የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዋና ዋና ክስተቶች
አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት መመለሳቸው መካከለኛው ምሥራቅን በውጥረት ሞልቶታል።
በሁለቱ አገራት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ከባድ የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ያሳለፍነው ማክሰኞ ነው።
የኢራን የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ እና ረቡዕ በተፈጸሙ ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።
ረቡዕ እና ዛሬም ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። የግጭቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦
- የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
- የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ የመቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ።
- በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ሃዲድ በተዘረጋበት ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል።
- የኢራን መገናኛ ብዙኃን የኒውክሌር ማብላያ ላይ ዛሬ ከሰዓት ጥቃት መፈጸሙን ዘግበዋል።
- ኢራን በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።
- ባህሬን ከኢራን የተሰነዘሩባትን ጥቃቶች ማክሸፍ መቻሏን ስትገልጽ፤ በኩዌት በተተኮሰ የሚሳዔል ስብርባሪዎች አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
- የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ 10 ሚሳዔል መተኮሱን ገልጿል። ዮርዳኖስ በበኩሏ ስምንት ሚሳዔሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።