የቀድሞው የብሪታኒያ ልዑል ከሰዓታት እስር በኋላ ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የብሪታኒያ ልዑል አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር በብልሹ አሰራር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ተለቀዋል።
ፖሊስ ሐሙስ ጠዋት ላይ የ66 ዓመቱን የቀድሞ ልዑል በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን፤ በሁለት መኖሪያ ቤቶቻቸው ላይም ብርበራ አድርጓል።
ወንድማቸው ንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ የአንድሪውን እስር በሚመለከት በሰጡት ምላሽ “ሕጉ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ መሆን አለበት” ያሉ ሲሆን፤ ለፖሊስ ሙሉ ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።
ፖሊስ ከዚህ ቀደም አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ከአሜሪካዊው የወሲብ ብዝበዛ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት እና ሚስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ጥርጣሬ ምርመራ ለመክፈት ስለማሰቡ አሳውቆ ነበር።
በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የነበረው የመልዕክት ልውውጥ በቅርቡ በአሜሪካ መንግሥት ይፋ ሆኗል።
ሐሙስ ምሽት ፖሊስ አንድሪው በምርመራ ላይ እያሉ ከእስር መለቀቃቸውን አስታውቋል።
ከጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዓመታት ስማቸው ሲነሳ የነበሩት የቀድሞው ልዑል በቁጥጥር ስር ሲውሉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ባለፉት ዓመታት ምንም ወንጀል አለመስራታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ፖሊስ ካደረገው “ጥልቅ ግምገማ” በኋላ በአንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ላይ ይፋዊ ምርመራ መከፈቱን ገልጿል።
የቀድሞው ልዑል በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከወሲባዊ ጥቃት ጥርጣሬ ጋር የተያያዘ አይደለም።



















