ትራምፕ በቀይ ካርድ ስለተቀጣው ተጫዋች ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸውን አረጋገጡ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸው ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች በቀይ ካርድ ምክንያት የተጣለበትን የአንድ ጨዋታ ቅጣት እንዲያጤነው ፊፋን መጠየቃቸውን አረጋገጡ።
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ በአሜሪካው አጥቂ ፎላሪን ባሎገን ላይ የተጣለውን እገዳ ማንሳቱ “ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ያሉት ትራምፕ ውሳኔው ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ በውድድሩ ላይ “ከፍተኛ ጠባሳ” ይጥል ነበር ብለዋል።
በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ተጫዋች ቀጣይ ጨዋታ እንዳይሰለፍ ቅጣት የሚጣልበት ቢሆንም ፊፋ ባልተለመደ ሁኔታ የአሜሪካዊውን ተጫዋች ቅጣት ለ12 ወራት ተግባራዊ እንዳይሆን አግዶታል።
ጉዳዩን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ዋይት ሐውስ ውስጥ እንደተናገሩት ቀይ ካርድ የተሰጠበት ድርጊት “ጥፋት ነው ብለው” ባለማመናቸው ፊፋ ቅጣቱን እንዲያጤነው ጠይቀዋል።
ትራምፕ ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር መነጋገራቸውን አረጋግጠው፤ በተጫዋቹ ላይ የተጣለው ቅጣት እንዲታገድ ሳይሆን ውሳኔው እንደገና እንዲታይ መጠየቃቸውን ብቻ ነው ያመለከቱት።
ትራምፕ ለተጫዋቹ ቀይ ካርድ መሰጠት የሌለበት አጋጣሚ እንደነበር እና ጨዋታውን የመሩትን የብራዚላዊን ዳኛ ውሳኔ “አስቀያሚ” በማለት ለተፈጠረው ችግርም ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቀው የፊፋ ውሳኔ ከአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበር፣ ከቤልጂየም እና የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከበርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ከባድ ትችት ገጥሞታል።
አሜሪካዊው ተጫዋች ጥፋቱን የፈጸመው ብሔራዊ ቡድኑ ከቦሲኒያ ኤርዜጎቪና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ሲሆን፣ አሜሪካ ወሳኝ ተጫዋቿን በቀይ ካርድ ብታጣም ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለቀጣይ ጨዋታ አልፋለች።
ለአሜሪካ ከፍተኛውን ግብ በማስቆጠር ተጠባቂ የሆነው ፎላሪን ባሎገን በጨዋታው በቀይ በመውጣቱ ነገ ማክሰኞ ከቤልጂየም ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፍ ታውቆ ነበር።
ነገር ግን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ፊፋ የቀይ ካርድ ቅጣቱን ተግባራዊነት በማገዱ አሜሪካ ከቤልጂየም ጋር በሚኖራት ወሳኝ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል አግኝቷል።