ቀጥታ, ትራምፕ “የተኩስ አቁሙ አብቅቷል” ካሉ በኋላ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈፀም ዛቱ

አሜሪካ በኢራን ውስጥ ጥቃቶችን ከፈጸመች እና ኢራን በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን ካሳወቀች በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ‘ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና እየገነባን ነው’

    የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ቀውስ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን “የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ” ሲሉ ገልፀውታል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት “የሻዕቢያን” ተልዕኮ እያስፈፀመ ያለ፤ ‘የራሱ ዓላማ የሌለው’ “መጥረቢያ” ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    “ኢትዮጵያ የሰላሟ መድፍረስ ምንጭ የት እንደሆነ ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳው ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና በመፍጠር ላይ የምንገኝ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት መግለፅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱን አንድነት እና ሉዓዊነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ “ማንኛውም ነገር ከመጣ” መከላከል የሚያችል ቁመና አለን ብለዋል።

    የውጭ ተልዕኮ አስፈፃሚ ብለው ያመለከቷቸው የአገር ውስጥ ኃይሎችን “ጉዳቱ የጋራ ስለሚሆን...መታገስ እና ማስተማር” ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።

  2. "የትግራይ ወጣቶች እያታፈሱ ወደ ሱዳን ጦርነት ተወስደዋል"

    ጠ/ሚ ዐቢይ

    የፎቶው ባለመብት, PMO

    የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ “አሸናፊ እና ተሸናፊ እኩል ቁጭ ብለው የተደራደሩበት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

    በትግራይ ወጣቶች “በጉልበት ታፍሰው ወደ ሱዳን ጦርነት ተወስደዋል” ያሉት ዐቢይ “በማያውቁት ጉዳይ ሕይወታቸውን እያጡ ነው” ብለዋል። አያይዘውም የትግራይ ሕዝብ በክልሉ ካለው አንጻር “በደሴ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር. . .” በሰላም ወጥቶ መግባት ይችላል ብለዋል።

    ይሄንኑ ንጽጽር ለአማራ ክልል እና ለኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ተጠቅመው “ዜጎች በገዛ ቀዬአቸው እየታመሱ ነው” ብለዋል።

    “ከቀዬ ሸሽቶ መኖር የተሻለ ሰላም የሚሰጥ” ሆኗል ሲሉ አክለዋል። “ትግራዋይ እና ኢትዮጵያዊ የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ ሆኗል” ሲሉም የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ገልጸዋል።

  3. ተፎካካሪዎች “በነፃነት እንዲያሸንፉ” 15 በመቶ ወንበሮችን ተለቅቋል

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ታይቶ የማይታወቅ” በሚል አሞካሽተውታል።

    በዘንድሮው ምርጫ ፓርቲያቸው ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ አግኝቶ ያሸነፈ ሲሆን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች “ተጭበረበረ ወይም መንግሥት በኃይል ወሰደ በማይሉበት ሁኔታ ብቻቸውን ይወዳደሩ” ብለው 15 በመቶ በሚሆኑ ወንበሮች እንደለቀቁ አስታውቀዋል።

    በ85 በመቶ ወንበሮች አለመወዳደራቸውን “ለዲሞክራሲ ቀናኢነት” ሲባል የተደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በፓርላማ 15 በመቶ አልወዳደርም የሚል ፓርቲ በድፍን አፍሪካ መኖሩን እጠራጠራለሁ” ሲሉ ዮፓርቲያቸውን ውሳኔ አሞካሽተዋል።

    “ብዙ ድምፆች እንዲገቡ ፍላጎት ነበር፤ ብዙ ሰዎች እንዲሳተፉ ፍላጎት ነበር” ሲሉ ገዢው ፓርቲ በፈቃደኝነት ወንበር መልቀቃቸውን ምክንያት አድርገው አቅርበዋል።

    ፓርቲያቸው ሳይፎካከራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዳደርረው እንዲያሸንፉ የተነደፈውን እቅድ “ወጣ ያለ ውሳኔ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሉታዊ ጎኑ ሳይሆን በአዎንታዊ መልኩ “ታይቶ አይታወቅም” ብለዋል። “15 በመቶ [ወንበር] ይቅርብን ያልነው ጉዳይ ብዙ ድምፅ ለመስማት ስለሆነ የብልፅግና ፓርቲ አባላት እንደዚህ ባለው ወጣ ያለ ውሳኔ አካል በመሆናችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል” ብለዋል።

  4. ግጭቶችን በተመለከተ

    ግጭትን በተመለከተ- ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶች እና ሰላም ማጣትን በተመለከተ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ “ታፍነው የቆዩ” ያሏቸው ችግሮች በማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች መስፋፋቱን ጠቅሰዋል።

    ነገር ግን አሁን ላይ “በሕዝብ እና ሕዝብ” “በሃይማኖት እና ሃይማኖት” መካከል የሚስተዋል ግጭት “እንደቀነሰ” ተናግረው ግጭቶች “በብሔር መካከል” መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በድርድር ወደ ሰላም የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ “የተቀሩትም ይመለሳሉ” ብለው እንደሚያኑ ገልጸዋል።

  5. ብልፅግና ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ አለመቆየት

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ “ምርጫው ዒላማ ሆኖ ነበር” ብለዋል።

    ሕዝቡ “ጥይት ሳይፈራ” ድምጽ እንደሰጠ ጠቅሰው፤ ምርጫውን ስላሸነፈው ፓርቲያቸው ብልጽግና ሲናገሩም “15 በመቶ አልወዳደርም የሚል ፓርቲ እንደሌለ” ተናግረዋል።

    ገዢ ፓርቲ ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ እንዳይቆይ ማድረግን እንደሚደግፉ አክለዋል።

  6. የኻሜኒ ገዳዮች ላይ “የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ” ኢራናውያን ጠየቁ

    የኻሜኒ ቀብር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒን የቀብር ሥነ ሥርዓት በርካቶች በቴህራን ታድመዋል።

    በመዲናዋ የሚካሄደው የሦስት ቀናት ሕዝባዊ ሐዘን ከኢማን ሑሴን አደባባይ ተነስቶ በአዚዲ አደባባይ አድርጎ በማዕከላዊ ቴህራን ተከናውኗል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሐዘንተኞች የአገሪቱን አውራ ጎዳናዎች ሞልተዋል።

    የኢራንን ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁም በቀልን የሚወክለውን ቀይ ጨርቅ አውለብልበዋል።

    “መነሳት አለብን” እያሉ ድምጻቸውን ያስተጋቡም ነበሩ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዲገደሉ በአደባባይ ተጠይቋል።

    የትራምፕ ፎቶ የሚታይባቸው ቢልቦርዶች ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ ሐዘንተኞች ታይተዋል።

    “አሜሪካ አባታችንን ገድላለች፤ አንለቃችሁም!” የሚለው ከመፈክሮቹ አንዱ ነው።

    የ22 ዓመቷ የዩኒቨርስቲ ተማሪ መላይካ ኖውሪን “እዚህ የተገኘሁት በክብር እና በኩራት ነው። ምን ያህል እንደምንወዳቸው እና ለሕዝቡ፣ ለኢስላሚክ ሪፐብሊኩ እንዲሁም ለሥርዓቱ ምን ያህል ታማኝ እንደሆንን ለማሳየት ነው” ስትል ለኤኤፍፒ ተናግራለች።

    ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን በኤክስ ገጻቸው “ኻሜኒ ለመላው ኢራናውያን ያስተማሩት የአገሪቱ ትልቅ ሃብት ሕዝቡ እና አንድነት መሆኑን ነው” ብለዋል።

    “ኢራናውያን የአገሪቱን ክብር፣ እድገት እና ታላቅነት ያስቀጥላሉ” ሲሉም ገልጸዋል።

  7. ትራምፕ በቀይ ካርድ ስለተቀጣው ተጫዋች ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸውን አረጋገጡ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ (ፎቶ ፋይል)

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸው ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በቀይ ካርድ ምክንያት የተጣለበትን የአንድ ጨዋታ ቅጣት እንዲያጤነው ፊፋን መጠየቃቸውን አረጋገጡ።

    የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ በአሜሪካው አጥቂ ፎላሪን ባሎገን ላይ የተጣለውን እገዳ ማንሳቱ “ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ያሉት ትራምፕ ውሳኔው ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ በውድድሩ ላይ “ከፍተኛ ጠባሳ” ይጥል ነበር ብለዋል።

    በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ተጫዋች ቀጣይ ጨዋታ እንዳይሰለፍ ቅጣት የሚጣልበት ቢሆንም ፊፋ ባልተለመደ ሁኔታ የአሜሪካዊውን ተጫዋች ቅጣት ለ12 ወራት ተግባራዊ እንዳይሆን አግዶታል።

    ጉዳዩን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ዋይት ሐውስ ውስጥ እንደተናገሩት ቀይ ካርድ የተሰጠበት ድርጊት “ጥፋት ነው ብለው” ባለማመናቸው ፊፋ ቅጣቱን እንዲያጤነው ጠይቀዋል።

    ትራምፕ ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር መነጋገራቸውን አረጋግጠው፤ በተጫዋቹ ላይ የተጣለው ቅጣት እንዲታገድ ሳይሆን ውሳኔው እንደገና እንዲታይ መጠየቃቸውን ብቻ ነው ያመለከቱት።

    ትራምፕ ለተጫዋቹ ቀይ ካርድ መሰጠት የሌለበት አጋጣሚ እንደነበር እና ጨዋታውን የመሩትን የብራዚላዊን ዳኛ ውሳኔ “አስቀያሚ” በማለት ለተፈጠረው ችግርም ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።

    ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቀው የፊፋ ውሳኔ ከአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበር፣ ከቤልጂየም እና የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከበርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ከባድ ትችት ገጥሞታል።

    አሜሪካዊው ተጫዋች ጥፋቱን የፈጸመው ብሔራዊ ቡድኑ ከቦሲኒያ ኤርዜጎቪና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ሲሆን፣ አሜሪካ ወሳኝ ተጫዋቿን በቀይ ካርድ ብታጣም ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለቀጣይ ጨዋታ አልፋለች።

    ለአሜሪካ ከፍተኛውን ግብ በማስቆጠር ተጠባቂ የሆነው ፎላሪን ባሎገን በጨዋታው በቀይ በመውጣቱ ነገ ማክሰኞ ከቤልጂየም ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፍ ታውቆ ነበር።

    ነገር ግን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ፊፋ የቀይ ካርድ ቅጣቱን ተግባራዊነት በማገዱ አሜሪካ ከቤልጂየም ጋር በሚኖራት ወሳኝ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል አግኝቷል።

  8. “ስምምነት ላይ እንደርሳለን አልያም የጀመርነውን እንጨርሳለን”- ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር “ስምምነት ላይ እንደርሳለን አልያም የጀመርነውን ሥራ እንጨርሳለን” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ቢዘጋም የነዳጅ ዋጋ ብዙም እንዳልጨመረ ተናግረዋል።

    “ነዳጅ በብዛት ወስደንባቸዋል። ማንም አላወቀም፤ ይሄ የሆነው በአንድ ወር ተኩል ነው” ብለዋል።

    የኢራንን ባሕር ኃይል እና አየር ኃይል ማውደማቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።

    “መቆጣጠሪያ ሥርዓት እንደሌላቸው አውቀዋል። መቆጣጠሪያ ሥርዓታቸው ስለወደመ በምሽት ዒላማ አድርገናቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

    ትራምፕ “ጉልበተኛው ባሕር ኃይላችን ማንም አይቶት የማያውቅ እገዳ ጥሏል። ለሁለት ወር አንድም መርከብ አላለፈም። ለስምምነት ስንቃረብ እገዳውን አላልተናል። ስምምነት ላይ እንደርስ ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

    “ዞሮ ዞሮ እናሸንፋለን። ወይ እንስማማለን ወይም ሥራውን እንጨርሳለን” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

    91 ሚሊዮን የኢራን ሕዝብ “እንዲጎዳ ስለማይፈልጉ” ስምምነት ላይ መድረስን እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

  9. የአሜሪካዊው የቀይ ካርድ ቅጣት ተግባራዊ አለመሆን ከባድ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

    ፎላሪን ባሎገን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ዋነኛ ግብ አስቆጣሪ ፎላሪን ባሎገን

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ የተቀለበሰው የቀይ ካርድ ቅጣት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ላይ ከባድ ተቃውሞ ቀስቅሶበታል።

    ፊፋ የአሜሪካዊውን የቀይ ካርድ ቅጣት ማንሳቱ የእግር ኳስ ጨዋታ ተአማኒነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት የአውሮፓ አገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዩኤፋ ተቃውሟል።

    አሜሪካ ከቦሲኒያ ኤርዜጎቪና ጋር በነበራት ጨዋታ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ የተሰናበተው አሜሪካዊ ተጫዋች ፎላሪን ባሎገን አገሩ ከቤልጂየም ጋር ማክሰኞ በምደታርገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ መሰለፍ አይችልም ነበር።

    ይህንን ውሳኔ የአውሮፓ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “ያልታየ፣ ለመቀበል አስቸጋሪ እና ምክንያታዊ ያልሆነ” በማለት ፊፋ በውሳኔው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ቅጣቱን ማገዱ “ቀይ መስመር ያለፈ” ነው ሲል ተችቶታል።

    የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ ለአሜሪካ ዋነኛ ግብ አስቆጣሪ በሆነው ተጫዋች ላይ የተላለፈውን የቀይ ካርድ ቅጣት ወዲያውኑ ተግባራዊ እንዳይሆን በማድረግ በቀጣዩ ወሳኝ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሮለታል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ቴሌቪዥን እንዳረጋገጠው ተጫዋቹ በቀጣይ ግጥሚያ ላይ እንዲሰለፍ የሚያደርገው ውሳኔ የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

    ከዚያም በኋላ እሁድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ትልቅ ኢፍትሐዊነት” ያሉት የቀይ ካርድ ቅጣት “በመቀልበሱ” ፊፋን አመስግነዋል።

    ማክሰኞ ከአሜሪካ ጋር የሚገጥመው የቤልጂየም እግር ኳስ ማኅበር የፊፋን ውሳኔ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አሜሪካዊው ተጫዋች በቀጣይ ግጥሚያ ላይ እንዲሳተፍ በመፈቀዱ “መገረሙን” ገልጿል።

    የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ፕሪቮት “ለዚህ ተቀባይነት ለሌለው ውሳኔ ስልክ መደወል ምክንያት ከሆነ፣ የእግር ኳስን እና የስፖርትን መሠረታዊ ደንብን በግልጽ መጣስ ነው” በማለት ተቃውመዋል።

    ከሙስና ጋር በተያያዘ በአሁኑ የፊፋ ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ከ10 ዓመት በፊት የተተኩት ሴፕ ብላተር በኤክስ ላይ ጉዳዩን በተመለከተ “እግር ኳስ የፖለቲካ ኃይል የመጫወቻ ሜዳ ፈጽሞ መሆን የለበትም” ሲሉ ጽፈዋል።

    የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ሲያገኝ ቀጣይ ጨዋታ ላይ እንዳይሰለፍ የሚጣለው ቅጣት “በፍላጎት የሚፈጸም ምርጫ ሳይሆን ደንብን መሠረት ደያረገ መርኅ ነው” ብሏል።

    የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር እና ፊፋ ባለፉት ወራት በበርካታ ጉዳዮች ሲወዛገቡ የቆዩ ሲሆን፣ ሶማሊያዊው ዳኛ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ሲከለከል ማኅበሩ ተቃውሞውን ለማሳየት ዳኛው የአውሮፓ ጨዋታን እንዲዳኝ ጋብዞታል።

  10. ሐማስ በጋዛ ያለውን አስተዳደር ማፍረሱ ተገለጸ

    የፈራረሱ ሕንጻዎች በጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት አብዛኛው የጋዛ ክፍል ከባድ ውድመት ደርሶበታል

    ሐማስ ላለፉት ሁለት አሥርታት የነበረውን የጋዛ አስተዳደር ማክሰሙ ተገለጸ። ውሳኔው በጋዛ ሰርጥ የሲቪል አስተዳደር ለመዘርጋት መንገድ የሚከፍት ፖለቲካዊ እርምጃ ነው ተብሏል።

    ሐማስ በአውሮፓውያኑ 2007 ከፋታህ ፓርቲ የጋዛ ሰርጥ አስተዳደርን ከተረከበ አንስቶ በአመራር ላይ ይገኛል። ቀደም ብሎም የፍልስጤም የምክር ቤት ምርጫንም አሸንፏል።

    ሐማስ እና እስራኤል ባለፈው ጥቅምት የተኩስ አቁም ላይ ከደረሱ ወዲህ ሐማስ ከጋዛ ሰርጥ የዕለት ከዕለት አስተዳደር ለመውጣት ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። የሐማስ የትጥቅ መፍታት ጉዳይ ግን እስካሁን እልባት አላገኘም።

    የሐማስ አስተዳደር የመረጃ ክፍል ኃላፊ ለኤኤፍፒ “የአስተዳደሩ የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ ኃላፊ መሐመድ ፋራ በይፋ መልቀቂያ አስገብተዋል” ብለዋል።

    “ለጋዛ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማስተላለፍም ኮሚቴውን ለማፍረስ ተወስኗል” ሲሉም አክለዋል።

    የጋዛ ብሔራዊ አስተዳደር ኮሚቴ አሁን መቀመጫውን ካይሮ ያደረገ ሲሆን፤ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ኮሚቴ የተቋቋመ ነው።

    የትራምፕ የሰላም ልዑካን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2025 የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማሸማገላቸው ይታወሳል።

    የሐማስ ቃል አቀባይ “ሐማስ አዲስ በወሰደው እርምጃ መሠረት ከዚህ በኋላ የጋዛ ሰርጥን በማስተዳደር ኃላፊነት ውስጥ የለበትም። ይህም ለወራሪዎቹን እና ለማጥፋት ዘመቻቸው ሰበብ ላለመስጠት ነው” ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

  11. በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ያለው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሽኝት

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥን

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጀመረው እና በቀጣይ ቀናትም የሚካሄደው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ቀጥሏል።

    ኻሜኒ ከአብዮታዊዋ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን መሪነታቸው በተጨማሪ በሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው መሪ ነበሩ።

    የቀድሞው መሪ የስንብት ሥነ ሥርዓት ከኢራን በተጨማሪ በኢራቅ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደማሉ ተብሏል።

    አስካሁን በኢራን ውስጥ የተካሄደውን ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ የተወሰኑ ምሥሎች እነሆ...

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና
    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመሰናበት አደባባይ የወጡ ሰዎች የትራምፕን ምሥል ይዘው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመሰናበት አደባባይ የወጡ ሰዎች የትራምፕን ምሥል ይዘው
    አደባባይ የወጡ ሐዘንተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባለሥልጣናት ለቀናት በሚካሄደው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ በሚሊዮኖች እንደሚገኙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል
    የአያቶላ ምሥል ያለበት ተሽከርካሪ እና ለስንብት አደባባይ የወጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  12. ኢራን ለአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ "ፍትሕ እንደምትፈልግ" የጦር አዛዧ ተናገሩ

    ከኻሜኒ ትልቅ ፎቶ ጎን የቆመ የታጠቀ ወታደር

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ የሆኑት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ አገሪቱ ለግድያው ፍትሕ እና ተጠያቂነትን ለማግኘት ጥረቷን እንደምትቀጥል የኢራን ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሐታሚ ተናገሩ።

    “ወንጀሉን የፈጸሙት ወገኖች የኢራን ሕዝብ እንባ፣ ሁላችንም ፍትሕ መጠየቃችንን ፈጽሞ እንደማናቋርጥ ሊያውቁ ይገባል” በማለት የጦር አዛዡ መናገራቸውን የኢራን ዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።

    ጨምረውም “ውጤት አስክናገኝ ድረስ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ውሳኔያችን ግልጽ ነው። ጥቃት ፈጻሚዎቹን እንዲሁ አንተዋቸውም” በማለት በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የጠቅላይ መሪው ደም በከንቱ ፈስሶ እንደማይቀር አመልክተዋል።

    ሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለክብር፣ ለነጻነት እና ለብሔራዊ ኩራት ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ጄነራሉ፤ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች “ያለምንም ማወላወል በቆራጥነት እና በጀግንነት” የአዲሱን እስላማዊ አብዮታዊት ኢራን ጠቅላይ መሪ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሞጅታባ ኻሜኒ አመራርን እንደሚከተል ገልጸዋል።

    ጄነራሉ አዲሱን መሪ ባገኙበት ጊዜ “የኢራን ሕዝብ እና መንግሥት ወንጀሉን የፈጸሙት እንዲሁ እንደማይተዋቸው ነግሬያቸዋለሁ” በማለት ለሞጅታባ ኻሜኒ የገቡትን ቃል አስታውሰዋል።

  13. በአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚታየው ቀይ ባንዲራ ምንድን ነው?

    ኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቀይ ባንዲራ የያዙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ለቀናት በሚዘልቀው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እየተገኘ ሲሆን በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ከኢራን ባንዲራ ይልቅ ሐዘንተኞቹ ቀይ ባንዲራ ይዘው በስፋት ይታያሉ።

    ሐዘንተኞቹ በጠቅላይ መሪው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቀይ ቀለም ያለው ሰንደቅ ዓላማ ወይም ረጅም ባነር መያዛቸው በሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ቀዩ ባንዲራ ያለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። ይህም የሟቹን መሪ ደም መበቀል አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ነው።

    በተጨማሪም ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ጽሁፍ የሰፈረባቸው ቀይ ጨርቆች በስፋት የሚታዩ ሲሆን ጽሁፉ ለኻሜኒን ግድያ በቀል ጥሪ የሚያርቡ ናቸው።

    በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩት ቀይ ባንዲራዎች ሰማዕትነትን፣ ለንጹኃን ግድያ ፍትሕ አለማግኘትን፣ እንዲሁም ለበቀል ሃይማኖታዊ ቃል መግባትን ያመለክታል። ይህ ቀይ ባንዲራ በአጥቂዎች ላይ የበቀል አጸፋ ሲመለስ ወይም በፍርድ ፍትሕ አስኪገኝ ድረስ እየተውለበለበ ይቆያል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት መጨረሻ በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱ ጊዜ በመጀመሪያው ቀን በፈጸሙት ጥቃት ጠቅላይ መሪው አሊ ኻሜኒ፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    ኢራንን ወደ 40 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጠቅላይ መሪነት ያስተዳደሩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከአገሪቱ ባሻገር በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው።

    ከቅዳሜ ጀምሮ አስከ ሐሙስ ድረስ የሚቆየው የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከኢራን ባሻገር በጎረቤት አገር ኢራቅ ውስጥም ይካሄዳል። የጠቅላይ መሪው አስከሬን ወደ ኢራን የሚወሰድ መሆኑም ተነግሯል።

  14. የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

    ትራምፕ ይገደሉ የሚል መፈክር የያዘች እና ሌሎች ሐዘንተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል።

    እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

    መጋቢት ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንስቶ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒን የጤና ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይናፈሳሉ። አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት እርሳቸውም እንደተጎዱ ይነገራል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ እስከሞቱበት የካቲት ወር ድረስ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ መርተዋል።

    አርብ ዕለት የተጀመረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ይፋዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚህ ሳምንትም በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ አካባቢዎች መካሄድ ይቀጥላል።

    የኢራን ባለሥልጣናት “የክፍለ ዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት” ሲሉ በገለጹት በዚህ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ12 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ሰዓት የኻሜኒ አስከሬን ቴህራን ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ መስጊድ ግራንድ ሞሳላ ውስጥ ተቀምጧል።

    እሁድ ዕለት በመላው ኢራን ክብረ በዓል ሆኖ የታወጀ ሲሆን አስከሬኑ ከመስጊዱ እንደሚወጣ እና ዛሬ ሰኞ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በጥንቃቄ የተሰናዳ ነው። በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የሞጅታባ ኻሜኒ አለመገኘት የተስተዋለው እስራኤል ልትገድላቸው ትፈልግ ይሆናል የሚል ስጋት ባደረበት በዚህ ወቅት ነው።

    ተፋላሚዎቹ አገራት በገቡበት ጠንካራ ያልሆነው ተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ ጋብ ብሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል።

    ይሁን እንጂ አሜሪካም ሆነ ኢራን ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ በድጋሚ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስከሚጠናቀቅ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር እንዲቆም መደረጉን ለአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙትን የኢራን ከፍተኛ አመራሮች “በአንድ ጥይት” ልትገድላቸው እንደምትችልም መናገራቸውን አክሲዮስ አስነብቧል። ። ነገር ግን "ይህንን አናደርግም፤ ምክንያቱም ከዚያ የምንደራደረው ሰው አይኖርም" ብለዋል።

    ትራምፕ ሕዝቡ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ ይጠላቸዋል ብለው ያስቡ እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ተናግረዋል።

    በቴህራን በተደረገው ሽኝት ላይ ታዳሚዎች 'ሞት ለትራምፕ' ሲሉ እንደነበር እንዲሁም ሞሐማድ ረሱሊ የተባሉ ገጣሚ ከጸሎት ሥነ ሥርዓት በፊት “ትራምፕን መግደል የእኛ ኃላፊነት ነው” የሚል ግጥም ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ዘ ጋርዲያን ዘግበዋል።