ባለፈው ሳምንት ከእስራኤል የአገርነት ዕውቅናን ያገኘችው ሶማሊላንድን በተመለከተ ኢትዮጵያ አስካሁን አቋሟን ሳታሳውቅ
ዝምታን መርጣለች።
ኢትዮጵያ የቅርብ ግንኙነት ካላት እና ከሁለት ዓመት በፊት የባሕር በር የማግኛ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመቻት የሶማሊላንድ
የዕውቅና ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሳይቀር መነጋገሪያ ሆኗል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላትን ተቃውሞም ሆነ ድጋፍን ሳትገልጽ ከመቆየቷ በተጨማሪ የመንግሥት መገናኛ
ብዙኃን ለዜናው ሽፋን ሳይሰጡ ቀናት ተቆጥረዋል።
የቢቢሲ የመገናኛ ብዙኃን መከታተያ ክፍል ቢቢሲ ሞኒተሪንግ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ የመንግሥት እና ለመንግሥት
ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጠዋል።
ቢቢሲ ሞኒተሪንግ እንደተከታተለው የመንግሥት ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ለመንግሥት ቅርብ የሆነው
ፋና እስራኤል የመጀመሪያ አገር በመሆን ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና ሽፋን አልሰጡትም።
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) ማክሰኞ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የነበረ
ቢሆንም ስለሶማሊላንድ ጉዳይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
የእስራኤልን ዕውቅና ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዙሪያቸው ላሉ አገራት መሪዎች እና የውጭ
ጉዳይ ሚኒስትሮች ስልክ በመደወል ድጋፋቸውን እንዲሰጧቸው እና የእስራኤልን እርምጃ እንዲያወግዙ ውይይት ማድረጋቸውን በገጻቸው ላይ
አመልክተዋል።
ባለሥልጣናቱ የሶማሊያ ዋነኛ ተጎራባች እና በአካባቢው ወሳኝ አገር ከሆነችው ኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ስለማድረጋቸው
አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ግብፅ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ኤርትራ የእስራኤልን እውቅና በይፋ የተቃወሙ ሀገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬንያ እና የኡጋንዳ መንግታት አቋመቸውን እስካሁን አላሳወቁም።
ነገር ግን እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅናን ከመስጠቷ ከቀናት በፊት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሼክ ሐሰን ሞሐሙድ
በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም. ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት በምላሹም ዕውቅና ለመስጠት
የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብታ በቱርክ አሸማጋይነት ስምምነት ተደርሷል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ቱርክ አንካራ ላይ የተፈራረሙት ስምምነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በፈረመችው ሰነድ ምክንያት
በአፍሪካ ቀንድ ተፈጥሮ የነበረውን የዲፕሎማሲ እና የደኅንነት ውጥረት ያረገበ ነው።
በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው አስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚደረስ የባሕር ጠረፍ ለኢትዮጵያ ያስገኛል የተባለው
ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ጉዳይም መቋጫው ዝምታ ሆኖ ቆይቷል።