የተባበሩት መንግሥታት በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ስምንት ሰዎች በመሞታቸው ስጋት እንደገባው ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, UGC
የተባበሩት መንግሥታት የኢራን ልዩ ራፖርተር የሆኑት ማይ ሳቶ በተቃውሞ ሰልፍ ወቅት በተገደሉ “ስምንት ተቃዋሚዎች” ስጋት እንደገባቸው ገለፁ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበኩላቸው “እየተካሄዱ ያሉትን ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እና የሚወጡትን ዘገባዎች በስጋት ውስጥ ሆነን እየተከታተልን ነው” ብለዋል።
በኢራን እየተካሄደ የሚገኘው ሕዝባዊ ተቃውሞ አርብ ዕለትም ቀጥሎ ውሏል።
በኢራን የተለያዩ ከተሞች እና ጎደናዎች ኣለይ በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ስምንት ያህል ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተገልጿል።
የቆም አውራጃ ደህንነት ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት በነበረ ተቃውሞ ወቅት አንድ ሰው በተወረወረ “ቦንብ ፍንዳታ” ተመትቶ መሞቱን አስታውቋል።
ልዑል ቴዛ ፓህላቪ ባስተላለፉት የጽሑፍ መልዕክት ላይ “ይህ መልዕክቴ በተለየ በጥንካሬ ሌላ ዙር ብሔራዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለጀመሩት ለቴህራን ሕዝብ ነው” በማለት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
17 የሲቪል እና ፖለቲካ አክቲቪስቶች በበኩላቸው የሕግ አካላት “የኢራንን ሕዝብ ሕይወት እና ደህንነት መጠበቅ የሆነውን እውነተኛ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ” ጥሪ አቅርበዋል።
ኢራን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የሰዎች ሞት የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ ትገባለች በማለት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና “ሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት” ዛቻ በኢራን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው በማለት አውግዟል።


















