ቀጥታ, ኢራን እና አሜሪካ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ተዘገበ

ኳታር፣ ፓኪስታን እና ሌሎችም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ውይይት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተዘገበ። የአሜሪካው አክሲዮስ እንደዘገበው አሸማጋዮቹ አሜሪካ እና ኢራን እንደ አዲስ የገቡበትን ግጭት አቁመው ኒውክሌርን የተመለከተ ውይይት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

  • ትራምፕ "የተኩስ አቁሙ አብቅቷል" ካሉ በኋላ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደሚፈፅሙ ዛቱ
  • መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያቋርጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ
  • በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች መመታታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈተች
  • ኢራን በ85 የአሜሪካ ዒላማዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች
  • የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በሶርያ ጉብኝት ላይ ሳሉ በደረሰ ፍንዳታ 18 ሰዎች ተጎዱ
  • የ325 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ የተቀበሉት የቻይና ባለሥልጣን ሞት ተፈረደየአሜሪካ ዛቻ እስከቀጠለ ድረስ ድርድር እንደማይጀመር የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቻይና በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሮኬት አስወነጨፈች

    ቻይና በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ሮኬት ማስወንጨፏ ተገለጸ።

    በአገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ዘርፍ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተመልክቷል።

    ዛሬ አርብ፤ ሎንግ ማርች 10ቢ የተባለው ሮኬት ከደቡባዊ ቻይና ሀይናን ተወንጭፎ ወደ ምድር መመለሱ ተገልጿል።

    አሜሪካ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች በማምረት በሕዋ ሳይንስ ያላትን ሥፍራ ቻይና መገዳደር የምትችልበት መንገድ ነው።

    የኢሎን መስክ ‘ስፔስ ኤክስ’ እና የጄፍ ቤዞስ ‘ብሉ ኦሪጅን’ እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች ያመርታሉ።

    ሮኬቶች አንዴ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ መልሰው አገልግሎት እንደማይሰጡ ይታመናል።

    ከምድር ሮኬቶች ሲወነጨፉ ጉዳት ስለሚደርስባቸው እና በድጋሚ ጥቅም ላይ ስለማይውሉ የጠፈር መንኮራኩር መላክ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።

    ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ የሚያስችለው ክፍል ዳግመኛ ጥቅም ላይ እንዲውል ማስቻል በከፍተኛ መጠን ወጪውን ይቀንሳል።

  2. የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአሜሪካ ጋር በማበሯ ዋጋ ትከፍላለች - ኢራን

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለወራት ጥቃት እየፈጸመች ካለችው አሜሪካ ጋር የምታደርገው ትብብር ዋጋ ያስከፍላትል ሲሉ አንድ የኢራን የምክር ቤት አባል ተናገሩ።

    በኢራን ፓርላማ ውስጥ የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚሽን አባል የሆኑት ኢስማኤል ኮዋሳሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አሜሪካ በአገራቸው ላይ እንደ አዲስ ከከፈተችው ጥቃት ጀርባ አለች ሲሉ ከስሰዋል።

    በዚህም ምክንያት አሜሪካ እየፈጸመችው ላለው ጥቃት ኤምሬትስ “ከዋሽንግተን ጋር ባላት ትብብር የተነሳ ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ የባሕረ ሰላጤዋን አገር አስጠንቅቀዋል።

    አስማኤል በተጨማሪም በኢራን ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ "እየወሰደችው ባለቻቸው እርምጃዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኢራን ጠላቶች ጋር ተሰልፋለች፤ ለዚህም የሚያስከፍላት ዋጋ በጣም ከባድ እንደሚሆን ልታውቀው ይገባል” ብለዋል።

    የኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ቀደም ሲል እንዳስታወቁት “ለወራሪ” ኃይሎች ማንኛውንም ድጋፍ የሚሰጥ ከኢራን የአጸፋ ቅጣት ይጠብቀዋል በማለት ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ የምክር ቤት አባሉ አጽንኦት ሰጥተው ጠቅሰዋል።

    ስለዚህም ኤምሬትስ በቀጣናው ያሉትን ለአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በምትሰጠው ድጋፍ ምክንያት “የባሕር እንቅስቃሴ መስመሯ፣ የባቡር እና የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶቿ እንዲሁም የነዳጅ እና የጋዝ ተቋማቷ የኢራን ጦር ሠራዊት እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ ዋነኛ ዒላማዎች ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቀዋል።

  3. ‘ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል አዲሱ የኢራን ዕቅድ’

    ኢራን ከወራት በፊት በተከፈተባት ጦርነት ጠቅላይ መሪዋን እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቷን የገደሉባትን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመበቀል አዲስ ዕቅድ ማውጣቷ ተዘገበ።

    ኢራን በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ግድያ ለመፈጸም አዲስ ዕቅድ ማዘጋጀቷን በተመለከተ እስራኤል ለአሜሪካ መረጃ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ዘግቧል።

    "የአሜሪካን መሪ፣ እኔን ሊገድሉ ይፈልጋሉ” እና “ስሜ በሁሉም ዝርዝራቸው ውስጥ ይገኛል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መረጃው እንዳሳሰባቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩን በይፋ አንስተው በተደጋጋሚ መናገራቸውን እንደሚያመልክት ጋዜጣው ዘግቧል።

    እስራኤል የኢራንን ዕቅድ በተመለከተ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጠችው መረጃ ከሁለት ዓመት በፊት ፔንሲልቬኒያ ውስጥ የተደረገባቸውን የግድያ ሙከራ የሚያካትት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱም መረጃውን ከደኅንነት ስጋት ባሻገር ለፖለቲካ ዓላማቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን አመልክቷል።

    የትራምፕ ተቺዎች መረጃውን ትራምፕ ከሕዝቡ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ነው ቢሉም፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በቀድሞው የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በነበሩት ጆን ቦልተን ላይ አድርጎታል የተባለው የግድያ ሙከራ በትራምፕም ላይ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

    ከአውሮፓውያኑ 1950 ወዲህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ላይ ከተፈጸመው ግድያ አንስቶ በትሩማን፣ በፎርድ እና በሬጋን ላይ ያልተሳኩ የግድያ ሙከራዎች ተፈጽመዋል።

    አንዳንዶች የግድያ ሙከራዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ጥቅም ላይ ይውላል ቢሉም ፕሬዝዳንት ትሩማን እና ፎርድ ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ በሕዝብ ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት ሲያሽቆለቁል፣ ሮናልድ ሬጋን ግን ከተሞከረባቸው ግድያ በኋላ ተቀባይነታቸው ጨምሯል።

  4. ኢራን እና አሜሪካ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት መጀመሩ ተዘገበ

    ኳታር፣ ፓኪስታን እና ሌሎችም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ውይይት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተዘገበ።

    የአሜሪካው አክሲዮስ እንደዘገበው አሸማጋዮቹ አሜሪካ እና ኢራን እንደ አዲስ የገቡበትን ግጭት አቁመው ኒውክሌርን የተመለከተ ውይይት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

    አክሲዮስ በአሜሪካ እና በአሸማጋዮቹ አገራት የሚገኙ ሁለት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ውይይቶች እንዲቀጥሉ ጥረቶች ተጀምረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስትያ ከኢራን ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም የተኩስ አቁሙ “አብቅቶለታል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ተመልሰዋል።

    ትራምፕ ትኩረታቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ገልጿል።

    አክሲዮስ እንደዘገበው ትራምፕ አሁንም ቢሆን የለየለት ጦርነት ውስጥ ተመልሰው መግባት አይፈልጉም።

    የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በኩዌት፣ በባሕሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሙን ገልጿል።

  5. የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዋና ዋና ክስተቶች

    አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት መመለሳቸው መካከለኛው ምሥራቅን በውጥረት ሞልቶታል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ከባድ የተኩስ ልውውጥ የተደረገው ያሳለፍነው ማክሰኞ ነው።

    የኢራን የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ እና ረቡዕ በተፈጸሙ ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል።

    ረቡዕ እና ዛሬም ተከታታይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። የግጭቱ ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦

    • የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፈጸመው ጥቃት በኢራን ወደ 90 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
    • የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በደቡብ ምሥራቅ ኢራን ቻባሀር ከተማ የመቆጣጠሪያ ማማ ላይ የደረሰ ጉዳትን ያሳያሉ።
    • በሰሜናዊ የኢራን ክፍል አቃላ ከተማ የባቡር ሃዲድ በተዘረጋበት ድልድይ ላይ ጉዳት መድረሱንም ማረጋገጥ ተችሏል።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን የኒውክሌር ማብላያ ላይ ዛሬ ከሰዓት ጥቃት መፈጸሙን ዘግበዋል።
    • ኢራን በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የድሮን ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።
    • ባህሬን ከኢራን የተሰነዘሩባትን ጥቃቶች ማክሸፍ መቻሏን ስትገልጽ፤ በኩዌት በተተኮሰ የሚሳዔል ስብርባሪዎች አንድ ሰው ላይ ጉዳት መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
    • የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዮርዳኖስ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር ላይ 10 ሚሳዔል መተኮሱን ገልጿል። ዮርዳኖስ በበኩሏ ስምንት ሚሳዔሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
  6. የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን እንደምትከላከል አስታወቀች

    ለተከታታይ ሁለት ቀናት በአሜሪካ ጥቃት የተሰነዘረባት ኢራን ጥቃቱ የሚቀጥል ከሆነ እራሷን የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ በተከታታይ በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት “በጽኑ የሚወገዝ” መሆኑን አመለክተዋል።

    ጥቃቶቹን ከሳምንታት በፊት ባለፈው ሰኔ ወር በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነትን የሚጥስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት ዋነኛ አሸማጋይ ለሆኑት ለፓኪስታኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እንደተናገሩት “የአሜሪካ ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን እራሷን ትከላከላለች” ብለዋል።

    በተጨማሪም አራግቺ ከኦማን እና ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ አገራት በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

  7. አሜሪካ እና ኢራን ወደ ጦርነት ሲመለሱ፣ ኢራናውያን አደባባይ ወጥተው የኻሜኒን ቀብር እየፈጸሙ ነው

    አሜሪካ በኢራን ላይ ለሁለተኛ ቀን የምትፈጽመው ጥቃት በቀጠለበት እና ኢራን የአጸፋ እርምጃ በጎረቤቶቿ ላይ እየወሰደች ባለበት በአሁኑ ጊዜ በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የተገደሉት የቀድሞው ጠቅላይ መሪ የመጨረሻ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

    ላለፉት ቀናት በተለያዩ አገራት እና ከተሞች ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ወደ ትውልድ ከተማቸው ማሻድ ተወስዶ ዛሬ ግብአተ መሬቱ ይጠናቀቃል።

    በሰሜን ምሥራቃዊ ኢራን ውስጥ በምትኘው ቅዱስ ከተማ ማሻድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ጎዳናዎች በሐዘንተኞች መጨናነቃቸው ተዘግቧል።

    የካቲት ወር ማብቂያ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱበት የመጀመሪያ ዕለት የተገደሉት ኻሜኒ የስንብት እና ቀብር ሥነ ሥርዓት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

  8. የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሩ ሥር መሆኑን አስታወቀ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአገሪቱ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አስታወቀ።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት “በቁጥጥሩ ሥር እንዳዋለ” እና በቀጣይ ሁለት ሳምንታት “ቀስ በቀስ” መተላለፊያው እንደሚከፈት ይፋ አድርጓል።

    ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅርብ የሆነው ታስኒም የዜና ምንጭ እንደዘገበው፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለው እንቅስቃሴ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር “ወደ 50 በመቶ እንደሚደርስ" ተገልጿል።

    ከኢራን “ፈቃድ ያገኙ” መርከቦች እንቅስቃሴ “እየጨመረ” መሆኑን አስታውቋል።

    “የውጭ ኃይሎች በዚህ መሬት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መብት እንደሌላቸው በድጋሚ እንገልጻለን” ሲል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ተናግሯል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ መግባት “አውዳሚ ምላሽ የሚያስከትል” ነው ሲልም አስጠንቅቋል።

    የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቢቢሲ ቬሪፋ ባገኘው መረጃ መሠረት ትናንት ረቡዕ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል 23 መርከቦች አልፈዋል።

  9. ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ አሜሪካ “ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች ስትል አሜሪካን ከሰሰች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት አሜሪካ ሰኔ ላይ የተፈረመው እና ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ያስገኘው የመግባቢያ ስምምነት ክፍሎች ላይ “ግልፅ ጥሰት” ፈጽማለች ሲል ከሰሰ።

    “ወታደራዊ ዘመቻዎች በአስቸኳይ እና በቋሚነት እንዲቆሙ” የጠየቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል “የሚደረግ የንግድ መርከቦች ጉዞን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተቻላትን እንደምታደርግ” ገልጿል።

    ሁለቱ ወገኖች የመግባቢያ ስምምነቱን የሚተረጉሙበት መንገድ የዚህ ግጭት ቁልፍ የውጥረት ምንጭ ሆኗል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አሜሪካ በወሽመጡ “ትዕዛዝ ባላከበሩ በርካታ መርከቦች ጋር ተፈጽሟል ለተባለ ክስተት” ምላሽ እሰጣለሁ በሚል “ሐሰተኛ ምክንያት” ጥቃት እንደፈጸመች በመግለጽ ከስሷል።

    አሜሪካ ከዚህ ቀደም ኢራን በወሽመጡ የሚጓዙ ሦስት መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም “የተኩስ አቁሙ ላይ ግልጽ ጥሰት” ፈጽማለች የሚል ክስ አቅርባ ነበር። ኢራን መርከቦቹ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን መሪዎች “ዋልጌ” በማለት “ያልተገራ ንግግር” አድርገዋል በማለት ወቅሷል።

    በተጨማሪም አሜሪካ ሁለት የባቡር ድልድዮችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ዒላማ በማድረግ "ከባድ የጦርነት ወንጀል" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

  10. በአሜሪካ የሁለት ቀናት ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን ኢራን ገለጸች

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ኢራን ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 78 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከሳምንታት በፊት የተኩስ አቁም እንዲደረስ ያደረገው የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው የነበሩት አሜሪካ እና ኢራን ከማክሰኞ አንስቶ በተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የፈጸመችው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ በነበሩ ሦስት ጭነት መርከቦች ተመትተዋል በሚል ነበር። ኢራን በምላሹ የባሕረ ሰላጤው አገራትን አጥቅታለች። ይህ የጥቃት ምልልስ ትናንትም ረቡዕ ሌሊትም ቀጥሏል።

    አሜሪካ ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት በኢራን አምስት ግዛቶች ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን የጤና እና ህክምና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆስኒ ኬርማንፑር ገልጸዋል።

    በእነዚህ ጥቃቶች 14 ሰዎች ተገድለው፤ 78 ሰዎች እንደሰቆሉ ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል። ከቆሰሉት ውስጥ 47 ያህሉ አሁንም ሆስፒታል ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በደቡባዊ ኢራን የሚገኘው ኢራንሻህር ግዛት ገዥ በበኩላቸው አሜሪካ የአየር ማረፊያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን አስታውቀዋል።

  11. የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ይጠናቀቃል

    ላለፉት ሰባት ቀናት ኢራን እና ኢራቅ ውስጥ የስንብት ሥነ ሥርዓታቸው ሲካሄድ የነበረው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን የኢራን ቅዱስ ከተማ ወደምትባለው ማሻድ ደረሰ።

    ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በዋና ከተማዋ የተጀመረው የኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሐሙስ የትውልድ ከተማ የሆነችው ማሻድ ውስጥ ይጠናቀቃል።

    ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የመጨረሻው የቀብር ሥነ ሥርዓት ማሻድ ውስጥ ከሰዓት በኋላ የሚከናወን ይሆናል።

    ለስድስት ቀናት በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ ከተሞች ውስጥ ለሕዝባዊ ስንብት ሲዘዋወር የቆየው የኻሜኒ አስከሬን ባለሥልጣናት እና በሚሊዮኖች የሚቆተሩ ሐዘንተኞች በተገኙበት የሽኝት ሥነ ሥርዓቶች ተካሂዶለታል።

    በዋና ከተማዋ ቴህራን በተካሄደው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ከበርካታ አገራት የመጡ ባለሥልጣናት እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

  12. ኢራን የአሜሪካን ሚሳዔል፣ የሳተላይት መገናኛ እና የነዳጅ ማከማቻ መምታቷን አስታወቀች

    የአሜሪካንን ጥቃት ተከትሎ የኢራን ሠራዊት በኩዌት፣ በባህሬን እና በኳታር የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎችን በድሮን ጥቃት ዒላማ ማድረጉን አስታወቀ።

    በዚህም ኩዌት የሚገኝ የአሜሪካ የፓትሪየት ሚሳዔል ማዕከል፣ ኳታር ውስጥ የሚገኝ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት የሆነ አንቴና፣ እና ባህሬን ውስጥ ያሉ የአሜሪካ የነዳጅ ማከማቻ ማዕከል “ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የተለያዩ ዓይነት” ድሮኖች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አመለክቷል።

    “በቀጣናው ውስጥ ባሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ” ሠራዊቱ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ተከታይ መሆኑን መሆኑን በማመልከት ግለጽ ቀጣይ መሆኑን ገልጿል።

    የኢራን ጦር ኃይል መግለጫ የአገሪቱን መንግሥታዊ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በበርካታ የኢራን የዜና ምንጮች በኩል እንዲሠራጭ ተደርጓል።

    ቀደም ሲል ባህሬን፣ ኩዌት እና ኳታርን ጨምሮ በርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

  13. የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኩዌት እና ባህሬን ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

    ለሁለተኛ ተከታታይ ቀን አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኩዌት እና ባህሬን ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

    አሜሪካ ሌሊቱን የፈጸመችው የአየር ጥቃት መጠናቀቁን ስትገልጽ፤ የአጸፋ ጥቃት የወሰደው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሰነዘረው “ስምምነት በጣሰችው አሜሪካ ላይ የመጀመሪያ ዙር የቅጣት እርምጃ” መሆኑን ጠቅሷል።

    አሜሪካ ጥቃቷን የምትቀጥል ከሆነ በቀጣናው ያሏትን ሌሎች የጦር ሰፈሮች ዒላማ በማድረግ ጥቃቱን እንደሚያሰፋም አስጠንቅቋል።

    አሜሪካ ኢራን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው ሌሊቱን ሲሆን ኢራንም በባሕረ ሰላጤው ውስጥ በሚገኙ አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት አድርሳለች።

    በአሜሪካ ጥቃት የኢራን ደቡባዊ የወደብ ከተማ የሆነችው ቻባሃር ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት እንደተፈጸመባት ተዘግቧል።

    ታስኒም የተባለው የኢራን ዜና ወኪል እንደዘገበው ወደ አስር የሚደርሱ ፍንዳታዎች በቻባሃር እና ኮናራክ ከተሞች ውስጥ ተሰምቷል። በቻባሃር ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ኤሌክትሪክ መቋረጡንም ዘግቧል።

    የባህሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የአየር ጥቃት ደወል በአገሪቱ መሰማቱን እና ዜጎች ተረጋግተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የአደጋ መጠለያ ቦታዎች እንዲገቡ በኤክስ ላይ መልዕክት አስተላልፏል።

  14. አሜሪካ በኢራን አዲስ ዙር ጥቃት ስትከፍት፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤ አገራትን አጠቃች

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኃይልን እንመታቸዋለን" በማለት ከተናገሩ በኋላ፤ የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተ።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የወደብ ከተሞች የሆኑትን ሲሪክን እና ባንደር አባስን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍሎች ፍንዳታ መከሰቱን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ትራምፕ ከአዲሱ ጥቃት በኋላ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ይህ ትናንት በኢራን ለተፈጸመው የመርከቦች ድብደባ የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ ነው። በድጋሚ ከተፈጠረ፤ ከዚህም የባሰ ይሆናል” ብለዋል።

    ከአሜሪካ እርምጃ በኋላ የባህረ ሰላጤው አገራት በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል። በባህሬን ዋና ከተማ መናማ ፍንዳታዎች መከሰታቸው የተገለጸ ሲሆን ኩዌት ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ማክሸፏን አስታውቃለች። ኳታር የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

    የኢራን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የፓርላማው አፈ ጉባኤ ሞሀማድ ባገር ጋሊባፍ፤ ዋሽንግተን “ጉልበተኝነት እና ቃል ኪዳንን ማጠፍ ዋጋ የማያስከፍሉ አለመሆናቸውን አሁንም አልተማረችም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    "በግልጽ ላስቀምጠው፤ ካጠቃችሁ፤ ትመታላችሁ” ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚከፈተው ኢራን በምትዘረጋው አሰራር እንጂ "በአሜሪካ ዛቻ" እንዳልሆነ ገልጸዋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “የኢራንን በንግድ መርከቦች እና በንጹኃን ሲቪል ባሕርተኞች ላይ ጥቃት የማድረስ አቅም ይበልጥ ለማዳከም” እንደሆነ አስታውቋል።

    ዕዙ ባወጣው መግለጫ በኢራን የሚገኙ 90 ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል። በኢራን የባሕር ዳርቻ የሚገኙ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች እና የወታደራዊ ሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶች ጥቃት ከደረሰባቸው ዒላማዎች መካከል እንደሆኑም አስታውቋል።

    ዕዙ፤ “የአሁኖቹ ጥቃቶቹ ትናንት ምሽት የታዩትን ስኬታማ የማጥቃት እርምጃዎች የተከተሉ ናቸው” ብሏል።

    ኮናራክ እና ቻባሃር የተባሉ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል።

    የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጸው ባንደር አባስ ከተማ ውስጥ ስምንት ፍንዳታዎች ተከስተዋል። በደቡብ ኢራን የሚገኙት ሲሪክ እና ጃስክ ወደቦች ደግሞ በሁለት ሚሳዔሎች መመታታቸውን ገልጿል።

    ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚወዛገቡበት አቡ ሙሳ ደሴትም ሁለት ጊዜ ጥቃት እንደደረሰበት ተዘግቧል።

    የአሜሪካ ጥቃቶች ያደረሱት የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጂ ቻባሃር ውስጥ የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠመ እና ቡሸህር ውስጥ በሚገኝ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጦር ሰፈር እሳት መነሳቱን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

  15. አሜሪካ ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ትራምፕ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ዛሬ ምሽት በኢራን ላይ በድጋሚ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ተናገሩ።

    ትራምፕ ይህን ያሉት በኔቶ ጉባኤ ላይ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።

    በመግለጫው ላይ ኢራንን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ባለፈው ምሽት በከባዱ መትተናቸዋል፤ በጣም በጣም በከባዱ” ያሉ ሲሆን፣ አገራቸው ምናልባት ዛሬ ምሽት በድጋሚ ከባድ ጥቃት እንደምትፈፅም ተናግረዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም "ትንሽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻቸዋለሁ፤ ዛሬ ማታ በድጋሚ በከባዱ እንመታቸዋለን” ብለዋል።

    በኢራን ደስተኛ እንዳልሆኑ የገለፁት ትራምፕ፣ ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያ መታጠቅ እንደማይፈቀድላት አሜሪካ ያላትን አቋም ደግመው ገልጸዋል።

    ትራምፕ “ሙሉ ጉዳዬ ስለአገዛዝ ለውጥ አይደለም” ሲሉም የአገሪቷን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማስቆም የሚያስችሉ ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን አክለዋል።

    “ኢራን ከዚህ በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል አይደለችም” ሲሉም የኢራንን አስተዳደር አጣጥለዋል።

  16. በኢራን ላይ ጥቃት ከተከፈተ በኋላ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የእስራኤል ጉብኝታቸውን ሰረዙ

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት መባባሱን ተከትሎ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ዛሬ ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረውን ጉዟቸውን እንደሰረዙ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

    ሄግሴት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ጉባኤ ለመታደም ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ቱርክ ነበሩ።

    ሚኒስትሩ ዛሬ ወደ እስራኤል ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት እቅድ በአሜሪካም ሆነ በእስራኤል በይፋ አልተገለፀም።

    ሆኖም በርካታ የዜና አውታሮች ጉብኝታቸው ኤፍ35 ተዋጊ ጄቶችን ለቱርክ የመሸጥ ሃሳብን በተመለከተ እስራኤል በሚኖራት ስጋት ላይ የሚደረግ ውይይትን እንደሚያካትት ዘግበዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በዓለም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የሆነው ኤፍ35 ተዋጊ ጄቶችን እና ተመሳሳይ የጦር መሣሪያዎችን ለቱርክ መሸጥ "ስህተት" እንደሚሆን ተናግረዋል።

    እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር ከመሆኗ ባሻገር በቀጣናው ብቸኛዋ የኤፍ-35 ጄት ባለቤት ናት።

    የጦር መሣሪያ አምራቹ ሎክሄድ ማርቲም መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ ኤፍ-35ኤ የጦር ጀት 82.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያወጣል።

    እስራኤልም ሆነች አሜሪካ በመከላከያ ሚኒስትሩ ጉዞ መሰረዝ ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።

  17. በሺዎች የሚቆጠሩ መርከበኞች በሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ ተገለፀ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ መርከቦች ላይ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፣ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በመርከቦች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሰላም መውጣት ባልቻሉ መርከቦች ላይ ያሉ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ መርከበኞችን "ስጋት እና የሥነ ልቦና ጫና ይበልጥ ያባብሰዋል" ብለዋል።

    መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ እና ኢራን ወሽመጡን ለማስከፈት የሚያስችል ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ መርከበኞች በባሕረ ሰላጤው እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ መቆየታቸውን ዶሚንጌዝ አስታውሰዋል።

    ዋና ፀሐፊው አሁንም አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት መርከቦች በሰላም እንዲወጡ ሁለቱም ወገኖች ሳይረፍድ ሁኔታውን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርበዋል።

    ከዓለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶ የሚጓጓዝበት ሆርሙዝ ወሽመጥ ከመዘጋቱ በፊት በየቀኑ 138 ገደማ መርከቦች ይተላለፉበት ነበር።

    ኢራን ወሽመጡን ከዘጋች በኋላ 1 ሺህ150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራተኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገድደዋል።

  18. መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያቋርጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

    የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት በመርከቦች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በማውገዝ የባሕር ትራንስፖርት ኩባንያዎች መርከቦቻቸውን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳይልኩ አሳሰበ።

    ይህ ማሳሰቢያ የተሰማው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን የአጻፋ እርምጃ ከወሰደች በኋላ ነው።

    በሆርሙዝ ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ “በመርከቦች ላይ የሚፈጸመው የግድየለሽነት ጥቃት በድጋሚ የመርከብ ላይ ሠራተኞችን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ ጀምሯል” ሲሉ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ ተናግረዋል።

    “የመርከብ ላይ ሠራተኞች ደኅንነትን ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ አገራት፣ የመርከብ ባለቤቶች፣ የመርከብ ትራንስፖርት ተቋማት እና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ባሕርተኞችን ካላስፈላጊ አደጋ ለመጠበቅ ሲሉ በሆርሙዝ በኩል ከመተላለፍ እንዲቆጠቡ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

    በጦርነቱ ምክንያት ለወራት ተዘግቶ የነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የመርከቦች እንቅስቃሴ ጨምሯል።

    የዓለማችን 20 በመቶ የነዳጅ እና የጋዝ ምርት በሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ሦስት መርከቦች ላይ ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ እስካሁን ለጥቃቶቹ ኃላፊነቱን የወሰደ የለም።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን አሳውቀዋል።

    ይህም በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ዳግም ውጥረት እንዲያገረሽ ያደረገ ሲሆን፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ስጋት ላይ ጥሎታል። በዚህም ምክንያት ቀንሶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተዘግቧል።

  19. ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “እንዳበቃ” ከተናገሩ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ተፈረመው ጊዜያዊ ስምምነት “አብቅቷል” ማለታቸውን ተከትሎ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በስድስት በመቶ ጨመረ።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው አስቀድሞ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ76 ዶላር በታች ሲሸጥ ነበር። ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከስድስት በመቶ በላይ በመጨመር 78.73 ዶላር መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሁኑ ጭማሪ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው እንደሆነም ተገልጿል። በኢራን ጦርነት ምክንያት ዋጋው አሻቅቦ ወራትን ያስቆጠረው ነዳጅ፤ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለመቋጨት የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ቅናሽ አሳይቶ ነበር።

    ይሁን እንጂ ከትናንት ሌሊት አሜሪካ የኢራን ይዞታዎችን ከደበደበች በኋላ መጨመር ጀምሯል። አሜሪካ ጥቃቱን የፈጸመችው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዙ የነበሩ ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በመመታታቸው እንደሆነ ገልጻለች።

    ለዋሽንግተን ጥቃት አጸፋ የሰጠችው ኢራን በበኩሏ፤ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ዒላማ ማድረጓን አስታውቃለች።

  20. የአሜሪካ ጥቃት በኢራኗ የወደብ ከተማ

    ሌሊት ላይ አሜሪካ በኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈጸሟን ካስታወቀች በኋላ ኢራንም በተመሳሳይ በባሕረ ሰላጤው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መምታቷን ገልጻለች።

    ይህ ቪዲዮ በኢራኗ የወደብ ከተማ ባንዳር አባስ በአሜሪካ ጥቃት ያጋጠመውን ፈንዳታ ያሳያል።