የኢራን እና አሜሪካ ንግግር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ

የኢራን እና አሜሪካ ድርድር የኳታር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ። ድርድሩ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ላይ እና በኢራን እንዳይንቀሳቀሱ በተደረጉ ሃብቶች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል። ኳታር በኢራን እና አሜሪካ መካከል ድርድር መጀመሩን አረጋግጣለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በጄኔቭ ሊካሄድ የነበረው የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተሰረዘ

    በስዊትዘርላንድ አርብ ዕለት ሊካሄድ የነበረው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ይፋዊ የፊርማ ሥነ ሥርዓት መሰረዙን ፓኪስታን አስታወቀች።

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢራን እና አሜሪካ ስምምነቱን በርቀት ፈርመው ይፋ ስላደረጉት በጄኔቫ ሊካሄድ የነበረው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተሰርዟል።

    አንድ የፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣን ቀደም ብለው ለቢቢሲ እንደገለጹት “ቀጣዩ የድርድር ምዕራፍ በተናጠል ቴክኒካዊ ደረጃ በርካታ ጉዳዮች የሚነሱበት በመሆኑ” የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ ወደ ጄኔቭ የሚያደርጉትን ጉዞ ወደ ሌላ ጊዜ አዘዋውረዋል።

    የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ መካሄዱ አጠያያቂ መሆን የጀመረው ሐሙስ ጠዋት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ካሰፈሩት ጽሁፍ ውስጥ ስለአርብ ዕለቱ የፊርማ ሥነ ሥርዓት የጻፉትን ክፍል ቆርጠው ከሰረዙ በኋላ ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን ከሦስት ወራት በላይ የቆየውን የባሕረ ሰላጤው ጦርነትን የሚያስቆመው የመግባቢያ ስምምነት ስዊትዘርላንድ ውስጥ እንደሚፈርሙ እና በዚያውም ቀጣይ ንግግር እንደሚያካሂዱ ሲነገር ቆይቷል።

    ዛሬ ማለዳ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ከያሉበት ሆነው የስምምነት ሰነዱን መፈረማቸውን በማሳወቅ ዝርዝሩ ይፋ ሆኗል።

  2. የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነት ኢራን እና እስራኤል ውስጥ ተቃውሞ እየገጠመው ነው

    ለወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም በኢራን እና በአሜሪካ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ከበርካታ የዓለም አገራት እና ተቋማት ተቀባይነት ቢያገኝም በኢራን እና በእስራኤል ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ግን ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

    የኢራን መሪዎች ስምምነቱን ቢፈርሙም የሟቹ መሪ አያቶላህ አሊኻሜኒ አክራሪ ተከታዮች እና ደጋፊዎች በስምምነቱ ደስተኛ አይደሉም።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ በመሆን የአባታቸውን ቦታ የያዙት እና ለወራት የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ በአደባባይ ያልተዩት ሞጅታባ ኻሜኒ በስምምነቱ ላይ ያላቸው አቋም አስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

    በሌላ በኩል ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ተሰልፋ ኢራንን የወጋቻት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የደረሱትን ስምምነት ውድቅ እንዲያደርጉ ከተቃዋሚዎቻቸው ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ ተዘግቧል።

    ከእነዚህም መካከል የእስራኤል ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው አቪግዶር ሊበርማን “ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የስምምነቱ አካል እንዳልሆኑ በእስራኤል ሕዝብ ፊት ቆመው ለአገራቸው እና ለዓለም አገራት ግልጽ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ” በማለት ጥያቄ አቅርበዋል።

    ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ጨምረውም “በኢራን እና በሊባኖስ መካከል ያለውን ግንኙነት አንቀበለውም” በማለት እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደችው ያለው ወደታራዊ ዘመቻ ከኢራን ስምምነት ጋር መያያዝ እንደሌለበት ተናግረዋል።

    ሊበርማን “እኛ እርምጃ የምንወስደው በብቸኝነት የእስራኤልን ጥቅም መሠረት አድርገን እንጂ የዓለም የነዳጅ ገበያን እና የአክሲዮን ዋጋን በመመልከት አይደለም” ብለዋል።

  3. ኢራን ለስምምነቱ የማትገዛ ከሆነ “የማያፈናፍን የእንቅስቃሴ ዕገዳ” ይጣልባታል - አሜሪካ

    ኢራን ለተደረሰው የስምምነት ነጥቦች የማትገዛ ከሆነ አሜሪካ “የማያፈናፍን የእንቅስቃሴ ገደብ መልሳ ለመጣል ከተገቢው በላይ ዝግጁ ናት” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግሴት ተናገሩ።

    አሜሪካ ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ወደ ኢራን በሚገቡ እና ከኢራን በሚነሱ ሁሉም መርከቦች ላይ የጣለችው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ዕገዳን ለማንሳት ተስማምታለች።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ያላትን ፍላጎት ለመተው “የተስማማችውን የማትተገብር ከሆነ አስፈላጊ ሲሆን የመከላከያ ሚኒስቴሩ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው” ብለዋል።

    የመከላከያ ሚኒስትር ሄግሴት የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እና የሚደረጉ ድርድሮች “ማዕከል የሚደያርጉት በኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ላይ ነው” በማለት ገልጸዋል።

    በተጨማሪም ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ሙሉ ለሙሉ የሚከፈተውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ነጻ ለማድረግ አውሮፓውያን አገራት ዝግጁ መሆናቸውን ሄግሴት ተናግረዋል።

  4. ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኢራን ኒውክሌር ስምምነት “ለተጨባጭ እርምጃ” ዝግጁ መሆኑን ገለጸ

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን በሚመለከት “ተጨባጭ እርምጃ” ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ገለፁ።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ላለማምረት እንዲሁም ላለመግዛት ዳግም ተስማምታለች።

    ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱም አገራት ኢራን ባላት የተብላላ ዩራኒየም ላይ ለመነጋገር ተስማምተዋል።

    ራፋኤል ግሮሲ ዛሬ ማለዳ በሰጡት መግለጫ በሚኖሩ ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች ላይ ግምታችንን እያስቀመጥን ጊዜያችንን ማባከን “ተገቢ አይደለም” ብለዋል።

    "ሁሉም ሰው በቀና ልቦና እንደሚሳተፍ እና ስምምነቱ እንዲሳካ እንደሚፈልግ በማመን ድርድሩን አስጀምራለሁ። ስምምነቱን ከፈረሙ. . . ይህን ለማድረግ በቁም ነገር እንደሚሰሩ ምልክት አድርጌ እወስዳለሁ።"

    አክለውም ኤጀንሲው ስለ የተወሰኑ ነገሮች እና ኤጀንሲው ሊደርስባቸው ስለሚገባቸው ቦታዎች "በጣም ጥሩ መረጃ" እንዳለላቸው ነገር ግን "ከሂደቱ በፊት መሄድ ትክክል አይደለም" ብለዋል።

    “ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ለመነጋገር ወሳኝ በሆነ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።”

  5. በአሜሪካ እና እስራኤል መካከል ሊባኖስን በሚመለከት “አስቸጋሪ ንግግር” እየተደረገ መሆኑ ተሰማ

    አንድ ለቤንያሚን ኔታንያሁ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን በአሜሪካ እና እስራኤል መካከል ሊባኖስን በሚመለከት "አስቸጋሪ ድርድር" እየተደረገ መሆኑን ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ አክለውም እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ወታደሮቿን ለማሰማራት እና አካባቢውን ተቆጣጥራ ለመቆየት ከያዘችው አቋም የመልቀቅ ፍላጎት አላሳየችም ብለዋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በየትኛውም ግንባር የሚካሄዱ ወታደራዊ እርመጃዎች ይቆማሉ ቢልም የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ግን የእስራኤል ጥቃት እንደቀጠለ መሆኑን ዘግበዋል።

  6. ኢራን በስዊትዘርላንድ በሚደረገው ንግግር ላይ ለመገኘት “ከውሳኔ ላይ አለመድረሷን” አስታወቀች

    ቴህራን በስዊትዘርላንድ በሚካሄደው አዲሱ ዙር ንግግር ላይ ለመሳተፍ "ከውሳኔ ላይ አለመድረሷን” የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ተናገሩ።

    መንግሥት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ “ውይይቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እና በአደራዳሪዎች በኩል በሚቀጥሉት ሰዓታት እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል” ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የስዊዝ መንግሥት የአሜሪካ እና ኢራን ተወካዮች ነገ በስዊትዘርላንድ ንግግራቸውን አንደሚጀምሩ መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

    "አሁን ያለው ዕቅድ አሜሪካ እና ኢራን፣ ከአደራዳሪዎች ፓኪስታን እና ኳታር እና ሌሎች ተሳታፊ አገራት ጋር ነገ በበርገንስቶክ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ለማድረግ ነው።”

    የስዊዝ ውጭ ጉደይ ሚኒስቴር በመግለጫው “ስለ ፕሮግራሙ እና ስለ ስብሰባው ዝርዝር ተጨማሪ መረጃ አሁን ማግኘት አይቻልም” ብሏል።

    አርብ ዕለት ትራምፕ እና የኢራን ፕሬዚዳንት ፊርማቸውን ያኖሩበት የመግባቢያ ሰነድ ላይ ይፋዊ የፊርማ ስነስርዓት ይኖራል ።

  7. ስዊትዘርላንድ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል አርብ ዕለት ንግግር እንደሚጀመር አስታወቀች

    የስዊዝ መንግሥት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው የመጀመርያ ዙር ንግግር አርብ ዕለት በተራራ ላይ በሚገኘው በርገንስቶክ ሪዞርት እንደሚጀመር አስታወቀ።

    ሁለቱ መንግሥታት ባለ አስራ አራት ነጥብ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

    "አሁን ያለው ዕቅድ አሜሪካ እና ኢራን፣ ከሸምጋዮቹ ፓኪስታን እና ኳታር እና ሌሎች ተሳታፊ አገራት ጋር ነገ በበርገንስቶክ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ለማድረግ ነው።”

    የስዊዝ ውጭ ጉደይ ሚኒስቴር በመግለጫው “ስለ ፕሮግራሙ እና ስለ ስብሰባው ዝርዝር ተጨማሪ መረጃ አሁን ማግኘት አይቻልም” ብሏል።

  8. ኢራን፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ስምምነቱን የጣሰ ነው አለች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ እስራኤል ሊባኖስን ማጥቃት የምትቀጥል ከሆነ የመግባቢያ ሰነዱን መጣስ አድርገን እንመለከተዋለን አሉ።

    ረቡዕ ዕለት እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ አዲስ ጥቃት መፈጸሟን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ተችተው ተናግረዋል።

    እስራኤል እና ሄዝቦላህ እሁድ ዕለት የኢራን ጦርነትን የሚያስቆም ስምምነት ቢደረስም ጥቃቶችን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ሲፈጽሙ ነበር።

    ትራምፕ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ከኔታንያሁ ጋር ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸው በርካታ ጥቃት በመፈጸሙ ደስተኛ አይደለሁም ብለዋል።

    ኔታንያሁ ደግሞ ሰኞ ዕለት ጦራቸው “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ” በሊባኖስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

  9. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ልታስከፍል ነው

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ እና ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈ ቃለ መጠይቃቸው “ከጦርነት በፊት ወደነበረው ሁኔታ አንመለስም” ሲሉ ተናገሩ።

    አክለውም “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሉዓላዊነት አላት እንዲሁም ለአገልግሎታችን ዋጋ መቀበላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

    ወሳኝ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ከ60 ቀናት በኋላ ማስከፈል ትጀምራለች ሲሉ ተናግረዋል።

    ትራምፐ እና የኢራኑ ፕሬዚዳንት በፈረሙት ስምምነት ላይ ቴህራን ከኦማን እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር በመሆን የሆርሙዝን ወሽመጥ እንዴት እናስተዳድር በሚለው ዙሪያ ሰፋ ያለ የስምምነት ሰነድ ያዘጋጃሉ ይላል።

    አሜሪካ ቴህራን መብቷን ለማስከበር የኃይል እርምጃዎችን እንደምትጠቀም የምታምን ቢሆንም የባሕረ ሰላጤው አገራት ወደፊት ቀረጥ የሚከፈልበትን መተላለፊያ ማየት “በፍጹም” አይፈልጉም ሲሉ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

  10. ትራምፕ እና የኢራኑ ፕሬዚዳንት ጦርነቱን የሚያስቆመውን የመጀመርያ ስምምነት ፈረሙ

    የአሜሪካ እና ኢራን ፕሬዚዳንቶች ጦርነቱን ከአሁን ጀምሮ የሚያስቆመውን የመጀመርያ ስምምነት ፈረሙ።

    ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና መክፈት፣ የ300 ቢሊዮን ዶላር ኢራን “መልሶ የመገንባት” ዕቅድ፣ አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለችውን “ሁሉንም ዓይነት ማዕቀቦች” የሚያስቆም ነው።

    ነገር ግን የኢራን ጦርነት እንዲቀሰቀስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የኒውክሌር ፕርግራም ሊራዘም በሚችል 60 ቀናት ውስጥ ድርድር የሚካሄድበት ጉዳይ ሆኗል።

    የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ፈረንሳይ በተካሄደው የቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ በተሳተፉበት ወቅት ፊርማቸውን ሲያኖሩ “ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን” የሚያስቀር ዕቅድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    ነገር ግን ከኢራን ጋር የመጨረሻው ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ “በቦምብ እንደበድባቸዋለን”ሲሉ ዝተዋል።

    የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ረቡዕ ዕለት ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ቴህራን አረጋግጣለች።

    የኢራን ቁልፍ ተደራዳሪ የሆኑት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ሞሃመድ ባግሃር ጋሊባፍ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ እንዳለ መሆኑን አስታውቀው “ጣቶቻችን አሁንም ቃታ ለመሳብ ዝግጁ ናቸው” ብለዋል።

    “ጠላት የተጠየቅነውን ቋንቋ ካልተረዳ ወደ ኃይል ቋንቋ ተመልሰን እንገባለን” ሲሉ ለፋርስ ኒውስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት የከፈተቱት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ነበር።

    ሁለቱ አገራት ጥቃት በፈጸሙበት የመጀመርያ ቀን የአገሪቱ ጠቅላይ መሪን አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ተገድለዋል።

    ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ የዓለም ኤነርጂ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል።

    ትራምፕ በፈረንሳይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዕቅዱ ዓለም አቀፍ ድብታን ይቀለብሳል።

    “የምጣኔ ሃብት ቀውስ ማየት አልፈልግም” ያሉት ትራመፕ “ጦርነቱ እንዲቀጥል የሚደረግ ከሆነ የሚከተለው ያ ነበር” ብለዋል።

  11. ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ከሦስት ወራት በላይ የተካሄደው ጦርነት የጀመረው ከዓመታት በፊት አሜሪካ የኢራንን ከፍተኛ ጄነራል ኢራቅ ውስጥ ከገደለች በኋላ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናገሩ።

    ትራምፕ በመጀመሪያው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው የቀደሙት ፕሬዝዳንት ከኢራን ጋር የደረሱትን የኒውለሌር ጦር መሳሪያ ስምምነት ውድቅ ካደረጉ በኋላ ከኢራን ጋር ፍጥጫው መጀመሩን በመጥቀስ ፍልሚያው የቆየ መሆኑን አመልክተዋል።

    ከዚያም በኋላ በአውሮፓውያኑ 2020 በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝው ባግዳድ ውስጥ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አንድ አካል የሆነው በውጭ አገራት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና በምሥጢራዊ ዘመቻ የሚታወቀው የቁዱስ ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄነራል ቃሲም ሱሌማኒ መገደላቸው ይታወሳል።

    አሁን ከወራት ጦርነት በኋላ ከስምምነት የተደረሰበት ጦርነት የጀመረው የካቲት 21/2018 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም ትራምፕ ግን ከኢራን ጋር ጦርነት የጀመሩት ከስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ መሆኑን ፈረንሳይ ውስጥ በቡድን ሰባት ስብሰባ ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም ከኢራን ጋር በተደረገው ጦርነት ሌሎች የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ያላሳኩትን ኢራን የኒውለሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት በማድረግ የነበረውን ስጋት ማስወገዳቸውም ተናግረዋል።

    ከእሳቸው የቀደሙት መሪ ከኢራን ጋር መጥፎ የሚባል የኒውክሌር ቁጥጥር ስምምነት በመፈራረም ተይዞባት የነበረ ገንዘቧን እንድታገኝ እና ማዕቀቦች እንዲነሱላት አድርገዋል በማለት ሲወቅሱ ቢቆዩም ይኸው ጉዳይ አሁን በተደረሰው ስምምነት ውስጥ ሳይካተት እንዳልቀረ በስፋት እየተነገረ ነው።

    ትራምፕ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር እና ባለፉት ሦስት ወራት በተካሄዱት ጦርነቶች ወቅት በተፈጸሙ ከፍተኛ ድብደባዎች የኢራን የኒውክሌር ተቋማት መውደማቸውን በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

    ነገር ግን በስምምነቱ ላይ ኢራን የዳበሩ የኒውክሌር ግንባታ ግብዓቶችን አሳልፋ እንድትሰጥ ወይም እንድታስወገድ ከስምምነት ተደርሷል እየተባለ ነው።

    አርብ የሚፈረመው የአሜሪካ እና የኢራን የመግባቢያ ስምምነት ሙሉ ዝርዝር ይዘት ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

  12. አርብ ስለሚፈረመው የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነት እስካሁን የምናውቀው

    አሜሪካ እና ኢራን ከሦስት ወራት በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የደረሱበት የመግባቢያ ስምምነት መፈረምን ዓለም በጉጉት እየተጠባበቀው ነው። የቡድን ሰባት አገራት በሁለቱ አገራት መካከል ተከታታይ እና ጠንካራ ስምምነት ሊደረስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

    ወሳኙ የመግባቢያ ስምምነት በኢራን እና በአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በስዊትዘርላንዷ የመዝናኛ ስፍራ በርገንስቶክ ውስጥ ከነገ ወዲያ አርብ ይፈረማል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

    ከሁለቱ አገራት እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ እና ዋነኛው ተደራዳሪ ሞሐማድ ባግሄር ጋሊባፍ እና የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ስምምነቱን በመፈረም ይፋ እንደሚደያርጉ ተነግሯል።

    ጦርነቱን ያስቆማል የተባለውን የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ የተለያዩ ይዘቶች እየወጡ ቢሆንም ይፋዊ የስምምነቱን ሃሳብ የያዘው ሰነድ ገና ይፋ አልተደረገም።

    የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት ስዊትዘርላንድ ውስጥ የሚገናኙት ስምምነቱን ለመፈረም ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይም ድርድር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    በድርድሩ ቁልፍ ጉዳይ የሆነው የኢራን የዳበሩ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ መሥሪያ ግብአቶች ጉዳይ እንደሚገኝበት ተነግሯል።

  13. ትራምፕ የቡድን ሰባት አገራት ስብስብ ‘አለቃው እኔ ነኝ’ ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል

    በፈረንሳይ የቡድን ሰባት አባል አገራት ጉባዔ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የባለጸጋ አገራቱ ስብስብ “አለቃው እኔ ነኝ” ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

    የዓለማችን ታላላቅ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት የሰባቱ አገራት መሪዎች ይህንን የትራምፕን ንግግር በሳቅ መቀበላቸውም ተዘግቧል።

    ትራምፕ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብደልፋታህ አል-ሲሲ ጋር ባደረጉት ንግግር ወቅት፤ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “ገና እንዳልተገባደደ” ጠቅሰው በመግባቢያ ሰነዱ አተገባበር ደስተኛ ካልሆኑ ቴህራን ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉም ዝተዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ኢንቨስት እንደማታደርግ፣ ቴህራን መቼም ቢሆን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማትፈቅድም በድጋሚ ተናግረዋል።

    ትራምፕ ከኳታር አሚር ጋር ባደረጉት ንግግር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን መተቸታቸው ተዘግቧል።

    “የሊባኖስን ጉዳይ በተመለከተ የተሻለ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት” ብለዋል። እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር የምታደርገውን ውጊያ በተመለከተም “ለረዥም ጊዜ በርካታ ሰዎች እየተገደሉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ቢተቹም አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ መፈጸሟ ተገልጿል።

  14. የቡድን ሰባት አገራት ኢራን እና አሜሪካ “ቀጣይ ስምምነት” ላይ እንዲደርሱ ጠየቁ

    የቡድን ሰባት አባል አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በቀጣይ “ጠንካራ” የሆነ ተከታይ ስምምነት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

    አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የተስተዋለውን “ጉልህ ለውጥ” እውቅና እንደሚሰጡት እና የድርሻቸውን ለማበርከት “ዝግጁ እንደሆኑ” አስታውቀዋል።

    “ፕሬዝዳንት ትራምፕ የደረሱበትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት የሚያመጣ፣ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ተከታይ ስምምነት እንዲፈረም በጽኑ እንደግፋለ” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “ገና እንዳልተገባደደ” ጠቅሰው፤ በመግባቢያ ሰነዱ አተገባበር ደስተኛ ካልሆኑ ቴህራን ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።

  15. ትራምፕ በስምምነቱ አተገባበር ደስተኛ ካልሆኑ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠነቀቁ

    ለቡድን ሰባት ጉባዔ ፈረንሳይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው ስምምነት “ገና እንዳልተገባደደ” ጠቅሰው በመግባቢያ ሰነዱ አተገባበር ደስተኛ ካልሆኑ ቴህራን ላይ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠነቀቁ።

    “የመግባቢያ ሰነድ ነው፤ ካልወደድኩት መተኮስ እና ቦምብ መጣል እንቀጥላለን። ጥሩ ባህሪ ካላሳዩ በድጋሚ ድብደባውን እንቀጥላለን” ብለዋል።

    የተደረሰው ስምምነት ከኢራን ላይ ማዕቀቦችን ማንሳትን እንደማያካትት ትራምፕ ጠቅሰዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም የተስማሙባቸውን ነጥቦች ትራምፕ ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደረጉ እንደሚችሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ቢተቹም አዲስ ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ መፈጸሟ ተገልጿል።

  16. እስራኤል ከስምምነቱ በኋላ በደቡባዊ ሊባኖስ አዲስ ጥቃት ፈጸመች

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ ቢተቹም አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ መፈጸሟ ተገለፀ።

    እስራኤል ረቡዕ ዕለት አየር ኃይሏ ከክፋር ትብኒት ወጣ ብሎ የሚገኙ አካባቢዎችን ማጥቃቷን የአገሪቱ ብሐራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር ስለጥቃቱ ምንም ዓይነት አስተያት ያልሰጠ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እንደሚደበድብ መግለጹ ይታወሳል።

    ምንም እንኳን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ነጥቦች ይፋ ባይሆኑም አደራዳሪዋ ፓኪስታን ሊባኖስን እንደሚያካትት አስታውቀለች።

    ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሊባኖስን በሚመለከት የበለጠ ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል” ብለዋል።

    ፈረንሳይ በሚካሄደው የቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ትራምፕ እስራኤል ሄዝቦላህን “ለረዥም ጊዜ ተዋግታለች እና በርካታ ሰዎች ተገድለዋል” ብለዋል።

    የኢራን ጦርነትን የሚያስቆም ስምምነት ላይ መደረሱን እሁድ ምሽት ይፋ ቢሆንም እስራኤል እና ሄዝቦላህ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

    ትራምፕ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ከኔታንያሁ ጋር “ጥብቅ ወዳጅነት” እንዳላቸው ገልጸው “በርካታ ጥቃት በመፈጸሙ ደስተኛ አይደለሁም” ብለዋል።

    አክለውም “ያለ አሜሪካ እስራኤል አትኖርም። ያለ እኔ እስራኤል አትኖርም፤ ምክንያቱም ሌላ ፕሬዚዳንት እኔ ያደረግኩትን ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆንም” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት ጦራቸው “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ” በሊባኖስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ፣ እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ወይም በግዛቲቱ ጦሩ መገኘትን እንደ ስምምነቱ ጥሰት እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።

  17. ከስምምነቱ በኋላ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የአሜሪካን እገዳ ማለፋቸውን መረጃዎች አመለከቱ

    በዚህ ሳምንት ዋሺንግተን እና ቴህራን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካሳወቁ በኋላ ቢያንስ ሦስት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የአሜሪካን እግድ አልፈው ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ መሄዳቸውን መረጃዎች አሳዩ።

    የመርከቦቹ እንቅስቃሴ ኢራን ወደ ውጪ የምትልከውኘ ነዳጅ ቀስ በቀስ መጀመሯን ያሳያል ተብሏል።

    ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ የሆኑት ሄሮ II እና ዲዮና እያንዳንዳቸው 2 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ጭነው የኦማን ባሕረ ሰላጤን አልፈው ወደ ምሥራቅ መቅዘፋቸውን የመርከቦችን መረጃ የሚከታተሉ ሁለት ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል።

    ሴዌዝማክስ ሶኒያ I የተባለችው እና 1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነች መርከብ እንዲሁ የአሜሪካ ባሕር ኃይል እገዳን አልፋ ወደ ሲንጋፖር ማምራቷን መረጃዎቹ ጠቁመዋል።

    ሄሮ II ነዳጁን የጫነችው በመጋቢት የመጨረሻ ሳምንት ሲሆን፣ ዲዮና እና ሶኒያ I ደግሞ በሚያዚያ ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ መጫናቸውን የኬፕለር መረጃ ያሳያል።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ ክልከላ በማድረጉ ቴህራን ወደ ውጭ የምትልከውን ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ቆይቷል።

    ኢራን በግንቦት ወር ወደ ውጭ የላከችው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከባለፉት ስድስት ዓመታት አንጻር ሲተይ በጣም ዝቅተኛ ነው።

    በግንቦት ወር በየቀኑ 260,000 በርሜል ነዳጅ ብቻ ትልክ እንደነበር ኬፕለር ይፋ አድርጓል።

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ሲስማሙ እገዳው እንደሚነሳ እና የነዳጅ ምርቷን ወደ ውጪ ለመላክ እንደምትችል መግባባታቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ማክሰኞ ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  18. የኢራን ስምምነት የ300 ቢሊየን ዶላር ፈንድን እንደሚያካትት እና ከግማሽ በላዩ መከፈሉን ምንጮች ለሮይተርስ ተናገሩ

    በአሜሪካ እና በኢራን የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ በቴሀራን ያለውን ኢንቨስትመንት ለማንቀሳቀስ በሚል 300 ቢሊየን ዶላር መቀመጡን እና ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሰጠቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሮይተርስ ተናገሩ።

    አርብ ዕለት የሚፈረመው ስምምነት የያዛቸው ዝርዝር ሃሳቦች ይፋ ባለመሆናቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ምንጮች ገንዘቡ የተቀመጠው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችላቸው የመጨረሻ ስምምነት ለመድረስ እንዲችሉ በሚል የምጣኔ ሃብት ማበረታቻ መሆኑን ገልጸዋል።

    ከዚህ ቀደም ሮይተርስ ለኢራን ስለሚሰጥ ገንዘብ የዘገበ ቢሆንም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት እሁድ ዕለት ጦርነቱን ለማስቆም በሚያችል ማዕቀፍ ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ቴህራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ በምላሹ ኢራን የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለቸ።

    አዲሱ ፈንድ የግል ኢንቨስትመንት ማሳለጫ እንደሚሆን እና ምንም ዓይነት የመንግሥት ገንዘብን እንደማያካትት ተገልጿል።

    አክለውም ገንዘቡን ለመስጠት መቀመጫቸውን አሜሪካ፣ የአረብ ሰላጤ አገራት፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ የሚገኙ ኩባንያዎች ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

    ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈስሱት በኢነርጂ፣ ሎጀስቲክ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ትራንስፖርት ላይ መሆኑን ምንጮች ጨምረው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የመልሶ ግንባታ እና የልማት ፈንድ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል በተባለው ፈንድ የቀጣናው አገራት በተለያዩ መንገዶች እንዲያዋጡ ይደረጋል ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።

    ይህም በብድር፣ ቀጥታ በጦርነት የወደሙ ቦታዎችን እና መሠረተልማቶችን መልሶ መገንባት ላይ መሳተፍ ይገኝተበታል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት መካከል ኢራን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ናት።

    ባለፉት አራት አስርት ዓመታት አንድም የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢራን ያልመጣ ሲሆን የዓለም አቀፍ እና የአሜሪካ ማዕቀቦችም ሃብቶቿን እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል።

    ኢራን በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ግዙፍ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት ስትሆን በነዳጅ ዘይት ክምችትም አራተኛዋ ናት።

  19. ትራምፕ ከኢራን ጋር የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ተባለ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነቱን ለማቆም የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደረጉ እንደሚችሉ ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ተናገሩ።

    ትራምፕ ስምምነቱ መፈረሙን ተናግረው የነበረ ሲሆን አርብ በስዊትዘርላንድ የሁለቱ አገራት ልዑካን በአካል ተገናኝተው ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ እየተነገረ ነው።

    ጄዲ ቫንስ የመግባቢያ ሰነዱ “አንድ ገጽ ከግማሽ” እና “በጣም ጥቅል” ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች መናገር ጀምረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ስምምነቱ በጄኔቫ በሚፈረምበት ዕለት አርብ ዳግም ይከፈታል ተብሏል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከአሜሪካ ጋር ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ የሚደረገው አዲሱ ዙር ውይይት በዚያው ዕለት ስዊትዘርላንድ ውስጥ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

    ለቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ፈረንሳይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ማክሰኞ ዕለት ከግብጽ፣ ኳታር እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በኢራን ዙሪያ መክረዋል።

    ሰኞ ዕለት ትራምፕ ከፈረንሳዩ ፕሬዚፈዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ጋር ሲነጋገሩ “ተፈርሟል ብዬ ስነግራችሁ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ስምምነቱ ተፈርሟል” ብለው ነበር።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስምምነቱ የትራምፕ፣ የምክትላቸው ቫንስ እና የኢራን የፖርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ ኤሌክትሮኒክስ ፊርማ ተቀምጦበታል ብለዋል።

    በዚህ ሳምንት የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ላይ እንዲሁም በኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ላይ መነጋገር ይጀመራል ተብሏል።

    ኢራን ላይ የተጣሉትን ማዕቀቦች ለማንሳት ወይም እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ ሃብቶቿን ለመልቀቅ ኢራን ለስምምነቱ ያላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

    ቫንስ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት በስምምነቱ መሠረት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ወደ ኢራን መግባት አለበት ብለዋል።

    “የስምምነቱ አንኳር ነጥቦች ከሆኑት መካከል አንዱ [ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ] እና ዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ ሁኔታ ተብላልቶ የተቀመጠውን ዩራኒየም እንድታስወግድ እንደሚደግፉ በግልጽ ተቀምጧል።”

    ትራምፕ የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች አርብ ዕለት ከተፈረሙ በኋላ ይፋ ይሆናሉ ብለው የነበረ ቢሆንም ቫንስ ግን ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ከዚያ በፊት ይፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

    ቫንሰ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታም ሰነዱ ጥቅል መሆኑን እና በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት በሚደረጉ ንግግሮች መግባባት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል ብለዋል።

  20. ጄዲ ቫንስ "የአሜሪካ ሰባራ ሳንቲም ወደ ኢራን አይሄድም” አሉ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባደረገቸው ስምምነት የተነሳ “ሰባራ ሳንቲም” ወደ ቴህራን አይሄድም ሲሉ ተናገሩ።

    ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለኢራን “ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ ሰጥተዋል” ሲሉ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር አነጻጽረዋቸዋል።

    ኳታር 300 ቢሊዮን ዶላር ለኢራን ትሰጣታለች እንዲሁም 24 ቢሊየን እንዳይንቀሳቀስ የተደረገ የቴህራን ሃብት ይለቀቃል ስለተባለው ሲጠየቁ ቫንስ “በመሠረቱ ይህ የኢራናውያን ፕሮፓጋንዳ ነው” ብለዋል።

    “እየሆነ ያለው የተወሰኑ ግለሰቦች ለአገር ውስጥ ማኅበረሰብ ስምምነቱ በጎ እንደሆነ በተቻለ መጠን ለማሳየት እየሞከሩ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    “የአሜሪካ ሰባራ ሳንቲም ወደ ኢራን አይሄድም። 300 ቢሊዮን ዶላር ወይም 24 ቢሊዮን ዶላር ምንም ዓይነት ገንዘብ”

    ይሁን አንጂ “ግዴታቸውን የሚወጡ ከሆነ ለኢራን ጥቅም አለው” በማለት ኳታር፣ ዩኤኢ ወይም ሳዑዲ አረቢያ በኢራን መዋዕለ ነዋያቸውን ሊያፈሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።