ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁሙ ማብቃቱን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካ በኢራን ውስጥ ጥቃቶችን ከፈጸመች እና ኢራን በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን ካሳወቀች በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢራን ላይ የተከፈተውን አዲስ ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የእስራኤል ጉብኝታቸውን ሰረዙ

    ፒት ሄግሴት ከማርክ ሩት፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ ማርኮ ሩቢዮ እና ስኮት ቢሴንት ጋር በኔቶ ስብሰባ ላይ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፒት ሄግሴት ከማርክ ሩት፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ ማርኮ ሩቢዮ እና ስኮት ቢሴንት ጋር በኔቶ ስብሰባ ላይ ታይተዋል

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት መባባሱን ተከትሎ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ዛሬ ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረውን ጉዟቸውን እንደሰረዙ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

    ሄግሴት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ጉባኤ ለመታደም ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ቱርክ ነበሩ።

    ሚኒስትሩ ዛሬ ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት እቅድ በአሜሪካም ሆነ በእስራኤል በይፋ አልተገለፀም።

    ሆኖም በርካታ የዜና አውታሮች ጉብኝታቸው ኤፍ35 ተዋጊ ጄቶችን ለቱርክ የመሸጥ ሃሳብን በተመለከተ እስራኤል በሚኖራት ስጋት ላይ የሚደረግ ውይይትን እንደሚያካትት ዘግበዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በዓለም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የሆነው ኤፍ35 ተዋጊ ጄቶችን እና ተመሳሳይ የጦር መሣሪያዎችን ለቱርክ መሸጥ "ስህተት" እንደሚሆን ተናግረዋል።

    እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር ከመሆኗ ባሻገር በቀጣናው ብቸኛዋ የኤፍ-35 ጄት ባለቤት ናት።

    የጦር መሣሪያ አምራቹ ሎክሄድ ማርቲም መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ ኤፍ-35ኤ የጦር ጀት 82.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያወጣል።

    እስራኤልም ሆነች አሜሪካ በመከላከያ ሚኒስትሩ ጉዞ መሰረዝ ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።

  2. በሺዎች የሚቆጠሩ መርከበኞች በሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ ተገለፀ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ተራርቀው የቆሙ ሁለት መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ መርከቦች ላይ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በመርከቦች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሰላም መውጣት ባልቻሉ መርከቦች ላይ ያሉ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ መርከበኞችን "ስጋት እና የሥነ ልቦና ጫና ይበልጥ ያባብሰዋል" ብለዋል።

    መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ እና ኢራን ወሽመጡን ለማስከፈት የሚያስችል ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ መርከበኞች በባሕረ ሰላጤው እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ መቆየታቸውን ዶሚንጌዝ አስታውሰዋል።

    ዋና ፀሐፊው አሁንም አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት መርከቦች በሰላም እንዲወጡ ሁለቱም ወገኖች ሳይረፍድ ሁኔታውን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርበዋል።

    ከዓለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶ የሚጓጓዝበት ሆርሙዝ ወሽመጥ ከመዘጋቱ በፊት በየቀኑ 138 ገደማ መርከቦች ይተላለፉበት ነበር።

    ኢራን ወሽመጡን ከዘጋች በኋላ 1 ሺህ150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራተኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገድደዋል።

  3. መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያቋርጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

    መርከቦች በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu/Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት በመርከቦች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በማውገዝ የባሕር ትራንስፖርት ኩባንያዎች መርከቦቻቸውን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳይልኩ አሳሰበ።

    ይህ ማሳሰቢያ የተሰማው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን የአጻፋ እርምጃ ከወሰደች በኋላ ነው።

    በሆርሙዝ ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ “በመርከቦች ላይ የሚፈጸመው የግድየለሽነት ጥቃት በድጋሚ የመርከብ ላይ ሠራተኞችን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ ጀምሯል” ሲሉ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ ተናግረዋል።

    “የመርከብ ላይ ሠራተኞች ደኅንነትን ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ አገራት፣ የመርከብ ባለቤቶች፣ የመርከብ ትራንስፖርት ተቋማት እና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ባሕርተኞችን ካላስፈላጊ አደጋ ለመጠበቅ ሲሉ በሆርሙዝ በኩል ከመተላለፍ እንዲቆጠቡ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    በጦርነቱ ምክንያት ለወራት ተዘግቶ የነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የመርከቦች እንቅስቃሴ ጨምሯል።

    የዓለማችን 20 በመቶ የነዳጅ እና የጋዝ ምርት በሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ሦስት መርከቦች ላይ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ እስካሁን ለጥቃቶቹ ኃላፊነቱን የወሰደ የለም።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን አሳውቀዋል።

    ይህም በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ዳግም ውጥረት እንዲያገረሽ ያደረገ ሲሆን፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ስጋት ላይ ጥሎታል። በዚህም ምክንያት ቀንሶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተዘግቧል።

  4. ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “እንዳበቃ” ከተናገሩ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ነዳጅ የሚቀዳ ሰው እጅ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ተፈረመው ጊዜያዊ ስምምነት “አብቅቷል” ማለታቸውን ተከትሎ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በስድስት በመቶ ጨመረ።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው አስቀድሞ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ76 ዶላር በታች ሲሸጥ ነበር። ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከስድስት በመቶ በላይ በመጨመር 78.73 ዶላር መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሁኑ ጭማሪ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው እንደሆነም ተገልጿል። በኢራን ጦርነት ምክንያት ዋጋው አሻቅቦ ወራትን ያስቆጠረው ነዳጅ፤ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለመቋጨት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።

    ይሁን እንጂ ከትናንት ሌሊት አሜሪካ የኢራን ይዞታዎችን ከደበደበች በኋላ መጨመር ጀምሯል። አሜሪካ ጥቃቱን የፈጸመችው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ የነበሩ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በመመታታቸው እንደሆነ ገልጻለች።

    ለዋሽንግተን ጥቃት አጸፋ የሰጠችው ኢራን በበኩሏ፤ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ ማድረጓን አስታውቃለች።

  5. የአሜሪካ ጥቃት በኢራኗ የወደብ ከተማ

    ሌሊት ላይ አሜሪካ በኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ ኢራንም በተመሳሳይ በባሕረ ሰላጤው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መምታቷን ገልጻለች።

    ይህ ቪዲዮ በኢራኗ የወደብ ከተማ ባንዳር አባስ በአሜሪካ ጥቃት ያጋጠመውን ፈንዳታ ያሳያል።

  6. ትራምፕ ከኢራን ጋር ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገውን ጦርነት ያስቆመው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    አሜሪካ ማክሰኞ ሌሊት፤ በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የተገደሉት የጠቅላይ መሪዋን የቀብር ሥነ ሥርዓት እያካሄደች ባለችው ኢራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ኢራንም በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟ ተነግሯል።

    በቱርክ እየተካሄደ ባለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ማኅበር (ኔቶ) ስብሰባ ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “ያበቃ ይመስለኝል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም "ከእነሱ ጋር ከዚህ በኋላ መነጋገር አልፈልግም፤ የሚታመኑ አይደሉም” ብለዋል። “እስከምረዳው ድረስ [የተኩስ አቁሙ] አብቅቷል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ሁለቱ ወገኖች “ሊነጋገሩ እንደሚችሉ” ነገር ግን ውጤት የማያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል። የሚደረጉ ንግግሮች ጊዜን የሚያባክኑ እንደሆኑ በመጥቀስም የኢራን ባለሥልጣናትን “ውሸታም” ሲሉ ወርፈዋል።

    የተኩስ አቁምን ማብቃት በተመለከተ በተደጋጋሚ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ የአረሪካ ልዑካን ከኢራን ጋር "ሊነጋገሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ጊዜያቸውን ማባከን ነው ብዬ ነው የማስበው” ብለዋል።

    "በግልጽ ለመናገር፣ ከእነሱ [ከኢራናውያን] ጋር ጊዜዬን ማጥፋት አልፈልግም" ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

  7. ኢራን በ85 የአሜሪካ ዒላማዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

    የኢራን ባሕር ኃይል ጀልባ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ጦር ኢራን ውስጥ በርካታ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ።

    የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ሌሊት ላይ ኢራን ውስጥ በሚገኙ ከ80 በላይ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በተመሳሳይም በአካባቢው አገራት ውስጥ የሚገኙ 85 የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።

    አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ኢራናውያን በከፍተኛ ቁጥር ወጥተው የታላቁ መሪያቸውን የቀብር ሥነ ሥርዓት እያካሄዱ ባለበት ጊዜ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን ገልጿል። “እርምጃው በድጋሚ በተደረሰው ስምምነት ላይ የተፈጸመ ጥሰት ነው” ሲልም አሜሪካ በኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጧል።

    ለዚህ ጥቃት በተሰጠው የመጀመሪያ ደረጃ ምላሽ የአገሪቱ የባሕር እና የአየር ኃይሎች “የጋራ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን" መፈጸማቸውን ገልጿል። በጥቃቱም "ባህሬን ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ሰፈር እና ኩዌት ውስጥ ያለው የአሜሪካ የአየር ኃይል ሰፈር” ላይ 85 ዒላማዎችን መመታታቸውን አስታውቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሙን ከማሳወቁ በፊት የኩዌት ሠራዊት “የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን” ለመከላከል የአየር መከላከያ ሥርዓቶቹን መጠቀሙን የገለጸ ሲሆን፣ ባህሬን ውስጥ ደግሞ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውል ተሰምቷል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት የፈጸመችው ማክሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ሲሆን፣ ኢራን ግን በጥቃቱ ውስጥ እጇ እንደሌለ አስታውቃለች።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ዩናይትድ ስቴትስ በመርከቦቹ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን ተጠያቂ አድርገዋል።

    ይህ በአሜሪካ ሠራዊት የተከፈተው እና ኢራን የአጸፋ ጥቃት የሰነዘረችበት ሁኔታ ከሳምንታት በፊት በሁለቱ ወገኖች በኩል ከተደረሰው ስምምነት በኋላ በአካባቢው አዲስ ወታደራዊ ፍጥጫ ቀስቅሷል።

  8. በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች መመታታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈተች

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ የነበሩ ሦስት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከተመቱ በኋላ አሜሪካ ኢራን ላይ “ጠንካራ” ጥቃት ከፈተች።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም)፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ ከ60 በላይ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አነስተኛ ጀልባዎችን ጨምሮ ከ80 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት ከሳምንታት በፊት የተፈረመውን የኢራን እና አሜሪካ መግባቢያ ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢራን “ቆራጥ እርምጃዎችን እንደምትወስድም” አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን መንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው ድብደባ የተፈጸመባቸው ቄሽም ደሴት እንዲሁም ባንደር አባስን እና ሲሪክን የተባሉት አካባቢዎች ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች በፍንጣሪ የተመቱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

    ኢራን፤ አሜሪካ ጥቃት እንድትከፍት ላደረጋት የሦስቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጥቃት በቀጥታ ኃላፊነት አልወሰደችም።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ከ60 አነስተኛ ጀልባዎች በተጨማሪ የኢራን የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ስፍራዎች እና የዕዝ ማዕከላትን መምታቱን አስታውቋል። ዒላማዎቹ የሚገኙበትን ቦታ ግን አልገለጸም።

    አሜሪካ፤ በሦስቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የተፈጸመው “ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው” ጥቃት መዘዝ እንደሚያስከትል ገልጻ ነበር።

    ጦሩ እንደገለጸው የአሜሪካ ጥቃቶች የተፈጸሙት "በዓለም አቀፍ የውሃ መስመር ላይ ንጹሃን በግለሰቦች የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦችን ዒላማ በማድረጋቸው እና ጥቃት በመሰንዘራቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍሉ ለማድረግ" ነው።

    ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ አሜሪካ ግምጃ ቤት ከዚህ ቀደም ኢራን ላይ የተጣለው የነዳጅ ማዕቀብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ያሳለፈውን ውሳኔ ቀልብሷል። የማዕቀብ ማላላት እርምጃው የተወሰደው ዋሽንግተን እና ቴህራን በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃው የመግባቢያ ስምምነቱን የሚጥስ እንደሆነ ገልጿል። የአሜሪካ መንግሥት “ቅን ልቦና እና ወጥ አቋም የሌለው እንዲሁም የማይታመን” መሆኑን እንዳረጋገጠም ጠቅሷል።

    አክሎም ኢራን "ብሔራዊ ጥቅሟን እና ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው የምትለውን የትኛውንም እርምጃ ትወስዳለች" ብሏል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲያልፉ የተመቱት መርከቦች የእነርሱ እንደሆኑ የገለጹት ኳታር እና ሳውዲ አረቢያ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ኢራንንም ተጠያቂ አድርገዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋኢ ግን የኳታርን ክስ "ከመልካም ጉርብትና መርህ ጋር የተቃረነ" ሲሉ ገልጸውታል።

  9. የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በሶርያ ጉብኝት ላይ ሳሉ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ተጎዱ

    ፍንዳታ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሶርያ ዋና ከተማ ደማስቆ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አርፈውበት የነበረ ሆቴል አቅራቢያ በተከሰተ ፍንዳታ 18 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የጸጥታ ኃይሎች ሁለት ፈንጂ መሣሪያዎችን አግኝተው የማክሸፍ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ፍንዳታው መድረሱን ‘ሳና’ የተባለው የመንግስት የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ አንደኛው መሣሪያ የቆመ ተሽከርካሪ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ተደብቋል።

    ከሶሪያው መሪ አህመድ አል ሻራ ጋር ለመወያየት ወደ ደማስቆ የተጓዙት ፕሬዝዳንት ማክሮን፤ በወቅቱ በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበሩ። ፕሬዝዳንቱ ደህና እንደሆኑ እና ፍንታውን እንዳልሰሙ ባለስልጣናቶቻቸው ገልጸዋል።

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት የሶሪያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ለኔቶ ጉባኤ ወደ ቱርክ እንደሚጓዙ ይጠበቃል።

    የሶርያ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ ከተጎዱት መካከል አራቱ የፖሊስ አባላት ናቸው። የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር የጥቃቱን ፈጻሚዎች ለመለየት ምርመራ እንደጀመረም ተዘግቧል።

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች እና ምስሎች፤ ሆቴል አቅራቢያ ከቆመ ተሽከርካሪ ላይ ጭስ እና እሳት ሲነሳ አሳይተዋል።

    ቢቢሲ አረቢክ ያነጋገራቸው አንድ የአይን እማኝ፤ የመጀመሪያው ፍንዳታ ሲከሰት በቱሪዝም ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ቆመው እንደነበር ገልጸዋል።

    እማኙ እንደሚያስረዱት፤ የመጀመሪያው ቦምብ ከፈነዳ በኋላ የደኅንነት ኃይሎች አጠራጣሪ ቁሶችን እየፈለጉ ነበር። ይህንን በሚያደርጉበት ሰዓት "ከመጀመሪያው ፍንዳታ በግምት 20 ሜትር ያህል ርቀት ላይ ሁለተኛ ፍንዳታ" መከሰቱን ተናግረዋል።

    የዓይን እማኙ፤ "የመጀመሪያው ፍንዳታ ንብረቶችን ቢጎዳም፤ ሰው አልቆሰለም። ሁለተኛው ፍንዳታ ግን በበርካታ የደኅንነት ኃይሎች እና በትራፊክ ፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት አድርሷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ከፍንዳታው በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የጻፉት ፕሬዝዳንት ማክሮን፤ “ምንም ነገር የሶሪያ ሴቶች እና ወንዶች በሙሉ ሉዓላዊነቷ፣ ደህንነቷ፣ ብዝሃነቷ እና አንድነቷ በተጠበቀ ሶሪያ ለመኖር ያላቸውን ምኞት አያደናቅፍም” ብለዋል።

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን እና የሶሪያው መሪ አህመድ አል ሻራ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  10. የ325 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ የተቀበሉት የቻይና ባለሥልጣን ሞት ተፈረደባቸው

    ተከሳሹ

    የፎቶው ባለመብት, CCTV

    በምሥራቃዊ ቻይና የሚገኝ ፍርድ ቤት በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ 2.2 ቢሊዮን ዩዋን በላይ ወይም 325 ሚሊዮን ዶላር በሙስና በመቀበል የተከሰሱት የቀድሞ የከተማዋ አስተዳደር ባለሥልጣን ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

    ቅጣቱ የተላለፈባቸው ያንግ ዩሊን ከአውሮፓውያኑ 1993 እስከ 2023 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በናንጂንግ ከተማ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

    የቀድሞው ባለሥልጣን በማጭበርበር፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም እና ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀሎች ተከስሰዋል። በእነዚህ ድርጊቶች አግኝተዋል የተባለው የገንዘብ መጠን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቀረቡ ክሶች ያልታየ ነው።

    የ69 ዓመቱ የቀድሞ ባለሥልጣን ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ሌሎች የኢንጂነሪንግ ውሎችን፣ የመሬት ባለቤትነት ዝውውር እና ገንዘብ እንዲያገኙ ማድረጋቸው ተገልጿል። ለዚህም በምላሹ ገንዘብ እና ቁሶችን መቀበላቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ያንግ ምርመራ የተከፈተባቸው፤ ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ በከፈቱት የፀረ ሙስና ዘመቻ ነው። ይህ ዘመቻ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች፣ ትልቅ ባንኮች እና ሌሎች ዘርፎችንም ነክቷል።

    ዢ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የፀረ ሙስና ዘመቻዎችን ከፍተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ዘመቻዎች የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለማጥቃት ውለዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።

    ቻይና ውስጥ ለእንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች የሞት ቅጣት ማስተለላፈው የተለመደ አይደለም። ክሱ ከአንድ ቢሊዮን ዩዋን በላይ ወንጀል የተፈጸመበት ሲሆን ግን የሞት ቅጣት የተሰጠባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

    በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ 1.1 ቢሊዮን ዩዋን በሙስና ተቀብለዋል የተባሉ አንድ ባለሥልጣን 2021 ላይ በሞት ተቀጥተዋል።

  11. የአሜሪካ ዛቻ እስከቀጠለ ድረስ ድርድር እንደማይጀመር የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የተጀመረውን “ሥራ እንደሚያጠናቅቁ” መናገራቸውን ተከትሎ፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛቻ እስከቀጠለ ድረስ ድርድር እንደማይጀመር ተናገሩ።

    የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በጄኔቫ የመጀመሪያ ዙር ንግግር ያደረጉት ዋሽንግተን እና ቴህራን፤ የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቀብር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድርድሩን መግታታቸውን ትራምፕ ገልጸው ነበር።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሰኞ ምሽት በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ስምምነት ላይ እንደርሳለን ወይም ሥራውን እናጠናቅቃለን። ሥራውን መጨረስ አስቸጋሪ አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እናሸንፋለን” ያሉት ትራምፕ፤ “የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቻቸውን መምታት እንችላለን…እነርሱም ያውቁታል” ብለዋል።

    ለዚህ የትራምፕ ንግግር ምላሽ ሰጡት ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው፤ ቴህራን ላይ የሚሰነዘረው “ዛቻ እስከቀጠለ ድረስ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ድርድር እንደማይጀምር” ገልጸዋል።

    ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ከአሜሪካ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትን አንቀጽ 13ን ጠቅሰው “ግልጽ” ነው ብለዋል።

    ሚኒስትሩ የጠቀሱት አንቀጽ በስምምነቱ ላይ የሰፈሩ ጉዳዮች ተግባራዊ እስካልሆኑ ድረስ ሁለቱ አገራት ለመጨረሻ ስምምነት የሚደረግን ድርድር እንደማይጀምሩ የሚገልጽ ነው።

    በስምምነቱ ድንጋጌዎች አንዱ ሁለቱም አገራት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ኃይል እንዳይጠቀሙ ወይም እንዳይዝቱ ያዝዛል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አራግቺ የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ ምሥሎችን ከፅሑፉ ጋር ለጥፈዋል። “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኩሩ ኢራናውያን በአንድነት ታላቁን አያቶላህ ኻሜኒን እና አሻራቸውን ለማግበር ወጥተዋል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም “እነርሱም ሆነ ደፋሩ ጦር ኃይላችን በማንኛውም ዛቻ አይነኩም” ብለዋል።

  12. “ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል”

    ጠ/ሚ ዐቢይ

    የፎቶው ባለመብት, PMO

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ “ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ፣ አእምሮ ከገዛ ለመነጋገር፣ ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

    አያይዘውም “ከሰላም ውጪ ያለው አይጠቅመንም” ሲሉም አክለዋል።

    በቀጣይ ዓመት በሚቋቋመው አዲስ ምክር ቤት ውስጥ የማይኖሩትን የሕዝብ እንደራሴዎች ባለፉት አምስት ዓመታት አስተዋጽኦቸው ምሥጋና አቅርበዋል።

    የብልጽግና አባል የሆኑም ያልሆኑም የምክር ቤት አባላትን “ኢትዮጵያም መንግሥታችንም አብዝቶ ያመሰግናችኋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት “ብርቱ ሰዎች፣ ሐሳባችሁን ለመግለጽ የደፈራችሁ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሞከራችሁ፣ ሐሳባችሁ ምንም ይሁን ምንም በግልጽነት የገለጻችሁ ጀግኖች ናችሁ” በማለትም አክለዋል።

    ዛሬ የመጨረሻ ስብሰባውን ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት መስከረም ማብቂያ ላይ አዲሱ ምክር ቤት ይተካል።

  13. ''በቀጣይ 5 ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች እንገነባለን''

    የቤት ጉዳይን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቀጣይ 5 ዓመታት ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶች እንገነባለን” ብለዋል።

    በመንግሥት፣ በግል፣ በመንግሥት እና በግል ዘርፍ ጥምረት የቤት ግንባታ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።

    ለዚህም የሦስት አውታር (3ዲ) ቴክኖሎጂን ጨምሮ የግንባታ ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካዎች መስፋፋት ያለውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል።

    የቤት ዘርፍ በሥራ ፈጠራ እና የምጣኔ ሃብት ማነቃቃት ያለውን ሚና አንስተዋል። ከሥራው ዘርፍ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ 13%፣ በውጭ አገራት 27% ዕድገት መኖሩን ጠቅሰው “5 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አስይዘናል” ብለዋል።

  14. “በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት”

    የኢንዱስትሪው ዘርፍ “ከለውጡ በፊት ከነበረበት 47% የማምረት አቅም ዛሬ ወደ 67% መድረሱን” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

    የማዕድን ዘርፍ 24% ዕድገት፣ የኢነርጂ ዘርፍ 23% ዕድገት፣ የአገልግሎት ዘርፍ 9.8% ዕድገት እንዳለ ጠቅሰዋል። ይህም ኢትዮጵያ 10.3 ማደግ እንደምትችል ያመለክታል ብለው ይህም “በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት ነው” ብለዋል።

    ጨምረውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያላት ሪዘርቭ (ተቀማጭ ገንዘብ) ከ20 አጥፍ በላይ አድጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አገሪቱ “የመቋቋም አቅሟ” ማደጉን በመጥቀስም “ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ወዲህ ያለ ሪዘርቭ የአሁኑ በእጥፍ ይበልጣል” ብለዋል።

    የኢትዮጵያ ገቢ በ27 ዓመት 1 ትሪሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑን በመጥቀስም፣ ዘንድሮ ከ1.5 ዶላር በላይ መድረሱን አመለክተዋል።

  15. “የ17 ዓመቱን በአንድ ዓመት ማምጣት ዕድገት ካልሆነ ምን ዕድገት ይሆናል?”

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በተመለከተ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት “ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ” መሆኑን ተናግረዋል።

    “የ17 ዓመቱን በአንድ ዓመት ማምጣት ዕድገት ካልሆነ ምን ዕድገት ይሆናል?” ሲሉ ለውጡን በንጽጽር ገልጸዋል። 38 ቢሊዮን ዶላር የውጭ አገር ካፒታል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ጠቅሰዋል።

    ኢትዮጵያ በ17 ዓመታት ከቡና ኤክስፖርት ያገኘችው 3.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁን ግን በአንድ ዓመት 3.1 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት መደረጉን ተናግረዋል።

    ወርቅ በ27 ዓመት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት እንደተደረገ እና አሁን ግን የወርቅ የውጭ ንግድ በአንድ ዓመት 5.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

  16. “እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለውም”-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደርግ መንግሥት በወደቀበት “ስሌት” መንግሥታቸውን ለመጣል የሚያስቡ ኃይሎች ስጋት እንደማያሳድሩ ገልፀው፤ አሰላለፋቸውንም “ምኞት” ብለውታል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃይሎች "መከላከል የሚያስችል ብቃት እየገነባን ነው ያለነው" ብለዋል።

    “ሰዎች ባረጀ ባፈጀ ስልት፤ ድሮ በሠራ ስልት አሁን ለመጠቀም መሞከር ጠቃሚ አይደለም” ያሉት ዐቢይ፤ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ራሱን በድሎ የሚዋጋ ኃይል የለም የሚል ነው።

    “ጊዜው ተቀይሯል” ብለዋል።

    “ሀብት እያፈራህ፤ ሀብትን እያጣጣምክ ራስን ደግሞ ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት አብሮ አይሄድም። አልፎበታል። ይህ ምኞት አይጠቅምም።”

    በትግራይ ክልል ጦርነቱ እንዲፈነዳ “ሰፊ ፍላጎት” አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እምቢ ያልንበት ምክንያት ትርፍ የለውም ብለን ነው” ብለዋል።

    “እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለውም” ብለዋል።

    ህወሓት 50 ዓመት የቆየ “አንጋፋ ፓርቲ ሆኖ ወጣቱን ማመን” አመቻሉን በንግግራቸው ጠቅሰው “ድል እና ህወሓት አራንባ እና ቆቦ” ናቸው ሲሉም አጣጥለዋል።

    አሁን ያለውን የአዲስ ትውልድ አስተሳሰብ እና አቅጣጫ አለመቀበል “የትም አያደርስም” ሲሉም ተናግረዋል።

    ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ 40 ምንጭ. . . እና ሌሎችም ከተሞች በመጥቀስ “ኮሪደር ልማት በመቀለ ማየት ነው ምኞታችን ከዛ ውጭ ያለውን አንፈልግም” ብለዋል።

    ስለ ህወሓት የሰጡት አስተያየት ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በማንሳት የሕዝቡ ያለው የትግል ሚና እንዳማይካድ ጠቅሰው “አሁን ያለው የተለየ ነው” ሲሉ የሁኔታዎችን መለወጥ ተናግረዋል።

  17. “መቋቋም፣ መጠቀም፣ መግራት”

    ጠ/ሚ ዐቢይ

    የፎቶው ባለመብት, PMO

    ጠቅላይ ሚኒስሩ የውጭ አገር ግንኙነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላት መርኅ “መቋቋም፣ መጠቀም፣ መግራት ነው” ብለዋል።

    የአገሪቷን “የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ” ግባቸው እንደሆነ የተናገሩት ዐቢይ፣ መቋቋም አገር እና ተቋም መፍጠር መሆኑን፣ መጠቀም ፈተናን ወደ ዕድል መቀየር መሆንን እና መግራት “በሰው አጀንዳ ከመገራት የራስን አጀንዳ ፈጥሮ በመግራት” መርኅ እንደሚመሩ ተናግረዋል።

    በሌላ በኩል “ጠላት” የሚከተለው ያሉት መካድ፣ መርሳት እና ምኞት ነው። ኢትዮጵያ በቀላሉ እንደማትበገር መካድ፣ የኢትዮጵያ ራሷን መከላከል እንደምትችል መርሳት እና ያለፈ ስልት እስረኛ የመሆን ምኞት እንዳለ ገልጸዋል።

  18. “የትምህርት ዘርፍን ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እንኮራበታለን”

    በብሔራዊ ፈተና የሚወድቁ ተማሪዎች መበራከት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ ከተነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን “በጣም የተሳካልን የሥራ መስክ የትምህርት ሚኒስቴር ነው” ብለዋል። የትምህርት ዘርፍን “ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እንኮራበታለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    በሰባት ዓመታት 35 ሺህ መዋዕለ ሕጻናት መገንባታቸውን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። እነዚህ ሕጻናት “ምርጫ አይመርጡንም፣ ፌስቡክ ላይክ አያደርጉንም. . . በ20 ዓመት የኢትዮጵያ ሕልውና ናቸው” ብለው የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳላቸው አስረድረዋል።

  19. "ከአርሲው ግድያ ጋር በተያያዘ 22 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል"

    “ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርሲ የተፈጸመው ግድያ “ሃይማኖታዊ ገጽታ” እንደሌለው አስረግጠው ተናግረዋል።

    “በሃይማኖት እና ብሔር ጥላ ሥር አየወደቀ” በማለትም የተለያዩ ፍላጎቶች ከጀርባው መኖራቸውን አመላክተዋል። “አዲስ አበባ ተቀምጠው ቤንዚን እያርከፈከፉ. . . እሳቱን ያቀጣጥላሉ” አሉ ሲሉም ከስሰዋል።

    በአርሲ የተፈጠረው “ምርጫውን ከማደናቀፍ ሙከራ” ጋር አያይዘው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃይማኖት ተቋማት “ቦምብ እና ክላሽ ስንይዝ ነበር” ብለዋል።

    “. . . ያቃታቸው ኃይሎች ሕዝብን ሊያጠቁ አንድ መንደር ሄዱ አርሲ ውስጥ። ሕዝብ የሚያጠቃ እና የሚከላከል ኃይል ተጋጠመ” በማለት በክስተቱ ከሞቱት 11 ሰዎች 8ቱ ሚሊሻ መሆናቸውን ጠቅሰው “ሕይወታቸውን ገብረው ለንጹኃን ሕይወት የተጎዱ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

    ክስተቱን “የሃይማኖት መልክ ለመስጠት ታስቦ ነበር” ብለውም በጥቃቱ ሙስሊሞችም መገደላቸውን እና 22 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

  20. ‘ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና እየገነባን ነው’

    የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ቀውስ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን “የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ” ሲሉ ገልፀውታል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት “የሻዕቢያን” ተልዕኮ እያስፈፀመ ያለ፤ ‘የራሱ ዓላማ የሌለው’ “መጥረቢያ” ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    “ኢትዮጵያ የሰላሟ መድፍረስ ምንጭ የት እንደሆነ ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳው ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና በመፍጠር ላይ የምንገኝ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት መግለፅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱን አንድነት እና ሉዓዊነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ “ማንኛውም ነገር ከመጣ” መከላከል የሚያችል ቁመና አለን ብለዋል።

    የውጭ ተልዕኮ አስፈፃሚ ብለው ያመለከቷቸው የአገር ውስጥ ኃይሎችን “ጉዳቱ የጋራ ስለሚሆን...መታገስ እና ማስተማር” ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።