ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች የዓለማችን መሪዎች ማዱሮ ስለመያዛቸው ምን አሉ?

ቬኒዙዌላ ላይ ድንገተኛ የኮማንዶ ጥቃት በመፈጸም አገሪቱ መሪ በአሜሪካ እጅ መግባታቸውን በተመለከተ ፕሬዝንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አስተማማኝ፣ ተገቢ እና ሕጋዊ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ቬንዙዌላን አሜሪካ ታስተዳድራለች” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል። ማዱሮ መያዛቸውን ተከትሎ የዓለማችን መሪዎች የተደበላለቀ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢትዮጵያ ለቀድሞ ተዋጊዎች ተሃድሶ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጣ

    በተሃድሶ ውስጥ ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎች

    የፎቶው ባለመብት, National Rehabilitation Commission

    በኢትዮጵያ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በማሰናበት ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ሂደት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።

    የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደተናገሩት በተለያዩ ክልሎች ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ ሂደት ውስጥ አልፈው ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

    ከእነዚህ መካከል ከ63 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከትግራይ ክልል መሆናቸውን ጠቅሰው ለዚህም ከ6.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።

    የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብ/ጄነራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው በእስካሁን የተሃድሶ ትግበራ ሂደት ከመከላከያ ሠራዊቱ ወጥተው “በሌላ ጎራ ከተሰለፉ ከ5200 በላይ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ውስጥ 520 የሚሆኑት” በተሃድሶ ሂደት ውስጥ ማለፋቸውን ተናግረዋል።

  2. እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመሥረት መብት አላት - አሜሪካ

    ታሚ ብሩስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እስራኤል ከተለያዩ ወገኖች ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት የመወሰን ነጻነት አላት ስትል አሜሪካ ገለጸች።

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ታሚ ብሩስ የአገራቸውን አቋም ባሰወቁበት ጊዜ “እንደማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመሥረት መብት አላት” ብለዋል።

    እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የሀገርነት እውቅና ከወራት በፊት የተለያዩ አገራት በተናጠል ለፍልስጤም ከሰጡት ዕውቅና ጋር የሚመሳሰል መሆኑንም አምባሰደሯ ጠቅሰዋል።

    “በዚህ ዓመት የዚህ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ለፍልስጤም ዕውቅና ሲሰጡ ነበር። ነገር ግን መሰል አስቸኳይ ስብሰባ አላደረግንም” ያሉት አምባሳደሯ ምክር ቤቱ ለተመሳሳይ ጉዳይ ወጥ አቋም አልያዘም ሲሉ ወቅሰዋል።

    ነገር ግን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ይሰጡ እንደሁ ተጠይቀው “ለጊዜው አንሰጥም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

    የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ያልሆነችው የሶማሊያ አምባሳደር አቡካር ኦስማን የእስራኤልን ዕውቅና አውግዘው “ይህ በሶማሊያ ግዛት ላይ መከፋፈልን ያነገበ የወረራ ተግባር” ነው ብለዋል። አክለውም ምክር ቤቱ በማያሻማ መልኩ እንዲያወግዘው ጠይቀዋል።

    በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የእስራኤልን ስም ሳይጠቅሱ ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

  3. እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ለፀጥታው ምክር ቤት አስታወቀች

    ተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል ተቀዳሚ አምባሳደር የሆኑት ጆናታን ሚለር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሰኞ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ ላይ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ለጉባዔው አሳወቀች።

    በርካታ የተባበሩት መንግሥታት ሀገራት የእስራኤል እርምጃ ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ ለማስወጣት አሊያም በአካባቢው የጦር ሠፈር ለማቋቋም አስባለች ሲሉ እስራኤልን ወቅሰዋል።

    እስራኤል ባለፈው አርብ ለሶማሊላንድ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።

    ከአረቡ ዓለም እና ከአፍሪካ የተውጣጡ 22 አባል ሀገራት ያሉት የአረብ ሊግ የእስራኤልን ውሳኔ ክፉኛ የተቃወመው ሲሆን፣ የሊጉ የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር ማጌድ አብድልፈታህ አብድልአዚዝ “በዚህ ውሳኔ ምክንያት የሚከሰት የትኛውንም የፍልስጤማዊያን ስደትም ሆነ በሰሜን ሶማሊያ የጦር ሰፈር ለማቋቋም የሚደረግ ውሳኔን እንቃወማለን” ብለዋል።

    በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል ተቀዳሚ አምባሳደር የሆኑት ጆናታን ሚለር “ይህ ሶማሊያ ላይ የተቃጣ ውሳኔ አይደለም። በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚኖር ውይይትንም አያግድም። ዕውቅና ዕድል እንጂ የእምቢተኝነት ምልክት አይደለም” ሲሉ ለጉባዔው ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምንት ለሶማሊላንድ ዕውቅና የሰጠችው እስራኤል ከሐርጌሳ ጋር በግብርና፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በምጣኔ ሀብት መስኮች አብራ መሥራት እንደምትጀምር አስታውቃለች።

    የቀድሞ የብሪታኒያ ቅኝ ተገዥ የነበረችው ሶማሊላንድ ላለፉት 30 ዓመታት ነፃነቷን አውጃ ብትቆይም ዕውቅና የሰጣት ሀገር አልነበረም።

  4. ዩናይትድ ኪንግደም ለሶማሊላንድን እውቅና እንደማትሰጥ አስታወቀች

    በተባበሩት መንግሥታት የዩናየትድ ኪንግደም ጉዳይ አስፈጻሚ (Chargé d’Affaires) የሆኑት አምባሳደር ጄምስ ካሪኡኪ

    የፎቶው ባለመብት, GOV.UK

    ዩናይትድ ኪንግደም ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንደማትሰጥ አስታወቀች።

    ለሶማሊያ ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት ያላትን ድጋፍም በድጋሚ አረጋግጣለች።

    ባለፈው ሳምንት እስራኤል፤ ለሶማሊላንድ ነጻ እና ሉዐላዊ አገርነት እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

    ይህንን ተከትሎም በርካታ አገራት እና ቀጣናዊ ተቋማት የእስራኤልን እርምጃ በመቃወም መግለጫዎችን አውጥተዋል። የቀድሞው የሶማሊላንድ ቅኝ ገዢ የሆነችው ዩናይትድ ኪንግደምም ይህንን ጎራ ተቀላቅላለች።

    በተባበሩት መንግሥታት የዩናየትድ ኪንግደም ጉዳይ አስፈጻሚ (Chargé d’Affaires) የሆኑት አምባሳደር ጄምስ ካሪኡኪ ትናንት በተደረገው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ዩናይትድ ኪንግደም ለሶማሊላንድ ነጻነት እውቅና አትሰጥም” ብለዋል።

    “በሶማሊላንድ [የእውቅና] ሁኔታ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ለውጥ በሞቃዲሾ እና በሐርጌሳ መካከል በሚደረግ ውይይት እና የጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት፤ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር ዓላማዎች እና መርሆዎች ጋር መጣጣም እንዳለበት እናምናለን” ሲሉ የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል።

    “የቀጣናውን ሰላም እና ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም እርምጃ ያሳዝነናል” ሲሉም አክለዋል።

    የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ እና “የጋራ ስጋት” በሚደቅኑባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

    “ከሶማሊያ የውስጥ ክፍፍል የሚጠቀሙት አልሸባብ እና ሌሎች ሽብርተኛ ቡድኖች ናቸው” ሲሉም በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

  5. ዶናልድ ትራምፕ ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ “አያስጨንቀንም” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቤይጂንግ በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ እንደማያሳስባቸው ተናገሩ።

    “ከፕሬዝደንት ዢ [ጂንፒንግ] ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ስለልምምዱ የነገረኝ ነገር የለም። እኔ ግን አይቸዋለሁ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    “አይ። ይህ ፍፁም አያስጨንቀኝም። ላለፉት 20 ዓመታት በአካባቢው የባሕር ላይ ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተዋል።”

    ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለት ሳምንታት በፊት መጠነ ሰፊ የተባለ የመሣሪያ ሽያጭ ለታይዋን ማድረጓ ይታወሳል። ይህ ሽያጭ ታይዋንን እንደ ተገንጣይ ክልል የምትቆጥረው ቻይናን ማስቆጣቱ ተዘግቧል።

    ለሁለት ቀናት የሚቆየው ወታደራዊ ልምምድ የደሴቷን ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎች መቆጣጠርን ያካተተ ሲሆን የቻይና መከላከያ “የታይዋን የነፃነት ተገንጣይ ኃይሎችን” እንዲሁም “የውጭ ጣልቃ ገቦችን” ለማስጠንቀቅ ያለመ መሆኑን አስታውቋል።

    ልምምድ የሚካሄደው ደሴቷን በሚከቡ አምስት አቅጣጫዎች ሲሆን ለ10 ሰዓታት የሚቆይ የተኩስ ልምምድ እንደሚደረግም ተሰምቷል።

    የታይዋን ፕሬዝደንታዊ ፅ/ቤት ወታደራዊ ልምምዱ ዓለም አቀፍ ሕግን ያልተከተለ ነው ሲል ወቀሳውን አሰምቷል።

    ማክሰኞ በማኅበራዊ ሚድያቸው መግለጫ የተለቀቁት የታይዋኗ ፕሬዝደንት ላይ ቪንግ-ቴ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ድርጊት “ኃላፊነት የሚሰማው ኃይል” የሚያደርገው አይደለም ብለዋል።

    አሜሪካ ከቻይና ጋር ኦፊሴላዊ ግንኙነት ቢኖራትም የታይዋን የቅርብ ወዳጅ እና የጦር መሣሪያ አቅራቢ ናት።

  6. አሜሪካ ለዩክሬን የ15 ዓመታት የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት ሃሳብ አቀረበች

    የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ የሚገኙት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አሜሪካ ለአገራቸው ለአስራ አምስት ዓመታት የሚቆይ የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት ሃሳብ ማቅረቧን ተናገሩ።

    ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማስቆም ቀደም ሲል በቀረበው የሰላም ዕቅድ ላይ በተደረገው ማሻሻያ ላይ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር እሁድ ዕለት ከተወያዩ በኋላ ነው ዜሌንስኪ ይህንን ይፋ ያደረጉት።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በውይይቱ ወደ 95 በመቶ ከስምምነት ላይ መደረሱን ቢጠቅሱም የዩክሬን መሪዎች አስከ 50 ዓመታት የሚደርስ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰቸጣው ጠይቀዋል።

    ጨምረውም ዩክሬናውያን ከአሜሪካ በኩል የሚያገኙት ዋስትና ከ15 ዓመት ከፍ ብሎ “30፣ 40 እና 50 ዓመታት የሚደርስበት ዕድል እንዲኖር” ይፈልጋሉ ብለዋል።

    በስምምነቱ ውስጥ አንዳንድ ይዞታዎችን ለሩሲያ መልቀቅ የሚካተት ሲሆን፣ ተጨማሪ ንግግር በአሜሪካ፣ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሊኖር እንደሚችል እየተጠቆመ ነው።

  7. በአድዋ ከተማ አምስት ሕጻናት በከሰል ጭስ ታፍነው ሞቱ

    ከሰል

    በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ አንድ ቤት ውስጥ ተኝተው የነበሩ አምስት ልጆች በከሰል ጭስ ታፍነው መሞታቸውን ፖሊስ ገለጸ።

    አደጋው የደረሰው በአድዋ ከተማ እንዳ ገብርኤል በሚባል ሰፈር ውስጥ ቅዳሜ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም. ሌሊት ሲሆን፣ ሕጻናቱ መሞታቸው የተወቀው በማግስቱ እሁድ እንደሆነ የአድዋ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር መኮንን አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    እናት በከሰል ማንደጃ ወጥ እየሠራች አምሽታ በዚያው እሳቱን ሳታጠፋው በር ዘጋግታ በመተኛቷ ልጆቹ ለኅልፈት መዳረጋቸውን የፖሊስ ኃላፊው ገልጸዋል።

    በማግስቱ ቤተሰብ እና ጎረቤት በር ከፍቶ ሲገባ እናት እራሷን ስትስት ዕድሜያቸው ከ3 እስከ 14 የሆኑት ሦስት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆች ሞተው ተገኝተዋል።

    በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው ልጆች “በአጠቃላይ 5 ሲሆኑ፣ ሦስቱ በሕክምና ላይ የምትገኘው ግለሰብ ልጆች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የባሏ እህት ልጆች” መሆቸናውን የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።

    ፖሊስ አደጋው ወደ ደረሰበት መስኮት የሌለው ቤት ሲገባ ቤቱ በጭስ ታፍኖ እንደነበር እና የልጆቹ ሕይወት አልፎ ነበር ያገኘው።

  8. ኔታኒያሁ በኢራን ላይ ሌላ ዙር ጥቃት ስለመፈጸም ከትራምፕ ጋር ሊወያዩ ይችላሉ ተባለ

    ፕሬዝደንት ትራምፕ እና ጠ/ሚ ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በፍሎሪዳ ተቀብለው ያነጋግራሉ።

    ሁለቱ መሪዎች የጋዛን ጉዳይ ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ስላሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

    መሪዎቹ የሚያስተላልፉት ውሳኔ በቀጣናው ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

    ሰኞ በሚደረገው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ኔታንያሁ ኢራን ላይ ሌላ ዙር ጥቃት ለመፈፀም ከአሜሪካ ፈቃድ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

    ባለፈው ሳምንት የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ኔታንያሁ በቁጥጥር ሥር የምትገኘውን ዌስት ባንክ ወደ ሀገራቸው ለማጠቃለል እያቀዱ እንደሆነ ዘግበዋል። ትራምፕ ይህንን ሐሳብ እንደማይቀበሉት ከዚህ ቀደም አሳውቀው ያውቃሉ።

    የእስራኤል መንግሥት ኢራን የሚሳዔል አቅሟን መልሳ እየገነባች ነው ብሎ ያምናል። ከወራት በፊት ለ12 ቀናት በቆየው ጦርነት የእስራኤል እና አሜሪካ ተዋጊ ጄቶች የኢራን የሚሳዔል ማምረቻዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ማደረሳቸው ይታወሳል።

    የኢራኑ ፕሬዝደንት ሀገራቸው ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር "የለየለት" ጦርነት ውስጥ እንደገባች ተናግረዋል።

    "ሀገራችን የተረጋጋች እንድትሆን አይፈልጉም" ሲሉ ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከቀናት በፊት እንደተናገሩ ተዘግቧል።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ ከ11 ወራት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኔታንያሁ ጋር ሲገናኙ ይህ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።

  9. “እስራኤል ውሳኔዋ ኃላፊነት እና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው” ዳኒ ዳነን

    አምባሳደር የሆኑት ዳኒ ዳነን

    የፎቶው ባለመብት, @dannydanon

    የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር የሆኑት ዳኒ ዳነን

    የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት በሚያደርገው ስብሰባ ላይ እስራኤል እንደምትሳተፍ እንዲሁም ውሳኔዋ ኃላፊነት እና ጥንቃቄ የተሞላበት መሆኑን አምባሳደሯ ገለጹ።

    በሶማሊያ ጠያቂነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል ለሶማሊላንድ በሰጠችው የአገርነት ዕውቅና ላይ ይወያያል።

    ይህ አስቸኳይ የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎች አገራት በተቃወሙት የእስራኤል ውሳኔ ላይ በዛሬው ዕለት [ሰኞ] ውይይት ያደርጋል።

    በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ዳኒ ዳነን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ከፖለቲካዊ ውይይቶች እራሳችንን አናርቅም” በማለት እስራኤል ተሳታፊ እንደምትሆን ገልጸዋል።

    አክለውም “ለቀጣናዊ መረጋጋት አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ አጋሮች ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እስራኤል በኃላፊነት እና በጥንቃቄ እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች” ብለዋል።

  10. “በእስራኤል ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ ግብዝነት ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳአር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና ላይ እየተሰነዘረ ያለው ተቃውሞ የግብዝነት ማሳያ ነው በማለት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አጣጣሉት።

    እስራኤል ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ የተለያዩ አገራት እና ድርጅቶች ተቃውሟቸውን ባለፉት ሦስት ቀናት ሲያሰሙ ቆይተዋል።

    ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ተለይታ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ራሷን ስታስዳድር ለቆየችው ሶማሊላንድ የነጻ አገርነት ዕውቅናን መስጠት እስራኤል የመጀመሪያዋ ሆናለች።

    በርካታ የአረብ አገራት፣ የአረብ ሊግ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ሌሎችም እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና አጥብቀው አውግዘውታል።

    የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር አገራቸው ለገጠማት ጠንካራ ተቃውሞ በሰጡት ምላሽ “ሶማሊላንድ ባለፉት ቀናት የተፈጠረች” አይደለችም በማለት ለሦስት አስርት ዓመታት በላይ የቆየች መሆኑን አመለክተዋል።

    ሶማሊላንድ “ከ34 ዓመታት በላይ እንደ አገር የቀየች ናት” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “እስራኤል በሰጠቻት ዕውቅና ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ግብዝነት ነው” በማለት አጣጥለውታል።

    “እስራኤል ለማን ዕውቅና እንደምትሰጥ እና ከማን ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲኖራት የምትወስነው በራሷ ነው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳአር አገራቸው የገጠማትን ተቃውሞ ውድቅ አድርገውታል።

  11. ታሊባን እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠቸው ዕውቅና "እስላማዊ አገርን ለመከፋፈል ያለመ” ነው አለ

    የአፍጋኒስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካሃን ሙታቅ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አፍጋኒስታንን የሚያስተዳድረው የታሊባን መንግሥት እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና አወገዘ።

    የአፍጋኒስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስራኤል ውሳኔ “እስላማዊ አገርን ለመከፋፈል ያለመ ነው” ሲል አውግዞታል።

    ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ውሳኔው ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ያለ ሲሆን፣ በቀጠናው መረጋጋት እና ሰላም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብሏል።

    እስራኤል ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ለሶማሊላንድ የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅና ሰጥታለች።

    የእስራኤል ዕውቅናን ተከትሎ ሶማሊያ፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ጂቡቲ እና የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔውን ተቃውመዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሶማሊላንድ ጋር ያላቸውን ትብብር በግብርና፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች እንደሚያሰፉ ተናግረዋል።

    የሶማሊላንዱ ፕሬዚዳንት አብድራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ የእስራኤልን ዕውቅናውን “ታሪካዊ” በማለት ውሳኔው በሁለቱ አገራት መካከል የስትራቴጂያዊ አጋርነት ጅማሮ ይሆናል ብለዋል።

  12. የየመኑ ሁቲ እስራኤል ወደ ሶማሊላንድ የምትገባ ከሆነ 'ዒላማ' እንደሚያደርጋት አስጠነቀቀ

    የሁቲ ታጣቂዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የሁቲ ታጣቂዎች

    የየመኑ ሁቲ አማፂያን መሪ እስራኤል ወደ ሶማሊላንድ የምትገባ ከሆነ እንደ “ወታደራዊ ዒላማ” እንደሚቆጥራት ማስጠንቀቁን የፈረንሳይ ዜና ወኪል-ኤኤፍፒ ዘገበ።

    አማፂ ቡድኑ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን የሰጠችው የእስራኤል በሶማሊላንድ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ እንደተገቢ ወታደራዊ "ዒላማ" በመቁጠር ጥቃት እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል።

    “በሶማሊላንድ የሚኖርን ማንኛውም ዓይነት የእስራኤል እንቅስቃሴ ለወታደራዊ ኃይላችን ስጋት ስለሚሆን እንደ ወታደራዊ ዒላማ አድርገን እንቆጥረዋለን” ብሏል።

    የቡድኑ መሪ አብዱልማሊክ አልሁቲ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ የእስራኤል በሶማሊላንድ መገኘት “በሶማሊያ እና የመን እንዲሁም የቀጠናው ደኅንነት ስጋት” መሆኑን ጠቅሶ አስጠንቅቋል።

    እስራኤል አርብ ዕለት ሶማሊላንድን እንደ ሉዓላዊ አገር ዕውቅና በመስጠት ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።

    የቡድኑ መሪ በመግለጫው የእስራኤል ውሳኔ ከባድ መመዘዝ እንደሚያስከትል አስጠንቅቆ፤ ለሶማሊላንድ የሰጠችው ዕውቅና “በሶማሊያ እና በዙሪያዋ ባሉ አፍሪካውያን እንዲሁም የመን፣ ቀይ ባሕር እና በቀይ ባሕር ዙሪያ ባሉ አገራት ላይ ያነጣጠረ ጠብ አጫሪነት ነው” ብሏል።

    ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ዕውቅና ለማግኘት ስትጥር የነበረችው ሶማሊላንድ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ወሳኝ ስፍራ ላይ ትገኛለች።

    የቀጠናው ፖለቲካ ተንታኞች ሶማሊላንድ ከእስራኤል ያገኘችውን ዕውቅና ተከትሎ የመን የሚገኙትን የሁቲ ታጣቂዎች በቀላሉ ማጥቃት የሚያስችላትን ወሳኝ ስፍራን በቀይ ባሕር ላይ ያስገኝላታል ሲሉ ተናግረዋል።

    ሁቲዎች ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት ወዲህ በእስራኤል እንዲሁም በቀይ ባሕር ላይ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽመዋል።

    እስራኤል በበኩሏ በሁቲ አማፂያን ወታደራዊ ይዞታዎች እና ከፍተኛ መሪዎች ላይ ድብደባዎችን በመፈጸም ወታደራዊ አመራሮችን ገድላለች።

  13. ቻይና "ተገንጣዮችን ለማስጠንቀቅ" በሚል በታይዋን አካባቢ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች

    ቻይና ወታደራዊ ልምምድ ስታደርግ

    የፎቶው ባለመብት, Eastern Theater Command

    ቻይና "ተገንጣይ ኃይሎችን" ለማስጠንቀቅ እና የደሴቷን ቁልፍ አካባቢዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ወታደራዊ ልምምድ በሰርጡ አቅራቢያ እያደረገች መሆኑ ተዘገበ።

    የአገሪቱ ጦር፣ ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል እና ሌሎችም ኃይሎች የተኩስ ልምምድን ጨምሮ ለወታደራዊ ልምምድ መሰማራታቸውን ቤይጂንግ አስታውቃለች።

    "የፍትኅ ተልዕኮ 2025" የሚል የመለያ ስም የተሰጠው ልምምዱ አሜሪካ ትልቅ የተባለውን የተለያዩ የወታደራዊ መሣሪያዎችን በ11 ቢሊዮን ዶላር ለታይዋን መሸጧን ባሳወቀች በቀናት ውስጥ የሚካሄድ ነው። ቻይና 'ተገንጣይ' የምትላትን ታይዋንን ለማስጠንቀቅ በዙሪያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች

  14. ቻይና በፀጥታው ምክር ቤት ከሶማሊያ ጎን እንድትቆም ኤርትራ ጠየቀች

    የፀጥታው ምክር ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ ዛሬ [ሰኞ] በሚያደርገው ስብሰባው ላይ ቻይና የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንድትከላከል ኤርትራ ጠየቀች።

    ቻይና እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና ከታይዋን ጋር በማመሳሰል ምክር ቤቱ “የማያወላውል ምላሽ እንዲሰጥ” የሚጠበቅባትን “የሞራል ኃላፊነት እንድትወጣ” ኤርትራ ጥሪ አቅርባለች።

    የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው ዕውቅና “ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ አደገኛ ቀውስ እና ብጥብጥ ለመፍጠር ለረጅም ጊዜ ሲብላላ የቆየ ጉዳይ ነው” ብሎታል።

    "ስለዚህም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና በአባላቱ ደረጃ የማያሻማ ምላሽ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው” ብሏል መግለጫው።

    "ከዚህ አንጻር ይህ ጉዳይ ከታይዋን ጉዳይ ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ከምታራምደው አቋም አንጻር ያለባትን ሞራላዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባታል” ስትል ኤርትራ ቻይና በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የሶማሊላንድን ዕውቅና የሚቃወም አቋም እንድታራምድ ጥሪ አቅርባለች።

    ቻይና እስራኤል የሰጠችውን ዕውቅና ከተቃወሙ አገራት መካከል ስትሆን ኤርትራም የእስራኤልን እርምጃ ተቃውማለች።

    ኤርትራ ከሁለት ኣመት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱትን ስምምነት ተቃውማ ይፋዊ ድጋፏን ለሶማሊያ መስጠቷ ይታወሳል።

    ባለፉት ሦስት ቀናት ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅናን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ንግግር ይደረግበታል።

  15. ታላቁ የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ ከመድረክ እየተሰናበተ ነው?

    ሙላቱ

    የፎቶው ባለመብት, mulatu

    የሙላቱ የሙዚቃ ጉዞ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። የተወለደው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዋ ከተማ ጅማ ነው። ነገር ግን ለዩናይትድ ኪንግደም ትልቅ ቦታ አለው። ትምህርቱን በዌልስ ነው የተከታተለው። ሙላቱ ወደ ሙዚቃው ዓለም እንዴት ገባ? ከዚህ በኋላስ መድረክ ላይ እናየው ይሆን? የሙላቱ አስታጥቄን ምላሽ እዚህ ይመልከቱ → ቪዲዮ

  16. የሶማሊላንድ የዕውቅና ጉዞ እና የእስራኤል ውሳኔ ቀጠናዊ አንድምታዎች

    በርካታ የሶማሊላንድ ዜጎች የግዛቲቱን ነጻ አገርነት አጥብቀው ይደግፋሉ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የሶማሊላንድ የሉዓላዊ አገርነት የዕውቅና ጥያቄ በአውሮፓውኑ 1960 ከብሪታንያ እንዲሁም ደቡባዊቷ ሶማሊያ ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ በወጡ ማግስት የሚጀምር ነው።

    ሶማሊላንድ ከብሪታንያ ነጻ በወጣች በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍቃዷ ከሶማሊያ ጋር ተዋሃዳ ነበር።

    በእነዚያ አጭር ቀናት ውስጥ እንደ ሉዓላዊ አገር ካወቋት ከ30 በላይ አገራት መካከል አንዷ እስራኤል ነበረች።

    ሆኖም በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በግዛቲቷ አብላጫ ቁጥር ያለው የኢሳቅ ጎሳ አማጺ ቡድን የማዕከላዊውን የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ወታደራዊ መንግሥት አፈና እና መድልዖ በመቃወም የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀመረ።

    ሶማሊያም በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገባች። ቡድኑ ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመተባበር የዚያድ ባሬን መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1991 ከጣለ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ነበር ሶማሊላንድ ነጻ አገር መኾኗን ያወጀችው።

    ከዚያም ሶማሊላንድ በ2001 (እአአ በመጀመሪያው ፕሬዝዳንቷ መሐመድ ኢጋል አመራር በ97 በመቶ ድምጽ የግዛቲቱን ነጻነት የሚያውጀውን ሕገመንግሥት በሕዝበ ውሳኔ አጽድቃለች። በዓለም አቀፍ ሕግ ይፋዊ የነጻ አገርነት ጥያቄዋ የሚጀምረው ያኔ ነው።

  17. ግብፃዊው አክቲቪስት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሠራጫቸው የቆዩ መልዕክቶች ከዩኬ እንዲባረር ተጠየቀ

    አላ አብደል ፋታህ

    የፎቶው ባለመብት, afp/getty

    የምስሉ መግለጫ, አላ አብደል ፋታህ

    ካይሮ ውስጥ በእስር ላይ የቆየው ግብፃዊው የዲሞክራሲ መብቶች ተከራካሪ ከዓመታት በፊት በትዊተር ላይ ያሠራጫቸው መልዕክቶች ዳግም መጋራት በመጀመራቸው ምክንያት ጥምር ዜግነቱ ተነጥቆ ከዩናይትድ ኪንግደም እንዲባረር ጥያቄ ቀረበ።

    ይህንንም ተከትሎ ግብፃዊው አክቲቪስት አላ አብደል ፋታህ ከእስር ተለቅቆ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መመለሱን ተከትሎ ከአገር እንዲባረር የሚቀርቡ ጥሪዎች በርትተዋል።

    በዚህም ሳቢያ አላ መነጋጋሪያ የሆኑት እና ጽዮናውያን እና ፖሊሶች ላይ ግድያ እንዲፈጸም ጥሪ በሚያደርጉት የማኅበራዊ ሚዲያ የቆዩ መልዕክቶቹ ይቅርታ ጠይቋል።

    ነገር የወግ አጥባቂ እና ሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪኦወች የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የግብፅ እና የዩኬ ጥምር ዜግነት ያለውን አላን ከዩናይትድ ኪንግደም እንዲያባርረው ጠይቀዋል።

    ዘ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው በአመራር ላይ ያለው ሌበር ፓርቲ አንዳንድ ከፍተና የምክር ቤት አባላትም የግለሰቡ ዜግነት እንዲገፈፍ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

    ቀደም ያሉ የትዊተር መልዕክቶቹን መለስ ብሎ ከተመለከተ በኋላ “መልዕክቶቹ ምን ያህል አስደንጋጭ እና ጎጂ እንደሆኑ በመረዳቴ ለሁሉም ያለማወላወል ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል።

  18. በ2025 በኢራን ውስጥ የሞት ቅጣት በእጥፍ መጨመሩን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ገለፁ

    እአአ በ2025 በኢራን የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሰዎች ቁጥር በ2024 በመላው አገሪቱ ከተፈጸሙት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እንደሚበልጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተናገሩ።

    በኖርዌይ የሚገኘው የኢራን የሰብዓዊ መብቶች ቡድን እስከ ታህሳስ ወር መጀመሪያ ድረስ ቢያንስ 1,500 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን ለቢቢሲ ተናግሯል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

    የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ብቻ 975 ሰዎች የሞት ቅጣት እደተፈጸመባቸው ማረጋገጡን ገልጿል።

    የኢራን ባለሥልጣናት መረጃዎችን ይፋ ስለማያደርጉ በትክክል የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ማወቅ አስቸጋሪ ነው።

    ይሁን እንጂ ቡድኑ የሰራው ግምገማ ሌላ ጉልህ የሆነ ዓመታዊ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም ሌሎች የኢራን የሞት ቅጣትን ከሚከታተሉ ቡድኖች መረጃ ጋር የተጣጣመ ነው ተብሏል።

    የኢራን መንግሥት ቀደም ሲል የሞት ቅጣትን የሚፈፀመው "በጣም ከባድ ወንጀሎች" በፈጸሙ ላይ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ የሚቀርብበትን ክስ ተከላክሏል።

    እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ማህሳ አሚኒ በእስር ቤት ከሞተች በኋላ በመላ አገሪቱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከመከሰታቸው በፊትም የሞት ቅጣት ቁጥር እየጨመረ ነበር ።

    የ22 ዓመቷ ኩርዲሽ ሴት ሂጃቧን "በአግባቡ አልለበሰችም" በሚል ክስ ነበር በቴህራን በሥነ ምግባር ፖሊስ ተይዛ የታሰረችው።

    በዚህም ምክንያት ባለሥልጣናት እአአ በ2022 ከነበረው 520 አካባቢ የሞት ቅጣት፣ በቀጣዩ ዓመት ወደ 832 ከፍ አድርገዋል ሲል የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ይገልጻል።

    በተቃዋሞ ወይም በስለላ በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የተወሰኑ የሞት ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ነገር ግን ከተገደሉት መካከል 99 በመቶ የሚሆኑት በነፍስ ማጥፋት ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል የተከሰሱ ናቸው።

    አክቲቪስቶች እንደሚሉት በኢራን የሚፈጸመው የሞት ቅጣት መጠን የሚጨምረው ገዥው አካል ስጋት ውስጥ ሲገባ ሲሆን ዓላማውም በሕዝቡ ውስጥ ፍርሃትን በመንዛት ተቃውሞን መከላከል ነው።