው በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ “የምሥጢራዊ የኒውክሌር መሣሪያ ልማት ፕሮግራም” አካል ሆኖ ፈንጂዎችን ለማምረት እና ሙከራዎችን ለማድረግ ይውል ነበር።

    መግለጫው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ውስጥ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች የአገሪቱ የኒውክሌር መሣሪያ ፕሮግራም ላይ “ከፍተኛ ጉዳት” እንዳደረሰም አንስቷል።

    አሁን ጥቃት ተፈጽሞበታል የተባለው ይህ ስፍራ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2024 ላይም ተመትቶ ነበር።

    ጦሩ በመግለጫው “ግቢው [በአውሮፓውያኑ] ጥቅምት 2024 ጥቃት ከደረሰበት በኋላ አገዛዙ በድጋሚ መልሶ ለማቋቋም እርምጃዎችን መውሰዱን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ለይቷል” ብሏል።

    የእስራኤል መንግሥት ይህንን ቢልም ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ለማምረት እየሠራች ነው በሚል የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች። የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል እንደሆነም ገልጻለች።

    ይሁን እንጂ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ሳትታጠቅ ለጦር መሣሪያነት በሚውል ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም ያላት ብቸኛዋ አገር ነች።

  5. ቪዲዮ፡ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በተወንጫፊ ተመትተው የወደሙት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች

    ረቡዕ ዕለት ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከኢራቅ አቅራቢያ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ “ምንነቱ ባልታወቀ” ተወንጫፊ ተመትተው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘግቦ ነበር። ዛሬ ሐሙስ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን መርከቦች የሚያሳዩ ምሥሎች እየወጡ ነው።

  6. ዴሞክራቶች በኢራን ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት የመከላከያ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ ጠየቁ

    የአሜሪካ ሴኔት አባላት የሆኑ ዴሞክራቶች የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት በኢራን በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት መልስ እንዲሰጡ ጠየቁ።

    አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት የመጀመሪያ ቀናት በትምህርት ቤቱ ላይ በደረሰ ጉዳት 110 ሕጻናትን ጨምሮ 168 ሰዎችን መሞታቸውን የኢራን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የፔንታጎን መርማሪዎች በጥቃቱ ጦሩ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል እምነት እንዳላቸው የዘገቡ ሲሆን ድምዳሜ ላይ ግን አለመድረሳቸው ጠቅሰዋል።

    ፔንታጎን በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ከመግለጽ ባሻገር የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

    በሴኔት ውስጥ አባል የሆኑ ዴሞክራቶች በሙሉ በሚናብ ስለተፈፀመው ጥቃት ለመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት ዝርዝር ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

    አሜሪካ በጥቃቱ ላይ ሚና እንደነበራት ከተረጋገጠ ባለፉት አስርት ዓመታት አገሪቱ በመካከለኛው ምሥራቅ በነበራት ተሳትፎ በአንድ ስፍራ ላይ በሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰችው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሞት ይሆናል።

    ምንም እንኳን የአሜሪካ ቶማሃውክ ሚሳዔል በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ በሚገኘው የኢራን ወታደራዊ ተቋም ላይ ድብደባ የፈጸመ ቢሆንም፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ምንም ማስረጃ ሳይጠቅሱ ኢራን ጥቃቱን መፈጸሟን ተናግረዋል።

    ሄግሴት ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ እንዳላደረገች እና ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

  7. 13ኛ ቀኑን በያዘው የፋርስ ባሕረሰላጤው ጦርነት ጥቃቶች ቀጥለዋል

    አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት 13ኛ ቀኑን በያዘበት ዕለት በቀጣናው የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቀጥለዋል።

    • እስራኤል በኢራን “መጠነ ሰፊ ጥቃት” መፈጸም መጀመሯን ገልጻለች። እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት የፈጸመችውን ድብደባ ተከትሎ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ከተገለፀ በኋላ በምሥራቅ ሊባኖስ የሚኖሩ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች።
    • ኢራን በቀጠናው የሚገኙ የተለያዩ አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለች። ጣሊያን በሰሜን ኢራቅ ኢርቢል በሚገኘው የጦር ሠፈሯ ላይ ትናንት ሌሊት ጥቃት መፈጸሙን ገልጻለች። በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያም የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል።
    • ሦስት የጭነት መርከቦች ትናንት ሌሊት ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሁለቱ በኢራቅ አንዱ ደግሞ በዩኤኢ ወደቦች ላይ ሳሉ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን የአንድ ሰው ሕእወት ማለፉ ተዘግቧል።
    • ሐሙስ ዕለት የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 100 ዶላር ደርሷል።
  8. ኢራን በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ እንደማትሳተፍ አስታወቀች

    ኢራን በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ እንደማትሳተፍ አስታወቀች።

    የኢራን ስፖርት እና ወጣቶች ሚኒስትር አህመድ ዶኒያማሊ አገሪቱ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ልትሳተፍ እንደማትችል አስታውቀዋል።

    ኢራን በመጪው ሰኔ ወር በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ እንደምትሳተፍ ተገልጾ ነበር።

    ኢራን ከኒውዚላንድ፣ ቤልጂየም እንዲሁም ግብጽ ጋር ግጥሚያዎችን በሎስ አንጀለስ እና ሲያትል እንደምታደርግ የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።

    አሜሪካ እና እስራኤል አገሪቱ ላይ ጥቃት ፈጽመው የአገሪቱን የበላይ መሪ ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን እና ወታደራዊ መሪዎችን መግደላቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ተሳትፎ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

    ረቡዕ ዕለት የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን መሳተፍ እንደምትችል እንዳረጋገጡላቸው ተናግረው ነበር።

    የፊፋው ፕሬዝዳንት በኢንስታግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው ስለ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

    ነገር ግን ዶኒያማሊ ማክሰኞ ከኢሪብ ስፖርት ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ይህ ብልሹ መንግሥት መሪያችንን ከገደለ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተስማሚ ሁኔታዎች የሉንም።

    "ልጆቻችን ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደለም፤ እና ልንሳተፍበት የምንችልበት ሁኔታም የለም።"

    አክለውም "ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጦርነቶች ተጭነውብናል፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተገድለዋል፤ ሰማዕት ሆነዋል። ስለዚህ በእርግጠኝነት የመሳተፍ እድል የለንም" ብለዋል።

  9. በመካለኛው ምሥራቅ ረቡዕ ሌሊት የደረሱ ጥቃቶች በምሥል

    ረቡዕ ሌሊት በመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ላይ በርካታ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ኢራንም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።

    የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር መርከብ ንግድ ድርጅት ረቡዕ ሌሊት ሦስት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል። ሁለቱ መርከቦች ላይ ጥቃት የደረሰው በኢራቅ ወደብ ላይ ሲሆን አንዱ ደግሞ በአረብ ኤምሬትስ ወደብ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

  10. እስራኤል በቤይሩት ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሔዝቦላህ ወደ እስራኤል ከ100 በላይ ሮኬቶችን ተኮሰ

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ ባካሄደችው የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲገደሉ በዋና ከተማዋ ቤይሩት በሚገኝ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ጥቃቱ በአንድ መኪና ላይ በቀጥታ የተፈጸመ ሲሆን ከተገደሉት በተጨማሪ 21 ሰዎች ቆስለዋል። በሁለተኛ ዙር ጥቃት ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ደርሷል።

    ረቡዕ ሌሊት ዋና ከተማዋ ቤይሩት ከባድ የአየር ድብደባ የተፈጸመባት ሲሆን በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል። በዚህም የተነሳ ከደቡባዊ የከተማዋ አካባቢ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጥቃቱን ለመሸሽ ቤታቸውን ጥለው ወጥተዋል።

    የተለያዩ የከተማዋ ክፍሎችን ዒላማ ያደረጉ ሌሎች የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት እንዳለው “መጠነ ሰፊ” ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ሌሊቱን ሊባኖስ ውስጥ መፈጸሙን አረጋግጦ፣ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ አስር የሔዝቦላህ ጽሕፈት ቤቶችን ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።

    በምላሹም ሔዝቦላህ ከ100 በላይ ሮኬቶችን ወደ ሃይፋ እና ሌሎች በሰሜን እስራኤል ወደሚገኙ አካባቢዎች ተኩሷል። ይህም ከወዳጁ ኢራን ጋር በመቀናጀት የተፈጸመ ጥቃት ነው ተብሏል።

  11. እስካሁን ድረስ ምን ያህል መርከቦች ጥቃት ደረሰባቸው?

    በአረቢያ ባሕረ ሰላጤ፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ ከአውሮፓውያኑ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 11 ድረስ ብቻ 13 መርከቦች ጥቃት እንደደረሰባቸው የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ንግድ ድርጅት አስታወቀ።

    ሌሊቱን በኢራቅ የባሕር ዳርቻ በባስራ ከተማ በሁም ቃስር ወደብ አቅራቢያ ተጨማሪ ሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በዩኤኢ ወደብ አቅራቢያ ደግሞ አንድ ኮንቴይነር የጫነ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።

    በጥቃቱ 38 ሠራተኞችን ከአደጋ ማትረፍ ሲቻል አንድ ሰው መሞቱን የኢራቅ ወደቦችን የሚያስተዳድረው ኩባንያ አስታወቋል።

    ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ሰሜናዊ ጀበል አሊ ወደብ አቅራቢያ ኮንቴይነር የጫነች መርከብ ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ ጥቃት እንደደረሰባት እና መጠነኛ እሳት መቀስቀሱን የዩኬ ባሕር ንግድ ድርጅት አስታውቋል። አክሎም ጉዳቱን መጠን ለማወቅ ጨለማ በመሆኑ እንዳልተቻለ ተገልጿል።

  12. በባሕረ ሰላጤው ሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ አሻቀበ

    ረቡዕ ሌሊት በኢራቅ ባስራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ኡም ቃስር ወደብ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ጥቃት ተፈጸመ።

    የኢራቅ ወደብን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ከመርከቦቹ ላይ የ38 ሠራተኞችን ሕይወት ማትረፉን እና አንድ ሰው መሞቱን ለአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

    መርከቦችን የሚከታተሉ ድረገጾች ሁለቱ ነዳጅ ጫኞች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ የሕይወት አድን ጀልባዎች ከብበዋቸው አሳይተዋል።

    መርከቦቹ ላይ ፍንዳታው በምን ምክንያት እንደተከሰተ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም። በባስራ የሚገኝ የደኅንነት ሠራተኛ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት ከሆነ ፈንጂ የተጠመደበት የኢራን ጀልባ ሁለቱ መርከቦችን እንዳጠቃች ይታመናል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የንግድ መርከብን የሚቆጣጠረው ተቋም ጥቃቱን በተመለከተ ተመሳሳይ መረጃ እንደደረሰው ያስታወቀ ሲሆን፣ የኢራቅ ነዳጅ ዘይት ገበያ ድርጅት በደረሰው አደጋ “በጥልቅ ማዘኑን" ገልጿል።

    በሁሉም የኢራቅ ወደቦች ለጊዜው ማንኛውም እንቅስቃሴ ተቋርጧል።

    ረቡዕ ዕለት ሦስት የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታታቸውን እና ቢያንስ አንዱ በእሳት መያያዙ ተዘግቧል።

    ይህ ጥቃት የተፈጸመው አሜሪካ በአካባቢው በነበሩ በርካታ የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማ ማውደሟን ካሳወቀች ከሰዓታት በኋላ ነው።

    የዩኬ የባሕር ንግድ መርከብ ጨምሮ እንዳስታወቀው “ያልታወቀ ተወንጫፊ” የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የጭነት መርከቦች ከሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲወጡ ተደርጓል።

    ኢራን አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት መፈጸማቸውን እስካላቆሙ ድረስ በወሽመጡ በኩል ነዳጅ አያልፍም ስትል አስጠንቅቃለች።

  13. ኤፍቢአይ ኢራን ወደ ካሊፎርኒያ ድሮኖችን ልታስወነጭፍ ትችላላች ሲል አስጠነቀቀ

    ባለፈው ሳምንት ኤፍቢአይ ለሎስ አንጀለስ የሕግ አስከባሪ አካላት በጻፈው የውስጥ ማስታወሻ ኢራን ወደ ካሊፎርኒያ ድሮኖች ልታስወነጭፍ እንደምትችል ማስጠንቀቁ ተዘገበ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ከሆነ ኢራን በካሊፎርኒያ ላይ “ድንገተኛ ጥቃት” ለመፈጸም ከባሕር ላይ ድሮን ልታስወነጭፍ ትችላለች ሲል አስጠንቅቋል።

    የአሜሪካ መንግሥት እና ካሊፎርኒያ ግዛት ሕግ አስከባሪ የደኅንነት ባለሥልጣናት ለዜና ተቋሙ እንደተናገሩት ማስታወሻው ላይ እንደሰፈረው የሚታወቅ ወይንም የተለየ ስጋት የለም።

    የሎስ አንጀለስ የሕግ አስከባሪ አካላት መረጃውን ያገኙት በኢራን ላይ አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከመክፈታቸው በፊት ነው።

    የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት "በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት የተለየ ስጋት እንዳለ ባናውቅም በግዛታችን ለሚከሰት ማንኛውም አደጋ ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን" ብለዋል።

  14. በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 1,100 ሕጻናት መቁሰላቸውን ወይም መሞታቸውን ዩኒሴፍ ገለፀ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት "በቀጣናው ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እሰቃቂ ነው" ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።

    አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ዕለት አንስቶ ከ1,100 በላይ ሕጻናት ጉዳት ወይም ሞት እንደደረሰባቸው ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    መግለጫው አክሎም ይህ መረጃ በኢራን የተገደሉ 200፣ በሊባኖስ 91፣ በእስራኤል አራት እንዲሁም በኩዌት አንድ ሕፃናትን ያጠቃልላል።

    ዩኒሴፍ "የሕፃናትን መገደል እና የአካልጉዳት ማድረስ ወይም ሕጻናት የሚገለገሉባቸውን አስፈላጊ አገልግሎቶች ማውደም እና መቋረጥ ምንም ምከንያት የሚቀርብበት ነገር አይደለም “ ብሏል።

    ድርጅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተዋጊ አካላት "ጦርነቱን ቆሞ ወደ ዲፕሎማሲ ድርድር እንዲመጡ" ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

    በተጨማሪም በጦርነት የሚሳተፉ አካላት "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ፣ ይህም ሕፃናትን የሚጎዱ ፈንጂዎችን ከመጠቀም መቆጠብን ጨምሮ፣ የጦር መሳሪያዎችን በመምረጥ ረገድ ሁሉንም አስፈላጊ ጥንቃቄዎች እንዲወስዱ" ጥሪ አቅርቧል።

  15. ጦርነቱ "እንዲያበቃ በፈለግኩ ጊዜ ያበቃል" - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የአሜሪካውፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአክሲዮስ የዜና ወኪል ከኢራን ጋር የሚደረገው ጦርነት “በቅርቡ” ያበቃል ሲሉ ተናግረው "ምንም ዒላማ የሚደረግ የቀረ ነገር የለም" አሉ።

    በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት "እንዲያበቃ በፈለግኩ ጊዜ ሁሉ ያበቃል" ሲሉ ትራምፕ መናገራቸውን የዜና አውታሩ ዘግቧል።

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ነበር።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ረቡዕ ዕለት ጦርነቱ "ያለምንም የጊዜ ገደብ ይቀጥላል" ብለው ነበር።

    ካትዝ እንዳሉት ጦርነቱ አስፈላጊ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ እና የእስራኤል እና የአሜሪካ የጋራ ዘመቻ ሁሉም ዓላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ እና ዘ ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል ዘግበዋል።

  16. አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ጉዳት ደርሶባቸው ከጥቃት መትረፋቸው እየተነገረ ነው

    የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ሆነው የተመረጡት የቀድሞው መሪ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ ያሉበት የጤናን ሁኔታ በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው።

    የአዲሱ ጠቅላይ መሪ ደኅንነት እንዲሁም ከተመረጡ በኋላ ለሕዝብ በይፋ አለመታየታቸው አጠያያቂ ከመሆኑ በተጨማሪ ለኢራን መንግሥት ቅርበት ያላቸው ምንጮች የሚሰጧቸው መረጃዎች የሞጅታባ ጤንነት ላይ ጥያቄ ፈጥሯል።

    በቆፕሮስ የኢራን አምባሳደር የሆኑት አሊሬዛ ሳላሪያን ለብሪታኒያው ጋዜጣ ‘ዘ ጋርዲያን’ ጠቅላይ መሪው “እግር እና እጆቻቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰምቻለሁ... የመቁሰል ጉዳት ስለደረሰባቸው ሆስፒታል እንደሆኑ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

    የሞጅታባ ደኅንነት ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑን ተከትሎ የፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በቴሌግራም ገጹ ላይ ጠቅላይ መሪው ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚገልጹ “ሪፖርቶችን አይቻለሁ” በማለት፣ ነገር ግን ሞጅታባ ደኅና መሆናቸውን ማረጋገጡን ጽፏል።

    በተጨማሪም ሰኞ ዕለት የሞጅታባ መመረጥ ዜና ከወጣ በኋላ የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር ቢጠቅስም ምንም ዓይነት ዝርዝር ግን ሳይሰጥ ቀርቷል።

    ቆፕሮስ ያሉት የኢራን አምባሳደር ጨምረው እንዳብራሩት ሞጅታባ ኻሜኒ ጉዳት የደረሰባቸው አባታቸውን እና ሌሎች አምስት የቤተሰባቸው አባላት በተገደሉበት ጥቃት መሆኑን አመልክተዋል።

    ሞጅታባ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሆነው ከተሰየሙ ሦስት ቀናት ያለፏቸው ቢሆንም እስካሁን ከእሳቸው በኩል ምንም ዓይነት መልዕክትም አልተሰማም፤ በአደባባይ አልታዩም ወይም ንግግር አላደረጉም ።

    አምባሳደሩ ይህንን በተመለከተ ለ ዘ ጋርዲያን እንደተናገሩት “በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ንግግር ለማድረግ የሚፈልጉ አይመስለኝም” ብለዋል።

    በመጀመሪያው ቀን የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተገደሉ ወታደራዊ አዛዦች የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት የተፈጸመ ሲሆን፣ ነገር ግን ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ አልተገኙም።

    በቆጵሮስ የኢራን አምባሳደር ለጋዜጣው ሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በሕይወት እያሉ የሃይማኖት መሪዎች ልጃቸው እንዲተካቸው ጥያቄ ቢቀርብላቸውም የቤተሰብ ሥርዓት እንዲሆን እንደማይፈልጉ በመግለጽ መቃወማቸውን ተናገረዋል።

    ነገር ግን ከአባታቸው መገደል በኋላ የከፍተኛ ሊቃውንቱ ጉባኤ ሞጅታባን ለመሪነት በመሰየም “ኃላፊነቱ የአንተ ነው መቀበል አለብህ” በማለት ለመሪነት እንደመረጧቸው ገልጸዋል።

    የአያቶላህ ኻሜኒ ግድያን በተመለከተም መኖሪያ ቤታቸው ከፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ስለነበረ ጥቃቱ ሲፈጸም ሚስታቸው፣ ሴት ልጃቸው፣ ባሏ እና የ14 ዓመት ልጇ ጭምር መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

  17. ኢራን 'አንድ ሊትር ነዳጅ' በሆርሙዝ በኩል እንዲያልፍ እንደማትፈቅድ ገለጸች

    ኢራን የአፀፋ ጥቃት የመሰንዘር ፖሊሲዋ መለወጡን የአብዮታዊ ዘብን እና የአገሪቱን ጦር የሚያስተባብረው ወታደራዊ ማዘዣ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ።

    የቴህራን ፖሊሲ አሁን "ጥቃትን በጥቃት መመለስ" ይሆናል ሲሉ ቃል አቀባዩ ኢብራሂም ዞልፋካሪ ተናግረዋል።

    ቴህራን "አንድ ሊትር ነዳጅ እንኳን" የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋርጦ አሜሪካ፣ እስራኤል እና አጋሮቿ ዘንድ እንዲደርስ አትፈቅድም ሲሉ ዞልፋካሪ አክለው ተናግረዋል።

    "ከእነሱ ጋር የተያያዘ ማንኛውም መርከብ ወይም ነዳጅ ጫኝ ዒላማ ይሆናል።"

    "የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 200 ዶላር እንደሚሆን ጠብቁ፤ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ የሚወሰነው ሰላሙን ባደፈረሳችሁት ቀጣና ደኅንነት ላይ ነው" ሲሉ ቃል አቀባዩ አክለዋል።

  18. የቡድን ሰባት አገራት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ለመቋቋም ከክምችታቸው ለመልቀቅ ተስማሙ

    የቡድን 7 አገራት አሜሪካ እና እስራኤል ከቴህራን ጋር ጦርነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተከሰተውን ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ለመቋቋም ከክምችታቸው እንዲለቀቅ እንደሚደግፉ አስታወቁ።

    አገራቱ ከዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኢኤ) ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፣ ከረቡዕ ከሰዓት ጀምሮ በነዳጅ ገበያ ውስጥ ትልቁ ነው የተባለውን መጠን ከመጠባበቂያ የነዳጅ ክምችታቸው መልቀቅ ይጀምራሉ።

    የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ግጭት በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚጓጓዘውን የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ያስቆመና በቀጣናው የሚመረተው ነዳጅ ዘይት እንዲቀንስ ያደረገ ነው።

    ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ የተባለ ጭማሪ አሳይቷል።

    ነገር ግን የነዳጅ ክምችት ከቡድን ሰባት አገራት ሊለቀቅ እንደሚችል ከተዘገበ በኋላ አንዳንድ ባለሙያዎች እርምጃው የአጭር ጊዜ መፍትሄ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን በርሜል የነዳጅ ዘይት ሊለቅ ይችላል ተብሏል። ይህም ሩሲያ በ2022 መጀመሪያ ላይ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ወረራ ባደረገችበት ወቅት ከተለቀቀው በእጥፍ ይበልጣል።

    ይህ መጠን የሁለት ወይም የሦስት ቀን የዓለም አቀፍ ገበያ አቅርቦት አልያም ከሆርሙዝ ሰርጥ ለሁለት ሳምንት የሚጓጓዘውን የሚተካ ብቻ ነው።

    የቡድን ሰባት የኢነርጂ ሚኒስትሮች ረቡዕ ዕለት ከአይኢኤ ጋር ባደረጉት ስብሰባ በኋላ “በመርህ ደረጃ፣ ስትራቴጂካዊ ክምችቶችን መጠቀምን ጨምሮ ሁኔታውን ለመፍታት ቅድመ ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግን እንደግፋለን” ብለዋል።

    ሁሉም የዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ አባል አገራት ዓለም አቀፍ መስተጓጎል ቢከሰት ለ90 ቀናት የሚበቃ መጠባበቂያ ነዳጅ መያዝ ይጠበቅባቸዋል።

  19. በሆርሙዝ ወሽመጥ ሦስት የንግድ መርከቦች “ምንነቱ ባልታወቀ” ተወንጫፊ ተመቱ

    ሦስት የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታታቸውን እና ቢያንስ አንዱ በእሳት መያያዙን የዩናይትድ ኪንግደም ባሕር ንግድ መርከብ አስታወቀ።

    ይህ ጥቃት የፈጸመው አሜሪካ በአካባቢው በነበሩ በርካታ የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማ ማውደሟን ካሳወቀች ከሰዓታት በኋላ ነው።

    የዩኬ የባሕር ንግድ መርከብ ጨምሮ እንዳስታወቀው “ያልታወቀ ተወንጫፊ” የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የጭነት መርከቦች ከሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲወጡ ተደርጓል።

    አደጋው የደረሰው በኦማን እና ዱባይ አቅራቢያ ሲሆን፣ አንዱ መርከብ በእሳት መያያዙ ተገልጿል።

    በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ጥቃት ከደረሰባቸው መርከቦች መካከል አንዱ የታይላንድ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልብ ነው ተብሏል።

    የታይላንድ ባሕር ኃይል ባወጣው መግለጫ ላይ 23 ባሕረኞች በመርከቡ ላይ ነበሩ ብሏል።

    የኦማን ባሕር ኃይል 20 የመርከቡን ሠራተኞች ማትረፉን አስታውቆ፣ ሦስት አንደሚቀሩት አስታውቋል። ጥቃቱ የደረሰበትን ምክንያት ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

    በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንደተነገራቸውም አስታውቋል።

    በሁለቱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ከመድረሱ በፊት መጀመሪያ ጥቃት የደረሰበት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አቅራቢያ እየተንቀሳቀሰ የነበረ ኮንቴይነር ጫኝ መርከብ ነው።

    በመርከቡ ላይ ጉዳት ቢደርስም ሁሉም የመርከቡ ሠራተኞች በደህና ሁኔታ ላይ አንደሚገኙ ታውቋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በአንድ ወር ውስጥ 3000 ያህል የንግድ መርከቦች ይንቀሳቀሳሉ።

    በዓለም ላይ እጅግ በጣም አንቅስቃሴ የሚበዛበት የባሕር አካል የሆነው ይህ ክፍል ከመካለኛው ምሥራቅ አገራት ወደ እስያ እና አውሮፓ አገራት ነዳጅ የሚመላለስበት ዋነኛ መስመር ነው።

    በሆርሙዝ ሰርጥ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እንደሚመላለስ መረጃዎች ያሳያሉ።

    በአካባቢው የሚገኙት ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አምራች አገራት የኢራን፣ የኢራቅ፣ የኩዌት፣ የኳታር፣ የሳዑዲ አረቢያ እና የኤምሬትስ ግዙፍ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የያዙ መርከቦችን የሚያንቀሳቅሱት በዚህ ጠባብ የባሕር አካል ነው።

    እንደ ዩኬ የባሕር ንግድ መርከብ መረጃ ከሆነ እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ በአካባቢው የሚደረገው የመርከብ እንቅስቃሴ የቀነሰ ሲሆን፣ 13 ያህል መርከቦች ላይም ጥቃት ደርሷል።

    በዚህ ሳምነት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ አሻቅቦ ነበር።

  20. ትራምፕ ኢራን በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ መሳተፍ ትችላለች ማለታቸውን የፊፋ ፕሬዝዳንት አስታወቁ

    ኢራን በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ መሳተፍ እንደምትችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መግለጻቸውን የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አስታወቁ።

    የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ውስጥ ቢሆንም እንኳ ኢራን በዓለም ዋንጫ መሳተፍ እንደምትችል ትራምፕ ተናግረዋል ተብሏል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ሳምንት ያለፈ ሲሆን፣ ኢራንም የአጸፋ ጥቃት መፈጸም ቀጥላለች።

    የፊፋው ፕሬዝዳንት በኢንስታግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው ስለ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

    በሰሜን አሜሪካ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የኢራን ብሔራዊ ቡድን አልፏል።

    የፊፋው ፕሬዝዳንት “የኢራን ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ መሳተፍ እንደሚችል ትራምፕ በውይይታችን ወቅት ጠቅሰዋል” ብለዋል።

    ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ የኢራን ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።