ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፅ/ቤት ኃላፊ ሾሙ

በዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ 47ኛ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከመመለሳቸው በፊት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቻቸውን ለመሾም ተዘጋጅተዋል። ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ያልተቋጩ ሥራዎችን ጨርሰው ሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል። ትራምፕ የዋይት ሐውስ ፅ/ቤት ኃላፊ ሹመዋል። ቢቢሲ አማርኛ የአሜሪካ ምርጫ ሂደትን የተመለከቱ ዘገባዎች በዚህ ገጽ በቀጥታ ያቀርባል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ
  • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለትራምፕ ‘የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት’ አስተላለፉ
  • ትራምፕ “አስደናቂ ድል ተቀዳጀሁ” አሉ
  • ትራምፕ ፕሬዝዳንት ለመሆን ሲቃረቡ፣ ሪፐብሊካኖች በሁለቱም ምክር ቤቶች የበላይነት እየያዙ ነው
  • ሪፐብሊካኖች የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ይቆጣጠራሉ- ትንበያ
  • የምርጫ ጣቢያዎች ተዘጉ፤ ዲሞክራቶች በፍራቻ ላይ ሲሆኑ ሪፐብሊካን ደስታቸውን እየገለጹ ነው
  • ትራምፕ ወሳኝ የምትባለውን የሰሜን ካሮላይና ግዛትን አሸነፉ
  • የአሜሪካዊ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤት እንደ ሩሲያ እና ቻይና ላሉ ኃያላን ሀገራት ምን ይፈይዳል?
  • የፕሬዚዳንታዊ እጩዎቹ የምርጫ ዘመቻ በእምነት ላይ የተመሰረተ ነው?
  • የአይዋ ግዛት ለምን የትኩረት ማዕከል ሆነች?
  • “የጋዛን ጦርነት ለማስቆም የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ” ካማላ ሃሪስ
  • ከምርጫው ቀን በፊት ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምጽ ሰጥቷል
  • እስካሁን ባለው ሂደት ከ78 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ይህም ከአራት ዓመት በፊት የነበረውን የመጀመሪያ መራጮች ተሳትፎ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው

የቀጥታ ሽፋን

  1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የትኛው ፓርቲ በበላይነት ይይዛል?

    ዋይት ኃውስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዋይት ሐውስ

    ዋይት ሐውስ እና የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ከዲሞክራቶች እጅ ወጥተዋል። ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት ሲሆኑ ሴኔቱ ደግሞ በሪፐብሊካኖች የበላይነት ተይዟል።

    ነገር ግን የተወካዮች ምክር ቤት የበላይነቱን የትኛው ፓርቲ ይይዛል የሚለው እስካሁን አልተወሰነም።

    አሁን ባለው ሁኔታ የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ 211 መቀመጫዎችን እንደሚያሸንፍ ተገምቷል። ነገር የምክር ቤቱን የበላይነት ለማግኘት 218 መቀመጫዎቸን ማግኘት አለበት። በተቃራኒው ዲሞክራቶች እስካሁን ያገኙት መቀመጫ 199 ነው።

    25 መቀመጫዎች እስካሁን አሸናፊያቸው ያልታወቀ ሲሆን ውጤታቸው በቅርቡ ይገለፃል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሪፐብሊካኖች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የበላይነት ካገኙ ሶስቱንም የመንግሥት መዋቅሮች ተቆጣጠሩ ማለት ነው። ይህ ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ያሻቸውን አጀንዳ ከማራመድ የሚያግዳቸው አይኖርም።

    ዲሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ከተቆጣጠሩት ምናልባት ለትራምፕ የሥልጣን ዘመን የተመቹ እንደማይሆን ይጠበቃል።

    ነገር ግን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደሚገምተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የበላይነት ሪፐብሊካኖች ሊወስዱት ይችላሉ።

  2. ትራምፕ አዲስ የፕሬዝደንት ፅ/ቤት ኃላፊ ሾሙ

    ሱዛን ዋይልስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሱዛን ዋይልስ የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያዋ ሹመኛ ሆነዋል።

    በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን “እጅግ የተፈሩ እና ብዙም ዕውቅና የሌላቸው ፖለቲከኛ” ተብለው የተገለፁት ሱዛን የፕሬዝንቱ ፅ/ቤት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

    ባለፈው ሚያዚያ ፖለቲኮ ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሱዚ “ወግ አጥባቂ ከሚባል ማኅበረሰብ የመጣሁ ነኝ” ማለታቸው ይታወሳል።

    የዋይት ሐውስ ፅ/ቤት ኃላፊ ማለት ከፍተኛ ሹመት ሲሆን በፕሬዝደንቱ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሥልጣን ነው።

    የፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት ኃላፊ በሌላ ቋንቋ የዋይት ሐውስ አስተዳዳሪ አሊያም የፕሬዝደንቱን ሚኒስትሮችን መልማይ ማለት ነው። አልፎም የፕሬዝደንቱን የየዕለት ተግባራት የመቆጣጠር ኃላፊነትም የዚህ ፅ/ቤት ነው።

    የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እንዳለው ሱዛን ዋይልስ የመጀመሪያዋ ሴት የዋይት ሐውስ ፅ/ቤት ኃላፊ ይሆናሉ።

    ዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ማሸነፋቸውን ባወጁበት ምሽት ሱዚ ዋይልስን ለድሉ አስተዋፅዖ ካበረከቱ ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው ሲሉ ምስጋና ችረዋቸዋል።

    በ1980ዎቹ የዶናልድ ሬገን የምርጫ ቅስቀሳን በመቀላቀል ወደ ፖለቲካ የገቡት ሱዚ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተዋወቁት በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር።

  3. ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ያልተቋጩ ሥራዎችን ጨርሰው ሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ አሳወቁ

    ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለተተኪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ስልክ ደውለው የእንኳ ደስ ያለዎት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።

    ባይደን አክለው ከዲሞክራቷ ዕጩ ካማላ ሀሪስ ጋር እንደተናጋገሩ አስታውቀው “መልካም አጋር እና የሕዝብ አገልጋይ” ናት ብለዋል።

    የካማላ የምርጫ ዘመቻን “አነቃቂ” ሲሉ ያሞገሱት ባይደን ምክትል ፕሬዝደንቷ በሥራቸው እንዲኮሩ መክረዋል።

    “አንዲት ሀገር ምርጫዋ አንድ ነው። ሕዝቡ የሚመርጠውን እንቀበላለን” ያሉት ባይደን “ስናሸንፍ ብቻ አይደለም ሀገራችንን የምንወደው፤ ስንስማማ ብቻ አይደለም ጎረቤታችንን የምንወደው” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ባይደን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንደሚኖር አስታውቀዋል። የምርጫ አስተባባሪዎችም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

    ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥር 12/2017 በኦፊሴላዊ መንገድ መንበረ-ሥልጣኑን ይረከባሉ።

    የ2024 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ “ታሪካዊ ነው” ያሉት ባይደን በሚቀጥሉት 74 ቀናት ያልተቋጩ ሥራዎችን ጨርሰው ሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ አሳውቀዋል።

    “መሸነፍ ያለ ነው። ነገር ግን ተስፋ መቁረጥ ይቅር የማንለው ነው” ብለዋል ባይደን።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ካሸነፉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ንግግር ያሰሙት ባይደን ደጋፊዎቻቸው “በእምነታቸው እንዲፀኑ” አሳስበዋል።

  4. ትራምፕ ቢያሸንፉም ዋይት ሃውስ የሚገቡት ከ74 ቀናት በኋላ ነው

    ትራምፕ እና ባለቤታቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡም ወደ ዋይት ሃውስ ለመግባት ከሁለት ወራት በላይ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

    ተመራጩ ፕሬዚዳንት በአሁኑ ወቅት በይፋ ፕሬዚዳንት ሆነው አልተሰየሙም።

    የአሜሪካ የስልጣን ርክክብ ለምሳሌ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ካሉ አገራት የተለየ ነው።

    ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ኬይር ስታርመር ማሸነፋቸው በታወቀበት እና የምርጫው ጣቢያዎች በተዘጉበት በሰዓታት ውስጥ ነው በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት።

    በወቅቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እቃዎቻቸውን ሸክፈው አልወሰዱም ነበር።

    ትራምፕ ሲመታቸው ከጥር 12/ 2017 ዓ.ም በፊት አይከናወንም። ጆ ባይደን ተግባራቸው የተገደበ ቢሆንም እስከዚያው ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ።

  5. “ጨለማ ዘመን ውስጥ እየገባን አይደለም” ካማላ ሃሪስ

    ካማላ ሃሪስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በምርጫው የተሸነፉት የዲሞክራት እጩ ካማላ ሃሪስ “በርካቶች ጨለማ ዘመን ውስጥ እየገባን እንደሆነ እየተሰማቸው ነው። ይህ እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናገሩ።

    በቀድሞ ዩኒቨርስቲያቸው ሃዋርድ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ካማላ ሃሪስ “በጨለማ ውስጥ ነው ከዋክብትን ማየት የሚቻለው” ሲሉም ደጋፊዎቻቸውን አበረታትዋል።

    ደጋፊዎቻቸው በአዎንታዊ መንፈስ እንዲቀጥሉም ጥሪ አድርገዋል።

    ሃሪስ የአሜሪካ ህዝብ በተለይም የዲሞክራሲ ደጋፊዎችን “ተስፋ አትቁረጡ። አሁንም ኃይል አላችሁ” ብለዋል።

    ምርጫው በትራምፕ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ “ሰዎች ትግላቸውን እንዳያቆሙም” ተናግረዋል።

    “አሁን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀምጥበት ጊዜ አይደለም” ሲሉም ተደምጠዋል።

    “ለነጻነት እና ለፍትህ እንዲሁም ሁላችንም በጋራ መገንባት እንደምንችል ለምናውቀው የወደፊት ለመደራጀት፣ ለመቀስቀስ እና ለመሳተፍ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

    በተለይም ወጣት ደጋፊዎቻቸውን “ሁሉ ጥሩ ይሆናል” ሲሉ አጽናንተዋል።

    ሃሪስ ለምትመለከቱኝ ወጣቶች ሲሉ በርካቶች ድጋፋቸውን በጩኸት የገለጹላቸው ሲሆን “ ማዘን እና መከፋት ምንም አይደለም። ነገር ግን ማወቅ ያለባችሁ ሁሉ ጥሩ እንደሚሆን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    “አንዳንድ ጊዜ ትግሉ ጊዜ ይወስዳል ይህ ማለት አናሸንፍም ማለት አይደለም”

    “ለአገራችን የሚደረገው ትግል ሁልጊዜም ዋጋ ያለው ነው” ብለዋል።

  6. ሁለተኛው የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ምን ሊመስል ይችላል?

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ለአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን በሁለተኛው ዙር እንዴት ሊሆን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ይላሉ።

    ዶናልድ ትራምፕ አሁን ሥልጣን መልሰው ሲጨብጡ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ማድረግ ካቆሙበት እንደሚቀጥሉ ብዙዎች ያምናሉ።

    አንደኛው ያልተጠናቀቀው ፕሮጀክት የአሜሪካን ደቡባዊ ድንበርን መዝጋት እና የድንበር አጥር ግንባታ ግንባታን ማጠናቀቅ ነው። ይህ የመጀመሪያው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ማሳያ ነው። የድንበር አጥሩን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ የአገሪቱ ኮንግረስ አልፈቀደላቸውም።

    ግንባታውን በማጠናቀቅ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የገቡትን ቃል ይጠብቃሉ ተብሎ ይገመታል።Link

  7. ካማላ ሃሪስ ሽንፈታቸውን ተቀብለው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ ተነጋገሩ

    ካማላ ሃሪስ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆነው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተፎካከሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ሽንፈታቸውን ተቀብለው ለተመራጩ ፕሬዝዳንት መልካም ምኞታቸውን ገለጹ።

    ትራምፕ በምርጫው አሸናፊ የሚያደርጋቸውን ድምጽ ማግኘታቸውን ተከትሎ ረቡዕ ማለዳ ላይ የአሸናፊነት ንግግር ካደረጉ በኋላ ውጤቱን ተቀብለው በይፋ መግለጫ ይሰጣሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሃሪስ፣ በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ለትራምፕ ስልክ ደውለው እንኳን ደስ አለዎ ማለታቸው ተዘግቧል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ሃሪስ ለትራምፕ ስልክ ደውለው የ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን በማሸነፋቸው ውጤቱን መቀበላቸውን የሚያመለክት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

    አንድ የሃሪስ ከፍተኛ ረዳት ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ከትራምፕ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ጊዜ በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ላይ እና ለሁሉም አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት በመሆን ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ ከሰዓታት በኋላ በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ ለሕዝቡም መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  8. ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከመመለሳቸው በፊት የሚቀሩት ሂደቶች የትኞቹ ናቸው?

    ትራምፕ ከሚስታቸው እና ከልጃቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ከሚስታቸው እና ከልጃቸው ጋር

    በበርካታ ክሶች ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የከረሙት እና በሳምንታት ልዩነት ውስጥ ከተቃጡባቸው ሁለት የግድያ ሙከራዎች ተርፈው ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳት ለመሆን ድምጽ ያገኙት ዶናልድ ትራምፕ ለዓመታት የዓለም መነጋገሪያ ርዕስ ሆነው ቆይተዋል።

    አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ዙር አራት ዓመታት የሥልጣን ዘመን የኃያሏ አገር የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዝዳንት መንበርን ለመረከብ ከሁለት ወራት ብዙም ያልበለጠ ጊዜ መጠበቅ አለባቸው።

    ከዚያ በፊት ግን የአሜሪካ ግዛቶች በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ያላቸው የመራጭ ድምጽ (ኤሌክቶራል ኮሌጅ) ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ። በዚህም መሠረት ግዛቶቹ ባላቸው የሕዝብ ብዛት መሠረት የተመደባላቸውን የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ እያንዳንዱ ግዛት የአብዛኛው ሕዝቡ ድምጽ ለሰጠው ዕጩ በይፋ አጠቃለው ይሰጣሉ።

    ይህም የሚረጋገጠው በታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም. ከሚደረገው ስብሰባ በኋላ ነው።

    ከዚያም አዲሱ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያውን ስብሰባ ሰኞ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም. በማድረግ በይፋ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከግዛቶች ያገኙትን የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ በመቁጠር የአዲሱን ፕሬዝዳንት መመረጥ ያጸድቃሉ።

    የወቅቱ ፕሬዝዳንት የጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን የሚጠናቀቀቀው እሁድ ጥር 11/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በተከታዩ ቀን ሰኞ በሚካሄደው ሲመተ በዓል ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ቃለ መሐላ ፈጽመው ወደ ዋይት ሐውስ ይገባሉ።

  9. ባለፉት ጥቂት ሰዓታት የአሜሪካ ምርጫ ዋና ዋና ሁነቶች

    ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ
    • ዶናልድ ትራምፕ ካማላ ሃሪስን በማሸነፍ ለታሪካዊው ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል።
    • ትራምፕ የሚያስፈልጋቸውን 270 የመራጮች ድምጽ በላይ በማግኘት ነው አሸናፊነትን የተቀዳጁት።
    • አሸናፊነታቸው ዕውን መሆኑን ተከትሎ ፍሎሪዳ ውስጥ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ሕዝብ “ከዚህ በፊት ያልታየ እና ኃያል ሥልጣን” እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
    • የትራምፕ በምርጫው አሸናፊ መሆንን የሚያመለክተው አሃዝ መታወቁን ተከትሎ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
    • ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከምጣኔ ሀብት አንጻር “የዋጋ ግሽበትን በማብቃት፣ በአሜሪካ [ምርት እና አገልግሎቶች] ርካሽ እንዲሆኑ አደርጋለሁ” ብለው ነበር።
    • በተጨማሪም ስደተኞችን በተመለከተ አሜሪካን እና ሜክሲኮን በሚያዋስነው ድንበር ላይ የሚገነባው የድንበር አጥር እንዲጠናቀቅ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
    • የምርጫ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እስካሁን ተጠቃሎ ያልገባ ሲሆን የኔቫዳ፣ የሚቺጋን እና የአሪዞና ግዛቶች ውጤቶች እየተጠበቁ ነው። ቢሆንም ግን የእነዚህ ግዛቶች ውጤት በትራምፕ አሸናፊነት ላይ ተጨማሪ ቁጥር ይጨምሩ ይሆናል እንጂ ለውጥ አያስከትሉም።
    • በምርጫው ሪፐብሊካኖች ፕሬዝዳንታዊ ዕጯቸውን በማስመረጥ ብቻ አይደለም ድል የቀናቸው፤ በአገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ውስጥ በዲሞክራቶች ተይዞ የነበረውን የበላይነት ነጥቀዋል።
    • በምርጫው ከ223 በላይ ብቻ የመራጮች ድምጽ በማግኘት ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን ድምጽ ሳያገኙ የቀሩት ዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ እስካሁን ስለምርጫው እና ስለሽንፈታቸው ምንም አላሉም።
    • ከዚህ በፊት እንደሚደረገው አሸናፊው የድል ንግግሩን ሲያደረግ ተሸናፊ ደግሞ ሽንፈቱን ተቀብሎ ለአሸናፊው መልካም ምኞቱን ይገልጻል። ካልሆነም ቅሬታውን ለሕዝብ ያቀርባል፤ ሃሪስም ይህንን ማድረጋቸው ስለማይቀር በጉጉት እየተጠበቁ ነው።
  10. “የአሜሪካ 47ኛ እና 45ኛ ፕሬዝዳንት እንድሆን ስለመረጣችሁኝ አመሰግናለሁ”

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, “የአሜሪካ 47ኛ እና 45ኛ ፕሬዝዳንት እንድሆን ስለመረጣችሁኝ አመሰግናለሁ”

    45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ በጆ ባይደን ተሸንፈው ከተሰናበቱ ከአራት ዓመታት በኋላ 47ኛው ፕሬዝዳንት ለመሆን ተመርጠው በመጪው ጥር ወደ ዋይት ሐውስ ይመለሳሉ። ለዚህም አሜሪካውያንን አመስግንው ያለዕረፍት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል።

  11. በአሜሪካ ታሪክ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በድጋሚ የተመረጡ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት

    ዶናልድ ትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ከሚሆኑት ጄ ዲ ቫንስ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ከሚሆኑት ጄ ዲ ቫንስ ጋር

    ታሪካዊ በሆነው ምርጫ ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚያስችላቸውን የበላይነት ያገኙት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ዋይት ሐውስ ሊመለሱ ነው።

    እስካሁን በተገኘው ውጤት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣንን መልሶ ለመያዝ ከሚያስችላቸው 270 የግዛቶች ድምጽ ከ279 በላይ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

    ትራምፕ ከአራት ዓመታት በፊት በጆ ባይደን ከተሸነፉ በኋላ በከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብተው ነበር።

    ደጋፊዎቻቸው የአገሪቱን ምክር ቤት እንዲወሩ አድርገው ተጭበርብሯል ያሉትን የምርጫ ውጤት በኃይል ለመቀልበስ ሞክረዋል በመባላቸው የፖለቲካዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ ይሆናል ተብሎ ነበር።

    በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተለይም በመዋሸት እና በማጭበርበር ከ90 በላይ ተደራራቢ ክሶች ቀርቦባቸው ለዓመታት ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የቆዩ ሲሆን፣ አሁንም ክሳቸው ዕልባት አላገኘም።

    በተጨማሪም በዘመናዊ የአሜሪካ የፕሬዝዳንቶች ታሪክ ውስጥ ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የተመረጡት የመጀመሪያውን የፕሬዝዳንትነት ጊዜያቸውን ተከትሎ ነበር።

    በዚህም ሳቢያ ትራምፕ ዋይት ሐውስን ከለቀቁ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መወዳደራቸው ውጤት አያስገኝላቸውም ተብሎ ነበር። ነገር ግን በአሜሪካ የፕሬዝዳንትነት ታሪክ በተለያየ ጊዜ በድጋሚ የተመረጡ ሁለተኛው ሰው ሆነዋል።

    በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ባልሆነ የሥልጣን ዘመን በሌላ ዙር ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡት የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ግሮቨር ክሌቭላንድ ናቸው።

    ፕሬዝዳንት ክሌቭላንድ በአውሮፓውያኑ ከ1885 እስከ 1889 በሥልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በቀጣዩ ምርጫ ተሸንፈው፤ ከአራት ዓመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በመወዳደር ተመርጠው ከ1893 እና 1897 ድረስ በድጋሚ አገልግለዋል።

  12. የትኞቹ ግዛቶች ወሳኙን ድምጽ ለትራምፕ ሰጡ?

    ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በመሆን አሸናፊ ሆነዋል። በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ከባድ ፉክክር በተደረገበት እና አሸናፊውን ቀድሞ ለመለየት አዳጋች በነበረው በዚህ ምርጫ ትራምፕ ከፍተኛውን የግዛቶች የምርጫ ድምጽ አግኝተው አሸናፊ ሆነዋል። ገና ውጤታቸው ሙሉ ለሙሉ ያልታወቁ ግዛቶች ቢኖሩም አሁን ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ተለይተዋል። የትኞቹ የአሜሪካ ግዛቶች ያላቸውን ወሳኝ ድምጽ ለማን ሰጡ?

    ካርታ
  13. ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ከስምንት ዓመት በፊት ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ ምርጫውን አሸንፈው አሜሪካን ለቀጣይ አራት ዓመታት ለመምራት ወደ ዋይት ሃውስ ይመለሳሉ።

    የ78 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው አስደናቂ ድል ተቀዳጀሁ” ሲሉ ድላቸውን ቀድመው አብስረዋል።

    አክለውም “ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ታላቅ ድል ነው፤ አሜሪካን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል” ሲሉም የምርጫ ዘመቻ መፈክራቸውን በመጠቀም ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫው ወሳኝ በሚባሉት ሰሜን ካሮላይና፣ ዊስኮንሰን፣ ፔንስልቬንያ እና ጆርጂያ ግዛቶችን ማሸነፋቸውን ተከትሎ 47ኛ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ያረጋገጡት።

    ትራምፕ ከሚያስፈልጋቸው 270 ኢሌክቶሪያል ኮሌጅ ውስጥ 279 በማግኘት አሸንፈዋል።

    የዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ሽንፈታቸውን አስመልክቶ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያልተነጋገሩ ሲሆን የመጨረሻው ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ነበር ደጋፊዎቻቸው የመመልከቻ ማዕከሏ ስፍራን ለቀው የሄዱት።

    በተጨማሪም ሪፐብሊካኖች የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔትን) አብላጫ ድምጽ በመያዝ የዲሞክራቶችን የበላይነት ወስደዋል።

  14. የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የሚታወቀው መቼ ነው? ድምፅ የሚቆጠረውስ እንዴት ነው?

    የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት

    አሜሪካዊያን ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አምርተው ለፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

    እርግጥ ነው በዩናይትድ ስቴትስ ሰዓት አቆጣጠር መሠረት ድምጽ መስጠቱ በአብዛኞቹ ግዛቶች ማክሰኞ ከሰዓት አካባቢ ተጀምሮ ረቡዕ ማለዳ ተጠናቋል።

    የድምፅ መስጫው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላም አሸናፊው ወይም አሸናፊዋ ለሰዓታት ላይታወቁ ይችላሉ። ሰዓታት ብቻ አይደለም፤ ቀናት አሊያም ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።

    በአሁኑ ምርጫ ግን ረቡዕ ረፋድ ላይ ዶናልድ ትራምፕ አብላጫውን በመያዝ በሰፊ ልዩነት ካማላ ሃሪስን በመምራታቸው አሸናፊነታቸው ዕውን እየሆነ ነው።

    እነሆ ስለምርጫው ውጤት ሊያውቋቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮችን እዚህ በዝርዝር ይመልከቱ የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የሚታወቀው መቼ ነው? ድምፅ የሚቆጠረውስ እንዴት ነው?

  15. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለትራምፕ እንኳን ደስ አለዎት አሉ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    የፎቶው ባለመብት, PM office

    የአሜሪካ የምርጫ ውጤት በይፋ ባይገለጽም የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ድል አድርጌያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላለፉ።

    በምርጫዎ ድልዎት እና ወደ ስልጠን በመለለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

    አክለውም “በእርስዎ የስልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት በበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሰራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  16. ትራምፕ ለአሜሪካ ከፈጣሪ የተላኩ መሪ ናቸው ብለው የሚያምኑት ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖች

    ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ሲጸልዩ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ሲጸልዩ

    በድሃ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናትን በማቋቋም፣ በባይብል ቤልት ውስጥ ያሉ ፓስተሮች በአማኞች መካከል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ብዙዎቹንም ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ ወግ አጥባቂ መስመር ይመራሉ።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ትራምፕ ለዚህ ቡድን ምርጥ መዘወሪያ ሆነዋል።

    የኦክላሆማው ፓስተር ጃክሰን ላህሜየር የትራምፕ ታማኝ ደጋፊ ናቸው።

    “ፓስተርስ ፎር ትራምፕ” [ትራምፕን የሚደግፉ ፓስተሮች] የተሰኘው ቡድን መሥራች የሆኑት ላህሜየር “ይህችን አገር እንዲያስተዳድር ትራምፕ በእግዚአብሔር ተልኳል” ብለዋል።

    ዓላማቸውም በሚቀጥለው ምርጫ ትራምፕን ለመደገፍ “የወንጌላዊውንን ድምጽ ማሰባሰብ” ነው።

    በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከግድያ ሙከራ መትረፋቸውን “መለኮታዊ ተአምር ነው” በማለት ላህሜየር ጠርተውታል።

    የቀድሞ የሴኔት ዕጩ ተወዳዳሪ በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “አገራችን ለእርስ በርስ ጦርነት አንድ እርምጃ ቀርቷታል” ብለዋል።

    የፕሮቴስታንት ፓስተሮቹ እና የፖለቲካ አክቲቪስቶቹ እንደ ክርስቲያን ብሔርተኛ ለመቆጠር ፈቃደኛ አልሆኑም።

    “ይህ መገናኛ ብዙኃን እኛን ለዲሞክራሲ ስጋት አድርገው ለመሳል በላያችን ላይ የጫኑት ስም ብቻ ነው። እውነት ግን አይደለም” ብለዋል። ሙሉውን እዚህ ያንብቡ ትራምፕ ለአሜሪካ ከፈጣሪ የተላኩ መሪ ናቸው ብለው የሚያምኑት ቀኝ ዘመም ክርስቲያኖች

  17. የአነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ የሕይወት ታሪክ - ከሪል ስቴት እስከ ፖለቲካ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድት ሦስት ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት በአሜሪካ ታዋቂ እና አነጋጋሪ ቢሊየነር ነበሩ።

    ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን የተወዳደሩት በአውሮፓውያኑ 2016 ነው። ነገር ግን በኒው ዮርክ ግዙፍ የሪል ስቴት ኩባንያ ባለቤት የሆኑትን ባለሀብት ከዚያም በፊትም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ነፍገዋቸው አያውቁም።

    ስማቸው ገናና መሆኑ እና ከዚህ ቀደም ለየት ባለ መልኩ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ጉምቱ ፖለቲከኞችን በመርታት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ሳያደርጋቸው አልቀረም። ቢሆንም አነጋጋሪው ፕሬዝደንት ከአራት ዓመታት በኋላ በምርጫ ተሸንፈው ከሥልጣን ተወግደዋል።

    ሥልጣን የለቀቁበትን ሽንፈታቸውን አሁን ድረስ በፀጋ ያልተቀበሉት የ78 ዓመቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ትራምፕ ድጋሚ መንበረ-ፕሬዝደንቱን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ሙሉውን ታሪክ እዚህ አንብቡ የአነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ የሕይወት ታሪክ - ከሪል ስቴት እስከ ፖለቲካ

  18. የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለትራምፕ ‘የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት’ አስተላለፉ

    ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንያሚን ናታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንያሚን ናታንያሁ

    የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ድል ማድረጋቸውን ማወጃቸውን ተከትሎ አንዳንድ የአለም መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

    “እንኳን ደስ አለዎት በታሪካዊው ታላቅ ድል። ወደ ዋይት ሃውስ ያደረጉት ታሪካዊ መመለስ ለአሜሪካ አዲስ ጅምር እና በእስራኤል እና በአሜሪካ ላለው ታላቅ ጥምረት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው” ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ተናግረዋል።

    አክለውም “ይህ ታላቅ ድል ነው” ብለዋል።

    የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው “በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታላቅ መመለስ ነው። ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቅ ድልዎ እንኳን ደስ አለዎ። ለዓለም በጣም መሰረታዊ ድል ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ በምርጫው ማሸነፋቸውን ቢያውጁም የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ እስካሁን አላገኙም። ከሚያስፈልጋቸው 270 ድምጽ አራት የጎደላቸው ሲሆን ካማላ ሃሪስ ያገኙት 218 ነው።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመርም በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕን “በታሪካዊው ድል” እንኳን ደስ አለዎት ብለዋቸዋል።

    በሚቀጥሉት ዓመታት ከእርስዎ ጋር ለመስራት በጉጉት እጠብቃለሁ “ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር

    “እንደ ቅርብ አጋርነታችን፣ የጋራ በሆኑት የነጻነት፣ የዲሞክራሲ እሴቶቻችንን ለመጠበቅ አንድ ላይ ቆመናል” ሲሉ አክለዋል።

  19. ትራምፕ “አስደናቂ ድል ተቀዳጀሁ” አሉ

    የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ የምርጫ ውጤት ተቆጥሮ ባያልቅም የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ “አስደናቂ ድል ተቀዳጀሁ” ብለዋል።

    ትራምፕ በመቀጠል ይህ የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን እንደሚሆን ተናግረዋል።

    “ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ታላቅ ድል ነው፤ አሜሪካን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል” ሲሉም የምርጫ ዘመቻ መፈክራቸውን በመጠቀም ተናግረዋል።

    ትራምፕ የሚያስፈልጋቸውን 270 የኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ማግኘታቸው ሳይታወቅ ድል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ድላቸውን ለደጋፊዎቻቸው በተናገሩበት የፍሎሪዳ መድረክ “አገራችን እንድትድን እንረዳታለን” ብለዋል።

    በድንበሮች ያሉ ጉዳዮችን እልባት እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ፓርቲያቸው እና እሳቸው ታሪክ የሰሩት በምክንያት ነው ብለዋል።

    ትራምፕ በዚህ የድል ንግግራቸው ይህችን ዕለት “በህይወታችሁ ጠቃሚ የምትባል ዕለት አድርጋችሁ እንደምትቆጥሯት” ተስፋ አለኝ ብለዋል።

    “አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ስልጣን ሰጥታናለች” በማለት ፓርቲያቸው የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱን የበላይነት ከዲሞክራቶች በመውሰድ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

  20. ሪፐብሊካኖች የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ይቆጣጠራሉ- ትንበያ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሪፐብሊካን ፓርቲ የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት፣ ሴኔትን በበላይነት ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ የውጤት ቆጠራዎችን መሰረት ያደረጉ ትንበያዎች አሳዩ።

    አሁንም ቢሆን የምርጫው ውጤቶች ተቆጥረው ባያልቁም ዲሞክራቶች የህግ የመወሰኛ ምክር ቤት የበላይነታቸውን እንደሚያጡ ግልጽ ሆኗል።

    ለሁለት ዓመታት ያህል ሴኔቱን ዲሞክራቶች በበላይነት ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም በኦሃዮ እና በዌስት ቨርጂኒያ የነበሩ የሴኔት መቀመጫቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ ሪፐብሊካን አብላጫ ድምጽ ማግኘታቸው ተገልጿል።

    ዲሞክራቶች ለሁለት ዓመታት ያህል የህግ መወሰኛውን ምክር ቤት በጠባብ አብላጫ እየመሩ ነበር።

    ይህም 47 ዴሞክራቶች እና አራት ገለልተኛ ሴናተሮች ለፓርቲው ከ100 መቀመጫዎች ውስጥ 51 በማግኘት በበላይነት ተቆጣጥረው ነበር። ነገር ግን ማክሰኞ፣ ሁለት ሴናተሮች መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣኑ ወደ ሪፐብሊካን እጅ ተመልሷል።