
የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ የነበሩ ሦስት
የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከተመቱ በኋላ አሜሪካ ኢራን ላይ “ጠንካራ” ጥቃት ከፈተች።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ ከ60 በላይ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አነስተኛ ጀልባዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል
የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ
የፈጸመችው ጥቃት ከሳምንታት በፊት የተፈረመውን የኢራን እና አሜሪካ መግባቢያ ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢራን “ቆራጥ እርምጃዎችን
እንደምትወስድም” አስጠንቅቀዋል።
የኢራን መንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው
ድብደባ የተፈጸመባቸው ቄሽም ደሴት እንዲሁም ባንደር አባስን እና ሲሪክን የተባሉት አካባቢዎች ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች በፍንጣሪ
የተመቱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
ኢራን፤ አሜሪካ ጥቃት እንድትከፍት ላደረጋት
የሦስቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጥቃት በቀጥታ ኃላፊነት አልወሰደችም።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ከ60 አነስተኛ
ጀልባዎች በተጨማሪ የኢራን የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ስፍራዎች እና የዕዝ ማዕከላትን መምታቱን አስታውቋል። ዒላማዎቹ የሚገኙበትን ቦታ
ግን አልገለጸም።
አሜሪካ፤ በሦስቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የተፈጸመው
“ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው” ጥቃት መዘዝ እንደሚያስከትል ገልጻ ነበር።
ጦሩ እንደገለጸው የአሜሪካ ጥቃቶች የተፈጸሙት
"በዓለም አቀፍ የውሃ መስመር ላይ ንጹሃን በግለሰቦች የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦችን ዒላማ በማድረጋቸው እና ጥቃት በመሰንዘራቸው
ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍሉ ለማድረግ" ነው።
ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ አሜሪካ ግምጃ ቤት
ከዚህ ቀደም ኢራን ላይ የተጣለው የነዳጅ ማዕቀብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ያሳለፈውን ውሳኔ ቀልብሷል። የማዕቀብ ማላላት እርምጃው
የተወሰደው ዋሽንግተን እና ቴህራን በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃው የመግባቢያ
ስምምነቱን የሚጥስ እንደሆነ ገልጿል። የአሜሪካ መንግሥት “ቅን ልቦና እና ወጥ አቋም የሌለው እንዲሁም የማይታመን” መሆኑን እንዳረጋገጠም
ጠቅሷል።
አክሎም ኢራን "ብሔራዊ ጥቅሟን እና
ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው የምትለውን የትኛውንም እርምጃ ትወስዳለች" ብሏል።
በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲያልፉ የተመቱት መርከቦች
የእነርሱ እንደሆኑ የገለጹት ኳታር እና ሳውዲ አረቢያ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ኢራንንም ተጠያቂ አድርገዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል
ባጋኢ ግን የኳታርን ክስ "ከመልካም ጉርብትና መርህ ጋር የተቃረነ" ሲሉ ገልጸውታል።