ኢራን ጠቅላይ መሪዋን ልትሰይም ነው፤ እስራኤል መራጮቹን እና ተመራጩን እያደነች መሆኗን ገለጸች

ቀጣዩን የኢራን ጠቅላይ መሪ ለመሰየም እየመከረ ያለው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ከፍተኛ የሊቃውንት ጉባዔ ከስምምነት ላይ መድረሱ ተነገረ። ጉባዔው የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ የጋራ አቋም ላይ መድረሱ አንድ አባሉ ሲናገሩ፣ እስራኤል ደግሞ መራጮችን እና ተመራጩን ዒላማ ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታወቀች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቪዲዮ፡ የቴህራንን ሰማይ በጭስ የሸፈኑት ፍንዳታዎች በከፊል

    ለስድስተኛ ቀን በቀጠለው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ዛሬ ሐሙስ ከፍተኛ ፍንዳታዎች በዋና ከተማዋ ውስጥ ተከስቷል። በከተማዋ አብዛኛው ክፍል ሰማይ ላይም ጭስ ተንሰራፍቶ ታይቷል። ይህ ቪዲዮም በከፊል ይህንን ክስተት ያሳያል። ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ቪዲዮዎችን ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይከተሉ፦ https://bbc.in/4rg4L8e

  2. ከባድ ፍንዳታ ቴህራንን ሲያናውጥ፣ ኢራን በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳዔሎችን ተኮሰች

    በቴህራን ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት ስድስተኛ ቀን ላይ በቴህራን እና በሌሎችም የኢራን ከተሞች ውስጥ ከባድ ፍንዳታዎች ሲሰሙ፣ ከኢራን በኩል ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ሚሳዔሎች በእስራኤል ላይ መተኮሳቸውን ጦር ሠራዊቷ አስታወቀ።

    ዛሬ ጠዋት በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የዋና ከተማዋ አብዛኛው ሰማይ በጥቁር ጭስ ተሽፍኖ የሚታይ ሲሆን፣ ከቴህራን በስተምዕራብ የምትገኘው ካራጅ ከተማ በድጋሚ በእስራኤል እና በአሜሪካ ጥቃት ተመትታለች። ቡካን እና ሳናንዳጅ ከተሞችም እንዲሁ ከባድ ጥቃት የተፈጸመባቸው ናቸው።

    በተመሳሳይ ኢራን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል መተኮሷን የእስራኤል ጦር ሠራዊት አስታውቆ፣ ሚሳዔሎቹን ለማክሸፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና የማስጠንቀቂያ መልዕክት በዜጎቹ ስልክ በኩል እየላከ ነው።

    የማስጠንቀቂያው መልዕክት የደረሳቸው ሰዎች ሌላ መልዕክት እስከሚደርሳቸው ድረስ በመሸሸጊያ ቦታዎች ውስጥ እንዲቆዩ ተመክረዋል።

    ኢየሩሳሌም ከተማ የሚገኙ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤኤፍፒ ዘጋቢዎች የጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች እና ፍንዳታዎችን መስማታቸውን ዘግቧል።

    በተጨማሪም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በኢራን ሚሳዔል እና ድሮኖች በተከታታይ ጥቃት እየተፈጸመባት ያለችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዛሬው ዕለት ሚሳዔሎችን እና ከ100 በላይ ድሮኖችን እንደተተኮሱባት አሳውቃለች።

    የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ‘ቢቢሲ ቬሪፋይ’ ያገኛቸው የሳተላይት ምሥሎች ከቅዳሜ ጀምሮ በኢራን ላይ እየተፈጸመ ባለው ጥቃት የኢራን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራር ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳዩ።

    በተመሳሳይም ኢራን ባህሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሰማይ ጠቀስ የመኖሪያ ሕንጻ ተመትቶ ጉዳት እንደደረሰበት የሳተላይት ምሥሎች አመለከቱ።

    ቫንተር በተባለው የመረጃ ተቋም ረቡዕ ዕለት የተነሱት የሳተላይት ምሥሎች በምዕራባዊ ቴህራን የሚገኘው የአገሪቱ አየር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት አሳይቷል።

    በኢራን ላይ ጥቃት ከተከፈተበት ዕለት አንስቶ 1,045 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከእነዚህም መካከል በአንድ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በመጀመሪያው ዕለት በተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያልተቋረጠ ጥቃት እየፈጸሙ ባለበት ጊዜ ኢራን በበኩሏ በእስራኤል እና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን የአጸፋ ጥቃቶችን እየፈጸመች ነው።

    በቴህራን ጉዳት የደረሰበት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  3. ዩኤኢ በሚሳዔል ስትመታ፤ እስራኤል የኢራን ሚሳዔሎች እንደተወነጨፉባት አስታወቀች

    የዱባዩ ጀበል አሊ ወደብ በከሸፈ ሚሳዔል ስብርባሪበመመታቱ በመርከብ ማቆሚያዎች ላይ የእሳት አደጋ ደርሶ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የዱባዩ ጀበል አሊ ወደብ በከሸፈ ሚሳዔል ስብርባሪ በመመታቱ በመርከብ ማቆሚያዎች ላይ የእሳት አደጋ ደርሶ ነበር

    በዛሬው ዕለት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተወነጨፉ ስድስት ባለስቲክ ሚሳዔሎችን እና 131 ድሮኖችን ማክሸፉ እና ማውደም መቻሉን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። አንድ ሚሳዔል እና ስድስት ድሮኖች ግን አገሪቱ ውስጥ መውደቃቸውን መከላከያ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት፤ “ግልጽ የሆነው የኢራን ጥቃት ከተጀመረበት” ቅዳሜ ዕለት አንስቶ 196 ባሊስቲክ ሚሳዔሎች ወደ አገሪቱ መወንጨፋቸው እንደታወቀ አስረድቷል። ስምንት ክሩዝ ሚሳዔሎች ደግሞ እንደተለዩ እና እንደወደሙ አስታውቋል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት የፓኪስታን፣ የኔፓል እና የባንግላዲሽ ዜግነት ያላቸው ሦስት ሰዎች እንደተገደሉ እና 94 ሰዎች እንደቆሰሉ መከላከያ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ አገሪቱን ዒላማ ያደረጉ ተከታታይ የኢራን ሚሳዔሎች መወንጨፋቸውን እና ወደ አገሪቱ እየመጡ መሆኑ እንደተለየ ገልጿል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባወጣው መረጃ፤ የአገሪቱ የመከላከያ ሥርዓቶች ሚሳዔሎቹን ለማክሸፍ እየሠሩ መሆኑን አስታውቋል። ጥቃት ሊደርስባቸው በሚችሉ አካባቢዎች ወደሚገኙ ሞባይል ስልኮችን የማስጠንቀቂያ መልዕክት መላኩንም አክሏል።

    የማስጠንቀቂያ መልዕክት የደረሳቸው ሰዎች ተጨማሪ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ በተጠበቁ መጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል ተብሏል።

  4. በርካታ የአውሮፓ አገራት ቆጵሮስን ለመጠበቅ የባሕር ኃይላቸውን መላክ ጀመሩ

    ቆጵሮስ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሰፈር እሁድ ዕለት የድሮን ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ቆጵሮስ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሰፈር እሁድ ዕለት የድሮን ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር

    የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆቸውን ቆጵሮስ ውስጥ የሚገኝ የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሰፈር ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ አገራት ደሴቲቷን ለመጠበቅ የባሕር ኃይላቸውን መላክ ጀመሩ።

    የጣልያን መከላከያ ሚኒስትር ጊዶ ክሮሴቶ አገራቸው ቆጵሮስን ለመከላከል ከስፔን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ ጋር በመሆን "የባሕር ኃይል መሣሪያዎችን” እንደምትልክ ተናግረዋል።

    የባሕር ኃይሎቹ ስምሪት በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሚከናወንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    የፈረንሳይ መንግሥትም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከጣልያን እና ግሪክ መሪዎች ጋር የስልክ ንግግር እንዳደረጉ እና አገራቱ ጦራቸውን ወደ ቆጵሮስ ለመላክ እንደተስማሙ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ከደቂቃዎች በፊት በሜዲትራኒያን ደሴት በምትገኘው ቆጵሮስ ውስጥ የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሰፈር ባለበት አክሮቲሪ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚገልጽ የማስጠንቀቂያ ደውል ተሰምቷል።

    ለአካባቢው ነዋሪዎች የተሰማው ማስጠንቀቂያ ድምጽ ለ10 ደቂቃ ገደማ ቆይቷል። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ ሳይፕረስን እየጎበኙ ባለበት በዛሬው ዕለት ነው።

    አገሪቱ መንግሥት ኋላ ላይ በሰጠው ማብራሪያ፤ አንድ ቁስን በተመለከተ የደረሰውን መረጃ እየመረመረ እንደነበር ገልጿል። ቁሱ ወደ ብሪታኒያ የጦር ሰፈር እያመራ መሆኑን የሚያሳይ ምንም ምልክት እንደሌለም አስታውቋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ሰፈር የሚገኝበት ይህ ስፍራ እሁድ ዕለት የድሮን ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።

  5. የኢራን መንግሥት፤ አሜሪካ እና እስራኤል "የሲቪሊያን አካባቢዎችን ዒላማ” አድርገዋል አለ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኤስማኢል ባቃኢ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አሜሪካ እና እስራኤል በአገሪቱ በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ሆነ ብለው የሲቪሊያን አካባቢዎችን ዒላማ እያደረጉ ነው ሲል ከሰሰ።

    የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኤስማኢል ባቃኢ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የሚፈጸሙት ጥቃቶች “ተጽዕኗቸው በዓለም አቀፉ ገበያ እየተሰማ፣ የኢነርጂ ዋጋን እየጨመሩ፣ የገንዘቦችን ተመን እያናጉ” እንደሆነ ገልጸዋል። “በዓለም ዙሪያ ያሉ መደበኛ ሰዎችን የመግዛት አቅም እያዳከሙ” መሆኑንም አንስተዋል።

    “ለእኛ ለኢራናውያን ግን ጉዳቱ ሊለካ በማይችል ደረጃ ከፍተኛ ነው” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ።

    “ወራሪዎቹ ሆነ ብለው የሲቪል አካባቢዎችን እንዲሁም ማድረስ የሚቻለው ከፍተኛ ስቃይ እና የሕይወት መጥፋት መፈጸም የሚችሉበትን ማንኛውም ቦታ ዒላማ በማድረጋቸው ህዝባችን በጭካኔ እየተገደለ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ በተከፈተው ዘመቻ የአገሪቱን የባለስቲክ ሚሳዔል አቅም እና የኒውክሌር መሣሪያ የመገንባት ችሎታ ለማውደም እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ዘመቻ በከፈቱበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሚናብ በተባለው የኢራን ከተማ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    ከቅዳሜ ዕለት አንስቶ እስከ ረቡዕ ባሉት ቀናትም በኢራን ከ1,000 በላይ ንጹኃን መገደላቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል ‘ሂራና’ ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ 181 ያህሉ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆነ ሕጻናት ናቸው።

    የአሜሪካ ጦር በሴቶች ትምህርት ቤት ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ እያጣራ መሆኑን ሲያስታውቅ፤ የእስራኤል ጦር ደግሞ በአካባቢው ላይ ስለተካሄደ ማንኛውም ዘመቻ “እንደማያውቅ” ገልጿል።

  6. ባህሬን ከ70 በላይ የኢራን ሚሳዔሎችን ማክሸፏን አስታወቀች

    ኢራን በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ በተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽማለች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ኢራን በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ በተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽማለች

    አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከከፈቱበት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ከኢራን የተወነጨፉ 75 ሚሳዔሎች እና 123 ድሮኖችን ማውደሟን ባህሬን አስታወቀች።

    የባህሬን መከላከያ ሠራዊት በኢንስታግራም ገጹ ባወጣው መረጃ፤ “ተከታታይ እና አስከፊ የሆኑትን የኢራን የሽብር ጥቃቶች መመከት” መቀጠሉን ገልጿል። ነዋሪዎች አስፈላጊ ካልሆነ በቀር ከቤታቸው እንዳይወጡም አሳስቧል።

    በሲቪል ዒላማዎች ሚሳዔል እና ድሮኖችን መጠቀም “ግልጽ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግጋትን ጥሰት” እንዲሁም “የቀጠናዊ ሰላም እና ደኅንነት” ስጋት እንደሆነም ጠቅሷል።

    የኢራን ጥቃት ዒላማ ካደረጋቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ባህሬን ነች። ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ የባህሬን ዋና ከተማ ማናማ በተደጋጋሚ የኢራን ጥቃቶች ዒላማ ሆኗል።

    ኢራን፤ ባህሬን ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ቅዳሜ ዕለት በአገሪቱ የሚገኘው የአሜሪካ ባሕር ኃይል “ለሚሳዔል ጥቃት እንደተዳረገ” ተገልጿል።

    እሁድ ዕለት በባሕር ኃይሉ ጣር ሰፈር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ደግሞ ከባድ እሳት ተከስቶ ነበር። ኢራን በአገሪቱ በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች እንደተጎዱ የባህሬን መንግሥት አስታውቋል።

  7. ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ልትልክ ነው

    ኢራን በቴህራን በፈጸመችው ጥቃት የወደመ አካባቢ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛዋን እንደምትልክ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ረቡዕ ዕለት ተናገሩ።

    ልዩ መልዕክተኛው በመካከለኛው ምሥራቅ እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር የጀመሩትን ጦርነት ያሸማግላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ቤይጂንግ የኢራን የቅርብ አጋር ስትሆን ቴህራን ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ተናግራለች። በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ጥቃታቸውን እንዲያቆሙም አሳስባለች።

    ቻይና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ልዩ መልዕክተኛዋን በመላክ “እንደምታሸማግል” ዋንግ ከሳዑዲ አረቢያ አቻቸው ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ወቅት ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ ልዩ መልዕክተኛው ማን እንደሆኑ እና ወደ የትኛው የመካከለኛው አገራት እንደሚጓዙ የተባለ ነገር የለም።

    ዋንግ ቤይጂንግ “ምንጊዜም የሰላም ኃይል ናት፤ እንዲሁም ገንቢ ሚናዋን መጫወቷን ትቀጥላለች” ብለዋል።

    ቻይና ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ውጥረትን ለማስወገድ በተቻለ ፍጥነት ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመለሱም ጥሪ አቅርባለች።

  8. ስድስተኛ ቀኑን በያዘው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያካሄዱት ጦርነት ምን ምን ዐበይት ጉዳዮች ተከናወኑ?

    እስራኤል በኢራን የፈጸመችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል መከላከያ በቆም ከተማ የሚገኝ የባለስቲክ ማስወንጨፊያ እና በኢስፋሃን የአየር መከላከያ ስርዓት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል

    አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ በጋራ ጥቃት ከከፈቱ ስድስተኛ ቀናቸውን የያዙ ሲሆን በባህረ ሰላጤው ውስጥ ያለው ውጥረትም ጨምሯል።

    • ኢራን የባህረ ሰላጤ አገሮች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት በመቀጠል በባህሬን እና በኳታር ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል።
    • የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢራን ድሮኖች ጥቃት መፈጸማቸውን እና ሁለት ሰላማዊ ዜጎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። አንደኛው የአየር ማረፊያ ተርሚናል ሕንፃ ላይ ሲወድቅ ሌላኛው ደግሞ በትምህርት ቤት ሕንፃ አቅራቢያ ወድቋል።
    • ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን በባህረ ሰላጤው ውስጥ ያለ አንድ የአሜሪካ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በኢራን ባሕር ኃይል ጥቃት እንደደረሰበት እና "በእሳት እንደተያያዘ" ገልጿል። ይህ የሆነው የዩኬ የባሕር ኃይል ድርጅት አንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በኩዌት የባህር ዳርቻ ላይ መመታቱን ካስታወቀ በኋላ ነው።
    • አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን አዳዲስ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። በኢራን ዋና ከተማ ላይ ጭስ የታየ ሲሆን ነዋሪዎች ጥቃቶቹን ሲመለከቱ የሚያሳዩ ፎቶዎች ተጋርተዋል።
    • የእስራኤል መከላከያ በቆም ከተማ የሚገኝ የባለስቲክ ማስወንጨፊያ እና በኢስፋሃን የአየር መከላከያ ስርዓት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
    • ኢራን ወደ ቴል አቪቭ የምታስወነጭፈውን ሚሳዔል ብትቀጥልም የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን የአየር ክልሉ በከፊል እንዲከፈት ወስነዋል። ይህንንም ተከትሎ የቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ከአምስት ቀናት በኋላ ዳግም ተከፍቷል ። ወደ ቴል አቪቭ እስራኤላውያን የጫነ አውሮፕላን መድረሱም ተዘግቧል።
    • ከመካከለኛው ምሥራቅ ዜጎችን ወደ ዩኬ የሚያጓጉዝ አውሮፕላን በ"ቴክኒክ ችግር" ምክንያት መዘግየቱን ተከትሎ ዛሬ ኦማንን ለቅቆ እንደሚወጣ ተገልጿል።
    • የኳታር አየር መንገድ ደግሞ ከሙስካት፣ ኦማን የሚነሱ የሰብዓዊነት በረራዎችን እንደሚኖሩ ሲገልጽ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስም ውስን በረራዎች እንደሚደረጉ አስታውቃለች።
  9. በመካከለኛው ምሥራቅ ለቀናት ተቋርጠው የነበሩ አንዳንድ የአውሮፕላን በረራዎች ተጀመሩ

    የሉፍታንዛ አውሮፕላን ከሙስካት ኦማን አውሮፕላን ማረፊያ የጀርመን ቱሪስቶችን አሳፍሮ  በርሯል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የሉፍታንዛ አውሮፕላን ከሙስካት ኦማን አውሮፕላን ማረፊያ የጀርመን ቱሪስቶችን አሳፍሮ በርሯል

    ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ለቀናት ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች መጀመራቸው እየተሰማ ነው።

    አንዳንድ በረራዎች በመካከለኛው ምስራቅ ከቀናት በኋላ መስተጓጎላቸውን ተከትሎ እንደገና ይቀጥላሉ።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ብሪታኒያውያንን ከኦማን ለመመለስ ያዘጋጀው በረራ ረቡዕ ምሽት በቴክኒክ ችግር ምክንያት ሳይበር ቀርቷል።

    "በረራው ዛሬ ዘግይቶ እንደሚነሳ ይጠበቃል" ሲል የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።

    ጀርመን፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድስ እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ከመካከለኛው ምሥራቅ ዜጎቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ማውጣት ችለዋል።

    በዩኤኢ ኤምሬትስ እና ኢታሃድ አየር መንገዶች የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን በረራዎችን እያደረጉ ነው። የተወሰኑ በረራዎች በዛይድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መጀመራቸውን የአቡ ዳቢ መገናኛ ብዙኃን ቢሮ አስታውቋል።

    የኳታር አየር መንገድ ዛሬ ጠዋት ከኦማን፣ ከሙስካት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የሚደረጉ የሰብዓዊ ድጋፍ በረራዎችን እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

    ከእነዚህም መካከል ወደ ለንደን፣ በርሊን፣ ኮፐንሃገን፣ ማድሪድ፣ ሮም እና አምስተርዳም የሚደረጉ በረራዎች ይገኙበታል።

    አየር መንገዱ ከዋና ከተማዋ ዶሃ የሚያደርጋቸው በረራዎች "የኳታር የአየር ክልል በመዘጋቱ ምክንያት ለጊዜው ተቋርጠዋል" ሲል በኤክስ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    የእስራኤል የትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ የእስራኤል ዜጎችን የጫነ አውሮፕላን በቴል አቪቭ አርፏል። በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ገቢ አጣ?

  10. በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ገቢ አጣ?

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመካከለኛው ምሥራቅ አሜሪካ እና እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስር መዳረሻዎች የሚያደርጋቸውን በረራዎች መሰረዙን ለቢቢሲ ገለፀ።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ ለቢቢሲ ተናግሯል።

    የአየር መንገዱ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በአየር መንገዱ ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት መንገደኞችን እንዲሁም ጭነቶችን ያመላልሳል።በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን ያህል ገቢ አጣ?

  11. የኢራን ድሮኖች አዘርባጃንን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ

    በአዘርባጃን የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽሞ ሁለት ሰላማዊ ዜጎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    "አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን በናክቺቫን ራስ ገዝ ሪፐብሊክ በሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ሕንፃ ላይ ጥቃት ሲያደርስ፣ ሌላኛው ደግሞ በሻካራባድ መንደር በሚገኝ የትምህርት ቤት ሕንፃ አቅራቢያ ወድቋል" ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የድሮን ጥቃቱ በአንድ የአውሮፕላን ማረፊያ ሕንፃ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ሁለት ሰላማዊ ዜጎችንም አቁስሏል።

    በአዘርባጃን የሚገኙት የኢራን አምባሳደር በጉዳዮ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠራታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጾ "ለኢራን ያለንን ጠንካራ ተቃውሞ እንገልጻለን” ብሏል።

  12. ኢራን የአሜሪካ የነዳጅ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገለጸች

    የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን የአገሪቱ የባሕር ኃይል ተዋጊዎቹ ዛሬ ጠዋት በሰሜናዊ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ አንድ የአሜሪካን የነዳጅ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዘገበ።

    መርከቧ "በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሰሜናዊ ክፍል በሚሳኤል ተመትታለች" እና "በአሁኑ ሰዓት በእሳት እየነደደች ነው" ሲል የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በመንግሥት ቴሌቪዥን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

    መግለጫው አክሎም በባህረ ሰላጤው መካከል እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ የሚዘልቀው የሆርሙዝ ሰርጥ ላይ "ሙሉ ቁጥጥር" እንዳለው ተናግሯል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ የሰጠው መግለጫ ትክክለኛነት በሌላ ወገን አልተረጋገጠም።

    የዩኬ የባሕር ንግድ ድርጅት ቀደም ሲል አንድ የጭነት መርከብ ዛሬ ጠዋት በሰሜናዊ ባሕረ ሰላጤ በኩዌት የባህር ዳርቻ ላይ መመታቱን ተናግሯል።

    የድርጅቱ መግለጫ አክሎም ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን እና ቀጥሎም ከአካባቢው አነስተኛ ጀልባ ሲወጣ መመልከቱን አስታውቋል።

    "ከጭነት መርከቡ የሚወጣ ነዳጅ ዘይት በውሃው ላይ ይታያል። ይህም አካባቢው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ . . . . የእሳት አደጋ ስለመድረሱ የተገለጸ ነገር የለም። የመርከቧ ሠራተኞችም በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው።"

  13. አሜሪካ ዘመቻው እስከመጨረሻው ድረስ እንዲቀጥል ትፈልጋለች- የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር

    የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የአሜሪካ አቻቸው ፒት ሄግሴት በኢራን ላይ የጀመሩት የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ "እስከ መጨረሻው" እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ገለፁ።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላእ ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ጦርነት ከፍተዋል። ሁለቱ አገራት በትምረት በፈጸሙት የመጀመርያው ጥቃት የኢራኑ የበላይ መሪ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ በርከታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

    ኢራን በመወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።

    ሐሙ ዕለት የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ካትዝ ትናንት ምሽት ከሄግሴት ጋር ያደረጉትን ውይይት ጠቅሶ “የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ‘እስከ መጨረሻው ቀጥሉ፣ ከእናንተ ጋር ነን’ ብለዋል” ብሏል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት የከፈተችው በኦማን አደራዳሪነት ለሦስት ዙር ድርድር ከተካሄደ በኋላ ነው።

    የኢራን ቀይ ጨረቃ አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት መፈጸም ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በ"174" ከተሞች በ"636" ቦታዎች ላይ "1332" ጥቃቶች መመፈጸማቸውን አስታውቋል።

    ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ በኢራን ውስጥ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ከ1000 ሰዎች በላይ ሰዎች መገደላቸውን የቀይ ጨረቃ አስታውቋል።

  14. ኳታር ዜጎቿን የአሜሪካ ኤምባሲ ካለበት አካባቢ ካስወጣች በኋላ በዶሃ ከባድ ፍንዳታ ተሰማ

    በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ከባድ የፍንዳታ ድምፅ መሰማቱን ኤኤፍፒ ዘገበ።

    ኳታር ቀደም ሲል ዶሃ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ የሚኖሩ ነዋሪዎችን “ለጥንቃቄ” በሚል ማስወጣት ጀመራ ነበር።

    ኳታር በዶሃ የአሜሪካ ኤምባሲ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎችን ለጥንቃቄ እርምጃ በሚል ማስወጣት መጀመሯን የኳታር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

    ሚኒስቴሩ በኤክስ ገፁ ላይ በሰጠው መግለጫ በኤምባሲው አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች “የአስፈላጊ የመከላከያ እርምጃ አካል ሆኖ ተስማሚ መጠለያ ተሰጥቷቸዋል” ብሏል።

    ኳታር ይህንን የወሰነችው በሳዑዲ አረቢያ እና በኩዌት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና በዱባይ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ከተፈፀመባቸው በኋላ ነው።

    በዚህ ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከቀጠናው የሚደረጉ በረራዎች የተሰረዙ ወይም የታገዱ ቢሆንም የአሜሪካ ዜጎች ከመካከለኛው ምሥራቅ እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    የአሜሪካ መንግሥት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዮርዳኖስ ላሉ የአሜሪካ ዜጎች አውሮፕላኖችን በማዘጋጀት ለማስወጣት ጥረት እያደረገ ነው።

    እንደ አውሮፓውያኑ ከየካቲት 28 ጀምሮ ወደ 17,500 የሚጠጉ ዜጎች ከመካከለኛው ምሥራቅ መመለሳቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ተናግረዋል።

  15. እስራኤል በቤይሩት የፈጸመችው የአየር ድብደባ ያደረሰው ውድመት

    እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት የፈራረሰ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በቤይሩት የምትፈጽመው የአየር ድብደባ እንደቀጠለ ሲሆን ያደረሰቻቸው ወድመቶችን የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው።

    የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ትናንት ምሽት በደቡባዊ ቤይሩት በተፈጸመ ሁለት ጥቃት፣ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ስድስቱ ደግሞ መጎዳታቸውን ዘግበዋል።

    እስራኤል ቀደም ብሎ “የአሸባሪው ሔዝቦላህ በርካታ የማዘዣ ማዕከላትን” መምታቷን ገልጻለች።

    የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል ድሮን በሊባኖስ በሚገኘው የፍልስጤም ስደተኞች መጠለያ አካባቢ የሚገኝ ሕንጻን መምታቱን ዘግቧል።

    በጥቃቱም ዋሲም አታላሀህ አል አሊ የተባለ ከፍተኛ የሐማስ ኃላፊ እና ባለቤቱ መገደላቸውን ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር ስለተገደለው የሐማስ መሪ ያለው ነገር ለም።

    በቤይሩት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የፈራረሰ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በቤይሩት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የፈራረሰ ሕንጻ
  16. የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቀበር ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩ ተገለጸ

    አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የተገደሉት አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት የመጀመርያ ዕለት ነው

    የፎቶው ባለመብት, WANA/Via Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የተገደሉት አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት የመጀመርያ ዕለት ነው

    አሜሪካ እና እስራኤል የሚፈጽሙትን ጥቃት አጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን ባለሥልጣናት የጠቅላይ መሪያቸውን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ ሌላ ጊዜ አስተላለፉ።

    የኢራን እስላማዊ የፕሮፓጋንዳ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ኃላፊ የሆኑት ሰይድ ሞህሴን ታስኒም ለተባለው ዜና ወኪል እንደተናገሩት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ “አመቺ ጊዜ አስኪፈጠር ድረስ” እንዲዘገይ መደረጉን ገልጸዋል።

    ረቡዕ ዕለት ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረው የአያቶላህ ኻሜኒ ቀብር እንዲዘገይ የተደረገው በርካታ ሕዝብ መሪውን ለመሰናበት ባለው ፍላጎት ለታዳሚው የሚበቃ የጸሎት ስፍራ ለማዘጋጀት እንደሆነ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

    የኻሜኒን ቀብር ተከትሎ ተተኪያቸው ይፋ እንደሚሆን እየተጠበቀ ሲሆን፣ በመሪው ምርጫ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ከፍተኛው የሃይማኖት እና ፖለቲካዊ ምክር ቤት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል።

    ነገር ግን አንድ የምክር ቤቱ አባል ጉባዔው የአያቶላህ ኻሜኒን ተተኪ ለመወሰን “ተቃርቧል” በማለት ተናግረዋል።

    ባለፈው ቅዳሜ ቴህራን ውስጥ በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈጸሙ ከባድ ጥቃቶች የኢራን ጠቅላይ መሪን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

    ለስድስተኛ ቀን ዛሬ በቀጠለው ጦርነት ኢራን እስራኤልን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሚሳዔሎችን እያስወነጨፈች ሲሆን፣ አሜሪካ እና እስራኤልም በኢራን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ቀጥለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት አሊ ላሪጃኒ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “የአሜሪካንን ሕዝብ ፍትሐዊ ወዳልሆነ ጦርነት ጎትተው አስገብተዋል ሲሉ” ወቅሰዋል።

  17. ዜሌንስኪ ለመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮቻቸው የድሮን ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ ጠየቁ

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አጋሮቻቸው ከኢራን የሚሰነዘርባቸውን የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት መከላከል እንዲችሉ የባለሙያዎች ቡድን ለመላክ ዕቅድ ማውጣታቸው ተሰምቷል።

    ማክሰኞ ዕለት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር እንዲሁም ረቡዕ ከዮርዳኖስ እና ባህሬንጋር መነጋገራቸውም ተገልጿል።

    ዜሌንስኪ ከሚኒስትሮች እና ከወታደራዊ አዛዦቻቸው ጋር ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ከተወያዩ በኋላ፣ የዩክሬንን የመከላከያ ኃይል ሳያዳክም አጋሮቻቸውን ለመርዳት አማራጮችን እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ዩክሬን ሕይወትን ለመጠበቅ እና ሁኔታውን ለማረጋጋት ታግዛለች..." ብለዋል።

    አክለውም "የእኛ ወታደሮች አስፈላጊው ችሎታ አላቸው። የዩክሬን ባለሙያዎች ከአገራቱ ጋር ይሠራሉ፣ እናም ቡድኖች ይህንን እያስተባበሩ ነው። ሕይወትን ለመጠበቅ፣ ሰላማዊ ዜጎችን ለመከላከል እና ሁኔታውን ለማረጋጋት እንዲሁም የቀጠናውን ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር ላይ ጉዞ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ ነን" ብለዋል።

  18. የመንግሥታቱ ድርጅት በጦርነቱ የመጀመሪያ 2 ቀናት 100 ሺህ ሰዎች ቴህራንን ለቅቀው መውጣታቸውን አስታወቀ

    በቴህራን በፍርስራሽ ውስጥ የምትራመድ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) የእስራኤል እና አሜሪካ ጥቃት በተጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ብቻ ከቴህራን 100 ሺህ ያህል ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰደዳቸውን አስታወቀ።

    ስድስተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ሐሙስ ማለዳ ኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል።

    የአሜሪካ ከፍተኛው ምክር ቤት የዶናልድ ትራምፕን የጦር አቅም ለመገደብ የቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አድርጎታል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከኳታሩ አቻቸው ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን፣ ኳታር በቴህራን የሚፈጸምባት ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቃለች።

    በኢራን ዋና ከተማ እና በሌሎች ስፍራዎች ከፍተኛ ፍንዳታዎችን መሰማታቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ የመንግሥት ሕንጻዎች እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መፈራረሳቸውን የሚወጡ ምሥሎች ያሳያሉ።

    ወታደራዊ ጥቃቱ እየቀጠለ እና እየሰፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢራናውያን ፍርሃታቸውን እና ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።

    የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በከፈቱበት ሁለት ቀናት ብቻ ከቴህራን 100 ሺህ ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ሲገልጽ፣ እስራኤል በሔዝቦላህ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመች መሆኑን በገለፀችበት ሊባኖስ ደግሞ 58 ሺህ ሰዎች በመጠለያ ውስጥ ናቸው ብሏል።

    በሶሪያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት ጨምሮ አስታውቋል።

  19. የጦርነቱ ኪሳራ በመካከለኛው ምሥራቅ

    በመላው መካከለኛ ምሥራቅ እየተካhደ ያለው ጦርነት የሚያደርሰው ጉዳት እና ኪሳራ በሊባኖስ፣ በኢራን እና በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ መታየት ጀምሯል።

    በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅው አገራት በረራዎች ተቋርጠዋል። መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች አክቲቪስቶች የዜና ወኪል ጦርነቱ ከተጀመረ እስከ ሰኞ ዕለት ድረስ ብቻ ኢራን ውስጥ 1000 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞቶች ደግሞ ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን ገልጿል።

    እስራኤል በቤይሩት እያካሄደችው ባለው ድብደባ የደረሰ ውድመት እና የተፈጠረ ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በደቡባዊ ቤይሩት እያካሄደችው ባለው ድብደባ የተነሳ የተፈጠረ ጭስ
    በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በፉጃይራ ወደብ ላይ በነዳጅ ዴፖዎች አቅራቢያ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የታየ ጭስ ወጣ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በፉጃይራ ወደብ ላይ በነዳጅ ዴፖዎች አቅራቢያ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የታየ ጭስ ወጣ
    ረቡዕ ዕለት በቤሩት፣ ሊባኖስ በተፈጸሙ ጥቃቶች በፈራረሱ ሕንፃዎች መካከል የሚንቀሰቀቀሱ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ረቡዕ ዕለት በቤሩት፣ ሊባኖስ በተፈጸሙ ጥቃቶች በፈራረሱ ሕንፃዎች መካከል የሚንቀሰቀቀሱ ሰዎች
    ኢራናውያን በጎ ፈቃደኞች በጥቃት በወደመ የፖሊስ ማዘዣ በኩል ሲያልፉ

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ኢራናውያን በጎ ፈቃደኞች በቴህራን በጥቃት በወደመ የፖሊስ ማዘዣ በኩል ሲያልፉ
  20. ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን የእስራኤል ጦር አስታወቀ

    የሚወነጨፍ ሮኬት በእስራኤል ሰማይ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሐሙስ ማለዳ የእስራኤል ጦር ኢራን በርከታ ሚሳዔሎችን ወደ ግዛቷ ማስወንጨፏን አስታወቀ። ኤኤፍፒ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር እንደሌለ የአገሪቱን የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።

    አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል በሁለት ሰዓታት ልዩነት ውስጥ ሦስት የማስጠንቀቂያ ደወሎች መሰማታቸውን እንዲሁም በኢየሩሳሌም ፍንዳታዎች እንደነበሩ ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር ከዚያ በኋላ ሰዎች ከገቡባቸው የደኅንነት መጠበቂያ ስፍራዎች እንዲወጡ አዝዟል።