ትራምፕ አሜሪካንን በኢራን ላይ በሚካሄደው ጥቃት ለማሳተፍ አስቸኳይ ስብሰባ አድረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በኢራን ላይ እያካሄደችው ባለው ጥቃት ውስጥ አሜሪካ ስለምትሳተፍበት ሁኔታ ለመወያየት ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር አድርገዋል።
አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ በቆየው ስብሰባ ላይ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ውስጥ አሜሪካ መሳትፍ እንዳለባት ለመወሰን መሆኑን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
ነገር ግን ምሽት ላይ በተካሄደው እና የትራምፕ የቅርብ አማካሪዎች በተሳተፉበት በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አሜሪካ በጥቃቱ ውስጥ ስለሚኖራት ተሳትፎ ሙሉ ስምምነት ላይ አለመደረሱ ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለቀናት ኢራን ወደ ኒውክሌር ድርድሩ እንድትመለስ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ከቆዩ በኋላ ነው እስራኤል በኢራን ላይ በከፈተችው ጦርነት ውስጥ አገራቸው በቀጥታ መሳተፍ ሊኖርባት ይችል እንደሆነ ማጤን የጀመሩት።
ማክሰኞ ማታ በተካሄደው የአሜሪካ መንግሥት የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ትራምፕ እና አማካሪዎቻቸው የኢራንን የኒውክሌር ማዕከላትን ለማጥቃት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም ዋነኛ ዒላማ ሊሆን የሚችለው ከተራራ ስር ከመሬት በታች የሚገኘው ፎርዶ የተባለው የዩራኒያም ማበልጸጊያ መሆኑ ተነግሯል። ይህንን ከመሬት በታች የሚገኝን ማዕከል ለማውደም የሚያስችል ቦምብ ያላት አሜሪካ ብቻ ናት።
ሲቢኤስ ኒውስ አንደዘገበው የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች አሜሪካን በጦርነቱ ውስጥ በሚኖራት ተሳትፎ ዙሪያ ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።
የአሜሪካ እና የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ከአስቸኳይ ስብሰባው በኋላ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የዘገቡ ሲሆን፣ ነገር ግን በምን ጉዳይ ላይ እንደተወያዩ አልታወቀም።
ባለፉት ሦስት ቀናት የአሜሪካ የጦር ጄቶች እና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ነዳጅ የሚሞሉ ቢያንስ 30 ነዳጅ ጫኝ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ወደ አውሮፓ እንዲጓዙ ተደርገዋል።
ከአስቸኳይ ስብሰባው በፊት ዶናልድ ትራምፕ በተከታታይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “ያለ ቅድመ ሁኔታ እጇን እንድትሰጥ” መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር።
ለዚህም ምላሽ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተከታታይ በሰጡት ምላሽ አገራቸው “ከጽዮናውያን ጋር ፈጽሞ እንደማይስማሙ” ገልጸዋል።





















