ቀጥታ, ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተመቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስታወቀች

በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ግጭቱ ካገረሸ በኋላ በመሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ አጸፋውን እንደምትመልስ እና እስራኤልም ከኢራን የአጸፋ ጥቃት እንደማትተርፍ የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት የበላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አስጠነቀቁ። ከማክሰኞ ጀምሮ የሚካሄደውን የአሜሪካንን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ባሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

  • ትራምፕ "የተኩስ አቁሙ አብቅቷል" ካሉ በኋላ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈፅሙ ዛቱ
  • መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያቋርጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ
  • በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች መመታታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈተች
  • ኢራን በ85 የአሜሪካ ዒላማዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች
  • የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በሶርያ ጉብኝት ላይ ሳሉ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ተጎዱ
  • የ325 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ የተቀበሉት የቻይና ባለሥልጣን ሞት ተፈረደየአሜሪካ ዛቻ እስከቀጠለ ድረስ ድርድር እንደማይጀመር የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን ገለጹ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል መስማማታቸውን፤ ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን ለኢራን እንዳረጋገጡላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።

    "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ድርድሩን እንድንቀጥል ጠይቀውናል። እኛም ይህንን ለማድረግ ተስማምተናል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    አክለውም "ነገር ግን አሜሪካ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን በማያሻማ ሁኔታ አሳውቃቸዋለች” ብለዋል።

    ለወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ሁለቱ አገራት ከሳምንታት በፊት የመግባቢያ ስምምነት ደርሰው ግጭቱ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ካላፈው ማክሰኞ ጀምሮ አሜሪካ በከፈተችው ጥቃት ጦርነቱ ዳግም ተቀስቅሷል።

    አሜሪካ እና ኢራን ድርድራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ትራምፕ ያሳወቁት ኳታር ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት አሸማጋዮችን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ ወደ ቴህራን ከላከች በኋላ ነው።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሲኤንኤን እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር ስትራቴጂ በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግጭቱ እንዳይባባስ ጋብ በማድረግ ለዲፕሎማሲያዊ ጥረት በር መክፈት ነው።

  2. የኻሜኒ ድረ ገጽ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ የመቃብር ቦታ ምሥል ይፋ አደረገ

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የመቃብር ሥፍራ

    የፎቶው ባለመብት, .

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ የኻሜኒ ድረ ገጽ የኢራንን እስላማዊ ሪፐብሊክ የቀድሞ መሪ የመቃብር ሥፍራን የሚያሳይ ምሥል ይፋ አደረገ።

    ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከሌሎች አራት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር ሐሙ ዕለት በሰሜን ምሥራቅ ኢራን ውስጥ በምትገኘው ቅዱስ ከተማ ማሻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ተፈፅሟል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ በመጀመሪያው ቀን የእስራኤል እና የአሜሪካ የተቀናጀ ጥቃት የተገደሉት ከአራት ወራት በፊት ነበር።

    ከእርሳቸውም ጋር በርካታ የኢራን ወታደራዊ እና የፖለቲካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ሴት ልጃቸው ቡሽራ ኻሜኒ፣ የልጅ ልጃቸው ዛህራ ሞሃመዲ፣ የልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ ሚስት ዛህራ ሃዳድ እና የልጃቸው ሆዳ ኻሜኒ ባል ኢስባህ ኡል ሃዳ ባጌሪ ተገድለዋል።

    በቀድሞው ጠቅላይ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የአገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናት የተገኙ ሲሆን እርሳቸውን የተካው ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ አልተገኘም።

    የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው ፕሬዝደንት ትራምፕ "ተኩስ አቁሙ አብቅቷል" ካሉ በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈተችው ጥቃት ለሁለተኛ ቀን በቀጠለበት ጊዜ ነበር።

  3. ኢራን መሠረተ ልማቶቿ ከተመቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስታወቀች

    አውሮፕላን ተሸካሚ የአሜሪካ የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከማክሰኞ ሌሊት ጀምሮ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ግጭቱ ካገረሸ በኋላ በመሠረተ ልማቶቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ አጸፋውን እንደምትመልስ እና እስራኤልም ከኢራን የአጸፋ ጥቃት እንደማትተርፍ የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት የበላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አስጠነቀቁ።

    ዋና ፀሐፊው ሞሐመድ ባቂር ዞልቃድር በአገሪቱ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው "ቀደም ሲል እንዳስታወቅነው በመሠረተ ልማቶቻችን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አጸፋን የሚያስከትሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ክፋቶች ጀርባ ያለው ወንጀለኛው ጽዮናዊ መንግሥትም ተዋጊዎቻችን ከሚፈጽሙት ጥቃት የሚያመልጥ አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ተኩስ አቁም አድርገው የነበሩት አሜሪካ እና ኢራን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ግጭት ተመልሰዋል።

    አሜሪካ፣ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ በሦስት መርከቦች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ሲያደርጉ ኢራን ግን አስተባብላለች።

    በመርከቦቹ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ አሜሪካ ከማክሰኞ ሌሊት ጀምራ ኢራን ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ስትፈጽም፣ ኢራን ደግሞ በፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

  4. ሜክሲኮ በአሜሪካ ይዞታ ሥር ሆነው የሞቱ ዜጎቿን በተመለከተ ክስ ልትመሠርት ነው

    በስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተገደለው ሎሬንዞ ሳልጋዶ አሩጆ ቤተሰቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተገደለው ሎሬንዞ ሳልጋዶ አሩጆ ቤተሰቦች

    ሜክሲኮ በአሜሪካ ይዞታ ሥር እያሉ የሞቱ ዜጎቿን በተመለከተ የወንጀል ክስ እንደምትመሠርት አስታወቀች።

    የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮቤርቶ ቬልሳኮ እንደተናገሩት ብዙ ዜጎቻቸው በአሜሪካ ይዞታ ሥር ሳሉ በመሞታቸው “የሕግ እርምጃ” ይወስዳሉ።

    በአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) ተይዘው የነበሩ 14 የሜክሲኮ ዜጎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ሦስት ተጨማሪ ዜጎቻቸው ደግሞ “በእስር ሒደት ላይ” መሞታቸውን ተናግረዋል።

    ሜክሲኳውያኑ መሞታቸው በአገሪቱ ካስነሳው ተቃውሞ በተጨማሪ ያለፈው ረቡዕ በአሜሪካ ሂዩስተን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድገዋል።

    የተቃውሞ ሰልፍ ከመካሄዱ አንድ ቀን አስቀድሞ ሎሬንዞ ሳልጋዶ አሩጆ የተባለ የሜክሲኮ ዜጋ በስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባልደረባ ተገድሏል።

    የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት (ዲኤችኤስ) በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ “አይስ [የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን] ሕገ ወጥ ሰውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ መኪና ለማስቆም ሞክሯል” ብሏል።

    ግለሰቡ የተገደለው “ከመያዝ ለማምለጥ ሲሞክር” እንደሆነም ገልጿል።

    ቤተሰቦቹ እንዳሉት ግን ሎሬንዞ ተተኩሶበት የተገደለው ወደ ሥራ እየሄደ ሳለ ነው።

  5. በስፔን ሰደድ እሳት ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ፣ 19 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም

    የእሳት አደጋ ሠራተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በደቡብ ስፔን፣ አንዳሉሲያ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት ምክንያት ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

    የግዛቱ አስተዳዳሪ ጁአናማ ሞሬኖ እንዳሉት 19 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

    በወደቀ የኤሌክትሪክ መስመር ምክንያት ሰደድ እሳቱ እንደተነሳ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስርጭቱን ለመቆጣጠር እየሞከሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    በደቡብ አውሮፓ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ የሙቀት ወጀብ መከሰቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሰደድ እሳት እያስከተለ ነው።

    በፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል እና ስፔን የእሳት አደጋ ሠራተኞች አደጋዎችን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

    በስፔን በሰደድ እሳት የሞቱ 11 ሰዎች አስከሬን ቤዳር በተባለች አነስተኛ መንደር ውስጥ ተገኝቷል። አብዛኞቹ ሰዎች የውጭ አገራት ዜጎች መሆናቸውን የግዛቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

  6. ቻይና በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሮኬት አስወነጨፈች

    ሎንግ ማርች 10ቢ የተባለው ሮኬት

    የፎቶው ባለመብት, China Aerospace Science and Technology Corporation

    ቻይና በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ሮኬት ማስወንጨፏ ተገለጸ።

    በአገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተመልክቷል።

    ዛሬ አርብ፤ ሎንግ ማርች 10ቢ የተባለው ሮኬት ከደቡባዊ ቻይና ሀይናን ተወንጭፎ ወደ ምድር መመለሱ ተገልጿል።

    አሜሪካ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች በማምረት በሕዋ ሳይንስ ያላትን ሥፍራ ቻይና መገዳደር የምትችልበት መንገድ ነው።

    የኢሎን መስክ ‘ስፔስ ኤክስ’ እና የጄፍ ቤዞስ ‘ብሉ ኦሪጅን’ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች ያመርታሉ።

    ሮኬቶች አንዴ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ መልሰው አገልግሎት እንደማይሰጡ ይታመናል።

    ከምድር ሮኬቶች ሲወነጨፉ ጉዳት ስለሚደርስባቸው እና በድጋሚ ጥቅም ላይ ስለማይውሉ የጠፈር መንኮራኩር መላክ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።

    ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ የሚያስችለው ክፍል ዳግመኛ ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል በከፍተኛ መጠን ወጪውን ይቀንሳል።

  7. የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአሜሪካ ጋር በማበሯ ዋጋ ትከፍላለች - ኢራን

    በዱባይ ከተማ የምሽት ሰማይ ላይ የሚታይ የኢራን ጥቃት የፈጠረው ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, Muskaan Kataria

    የምስሉ መግለጫ, ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ ኢታን ኤምሬትስን በሚሳዔሎች እና በድሮኖች በተደጋጋሚ አጥቅታለች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለወራት ጥቃት እየፈጸመች ካለችው አሜሪካ ጋር የምታደርገው ትብብር ዋጋ ያስከፍላትል ሲሉ አንድ የኢራን የምክር ቤት አባል ተናገሩ።

    በኢራን ፓርላማ ውስጥ የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚሽን አባል የሆኑት ኢስማኤል ኮዋሳሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አሜሪካ በአገራቸው ላይ እንደ አዲስ ከከፈተችው ጥቃት ጀርባ አለች ሲሉ ከስሰዋል።

    በዚህም ምክንያት አሜሪካ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት ኤምሬትስ “ከዋሽንግተን ጋር ባላት ትብብር የተነሳ ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ የባሕረ ሰላጤዋን አገር አስጠንቅቀዋል።

    አስማኤል በተጨማሪም በኢራን ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ "እየወሰደችው ባለቻቸው እርምጃዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኢራን ጠላቶች ጋር ተሰልፋለች፤ ለዚህም የሚያስከፍላት ዋጋ በጣም ከባድ እንደሚሆን ልታውቀው ይገባል” ብለዋል።

    የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ቀደም ሲል እንዳስታወቁት “ለወራሪ” ኃይሎች ማንኛውንም ድጋፍ የሚሰጥ ከኢራን የአጸፋ ቅጣት ይጠብቀዋል በማለት ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ የምክር ቤት አባሉ አጽንኦት ሰጥተው ጠቅሰዋል።

    ስለዚህም ኤምሬትስ በቀጣናው ያሉትን ለአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በምትሰጠው ድጋፍ ምክንያት “የባሕር እንቅስቃሴ መስመሯ፣ የባቡር እና የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶቿ እንዲሁም የነዳጅ እና የጋዝ ተቋማቷ የኢራን ጦር ሠራዊት እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ ዋነኛ ዒላማዎች ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቀዋል።

  8. ‘ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል አዲሱ የኢራን ዕቅድ’

    ትራምፕ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ከመድረግ ሲወርዱ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ፔንሲልቬኒያ ውስጥ ለተደረገባቸውን የግድያ ሙከራ ኢራን ላይ ጣታቸውን ይጠቁማሉ

    ኢራን ከወራት በፊት በተከፈተባት ጦርነት ጠቅላይ መሪዋን እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቷን የገደሉባትን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመበቀል አዲስ ዕቅድ ማውጣቷ ተዘገበ።

    ኢራን በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ግድያ ለመፈጸም አዲስ ዕቅድ ማዘጋጀቷን በተመለከተ እስራኤል ለአሜሪካ መረጃ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ዘግቧል።

    "የአሜሪካን መሪ፣ እኔን ሊገድሉ ይፈልጋሉ” እና “ስሜ በሁሉም ዝርዝራቸው ውስጥ ይገኛል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መረጃው እንዳሳሰባቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩን በይፋ አንስተው በተደጋጋሚ መናገራቸውን እንደሚያመልክት ጋዜጣው ዘግቧል።

    እስራኤል የኢራንን ዕቅድ በተመለከተ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጠችው መረጃ ከሁለት ዓመት በፊት ፔንሲልቬኒያ ውስጥ የተደረገባቸውን የግድያ ሙከራ የሚያካትት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱም መረጃውን ከደኅንነት ስጋት ባሻገር ለፖለቲካ ዓላማቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን አመልክቷል።

    የትራምፕ ተቺዎች መረጃውን ትራምፕ ከሕዝቡ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ነው ቢሉም፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በቀድሞው የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በነበሩት ጆን ቦልተን ላይ አድርጎታል የተባለው የግድያ ሙከራ በትራምፕም ላይ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

    ከአውሮፓውያኑ 1950 ወዲህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ላይ ከተፈጸመው ግድያ አንስቶ በትሩማን፣ በፎርድ እና በሬጋን ላይ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች ተፈጽመዋል።

    አንዳንዶች የግድያ ሙከራዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ጥቅም ላይ ይውላል ቢሉም ፕሬዝዳንት ትሩማን እና ፎርድ ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት ሲያሽቆለቁል፣ ሮናልድ ሬጋን ግን ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ ተቀባይነታቸው ጨምሯል።

  9. ኢራን እና አሜሪካ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ተዘገበ

    ኢራን

    የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / AFP via Getty Images

    ኳታር፣ ፓኪስታን እና ሌሎችም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ውይይት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተዘገበ።

    የአሜሪካው አክሲዮስ እንደዘገበው አሸማጋዮቹ አሜሪካ እና ኢራን እንደ አዲስ የገቡበትን ግጭት አቁመው ኒውክሌርን የተመለከተ ውይይት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

    አክሲዮስ በአሜሪካ እና በአሸማጋዮቹ አገራት የሚገኙ ሁለት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ውይይቶች እንዲቀጥሉ ጥረቶች ተጀምረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስትያ ከኢራን ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም የተኩስ አቁሙ “አብቅቶለታል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ተመልሰዋል።

    ትራምፕ ትኩረታቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ገልጿል።

    አክሲዮስ እንደዘገበው ትራምፕ አሁንም ቢሆን የለየለት ጦርነት ውስጥ ተመልሰው መግባት አይፈልጉም።

    የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በኩዌት፣ በባሕሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሙን ገልጿል።

  10. የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዋና ዋና ክስተቶች

    በአሜሪካ ጥቃት የተመታ የባሕር ዳርቻ

    የፎቶው ባለመብት, Mehr News Agency

    አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት መመለሳቸው መካከለኛው ምሥራቅን በውጥረት ሞልቶታል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ከባድ የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ያሳለፍነው ማክሰኞ ነው።

    የኢራን የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ እና ረቡዕ በተፈጸሙ ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።

    ረቡዕ እና ዛሬም ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። የግጭቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

    • የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
    • የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ የመቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ።
    • በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ሃዲድ በተዘረጋበት ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን የኒውክሌር ማብላያ ላይ ዛሬ ከሰዓት ጥቃት መፈጸሙን ዘግበዋል።
    • ኢራን በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።
    • ባህሬን ከኢራን የተሰነዘሩባትን ጥቃቶች ማክሸፍ መቻሏን ስትገልጽ፤ በኩዌት በተተኮሰ የሚሳዔል ስብርባሪዎች አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
    • የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ 10 ሚሳዔል መተኮሱን ገልጿል። ዮርዳኖስ በበኩሏ ስምንት ሚሳዔሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
    ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ መቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Instagram

    የምስሉ መግለጫ, ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ መቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ
    በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim

    የምስሉ መግለጫ, በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል
  11. የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን እንደምትከላከል አስታወቀች

    አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    ለተከታታይ ሁለት ቀናት በአሜሪካ ጥቃት የተሰነዘረባት ኢራን ጥቃቱ የሚቀጥል ከሆነ እራሷን የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ በተከታታይ በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት “በጽኑ የሚወገዝ” መሆኑን አመለክተዋል።

    ጥቃቶቹን ከሳምንታት በፊት ባለፈው ሰኔ ወር በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነትን የሚጥስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት ዋነኛ አሸማጋይ ለሆኑት ለፓኪስታኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እንደተናገሩት “የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን ትከላከላለች” ብለዋል።

    በተጨማሪም አራግቺ ከኦማን እና ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ አገራት በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

  12. አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት ሲመለሱ፣ ኢራናውያን አደባባይ ወጥተው የኻሜኒን ቀብር እየፈጸሙ ነው

    በማሻድ አደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለሁለተኛ ቀን የምትፈጽመው ጥቃት በቀጠለበት እና ኢራን የአጸፋ እርምጃ በጎረቤቶቿ ላይ እየወሰደች ባለበት በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የመጨረሻ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

    ላለፉት ቀናት በተለያዩ አገራት እና ከተሞች ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ወደ ትውልድ ከተማቸው ማሻድ ተወስዶ ዛሬ ግብአተ መሬቱ ይጠናቀቃል።

    በሰሜን ምሥራቃዊ ኢራን ውስጥ በምትኘው ቅዱስ ከተማ ማሻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ጎዳናዎች በሐዘንተኞች መጨናነቃቸው ተዘግቧል።

    የካቲት ወር ማብቂያ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱበት የመጀመሪያ ዕለት የተገደሉት ኻሜኒ የስንብት እና ቀብር ሥነ ሥርዓት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

    በማሻድ ጎዳና ላይ የተሰበሰቡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በማሻድ አደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  13. የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሩ ሥር መሆኑን አስታወቀ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አስታወቀ።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት “በቁጥጥሩ ሥር እንዳዋለ” እና በቀጣይ ሁለት ሳምንታት “ቀስ በቀስ” መተላለፊያው እንደሚከፈት ይፋ አድርጓል።

    ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ታስኒም የዜና ምንጭ እንደዘገበው፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለው እንቅስቃሴ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር “ወደ 50 በመቶ እንደሚደርስ" ተገልጿል።

    ከኢራን “ፈቃድ ያገኙ” መርከቦች እንቅስቃሴ “እየጨመረ” መሆኑን አስታውቋል።

    “የውጭ ኃይሎች በዚህ መሬት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መብት እንደሌላቸው በድጋሚ እንገልጻለን” ሲል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ተናግሯል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት “አውዳሚ ምላሽ የሚያስከትል” ነው ሲልም አስጠንቅቋል።

    የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋ ባገኘው መረጃ መሠረት ትናንት ረቡዕ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል 23 መርከቦች አልፈዋል።

  14. ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ አሜሪካ “ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች ስትል አሜሪካን ከሰሰች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት አሜሪካ ሰኔ ላይ የተፈረመው እና ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ያስገኘው የመግባቢያ ስምምነት ክፍሎች ላይ “ግልፅ ጥሰት” ፈጽማለች ሲል ከሰሰ።

    “ወታደራዊ ዘመቻዎች በአስቸኳይ እና በቋሚነት እንዲቆሙ” የጠየቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “የሚደረግ የንግድ መርከቦች ጉዞን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቻላትን እንደምታደርግ” ገልጿል።

    ሁለቱ ወገኖች የመግባቢያ ስምምነቱን የሚተረጉሙበት መንገድ የዚህ ግጭት ቁልፍ የውጥረት ምንጭ ሆኗል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አሜሪካ በወሽመጡ “ትዕዛዝ ባላከበሩ በርካታ መርከቦች ጋር ተፈጽሟል ለተባለ ክስተት” ምላሽ እሰጣለሁ በሚል “ሐሰተኛ ምክንያት” ጥቃት እንደፈጸመች በመግለጽ ከስሷል።

    አሜሪካ ከዚህ ቀደም ኢራን በወሽመጡ የሚጓዙ ሦስት መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም “የተኩስ አቁሙ ላይ ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች የሚል ክስ አቅርባ ነበር። ኢራን መርከቦቹ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን መሪዎች “ዋልጌ” በማለት “ያልተገራ ንግግር” አድርገዋል በማለት ወቅሷል።

    በተጨማሪም አሜሪካ ሁለት የባቡር ድልድዮችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ዒላማ በማድረግ "ከባድ የጦርነት ወንጀል" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

  15. በአሜሪካ የሁለት ቀናት ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች

    አሜሪካ በሁለቱ ቀናት ጥቃት 170 ዒላማዎችን መምታቷን አስታውቃለች

    የፎቶው ባለመብት, centcom

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በሁለቱ ቀናት ጥቃት 170 ዒላማዎችን መምታቷን አስታውቃለች

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ኢራን ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 78 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከሳምንታት በፊት የተኩስ አቁም እንዲደረስ ያደረገው የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው የነበሩት አሜሪካ እና ኢራን ከማክሰኞ አንስቶ በተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የፈጸመችው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ በነበሩ ሦስት ጭነት መርከቦች ተመትተዋል በሚል ነበር። ኢራን በምላሹ የባሕረ ሰላጤው አገራትን አጥቅታለች። ይህ የጥቃት ምልልስ ትናንትም ረቡዕ ሌሊትም ቀጥሏል።

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት በኢራን አምስት ግዛቶች ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆስኒ ኬርማንፑር ገልጸዋል።

    በእነዚህ ጥቃቶች 14 ሰዎች ተገድለው፤ 78 ሰዎች እንደሰቆሉ ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። ከቆሰሉት ውስጥ 47 ያህሉ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በደቡባዊ ኢራን የሚገኘው ኢራንሻህር ግዛት ገዥ በበኩላቸው አሜሪካ የአየር ማረፊያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን አስታውቀዋል።

  16. የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ይጠናቀቃል

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን አስከሬን የያዘው አውሮፕላን ማሻድ ከተማ ሲደርስ

    የፎቶው ባለመብት, IRIB

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን አስከሬን የያዘው አውሮፕላን ማሻድ ከተማ ሲደርስ

    ላለፉት ሰባት ቀናት ኢራን እና ኢራቅ ውስጥ የስንብት ሥነ ሥርዓታቸው ሲካሄድ የነበረው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን የኢራን ቅዱስ ከተማ ወደምትባለው ማሻድ ደረሰ።

    ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በዋና ከተማዋ የተጀመረው የኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሐሙስ የትውልድ ከተማ የሆነችው ማሻድ ውስጥ ይጠናቀቃል።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የመጨረሻው የቀብር ሥነ ሥርዓት ማሻድ ውስጥ ከሰዓት በኋላ የሚከናወን ይሆናል።

    ለስድስት ቀናት በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ ከተሞች ውስጥ ለሕዝባዊ ስንብት ሲዘዋወር የቆየው የኻሜኒ አስከሬን ባለሥልጣናት እና በሚሊዮኖች የሚቆተሩ ሐዘንተኞች በተገኙበት የሽኝት ሥነ ሥርዓቶች ተካሂዶለታል።

    በዋና ከተማዋ ቴህራን በተካሄደው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ከበርካታ አገራት የመጡ ባለሥልጣናት እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

  17. ኢራን የአሜሪካን ሚሳዔል፣ የሳተላይት መገናኛ እና የነዳጅ ማከማቻ መምታቷን አስታወቀች

    የኢራን ድሮን

    የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

    የአሜሪካንን ጥቃት ተከትሎ የኢራን ሠራዊት በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎችን በድሮን ጥቃት ዒላማ ማድረጉን አስታወቀ።

    በዚህም ኩዌት የሚገኝ የአሜሪካ የፓትሪየት ሚሳዔል ማዕከል፣ ኳታር ውስጥ የሚገኝ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት የሆነ አንቴና፣ እና ባህሬን ውስጥ ያሉ የአሜሪካ የነዳጅ ማከማቻ ማዕከል “ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የተለያዩ ዓይነት” ድሮኖች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አመለክቷል።

    “በቀጣናው ውስጥ ባሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ” ሠራዊቱ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ተከታይ መሆኑን መሆኑን በማመልከት ግለጽ ቀጣይ መሆኑን ገልጿል።

    የኢራን ጦር ኃይል መግለጫ የአገሪቱን መንግሥታዊ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በበርካታ የኢራን የዜና ምንጮች በኩል እንዲሠራጭ ተደርጓል።

    ቀደም ሲል ባህሬን፣ ኩዌት እና ኳታርን ጨምሮ በርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

  18. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኩዌት እና ባህሬን ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    ለሁለተኛ ተከታታይ ቀን አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኩዌት እና ባህሬን ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

    አሜሪካ ሌሊቱን የፈጸመችው የአየር ጥቃት መጠናቀቁን ስትገልጽ፤ የአጸፋ ጥቃት የወሰደው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሰነዘረው “ስምምነት በጣሰችው አሜሪካ ላይ የመጀመሪያ ዙር የቅጣት እርምጃ” መሆኑን ጠቅሷል።

    አሜሪካ ጥቃቷን የምትቀጥል ከሆነ በቀጣናው ያሏትን ሌሎች የጦር ሰፈሮች ዒላማ በማድረግ ጥቃቱን እንደሚያሰፋም አስጠንቅቋል።

    አሜሪካ ኢራን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው ሌሊቱን ሲሆን ኢራንም በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በሚገኙ አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት አድርሳለች።

    በአሜሪካ ጥቃት የኢራን ደቡባዊ የወደብ ከተማ የሆነችው ቻባሃር ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት እንደተፈጸመባት ተዘግቧል።

    ታስኒም የተባለው የኢራን ዜና ወኪል እንደዘገበው ወደ አስር የሚደርሱ ፍንዳታዎች በቻባሃር እና ኮናራክ ከተሞች ውስጥ ተሰምቷል። በቻባሃር ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ኤሌክትሪክ መቋረጡንም ዘግቧል።

    የባህሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የአየር ጥቃት ደወል በአገሪቱ መሰማቱን እና ዜጎች ተረጋግተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የአደጋ መጠለያ ቦታዎች እንዲገቡ በኤክስ ላይ መልዕክት አስተላልፏል።

  19. አሜሪካ በኢራን አዲስ ዙር ጥቃት ስትከፍት፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤ አገራትን አጠቃች

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኃይልን እንመታቸዋለን" በማለት ከተናገሩ በኋላ፤ የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተ።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የወደብ ከተሞች የሆኑትን ሲሪክን እና ባንደር አባስን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍሎች ፍንዳታ መከሰቱን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ትራምፕ ከአዲሱ ጥቃት በኋላ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ይህ ትናንት በኢራን ለተፈጸመው የመርከቦች ድብደባ የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ ነው። በድጋሚ ከተፈጠረ፤ ከዚህም የባሰ ይሆናል” ብለዋል።

    ከአሜሪካ እርምጃ በኋላ የባህረ ሰላጤው አገራት በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል። በባህሬን ዋና ከተማ መናማ ፍንዳታዎች መከሰታቸው የተገለጸ ሲሆን ኩዌት ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ማክሸፏን አስታውቃለች። ኳታር የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

    የኢራን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የፓርላማው አፈ ጉባኤ ሞሀማድ ባገር ጋሊባፍ፤ ዋሽንግተን “ጉልበተኝነት እና ቃል ኪዳንን ማጠፍ ዋጋ የማያስከፍሉ አለመሆናቸውን አሁንም አልተማረችም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    "በግልጽ ላስቀምጠው፤ ካጠቃችሁ፤ ትመታላችሁ” ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚከፈተው ኢራን በምትዘረጋው አሰራር እንጂ "በአሜሪካ ዛቻ" እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “የኢራንን በንግድ መርከቦች እና በንጹኃን ሲቪል ባሕርተኞች ላይ ጥቃት የማድረስ አቅም ይበልጥ ለማዳከም” እንደሆነ አስታውቋል።

    ዕዙ ባወጣው መግለጫ በኢራን የሚገኙ 90 ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል። በኢራን የባሕር ዳርቻ የሚገኙ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች እና የወታደራዊ ሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶች ጥቃት ከደረሰባቸው ዒላማዎች መካከል እንደሆኑም አስታውቋል።

    ዕዙ፤ “የአሁኖቹ ጥቃቶቹ ትናንት ምሽት የታዩትን ስኬታማ የማጥቃት እርምጃዎች የተከተሉ ናቸው” ብሏል።

    ኮናራክ እና ቻባሃር የተባሉ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል።

    የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጸው ባንደር አባስ ከተማ ውስጥ ስምንት ፍንዳታዎች ተከስተዋል። በደቡብ ኢራን የሚገኙት ሲሪክ እና ጃስክ ወደቦች ደግሞ በሁለት ሚሳዔሎች መመታታቸውን ገልጿል።

    ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚወዛገቡበት አቡ ሙሳ ደሴትም ሁለት ጊዜ ጥቃት እንደደረሰበት ተዘግቧል።

    የአሜሪካ ጥቃቶች ያደረሱት የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጂ ቻባሃር ውስጥ የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠመ እና ቡሸህር ውስጥ በሚገኝ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጦር ሰፈር እሳት መነሳቱን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

    አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, centcom

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት
    አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, centcom

    የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት
  20. አሜሪካ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ትራምፕ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ዛሬ ምሽት በኢራን ላይ በድጋሚ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ተናገሩ።

    ትራምፕ ይህን ያሉት በኔቶ ጉባኤ ላይ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።

    በመግለጫው ላይ ኢራንን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ባለፈው ምሽት በከባዱ መትተናቸዋል፤ በጣም በጣም በከባዱ” ያሉ ሲሆን፣ አገራቸው ምናልባት ዛሬ ምሽት በድጋሚ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ተናግረዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም "ትንሽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻቸዋለሁ፤ ዛሬ ማታ በድጋሚ በከባዱ እንመታቸዋለን” ብለዋል።

    በኢራን ደስተኛ እንዳልሆኑ የገለፁት ትራምፕ፣ ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያ መታጠቅ እንደማይፈቀድላት አሜሪካ ያላትን አቋም ደግመው ገልጸዋል።

    ትራምፕ “ሙሉ ጉዳዬ ስለአገዛዝ ለውጥ አይደለም” ሲሉም የአገሪቷን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማስቆም የሚያስችሉ ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን አክለዋል።

    “ኢራን ከዚህ በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል አይደለችም” ሲሉም የኢራንን አስተዳደር አጣጥለዋል።