በኢራን ዋና አየር ማሪፊያ ከፍተኛ ፍንዳታ መታየቱን የዐይን እማኞች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ የሚገኘው እና ከዋነኛዎቹ የንግድ አየር ማረፊያዎች አንዱ የሆነው መህራባድ አየር ማረፊያ ከፍተኛ ጥቃት እንደደረሰበት የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጡ።
በርካታ ሰዎችን በማስተናገድ ቀዳሚ እና የአገር ውስጥ በረራ ማዕከል በሆነው መህራባድ አየር ማረፊያ ውስጥ የሚቃጠል አውሮፕላን እና ወደላይ የሚወጣ ከፍተኛ ጭስ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሰራጭተዋል።
አርብ ዕለት የተነሳ የሳተላይት ምሥል አየር ማረፊያው ውስጥ በርካታ አውሮፕላኖች እንደነበሩ አሳይቷል። የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃንም የአየር መንገዱ የተወሰነ ክፍል የጥቃት ዒላማ መደረጉን ዘግቧል።
አየር ማረፊያው የመመታቱ ዜና የተሰማው የእስራኤል ጦር ኢራን ውስጥ “አዲስ ዙር መጠነ ሰፊ ጥቃት” መክፈቱን ካስታወቀ በኋላ ነው።
ረቡዕ ዕለትም አየር ማረፊያውን ዒላማ አድርጎ የነበረው የእስራኤል ጦር፤ በዚህ ጥቃት ለእስራኤል አየር ኃይል ስጋት የሆኑ የመከላከያ እና የጥቃት መለያ ሥርዓቶችን መደምሰሱን ገልጾ ነበር። በጥቃቱ ዒላማ ከተደረጉት መካከል ሄሊኮፕተር የሚመረትበት የአየር ማረፊያው ክፍል ይገኝበታል።
በአሁኑ ጥቃት የትኛው የአየር ማረፊያ ክፍል እንደተደበደበ ግልጽ አይለም። የዐይን እማኞች በበኩላቸው ከቀናት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የትናንት ምሽቱ ጥቃት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images





















