ምዕራባውያን አሜሪካ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ማንሳቷን ተቹ
የአውሮፓ መሪዎች አሜሪካ ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልከው ነዳጅ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለጊዜው ለማላላት መወሰኗን ተቹ።
ይህ የአሜሪካ ውሳኔ አገራት በመርከቦች ላይ ተጭኖ ያለ ነገር ግን በማዕቀብ ምክንያት ያልተሸጠ የሩሲያ ነዳጅን እንዲገዙ ያስችላቸዋል።
የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ አርብ ዕለት"የአውሮፓን ደኅንነት ስለሚጎዳ" የአሜሪካ ውሳኔ "በጣም አሳሳቢ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
“የማዕቀቦቹ መላላት ሩሲያ ሀብቶቿን በዩክሬን ላይ ጦርነት ለማካሄድ ዳግም ታውላቸዋለች” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተናገሩት በዚህ እርምጃ ሩሲያ 10 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች ማለት ሊሆን ይችላል ሲሉ "ለሰላም አይረዳም" ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከዜሌንስኪ ጋር በመሆን የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱ "በምንም መልኩ" ማዕቀቡን ለማንሳት ምክንያት እንደማይሆን ተናግረዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ቀደም ሲል በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲናገሩ፣ የካናዳ አቋም "በሩሲያ ላይ የተጣሉትን ማዕቀቦች ማስቀጠል" እንደሆነ ተናግረዋል።
የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪሽ ሜርዝ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ ላይ ውሳኔውን "ስህተት" ብለዋል።