የኢራን እና አሜሪካ ንግግር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ

የኢራን እና አሜሪካ ድርድር የኳታር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ። ድርድሩ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ላይ እና በኢራን እንዳይንቀሳቀሱ በተደረጉ ሃብቶች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል። ኳታር በኢራን እና አሜሪካ መካከል ድርድር መጀመሩን አረጋግጣለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሊባኖስ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ስጋት ከተደቀነባቸው እርምጃ ለመውሰድ ነጻ መሆናቸውን እዝራኤል ካትዝ ተናገሩ

    የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ እሁድ ዕለት ጦራቸው በሊባኖስ ያለውን ስጋት ለማስወገድ ያለ ገደብ እርምጃ ለመውሰድ ነጻ መሆኑን ተናግረው ወታደሮቹ እስራኤል የጸጥታ ቀጣና በምትለው ስፍራ ላይ እንዳሉ አስታወቁ።

    አርብ ዕለት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም ቅዳሜ ጦሩ በሊባኖስ ላይ ጥቃት ፈጽሞ 20 ሰዎች መግደሉን የሊባኖስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    እስራኤል ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ሄዝቦላህ ከደቡባዊ ሊባኖስ ተወንጫፊዎችን በመተኮሱ እንደሆነ ተናግራለች።

    የእስራኤል ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመው “በሄዝቦላህ ዒላማዎች” ላይ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ዛሬ በስዊትዘርላንድ የተጀመረው ንግግር ማዕከላዊ ነጥብ ሊባኖስ እንደምትሆን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ አካባቢዎችን ወርረው ይዘዋል።

    ሄዝቦላህ በሊባኖስ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች የመዋጋት መብት እንዳለው አስታውቆ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ግን ጥቃቶችን እንደማይፈጽም አስታውቋል።

    ካትዝ በበኩላቸው ጦራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ የደህንነት ቀጣናዎች ሲሉ በሰየሟቸው አካባቢዎች እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

    አገራቸው ይህንን እርምጃ የምትወስደው በሰሜናዊ እስራኤል የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ለመከላከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

    “ሁሉም ጦሩ በዘመቻው ያስመዘገባቸው ስኬቶች ይጠበቃሉ። በሊባኖስ የደህንነት ቀጣናዎች ተብለው በተለዩት አካባቢዎች ወታደሮች ይሰማራሉ። እዚያም ሆነው በአሸባሪዎች እና በአሸባሪው መሠረተልማቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳሉ” ሲሉ እሁድ ዕለት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

  2. የኢራን እና አሜሪካ ንግግር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ

    የኢራን እና አሜሪካ ድርድር የኳታር አደራዳሪዎች በተገኙበት በስዊትዘርላንድ ተጀመረ።

    ድርድሩ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ላይ እና በኢራን እንዳይንቀሳቀሱ በተደረጉ ሃብቶች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

    ኳታር በኢራን እና አሜሪካ መካከል ድርድሩ መጀመሩን አረጋግጣለች።

  3. የኢራኑ ፕሬዚዳንት የአገሪቱ ወታደራዊ አዛዦች በሙሉ ድምጽ ድርድሩን መደገፋቸውን ተናገሩ

    የኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በጠቅላይ ብሔራዊ የጸጥታው ምክር ቤት ሁሉም አባላት ለድርድር ድምጽ መስጠታቸውን ተናገሩ።

    የኢራኑ ፕሬዚዳንት ከቴህራን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ሁሉም የጦሩ አዛዦች እና የደህንነት ምክር ቤት አባላት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዚዳንቱ የአብዮታዊ ዘብ አዛዦች እንዲሁም የኢራን ጦር አዛዠች ሁሉም በሥፍራው እንደነበሩ በአንድ ድምጽ ድርድሩን መደገፋቸውን ገልጸዋል።

    ፕሬዚዳንት ፔዚኪያን ሁሉም ከፍተኛ አመራሮች “ድርድሩ መካሄድ እንዳለበት” ተስማምተዋል ብለዋል።

    የዛሬ ሳምንት በሁለቱ አገራት መካከል ከስምምነት የተደረሰበት የመግባቢያ ሰነድ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ያካትታል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ፣ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኳታር ልዑካን ከኢራን ተደራዳሪዎች ጋር በስዊዘርላንድ ለድርድር ተገናኝተዋል።

    ነገር ግን ትናንት ቴህራን፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ አላቆመችም በሚል ወሽመጡን መዝጋቷን አስታውቃለች።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተፈረመው ጊዜያዊ የሰላም ስምምነት ላይ ተጨማሪ ንግግሮች ለማድረግ በስዊዘርላንድ የተገናኙት ልዑካን ላይ ይህ የቴህራን እርምጃ ጥላ አጥልቶበታል።

  4. የዛሬው የአራትዮሽ ንግግር በመግባቢያ ስምምነቱ ጥሰት እና መፍትሔዎችን መለየት ላይ እንደሚያተኩር ኢራን ተናገረች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ በስዊትዘርላንድ በሚደረገው ንግግር የስምምነቱን መጣስ በግልፅ በማሳየት እና የመፍትሔ መንገዶችን በመለየት የቴህራን ተልዕኮ “ቅድመ ሁኔታዎቿን ማቅረብ” ላይ የሚያተኩር ነው ብለዋል።

    ‘ሳዳ-ቫሲማ’ ለተባለው መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት በስዊትዘርላንድ የኢራን ልዑክ ሲገኝ ከቅዳሜ ጀምሮ ያልፀና የተኩስ አቁም በሊባኖስ መፈጠሩን ተናግረዋል።

    ይህም የሆነው በዲፕሎማሲያዊ የቅርብ ትብብር ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

    ኢራን በቀላሉ ስምምነት ፈርማ የተፈፃሚነት ሂደቱ በራሱ እንዲተገበር አትተውም ብለዋል።

    ከዚህ ይልቅ የሌላኛውን ወገን እርምጃዎች በቅርብ መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገቡ ቃል ኪዳኖች መፈፀማቸውን ለማረጋገጥ ሁሉንም መንገዶች እንጠቀማለን ብለዋል።

    “ቃል ቃል ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህ መመሪያ ያለፉ ጉዳዮችን ላለመድገም አስፈላጊ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

    እስማኤል ባጋይ የስዊትዘርላንዱ ንግግር ለአንድ ቀን የሚቆይ እና ይራዘማል ተብሎ እንደማይጠበቅ ገልፀዋል።

  5. ኢራን በዛሬው ድርድር በቅድሚያ ከአሸማጋዮቹ ጋር እንደምትወያይ አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በስዊትዘርላንድ በሚካሄደው ድርድር በቅድሚያ የአራትዮሽ ውይይት እንደሚካሄድ አስታወቀ።

    ኢራን፣ አሜሪካ፣ ኳታር እና ፓኪስታን በተራራ ላይ በተሰየመው በርጀንስቶክ ሪዞርት ተገናኝተው ይወያያሉ።

    የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ቴህራን መጀመርያ ላይ ከአደራዳሪዎቹ ኳታር እና ፓኪስታን ጋር ትወያያለች ብለዋል።

    ስብሰባው የሚሆነው በዚህ ሳምንት በሁለቱ አገራት ፕሬዚዳንቶች የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ተግባራዊነት ላይ እንደሆነ ጨምረው አስታውቀዋል።

    ድርድሩ የሚካሄድበት በርጀንስቶክ ሪዞርት የዓለም አቀፍ የዜና ርዕስ የሆነው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደው ውይይትን እንደሚያስተናግድ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ነው።

    ይህ ቅንጡ ሪዞርት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች የሚካሄዱበት የአውሮፓ መዳረሻ ሆኗል።

    በርጀንስቶክ እአአ በ2024 ሰኔ ወር ላይ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የዩክሬን የሰላም ጉባዔ አስተናግዷል።

    በዚህ ጉባዔ ላይ ሩሲያ ባትገኝም ከ90 በላይ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅት የመጡ ተወካዮች ታድመው ነበር።

  6. የአሜሪካ እና የፓኪስታን ልዑካን በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ስዊትዘርላንድ ገቡ

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻህቤዝ ሻሪፍ እና የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት በድርድሩ ላይ ለመገኘት ስዊትዘርላንድ ገቡ።

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ከጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ ጋር አብረው ወደ ጄኔቫ መጓዛቸው ታውቋል።

    ፓኪስታን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ስታሸማግል ቆይታለች።

    የፓኪስታው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ብሎ በስዊትዘርላንድ በሚደረገው ንግግር ላይ ለመካፈል የኳታር ልዑካን እንደሚገኙ አስታውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ድርድሩ በሚደረግበት ሪዞርት መድረሳቸው ተነግሯል።

    የኢራን እና አሜሪካ ልዑካን ድርድራቸውን ዛሬ ይጀመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር እንዲደረግ የሚያስችል የ60 ቀናት ተኩስ አቁም የተደረሰ ቢሆንም የእስላማዊ ሪፐብሊኩ ግን ቅዳሜ ዕለት እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አላቆመችም በሚል ሆርሙዝን መዝጋቱን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር ግን ወሽመጡ ክፍት ነው ሲል አስተባብሏል።

  7. እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት የአል ጃዚራ ባልደረባን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ

    እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የአል ጃዚራን የካሜራ ባለሙያ እና አንድ ሕጻንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የጤና ባለሥልጣናት እና የሕይወት አድን ሠራተኞች ተናገሩ።

    አል ጃዚራ ቅዳሜ ዕለት በማዕከላዊ ጋዛ ቤቱ ውስጥ ሳለ በተፈጸመ ጥቃት የተገደለውን አህመድ ዊሻህ የተባለው ሠራተኛውን ሞት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “ይህንን አስከፊ ሰዎችን ዒላማ የማድረግ እና የመግደል ወንጀል በጥብቅ እናወግዛለን” ሲል ተቃውሟል።

    የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ዊሻህ “በሐማስ ውስጥ ያለ ወታደራዊ ክንፍ አልሞ ተኳሽ አሸባሪ ነው” ሲል ወንጅሎታል።

    በጋዛ የሚገኘው የሐማስ ጤና ሚኒስቴር ሐማስ እና እስራኤል በጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ከደረሱ በኋላ በተፈጸሙ ጥቃቶች 1,007 መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።

    አል ጃዚራ ቅዳሜ ዕለት የዊሻህ ሞት "ሁሉንም ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ደንቦች የሚጥስ አዲስ እና ግልጽ የሆነ እርምጃ ነው፤ እንዲሁም ጋዜጠኞችን ዒላማ የማድረግ እና የእውነትን ድምጽ የማጥፋት ቀጣይ ስልታዊ ፖሊሲን ያንፀባርቃል" ብሏል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ ዊሻህ ከቅርብ ወራት ወዲህ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ወደ ሚሰነዘሩ የስናይፐር ጥቃት እቅዶች ተሸጋግሯል ሲል ተጨማሪ ማስረጃ ሳያቀርብ ተናግሯል።

    እንደ ሆስፒታል እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መረጃ ከሆነ በቡሬጂ የስደተኞች መጠለያ በሚገኘው የዊሻህ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሌሎች ሁለት ሰዎችም ተገድለዋል።

    የእስራኤል ጦር ሌሎች የተገደሉት ሠዎችም የሐማስ አባላት ናቸው ሲል ወንጅሏል።

    የአል ጃዚራ ዘጋቢ የሆነው የዊሻህ ወንድም ሞሐመድ ሚያዚያ ወር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተገድሏል።

    የእስራኤል ጦር በሐማስ ሮኬት እና ጦር መሣሪያ ማምረቻ ዋና መሥሪያ ቤት ይሰራ ነበር ሲል ያለ ተጨማሪ መረጃ ከስሶታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ከተማ ሳብራ በሚባል አካባቢ አራት የቤተሰብ አባላት ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውን በአቅራቢያው የሚገኝ ሆስፒታል፣ የሲቪል መከላከያ እና ቤተሰቦች ተናግረዋል።

    ሺፋ ሆስፒታል ለጋዜጠኞች የሁለት ሕጻናትን ጨምሮ የቤተሰቡን አስከሬን መረከቡን ተናግሯል።

    የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ ጥቃት ከሞቱት መካከል ሁለት ሴቶች እና አንድ ሕጻን እንደሚገኙበት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    በሰሜናዊ ጋዛ ተጨማሪ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተሰምቷል።

    እስራኤል እና ሐማስ በጥቅምት ወር የተደረሰውን የተኩስ አቁም በመጣስ እርስ በእርሳቸው ይካሰሳሉ።

  8. ኢራን ሆርሙዝን እንደዘጋች ብታሳውቅም ከአሜሪካ ጋር በስዊትዘርላንድ ንግግራቸውን ሊጀምሩ ነው

    የኢራን ጦር እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃት መፈጸሟን በመቀጠሏ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቱን ቢያሳውቅም ቴህራን ከዋሺንግተን ጋር የምታደርገውን ድርድር በስዊትዘርላንድ ልትጀምር ነው።

    የአሜሪካ ጦር ወሽመጡ አልተዘጋም “መርከቦች እየተንቀሳቀሰ ነው” ቢልም ኢራን ግን እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት ጦርነቱን ለማቆም የተፈረመውን ስምምነት የጣሰ ነው በሚል መዝጋቷን አስታውቃለች።

    ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በድርድሩ ላይ ለመካፈል ወደ ስዊትዘርላንድ ማምራታቸው ተሰምቷል።

    የኢራን ልዑካን ቡድን አባላት የሆኑት የፓርላማው አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ በስዊትዘርላንድ ቀድመው ደርሰዋል።

    የመጀመርያው ዙር ንግግር እሁድ ይጀመራል የተባለ ሲሆን ቫንስ “በኒውክሌር ጉዳዮች ዙሪያ” እንዲሁም “በሊባኖስ የተኩስ አቁም ላይ” መግባባት ሊኖር ይችላል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

    ቫንስ አውሮፕላናቸው ከመነሳቱ በፊት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ስላለው ግጭት ተጠይቀው “ነገሮች እዚያ እየተሻሻሉ ነው፤ እና ደግሞ ነገሮች ትንሽ እየዘገዩም ነው” ብለዋል።

    "እስራኤል እና ሊባኖስ ሁለቱም ሰላማቸው እና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለማቋረጥ መነጋገር ያለብን ይሆናል። የዚህ ዓላማ በመሠረቱ ያ ነው፤ መላውን ቀጣና ሰላማዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ" ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢስማኤል ባጋይ አገራቸው “ሌላው ወገን ግዴታውን ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ትፈልጋለች” ብለዋል።

    የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በንግግሩ ላይ እንደሚሳተፉ ጽህፈት ቤታቸው ለቢቢሲ አረጋግጧል።

    ፓኪስታን በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚካሄደውን ድርድር በማሸማገል እየተሳተፈች ሲሆን ከዚህ በፊት የተካሄዱ ውይይቶችን በኢዝላማባድ አስተናግዳለች።

    በዚህ ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እና የኢራኑ አቻቸው ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል 14 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

    ስምምነቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር እና ተጨማሪ ድርድር በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ እንደሚደረግ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

    የስምምነቱ እንቅፋት የሆነው በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ነው።

    ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ተከታታይ ጥቃት 47 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    የእስራኤል መከላከለያ በበኩሉ 80 የሄዝቦላህ ዒላማዎችን እና “በርካታ” አባላቶቹን መደብደቡን ይፋ አድርጓል።

    ጦሩ አክሎም አራት ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል።

    አሜሪካ እና ኢራን መስማማታቸውን ይፋ ካደረጉ ጊዜ ጀምሮ ሄዝቦላህ እና እስራኤል አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

    ነገር ግን አርብ ዕለት በሁለቱ መካከል ስምምነት መደረሱ ተገልጾ ነበር።

  9. የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት መርከቦችን አስጠነቀቀ

    የኢራን ማዕከላዊ ወታደራዊ ዕዝ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ በመሆኑ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቱን አስታወቀ።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል የባሕር መተላለፊው ለሁሉም መርከቦች በመዘጋቱ ማናቸውም መርከቦች የወደ ወሽመጡ የሚቀርቡ ከሆነ ለአደጋ ስለሚጋለጡ እራሳቸውን ከሆርሙዝ እንዲያርቁ አስጠንቅቋል።

    ዕዙ አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ አርብ ዕለት ሙሉ ለሙሉ የተከፈተው ወሳኙ የባሕር ላይ መተላለፊያ ለሁሉም መርከቦች ዝግ እንደሚሆን አሳውቋል።

    ኻታም አል አንቢያ በመባል የሚታወቀው ወደታራዊ ዕዙ ጨምሮም “ይህ ጠላት የገባውን ቃል ባለማክበሩ የተወሰደ የመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ነው፤ ጠላት ግዴታውን እንዲወጣ በቀጣይነት ተጨማሪ እርምጃዎች በማቀድ የሚወሰዱ ይሆናል” ብሏል በአገሪቱ ቴሌቪዥን በቀረበው መግለጫ ላይ።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት ላይ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታካሂደው ተከታታይ ጥቃት እንደሚቆም የተገለጸ ቢሆንም ግጭቱ በመቀጠሉ ኢራን ስምምነቱ ተጥሷል ብላለች።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲዘጋ በኢራን የተላለፈው ውሳኔ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ እየፈጸመችው ነው ባለችው ”የጭካኔ ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል” አለመቆሙ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

    የስምምነቱ የመጀመሪያ ነጥብ አሜሪካ፣ ኢራን እና አጋሮቻቸው ሊባኖስን ጨምሮ “በሁሉም ግንባሮች” የሚያካሂዷቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎች “በአስቸኳይ እና በዘላቂነት ማቆማቸውን” ያውጃሉ ብሏል።

    የኢራን ወታደራዊ ዕዝ ጨምሮም የእስራኤል ኃይሎች ከደቡባዊ ሊባኖስ አለመውጣታቸው ለሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አመለክቷል።

    እስራኤል እና ሄዝቦላህ አርብ ዕለት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ቢዘገብም ግጭቱ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ኢራን እና አሜሪካ ለቀጣይ ድርድር ስዊትዘርላንድ ውስጥ ይገናኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

  10. አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ጥቃት ፈጸመች

    እስራኤል እና ሄዝቦላህ የደረሱበት አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት 24 ሰዓት ሳይሞላው እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ብዙ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    የሊባኖስ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደዘገበው ቢያንስ 16 ሰዎች በእስራኤል የድሮን እና የጦር አውሮፕላን ጥቃት ተገድለዋል።

    አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ናባቲያህ በተባለው አካባቢ መሆኑም ተገልጿል።

    የእስራኤል ጦር “የአሸባሪው ሄዝቦላህ ዒላማዎችን መትተናል” ብሏል። ጥቃቱ የተፈጸመው ከደቡብ ሊባኖስ ወደ እስራኤል 50 ተተኳሾች ከተወነጨፉ በኋላ መሆኑንም ጦሩ ገልጿል።

    እስራኤል በሊባኖስ እየፈጸመች ያለውን ጥቃት አሜሪካ አውግዛለች።

    አሜሪካ እና ኢራን የደረሱበት ስምምነት እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በምታደርሰው ጥቃት ሳቢያ አደጋ ተጋርጦበታል።

  11. ማዕቀብ የተጣለባቸው የኢራን ሃብቶች "በሒደት እንደሚለቀቁ" ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናገሩ

    የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ ጃፋር ጋምፔናህ ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ማዕቀብ የተጣለባቸው የቴህራን ሃብቶች “በሒደት እንደሚለቀቁ” ተናገሩ።

    አጠቃላይ ማዕቀብ የተጣለበት የኢራን ሃብት ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ገልጸዋል።

    ከኢርና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ እና ሌሎችም ተደራዳሪዎች የቴህራን ሃብት እንዴት እንደሚለቀቅ ከውሳኔ ላይ የሚደርሱ ይሆናል።

    የጦርነቱ መቆም የሕዝቡን ምጣኔ ሃብታዊ ጫና እንደሚያቀልለው ገልጸዋል።

    “ማዕቀብ የተጣለባቸው የኢራን ሃብቶች ሲለቀቁ መንገድ፣ አውሮፕላን ማረፊያ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ላይ በመዋል የሕዝባችንን ደኅንነት እና ምቾት ያስጠብቃሉ” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ያመራችው “ተዳክማ” ነው ብለዋል።

    “የተደራደርነው ተስፋ ስለቆረጥን አይደለም። ኢራን ነች ተስፋ የቆረጠችው። አብቅቶላቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

    ኢራን “ስባሪ ሳንቲም” እንደማይሰጣትም ትራምፕ አስረግጠው ተናግረዋል።

  12. 11 የኢራን ብሔራዊ ቡድን አባላት የአሜሪካ ቪዛ መከልከላቸው ተዘገበ

    የኢራን ብሔራዊ ቡድን ከቤልጂየም ጋር ለሚያደርገው ግጥሚያ ወደ አሜሪካ ሊጓዙ የነበሩ 11 የቡድን አባላት ቪዛ መከልከላቸው ተዘገበ።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሐፊን ጠቅሰው እንደዘገቡት “ለሁለተኛ ጊዜ” ቪዛ ተከልክለዋል።

    “የተወሰኑ የቡድኑ መሪዎች እንደጠበቅነው ለሁለተኛ ጊዜ ቪዛ ተከልክለዋል። ቪዛ ባለማግኘታቸው ከቤልጂየም ጋር በሚደረገው ጨዋታ ወቅት አይኖሩም” ማለታቸው ተገልጿል።

    ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ እንደተመለከተው፤ በዓለም ዋንጫ በሚሳተፈው የኢራን ብሔራዊ ቡድን ላይ የቪዛ ክልከላ ለመጣል ታስቧል።

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጽህፈት ቤት የዓለም ዋንጫ ግብረ ኃይል ዋና ኃላፊ አንድሪው ጂሊያኒ እንደተናገሩት ሎስ አንጀለስ ከተካሄደው ጨዋታ በኋላ የኢራን ብሔራዊ ቡድን ወደ ሜክሲኮ፣ ቲጁዋና እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል።

    በሲያትል የሚካሄደውን ቀጣይ ጨዋታ በተመለከ የደኅንነት ጉዳዮች ከግምት ገብተው ግምገማ እየተካሄ መሆኑን አክለዋል።

    የኢራን የእግር ኳስ ፌደሬሽን ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ እንደገለጸው የቪዛ ክልከላዎች ለዓለም ዋንጫ እኩል ዕድል መስጠትን ያማከሉ አይደሉም።

    ክልከላዎቹ በድኑ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድሩ እና ለፊፋ ይፋዊ ቅሬታ እንደሚያቀርብም ፌደሬሽኑ አስታውቋል።

  13. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቀጣይ ዒላማቸው ኩባ ልትሆን እንደምትችል ጠቆሙ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቬንዙዌላ እና ኢራን ቀጥላ ኮሚኒስቷ ጎረቤታቸው ኩባ ዒላማቸው ልትሆን እንደምትችል ጠቆሙ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካው መገናኛ ብዙኃኝ አክሲዮስ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ ከኢራን ጋር የደረሱበት ስምምነት “ዓለምን ከምጣኔ ሃብት ውድቀት እንደታደገ” ተናግረዋል።

    ከኢራን ጦርነት በኋላ ሥልጣናቸው ላይ ገደብ ይኖር ከሆነ ተጠይቀው “ምንም ገደብ የለም” ሲሉም መልሰዋል። ምናልባት የሥልጣን ገደቦች ሊኖሩ ቢችሉም “ገና ትምህርት እንዳልወሰዱ” ሲሉ አክለዋል።

    የኢራን ጦርነት ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት መላሸቅ ሊያስከትል ይችል እንደነበር ጠቅሰው፤ አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት መፈረማቸው ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ እንደቀለበሰው ገልጸዋል።

    ትራምፕ ተመሳሳይ እርምጃ በኩባ ላይ ሊወስዱ እንደሚችሉ በቃለ ምልልሱ ወቅት ጠቁመዋል።

    ከኢራን “በበለጠ” ኩባ እና ቬንዝዌላ ለአሜሪካ ካላቸው ቅርበት አንጻር እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

  14. የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ እንደሚሄዱ ተነገረ

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ በተናጠል ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ስዊትዘርላንድ እንደሚያቀኑ ተነገረ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሚቀጥለው ሳምንት ከባሕረ ሰላጤው አጋሮቻቸው ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚያቀኑ ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ደግሞ ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ለመገኘት ወደ ጄኔቭ ተጉዘዋል።

    የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ እንደዘገበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ቀናት በባሕረ ሰላጤው በተካሄደው ጦርነት የኢራን ዋነኛ ዒላማ የነበሩት የአሜሪካ ወዳጆች ወደሆኑት ኩዌት፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ባህሬን ይጓዛሉ።

    በተጨማሪም ማርኮ ሩቢዮ ባህሬን ውስጥ በሚካሄደው የባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

    ነገር ግን የሚኒስትሩን ጉዞ በተመለከተ ሮይተርስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸውን ማረጋገጫ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    በተመሳሳይ የፕሬዝዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በኢራን የኒውለሌር መረሃ ግብር ላይ በሚደረገው የመጀመሪያ ዙር ንግግር ለመገኘት ወደ ስዊትዘርላንድ ተጉዘዋል።

    የአሜሪካ መንግሥት አንድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ከዊትኮፍ ቀደም ብለው የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ባል እና አንደኛው መልዕክተኛ ጃሬድ ኩሽነር ስዊትዘርላንድ ውስጥ ይገኛሉ።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር አርብ ዕለት ይጀመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላህ ላይ እየፈጸመችው በነበረው ጥቃት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል። አሁንም ንግግሩ የሚጀመርበት ቀን በትክክል አልታወቀም።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚካሄደው ንግግር ዋነኛው አደራዳሪ የሆኑት የኳታሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አርብ ዕለት ስዊትዘርላንድ ገብተዋል።

    የአሜሪካንን ተደራዳሪዎች ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ይመራሉ ተብሎ የተነገረ ቢሆንም ሐሙስ ዕለት ጉዟቸው መሰረዙ ተነግሯል፤ ነገር ግን በቀጣይ ቀናት ወደ ስዊትዘርላንድ ይጓዙ እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ የመግባቢያ ስምምነቱ ቀደም ሲል የተፈረመ በመሆኑ “ስዊትዘርላንድ ውስጥ ለሚደረገው ንግግር የሚያጣድፍ ነገር የለም። ነገር ግን በቀጣይ ቀናት ለመገናኘት ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል።

  15. 18 ሊባኖሳውያን እና 4 የእስራኤል ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረሰ

    አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ይቆማል የተባለው እስራኤል ሄዝቦላህን ዒላማ አድርጋ ሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደው ጦርነት ከተባባሰ በኋላ የተኩስ አቁም መደረሱ ተነገረ።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት እስራኤል እና ሄዝቦላህ ዛሬ አርብ በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ከ10 ሰዓት ጀምሮ ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል።

    የተኩስ አቁሙ የተሰማው ሐሙስ ሌሊት እስራኤል ተከታታይ የአየር ድብደባዎችን ሊባኖስ ውስጥ ፈጽማ ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ካስታወቀ በኋላ ነው።

    በተጨማሪም በእስራኤል በኩል አራት ወታደሮቿ መገደላቸውን ይፋ አድርጋለች።

    ቀደም ሲል የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሊባኖስ ውስጥ በኢራን ከሚደገፈው ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው ይዞታዎች ናቸው ያላቸውን 80 ዒላማዎችን በመምታት “በርካታ” አባላቱን መግደሉን አስታውቆ ነበር።

    የተኩስ አቁም ስምምነቱ የተሰማው አሜሪካ እና ኢራን በሊባኖስ ውስጥ ዘላቂ የግጭት ማስቆምን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ግጭት ለማብቃት ስምምነት ከፈረሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

  16. የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር ወደ ሌላ ጊዜ ሲተላለፍ፣ ሊባኖስ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ተባብሷል

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሊጀምር የነበረው የቀጥታ ንግግር የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጉዟቸውን በማዘግየታቸው ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ።

    ንግግሩ የሁለቱ አገራት መሪዎች ጦርነቱን ለማስቆም ከስምምነት ደርሰው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥላው የነበረውን የባሕር ላይ ዕገዳ ካነሳች በኋላ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ይሆናል ተብሎ ነበር።

    ምንም እንኳን ስምምነቱ አስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደውን ጥቃት ያስቆማል ቢባልም ሐሙስ ሌሊት በደቡብዊ ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸመ የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

    አሜሪካ መግለጫ ከማውጣቷ ከሰዓታት በፊት ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያለው የመገናኛ ብዙኃን በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ንግግር የማይካሄደው በእስራኤል ጥቃት ምክንያት መሆኑን ዘግቦ ነበር።

    አሜሪካ ግን ለድርድሩ የሚያስፈልገው ዕቅድ “ገና አለመጠናቀቁን” ነገር ግን “ቴክኒካዊው ንግግሩ በታቻለ ፍጥነት በቶሎ እንዲጀመር” ፍላጎት እንዳለት ገልጻለች።

    ድርድሩ የመግባቢያ ስምምነት በመባል የሚጠራውን ሰነድ በመተግበር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ እየተጠበቀ የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራምን ጨምሮ በሌሎች ዘላቂ ጉዳዮች ላይ ይሆናል ተብሎ ነበር።

    አስራ አራት ነጥቦች ያሉት የመግባቢያ ሰነድ የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት፣ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ማድረግ፣ ለኢራን መልሶ ግንባታ የ300 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ እና በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቅቦችን ማንሳትን ያካትታል።

    ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች ተከታታይ ንግግሮችን በማድረግ ሊራዘም በሚችል ነገር ግን ቢበዛ በ60 ቀናት ውስጥ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ያስገድዳል።

    የአሜሪካ እና የኢራን ንግግር አካል የሆነው እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ የምታካሂደው ወታደራዊ ጥቃት ማቆም ጉዳይ ተግባራዊ ባለመሆኑ የስምምነቱን ዘላቂነት አሳሳቢ አድርጎታል።

  17. በእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን ሊባኖስ ገለጸች

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ተከታታይ የአየር ጥቃት ምክንያት ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    እስራኤል በበኩሏ በሄዝቦላህ ጥቃት አራት ወታደሮቿ እንደተገደሉ ገልጻለች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ዒላማ ያደረገው ታጣቂዎችን እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሚጠቀምባቸውን መሠረተ ልማቶችን እንደሆነ ተናግሯል።

    ኢራን እና አሜሪካ የደረሱበት ስምምነት ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ጦር ግንባሮች ተኩስ አቁም ማድረግን ያካትታል።

    ስምምነቱ ላይ ከተደረሰ በኋላ እስራኤል እና ሄዝቦላህ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ጥቃት መሰንዘር ቀጥለዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው “የደኅንነት ማስከበሪያ ቀጣና” ካሉት ደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ እንደማይወጣ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የተኩስ አቁም “በሁሉም ግንባሮች” ይተገበራል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

  18. አሜሪካ ስምምነቱን ከጣሰች ከባድ ምላሽ ይጠብቃታል ስትል ኢራን አስጠነቀቀች

    አሜሪካ ከኢራን ጋር የደረሰችውን ስምምነት የምትጥስ ከሆነ ከባድ ምላሽ እንደሚገጥማት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጊር ጋሊባፍ ተናገሩ።

    ከአሜሪካ ጋር ለተደረሰው ስምምነት ዋነኛ ተደራዳሪ የነበሩት አፈ ጉባዔው በኤክስ ገጻቸው ላይ የኢራን አብዮታዊ እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒን መልዕክት ተከትሎ ባሰፈሩት መልዕክት ነው ኢራን አሜሪካ የገባችውን ቃል እንድታከብር ያሳሰቡት።

    በዚህም ጋሊባፍ የጠቅላይ መሪውን “ትዕዛዝ በመቀበል” ከአሜሪካ ጋር ከመግባባት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች እና አንቀጾች ተግባራዊ መሆናቸውን እንደሚከታተሉ አሳውቀዋል።

    ነገር ግን አሜሪካ “ታማኝ ሳትሆን በመቅረት ስምምነቱን የምትጥስ ከሆነ” ኢራን ያለማወላወል የሚደመስስ እርምጃ እንደምተወስድ አፈ ጉባዔው ጽፈዋል።

    ጨምረውም አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው ጦርነት ድል መቀዳጀቷን በመጥቀስ “አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ለመጓዝ ከመረጡ የበለጠ ከባድ ምት ይጠብቃቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  19. ኔታንያሁ እስራኤል ከደቡብ ሊባኖስ እንደማትወጣ አስታወቁ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸው “የደኅንነት ማስከበሪያ ቀጣና” ካሉት ደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ እንደማይወጣ አስታወቁ።

    “ከጋዛ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ደኅንነት እና ብልጽግናን እንዳረጋገጥነው ሁሉ በሰሜን እስራኤል መንደሮች እና ከተሞችም ውስጥ ደኅንነት እና ብልጽግናን እናስከብራለን” ሲሉ በአንድ አውራ ጎዳና ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

    ይህንን ለማረጋገጥም “በደቡብ ሊባኖስ ከውጊያ ውጭ ከሆኑ ይዞታዎች እንደማያፈገፍጉ” ገልጸዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር የደረሰችበት የመግባቢያ ሰነድ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ማድረግን እና የግዛት ሉዓላዊነት ማስጠበቀን እንደሚያካትት አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በስምምነቱ መሠረት “ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ማድረግን ጨምሮ በሁሉም የውጊያ አውድማዎች የተኩስ አቁም እንደሚተገበር እንጠብቃለን” ብለዋል።

  20. አሜሪካ የኢራንን የባሕር መተላለፊያ ማዕቀብ ስታነሳ ጠቅላይ መሪው ስምምነቱን ተቹ

    አሜሪካ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረውን የባሕር ላይ መተላለፊያ ማዕቀብ አንስታለች።

    ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለማቆም መስማማታቸውን ተከትሎ ክልከላው መነሳቱን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አረጋግጧል።

    ውሳኔው የተላለፈው “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት” እንደሆነ የገለጸው ማዕከላዊ ዕዙ፤ የአሜሪካ መርከቦች “በአካባቢው እንደሚቆዩ” አስታውቋል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጃትባ ኻሜኒ በበኩላቸው ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም “የተለየ ዕይታ” እንዳላቸው ተናግረዋል።

    ስምምነት ላይ እንዲደረስ የፈቀዱት ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን “የኢራናውያንን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስጠብቁ” ማረጋገጫ ስለሰጧቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

    ጠቅላይ መሪው እንዳሉት፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ተስፋ በመቁረጣቸው ሁሉንም አማራጭ እየተጠቀሙ” ስለነበረ ስምምነቱ ተፈርሟል።

    በቀጣይ በየሁለቱ አገራት መሪዎች በአካል ተገናኝተው ድርድር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

    የመግባቢያ ሰነዱ ላይ መስማማት “የጠላትን አቋም መቀበል” ማለት እንዳልሆነ ጠቅላይ መሪው አክለዋል።

    ሞጃትባ ኻሜኒ ስለ ስምምነቱ አስተያየታቸውን በይፋ ሲሰጡ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጥታ ለጠቅላይ መሪው ምላሽ ባይሰጡም፤ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የተኩስ አቁም “በሁሉም ግንባሮች” ይተገበራል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።