ኢራን፤ ኒውክሌርን በተመለከተ “በዋነኛ መርሆች” ላይ ከአሜሪካ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን፤ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር “በዋነኛ መርሆች” ላይ እንደተግባቡ አስታወቀች።
ሁለቱ አገራት በጄኔቫ ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ካደረጉ በኋላ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እንደተናገሩት፤ የኒውክሌር “ዋነኛ መርሆችን” በተመለከተ መግባባት ላይ ተደርሷል። አሜሪካም “በውይይቱ መሻሻል ታይቷል” ስትል ገልጻለች።
የአሸማጋይዋ ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳዲ “የጋራ ግቦችን በመለየት እና የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ድርድሩ ጥሩ መሻሻል ታይቶበታል” ብለዋል።
የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ስትዝት ቆይታለች።
አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ፤ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ልትገነባ ነው ቢሉም ቴህራን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
አሜሪካ እና ኢራን ከሚደራደሩባቸው ነጥቦች ዋነኛው የኒውክሌር ጉዳይ ነው።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን “መሻሻል ቢኖርም ብዙ የምንወያይባቸው ዝርዝር ነጥቦች አሉ። የምንለያይባቸውን ነጥቦች በተመለከተ ኢራናውያን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ምክረ ሐሳም ይዘው እንደሚመጡ ገልጸዋል” ሲሉ ስለ ድርድሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በበኩላቸው “አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ድርድሩ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል። ፕሬዝዳንቱ ቀይ መስመር ብለው ያስቀመጧቸው እና ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው ነጥቦችም አሉ” ሲሉ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።


















