ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች የዓለማችን መሪዎች ማዱሮ ስለመያዛቸው ምን አሉ?

ቬኒዙዌላ ላይ ድንገተኛ የኮማንዶ ጥቃት በመፈጸም አገሪቱ መሪ በአሜሪካ እጅ መግባታቸውን በተመለከተ ፕሬዝንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አስተማማኝ፣ ተገቢ እና ሕጋዊ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ቬንዙዌላን አሜሪካ ታስተዳድራለች” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል። ማዱሮ መያዛቸውን ተከትሎ የዓለማችን መሪዎች የተደበላለቀ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት መንግሥታት በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ስምንት ሰዎች በመሞታቸው ስጋት እንደገባው ገለፀ

    የተባበሩት መንግሥታት የኢራን ልዩ ራፖርተር የሆኑት ማይ ሳቶ በተቃውሞ ሰልፍ ወቅት በተገደሉ “ስምንት ተቃዋሚዎች” ስጋት እንደገባቸው ገለፁ።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ በበኩላቸው “እየተካሄዱ ያሉትን ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እና የሚወጡትን ዘገባዎች በስጋት ውስጥ ሆነን እየተከታተልን ነው” ብለዋል።

    በኢራን እየተካሄደ የሚገኘው ሕዝባዊ ተቃውሞ አርብ ዕለትም ቀጥሎ ውሏል።

    በኢራን የተለያዩ ከተሞች እና ጎደናዎች ኣለይ በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ስምንት ያህል ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተገልጿል።

    የቆም አውራጃ ደህንነት ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት በነበረ ተቃውሞ ወቅት አንድ ሰው በተወረወረ “ቦንብ ፍንዳታ” ተመትቶ መሞቱን አስታውቋል።

    ልዑል ቴዛ ፓህላቪ ባስተላለፉት የጽሑፍ መልዕክት ላይ “ይህ መልዕክቴ በተለየ በጥንካሬ ሌላ ዙር ብሔራዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለጀመሩት ለቴህራን ሕዝብ ነው” በማለት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

    17 የሲቪል እና ፖለቲካ አክቲቪስቶች በበኩላቸው የሕግ አካላት “የኢራንን ሕዝብ ሕይወት እና ደህንነት መጠበቅ የሆነውን እውነተኛ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

    ኢራን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የሰዎች ሞት የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ ትገባለች በማለት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና “ሌሎች የአሜሪካ ባለሥልጣናት” ዛቻ በኢራን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው በማለት አውግዟል።

  2. ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከሙስና ውዝግብ በኋላ የስለላ ኃላፊውን የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አድርገው ሾሙ

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የቀድሞ የፕሬዝዳንታዊ ፅ/ቤት ኃላፊያቸው በሙስና ውዝግብ ምክንያት ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩትን ክታእሎ ቡዳኖቭን ኃላፊ አድርገው ሾመዋል።

    ዜሌንስኪ ሹመቱን አስመልክተው በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “በዚህ ጊዜ ዩክሬን የደኅንነት ጉዳይ ላይ በእጅጉ ልታተኩር ይገባል” ብለዋል።

    የ39 ዓመቱ አዲሱ የፕሬዝዳንታዊ ፅ/ቤት ኃላፊ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ተደጋጋሚ የሩሲያ ጥቃት ያስተናገደውን የወታደራዊ መረጃ ደኅንነትን ይመሩ ነበር።

    ዜሌንስኪ የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ደኒስ ሽማይሃል በሌላ ሚኒስትር የመተካት ሀሳብ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

    በሙስና ስማቸው የተነሳው አንድሪይ ርማርክ ትልቅ የፖለቲካ ድጋፍ የነበራቸው እና ጦርነቱን ለመቋጨት ከአሜሪካ ጋር በተደረጉ ንግግሮች የዩክሬንን ልዑክ መርተዋል።

    የዩክሬን ፕሬዝዳንታዊ ፅ/ቤት በታሪክ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ያለው ነው።

  3. የኢራን መንግሥት ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር እርምጃ እወሰደ ነው

    እየተባባሰ ያለውን የኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ፖሊስ “በውጭ ወራሪዎች እና የአገር ውስጥ ቅጥረኛ ኃይሎች” ባላቸው እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

    የኢራን ፖሊስ ዋና አዛዥ አህመድ ሬዛ ራዳን በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በኩል በተላለፈ መግለጫ “የጠላቶች የብጥብጥ እና የመከፋፈል እንቅስቃሴ እየከሸፈ ነው” ብለዋል።

    የኢራን የፀጥታ እና የሕግ ተቋማት በተቃውሞዎች ውስጥ በሚሳተፉት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ ነው።

    ለቀናት በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ እስካሁን ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    የሰዎች ሞትን ሰበብ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግድያው የማይቆም ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ እንደምትገባ መግለጻቸው የኢራን ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል።

    ቀደም ሲል የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ውስጥ እጇን እንዳታስገባ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ በሰጡት ምላሽ ደግሞ አሁን ትራምፕ ለኢራናውያን ያሳዩት “ሐዘኔታ” አሜሪካ በታሪክ በኢራናውያን ላይ ከፈጸመችው ድርጊት ጋር የማይመሳሰል ነው በማለት አታጥለውታል።

    ለዚህም አሜሪካ በኢራን እና በሕዝቧ ላይ ፈጽማለች ያሏቸውን ነገሮች ታሪክን እያጣቀሱ በመዘርዘር “አሁን ግን ለኢራናውያን በማዘን ሰበብ” በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ነው ብለውታል።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም “ኢራናውያን ለጉዳያቸው መፍትሄ ለማግኘት ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን አይፈቅዱም” በማለት የትራምፕን አስተያየት ጣልቃ ገብነት ብለውታል።

    የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አማካሪ አሊ ላሪጃኒ ቀደም ሲል በሰጡት አስተያየት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ከሚያመጣው መፍትሄ ይልቅ መካከለኛው ምሥራቅን የሚያናጋ ነው በማለት አስጠንቅቀዋል።

  4. ኢራን በውስጥ ጉዳይዋ አሜሪካ ጣልቃ እንዳትገባ አስጠነቀቀች

    ሳምንት ሊሞላው በተቃረበው ኢራን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የሰዎች ሞት የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ ትገባለች በማለት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸው ከኢራን መንግሥት የማስጠንቀቂያ ምላሽ ተስጥቶታል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከፍተኛ አማካሪ አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ከሞከረች በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ይከሰታል በማለት አስጠንቅቀዋል።

    እየተባባሰ ባለ የኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት በተለያዩ የኢራን ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ ምክንያት አስከ ሐሙስ ድረስ ቢያንስ ስድስት ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    ይህንን ተከትሎ ትራምፕ በትሩዝ የሶሻል ሚዲያ ገጽ ላይ "የኢራን መሪዎች እንደልማዳቸው ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በጥይት የሚገድሉ ከሆነ አሜሪካ ልትታደጋቸው ጣልቃ ትገባለች" በማለት በመጻፋቸው ነው ኢራንን ያስቆጡት።

    የኢራን መሪ ዋነኛ አማካሪ የሆኑት አሊ ላሪጃኒ ለዚህ የትራምፕ ዛቻ ወዲያውኑ በሰጡት ምላሽ ማንኛውም ዓይነት የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ቀጣናውን ያናጋል ብለዋል።

    "በዚህ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት ማለት አጠቃላይ ቀጣናውን ማናጋት እና የአሜሪካ ጥቅሞችን ማውደም ማለት መሆኑን ትራምፕ ሊያውቁ ይገባል" በማለት ላሪጃኒ በጽሁፍ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ትራምፕ በመልዕክታቸው ኢራናውያን ተቃዋሚዎችን ለማዳን አሜሪካ በኢራን ባለሥልጣናት ላይ ምን ዓይነት እርምጃ ልትወስድ እደምትችል አልገለጹም።

  5. ኢራን ተቃዋሚ ሰልፈኞችን መግደል የምትቀጥል ከሆነ ጣልቃ እንገባለን - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ኢራን ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን የምትገድል ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ በመግባት እንደምታድናቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

    በኢራን የተለያዩ ከተሞች የኑሮ ውድነትን እና የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆሉን በመቃወም በርካታ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።

    በዚህም ሳቢያ ትራምፕም ኢራን ተቃዋሚዎችን በጭካኔ በጥይት የምትገድል ከሆነ "እርምጃ ለውሰደ ዝግጁ ነን" በማለት በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት ከሦስት ዓመት ወዲህ በኢራን ውስጥ ያጋጠመ ነው በተባለው የአሁኑ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የሚያመለክቱ ዜናዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

    በተቃዋሚዎች እና በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ባለፈው ዕሁድ ባለሱቆች በፍጥነት እየጨመረ ያለውን የዋጋ ንረት እና መንግሥት እያሽቆለቆለ ያለውን የአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ ለመታደግ ምንም አላደረገም በሚል ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከኢራን ጋር ከተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት ከወጡ በኋላ ተነስቶላት የነበረውን ማዕቀብን በአውሮፓውያኑ 2018 መልሰው ስለጣሉባት የኢራን ምጣኔ ሀብት ችግር ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

    በኢራን የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚካሄደው ተቃውሞ እየተባባሰ የቀጠለ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ የሰው ሕይወት እያለፈ መሆኑ ተዘግቧል።

  6. በጋምቢያ የባሕር ዳርቻ የስደተኞች ጀልባ ሰጥማ ሰባቱ ሲሞቱ በርካቶች መጥፋታቸው ተነገረ

    ወደ 200 የሚጠጉ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በጋምቢያ የባሕር ዳርቻ ላይ ሰጥማ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ደግሞ የደረሱበት መጥፋቱን ባለሥልጣናት ገለጹ።

    ጀልባዋ ረቡዕ እኩለ ሌሊት በጂናክ መንደር አቅራቢያ ተገልብጣ በኋላ ላይ “በአሸዋ ክምችት ላይ ተተክላ ተገኝታለች” ሲል የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

    እስካሁን ዘጠና ስድስት ሰዎችን መታደግ የተቻለ ሲሆን፣ ሌሎቹን ለማግኘት ፍለጋው ቀጥሏል። ጀልባዋ ወደ ስፔን ካናሪ ደሴቶች እያመራች ነበር።

    ወደ አውሮፓ ለመድረስ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚደረገው አደገኛ ጉዞ በአፍሪካ ስደተኞች የተለመደ ሆኗል።

    በ2024 ወደ 47 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ካናሪ ደሴቶች ደርሰዋል። የስፔኑ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ካሚናንዶ ፍሮንቴራስ ከ9,000 በላይ ስደተኞች ሞተዋል ሲል ግምቱን አስቀምጧል።

    ረቡዕ ዕለት ከደረሰው አደጋ በኋላ የጋምቢያ የባሕር ኃይል በርካታ መርከቦችን እና ለመርዳት የመጡ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎችን ያካተተ የፍለጋ እና የማዳን ዘመቻ ጀምሯል ሲል የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናግሯል።

    ባለሥልጣናት እንዳሉት ብዙዎቹ ተጎጂዎች የጋምቢያ ዜጎች አይደሉም፤ ማንነታቸውም እየተጣራ ይገኛል።

    ከሰመጠት መካከል የሰባት ሰዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆን፣ ከተረፉት ውስጥ አስሩ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተነግሯል።

    በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ጥገኝነት ፈላጊዎች ወደ ስፔን ካናሪ ደሴቶች በመሻገር ወደ አውሮፓ ለመግባት ጋምቢያን እንደመነሻ እየተጠቀሙባት ይገኛል።

    የአውሮፓ ኅብረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሰሜን አፍሪካ አገራት ጋር መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመቀነስ ስምምነት ላይ ደርሷል። ይህ ስምምነት ብዙ ስደተኞች ረጅሙን እና አደገኛ የሆነውን የአትላንቲክ ውቅያኖስ መንገድ እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል ተብሏል።

  7. የጃፓኗ ጠ/ሚኒስትር በፓርላማው ውስጥ በቂ የሴቶች መጸዳጃ ቤት እንዲኖር የተጀመረውን ዘመቻ ተቀላቀሉ

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኢ ታካይቺ በፓርላማው ውስጥ ተጨማሪ የሴቶች ንጽሕና ቤት እንዲሠራ ፊርማ ያሰባሰቡ 60 የምክር ቤት አባላትን ተቀላቀሉ።

    የፓርላማ አባላቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ እያደገ የመጣውን የሴቶች ውክልና ተከትሎ በፓርላማው ሕንፃ ውስጥ ተጨማሪ የሴቶች መጸዳጃ ቤቶች እንዲኖር ጠይቀዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2024 ጥቅምት ወር 465 መቀመጫዎች ላለው የታችኛው ምክር ቤት 73 ሴቶች ተመርጠዋል፤ ይህም ቀደም ሲል ከነበረው 54 ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ የሕግ አውጪ ያሱኮ ኮሚያማ እንደተናገሩት "ብዙውን ጊዜ አጠቃላይ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በመጸዳጃ ቤቱ ፊት ለፊት ረጅም ወረፋ ይታያል" ብለዋል።

    እኚህ የምክር ቤቱ አባል ሌላ ሴት የፓርላማ አባልን በመጥቀስ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ወደ መጸዳጃ ቤት መሄድ ላይ "ተስፋ መቁረጧን" ተናግረዋል።

    በመሰብሰቢያ አዳራሹ አቅራቢያ ሁለት ክፍሎች ያሉት አንድ የሴቶች መጸዳጃ ቤት ይገኛል። አጠቃላይ የምክር ቤቱ ሕንፃ 22 ክፍሎች ያሉት ዘጠኝ የሴቶች መጸዳጃ ቤቶች አሉት።

    እንደ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከሆነ በምክር ቤቱ 67 ክፍሎች ያሏቸው 12 የወንዶች መጸዳጃዎች ይገኛሉ።

    አሁን ያለው ሁኔታ ሴት ሠራተኞች እና ጎብኚዎች ተመሳሳይ መጸዳጃ ቤት ስለሚጠቀሙ "ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው" ያሉት ደግሞ የተቃዋሚው ኮንስቲትዩሽናል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል የሆኑት ኮሚያማ ናቸው።

    "ወደፊት ሴቶች ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የፓርላማ መቀመጫዎች የሚይዙበትን ቀን ለማሰብ ድምፄን እያሰማሁ መጠበቅ እፈልጋለሁ" በማለት በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    የጃፓን የፓርላማ ሕንፃ የተገነባው እአአ በ1936 ሲሆን ሴቶች የመምረጥ መብት የተፈቀደላቸው ደግሞ ከአስር ዓመት በኋላ እአአ በ1945 ነው።

    የመጀመሪያዎቹ ሴቶች ተመርጠው ወደ ምክር ቤቱ የገቡት እአአ በ1946 ነው።

  8. በኢራን በተቃዋሚዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በቀጠለው ግጭት ተጨማሪ ሰዎች ተገደሉ

    በኢራን በኑሮ ውድነት መጨመር እና የገንዘብ የመገዛት አቅም መውደቅ የተነሳ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ እና አለመረጋጋት ለአምስተኛው ቀን ቀጥሎ ተጨማሪ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ።

    የፋርስ የዜና ወኪል እና የሰብዓዊ መብቶች ቡድን የሆነው ሄንጋው በደቡብ ምዕራብ ኢራን በምትገኘው ሎርዴጋን ከተማ በተቃዋሚዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። በአዝና ሦስት ተጨማሪ ሰዎች በኩህዳሽት ደግሞ አንድ ሰው መገደሉን ፋርስ ዘግቧል።

    በሐሙስ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለጠፉ ቪዲዮዎች ላይ በተቃዋሚዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተደረጉ ግጭቶች ወቅት መኪኖች በእሳት እንደተቃጠሉ አሳይተዋል።

    ብዙ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን አገዛዝ ከመንበሩ እንዲወርድ ጥሪ አቅርበዋል። አንዳንዶች አስተዳደሩ ወደ ንጉሣዊው አገዛዝ እንዲመለስ ጠይቀዋል።

    በገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያት የተጀመረው ተቃውሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለአምስተኛ ቀን መቀጠሉን ተሰምቷል።

    በቢቢሲ ፐርሽያ የተረጋገጡ ቪዲዮዎች ሐሙስ ዕለት ዋና ከተማዋ ቴህራን ጨምሮ በሎርደጋን እና ማርቭዳሽት ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሄንጋው በሎርጋን የተገደሉት ሁለቱ ተቃዋሚዎች መሆናቸውን ጠቅሶ አህመድ ጃሊል እና ሳጃድ ቫላማኔሽ እንደሚባሉ ገልጿል።

    ቢቢሲ ፐርሽያ የሟቾቹን ሞት ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

    የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ከኢራን አብዮታዊ ጥበቃ (አይአርጂሲ) ጋር ግንኙነት ያለው የጸጥታ ኃይል አባል ረቡዕ ምሽት በምዕራባዊ ሎሬስታን ግዛት በኩህዳሽት ከተማ ከተቃዋሚዎች ጋር በተፈጠረው ግጭት መገደሉን ዘግበዋል።

    ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ ባይችልም ተቃዋሚዎች ግለሰቡ ተቃዋሚ እንደሆነ እና በጸጥታ ኃይሎች በጥይት እንደተገደለ ተናግረዋል።

    በአካባቢው በድንጋይ ጥቃት የደረሰባቸው 13 የፖሊስ መኮንኖች እና የባሲጅ አባላት ቆስለዋል ሲል የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።

    ባለሥልጣናት ረብሻውን ለማፈን በሚያደርጉት ጥረት ዕረፍት ከታወጀ በኋላ ረቡዕ ዕለት ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የመንግሥት ተቋማት በመላ አገሪቱ ተዘግተዋል።

    ብዙዎች እረፍት የተሰጠው ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ቢሉም መንግሥት ግን በቀዝቃዛው የአየር ሁኔታ ምክንያት የሚባክንን ኃይል ለመቆጠብ ተብሎ መሰጠጡ ተነግሯል።

    ተቃውሞው የጀመረው በቴህራን ሲሆን የኢራን ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ያለው ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ በመውደቁ በተበሳጩ ነጋዴዎች የተጀመረ ነው።

    ማክሰኞ ዕለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተቃውሞ የተሳተፉ ሲሆን ወደ በርካታ ከተሞችም ተሰራጭተዋል። ብዙዎችም በአገሪቱ መንግሥት ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

  9. የሶማሊያ መንግሥት 30 የሚደርሱ የአል ሻባብ አባላት መገደላቸውን አስታወቀ

    የሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ከዓለም አቀፍ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በፈጸሙት ጥቃት ወደ 30 የሚጠጉ የአል ሻብብ ታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ጃባድ ጎዳኔ በተባለ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው የአየር ጥቃት 29 የአል ሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና በተጨማሪም ለሽብር ጥቃት ሊውሉ የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች መውደማቸውን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ሚኒስቴሩ በኤክስ ገጹ ላይ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው በቡድኑ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ማንነታቸውን ያልገለጻቸው ዓለም አቀፍ አጋሮች መሳተፋቸውን ገልጾ፤ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋናውን ገልጿል።

    በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን ለመዋጋት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የተለያዩ አገራት ወታደሮች በአገሪቱ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ደግሞ የአየር ጥቃትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፍን ይሰጣሉ።

    በተለይ አሜሪካ በቡድኑ ይዞታዎች፣ መሪዎች እና ታጣቂዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም ትታወቃለች።

    አል ሻብብ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያለውን የሶማሊያ መንግሥትን በመጣል በጥብቅ የሸሪዓ ሕግ የሚመራ አስተዳደር ለመመሥረት ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ የሽምቅ ጥቃት እያካሄደ ይገኛል።

    ከኣለም አቀፉ ቡድን አል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አል ሻብብ በዓለም ላይ ከሚጠቀሱ የሽብር ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።

  10. የጋቦን ብሔራዊ ቡድን እና ኦባምያንግ በመንግሥታቸው ታገዱ

    የጋቦን መንግሥት ከአፍሪካ ዋንጫ በጊዜ የተሰናበተውን ብሔራዊ ቡድን፣ አጥቂውን ፒየር-ኤሜሪክ ኦባምያንግን እና አሰልጣኙን ቴሪ ሙዩማ ማገዱን አስታውቋል።

    የስፖርት ሚኒስትሩ ሲምፕሊስ-ዴዜሬ ማምቡላ ብሔራዊ ቡድኑ በአይቮሪ ኮስት 3 ለ 2 ከተሸነፈ በኋላ እርምጃዎቹ መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።

    ጋቦን ቀደም ሲል በካሜሩን እና በሞዛምቢክ በመሸነፏ ከሞሮኮው አፍሪካ ዋንጫ ከምድቧ የመጨረሻ ግርጌ ላይ ሆና ማጠናቀቋን ማምቡላ "አሳፋሪ" ሲሉ ገልጸውታል።

    “ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያሳየውን አሳፋሪ ብቃት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግሥት የአሰልጣኞች ቡድኑን ለማባረር፣ ብሔራዊ ቡድኑን እስከሚቀጥለው ጊዜ ድረስ ለማገድ እና ብሩኖ ኢኩዌሌ ማንጋ እና ፒየር-ኤሜሪክ ኦባምያንግን ለማግለል ወስኗል" ብለዋል።

    ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ከውድድሩ መሰናበቷን ያረጋገጠቸው ጋቦን በማራኬሽ በተደረገው ጨዋታ ሁለት ጎሎችን አይቮሪ ኮስት ላይ ብታስቆጥርም ከሽንፈት አላመለጠችም።

    የቀድሞው የአርሴናል እና የቼልሲ አጥቂ ኦባምያንግ በጭንቅላት ጉዳት ምክንያት ሕክምና ለማግኘት ወደ ማርሴይ በመመለሱ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ አልተሳተፈም።

    "የቡድኑ ችግሮች ከእኔ ከአንዱ ግለሰብ በጣም የበለጡ ናቸው ብዬ አስባለሁ" ብሏል።

    ሙዩማ ብሔራዊ ቡድኑን ከሁለት ዓመታት ትንሽ ለሚልቅ ጊዜ መርቷል።

    የአፍሪካ መንግሥታት መጥፎ ውጤቶችን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኖችን ማፍረሳቸው የተለመደ ቢሆንም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዙሪያ ፊፋ ጥብቅ አቋም ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ብዙ ጊዜ ሲከሰት አልታየም።

  11. ሶማሊላንድ ፍልስጤማውያንን ልታሰፍር ነው መባሏን አስተባበለች

    ሶማሊላንድ ከአስራኤል የአገርነት ዕውቅናን ያገኘችው በምላሹ ፍልስጤማውያንን ለማስፈር እና ለአስራኤል ወታደራዊ ሰፈር ለመስጠት ተስማምታ ነው በማለት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መናገራቸውን ውድቅ አደረገች።

    የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከእስራኤል ጋር የሚኖረው ግንኙነት ዓለም አቀፍ ሕግን እና የሁለቱን አገራት ሉዓላዊነት ያከበረ ፍጹም ዲፕሎማሲያዊ ነው በማለት የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድን ክስ አጣጥሎታል።

    የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሶማሊላንድ የእስራኤልን ዕውቅና ለማግኘት ፍልስጤማውያንን ለማስፈር፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ዳርቻ እስራኤል ወታደራዊ ሰፈር እንድታቋቁም እና በአብርሃም ስምምነት ውስጥ ለመሳተፍ ስለተስማማች መሆኑን የደኅንነት መረጃ እንዳላቸው ለአልጀዚራ ተናግረው ነበር።

    የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሰጠው ምላሽ የፕሬዝዳንቱን ክስ “መሠረት ቢስ” በማለት፤ ዓላማው “ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማሳሳት እና የሶማሊላንድን ዲፕሎማሲያዊ ውጤትን ለማጣጣል ነው” በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል።

    አክሎም ሶማሊላንድ ለቀጣናው መረጋጋት እና ለዓለም አቀፍ ሰላማዊ ትብብር ቁርጠኛ ሆና ትቀጥላለች ብሏል።

    ሶማሊላንድ ከእስራኤል የመጀመሪያዋን የነጻ አገርነት ዕውቅናን ባለፈው ሳምንት ካገኘች በኋላ የሶማሊያ መንግሥት ጠንካራ ተቃውሞ እያሰማ ሲሆን፣ ጉዳዩንም ወደ ተባበሩት መንግሥታት በመውሰድ ዕውቅናው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

  12. ቼልሲ አሠልጣኙን አሰናበተ

    የቼልሲ አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ከቡድናቸው ጋር የዓለም የክለቦች ዋንጫን ካሸነፉ ከስድስት ወራት በኋላ ተሰናበቱ።

    የ45 ዓመቱ ማሬስካ ከአሠልጣኝነታቸው የተነሱት ቼልሲ በፕሪሚየር ሊጉ ሰንጠረዥ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እያለ ነው።

    የምዕራብ ለንደኑ ክለብ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት የክለቡ ከፍተኛ የቦርድ አመራር አባላት ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ነው።

    በዚህም መሠረት የፊታችን እሁድ ቼልሲ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ቡድኑን እንደማይመሩ ተረጋግጧል። ክለቡ የእርሳቸውን ምትክ በማፈላለግ ላይ መሆኑም ተሰምቷል።

    ማሬስካ ካለፉት ሰባት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በዚህም ከደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ቆይቷል።

    ጣልያናዊው ማርሴካ በበኩላቸው በመጪው ክረምት የፔፕ ጋርዲዮላ ተተኪ በመሆን ወደ ኢትሃድ እንደሚያመሩ ተገምቷል።

  13. በስዊትዘርላንድ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመዝናኛ ስፍራ በደረሰ የእሳት አደጋ በርካቶች ሞቱ

    በስዊትዘርላንድ በመዝናኛ ስፍራ በደረሰ የእሳት አደጋ በርካቶች ሲሞቱ ከ100 በላይ ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።

    በደቡባዊ ስዊትዘርላንድ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በተነሳ እሳት በርካቶች እንደሞቱ ከመገለጹ ውጪ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደሆኑ እንደማይታወቅ ተገልጿል።

    የስዊትዘርላንድ ፖሊስ ሐሙስ ማለዳ በሰጠው መግለጫ የሟቾችን ቁጥር ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

    የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስዊስ ፖሊስን በመጥቀስ 40 ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል።

    ጉዳት ከደረሰባቸው 100 ያህል ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በእሳት መቃጠላቸውን የስዊስ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

    ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ሲወሰዱ፤ አስር ሂሊኮፕተሮች፣ 40 አምቡላንሶች እና 150 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መሰማራታቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    የሟቾቹን ማንነት ለመለየት እና በፍጥነት ለቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸውን ለማስረከብ ጥረት እየተደረገ ነውም ተብሏል።

    በስዊትዘርላንድ የጣሊያን አምባሳደር የሞቱትን ሰዎች ማንነት ለመለየት ሳምንታት ይወስዳል ብለዋል።

    ከሞቱት መካከል የተለያዩ አገራት ዜጎች እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን፣ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ቢያንስ ሁለቱ ፈረንሳያዊን ናቸው ብለዋል።

    የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማርኮን ለስዊትዘርላንድ “የፈረንሳይ አጋርነት እና የወንድማማችነት ድጋፍ አይለያችሁም” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

  14. አቶ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

    የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።

    የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ-ሽብር እና ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም የቀረቡት አቶ ታዬ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል አንዱ እንዲሻሻል ወስኗል።

    ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው በአቶ ታዬ ላይ ዐቃቤ ሕግ በመሠረታቸው ሦስት ተጨማሪ ክሶች ላይ በቀረበው የክስ መቃወሚያ እና የዋስትና ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ነበር።

    አቶ ታዬ ረቡዕ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም. በካቴና ታስሬ ችሎት አልቀርብም ብለው በመቃወማቸው የተነሳ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊያቀርባቸው እንዳልቻለ ተናግሮ ነበር።

    በዛሬው ዕለት እጃቸው በካቴና ታስሮ ችሎት የቀረቡት አቶ ታዬ፣ ከዚህ በፊት ያለ ካቴና እንዲቀርቡ በቃል ትዕዛዝ ተሰጥቶላቸው እንደበር በመግለጽ ያ ውሳኔው አለመከበሩን ተናግረዋል።

    ነገር ግን የችሎቱ ትዕዛዝ በጽሑፍ በክስ መዝገቡ ላይ ባለመካተቱ የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ተፈጻሚ ማድረግ እንዳልቻሉ ተነግሯል።

    ችሎቱ በሐሙስ ውሎው አቶ ታዬ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አንዱ ክስ እንዲሻሻል ወስኗል።

    ተከሳሹ እጃቸው በካቴና ታስሮ ችሎት ላይ ላለመቅረብ የወሰኑት አለርጂ አለብኝ በማለት ነበር።

    አቶ ታዬ ከዚህ ቀደም ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ሲባሉ የጦር መሣሪያ ሕግን በመተላለፍ ክስ ግን ጥፋተኛ ተብለው የሰባት ዓመት ከሁለት ወር እስር ተፈርዶባቸዋል።

    ችሎቱ የአቶ ታዬን መዝገብ ለማየት ለጥር 13/2018 ዓ.ም. ቀጣይ ቀጠሮ ሰጥቷል።

  15. 600 ኪሜ ከመኪና ሥር ተደብቆ አዲስ አበባ የገባው ታዳጊ እና እናቱ

    የ10 ዓመቱ ታዳጊ ገመቹ ከደምቢዶሎ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ የሕዝብ መኪና ማመላለሻ ስር በመደበቅ ከ600 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ሆለታ ሲደርስ ባሰማው ጩኸት ምክንያት መገኘት ችሏል።

    ታዳጊው መኪና ስር በመደበቅ 600 ኪሎ ሜትሮች ያህል በመጓዝ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

    የታዳጊው እናት የሆኑት ወ/ሮ ማርታ ታደሰ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጠፍቶ አዲስ አበባ ስለገባው ልጃቸው ተናግረዋል።

    ቄለም ወለጋ ተወልደው ያደጉት ማርታ ታደሰ የሁለት ልጆች እናት ናቸው።

    ባለቤታቸው ሁለተኛ ልጃቸውን ነፍሰጡር እያሉ በመሞታቸው ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

    “ለስምንት ዓመት ያህል ደምቢዶሎ ነው የኖርኩት። በየሰዉ ቤት እየሠራሁ እና ልብስ እያጠብኩ ነው ልጆቼን የማሳድገው። ልጆቼ እንዳይራቡ ደፋ ቀና እላለሁ፤ የምጠለልበት የራሴ ቤት ወይንም ከዕለት ጉርስ የሚያልፍ ነገር የለኝም” ይላሉ።

    ሕይወት በደምቢዶሎ ሲከብዳቸው የቀን ሥራ ለመሥራት ወደ አንፊሎ ሄዱ።

    እዚያ ከደረሱ በኋላ ግን የመጀመሪያ ልጃቸው ነገር ፋታ የሚነሳቸው ሆነ። ስለዚህ ወደ ደምቢዶሎ መልሰው ላኩት።

    ልጃቸው ደምቢዶሎ ሲልኩት ደስተኛ ያልነበረ ሲሆን “የማታይኝ አገር እሄዳለሁ” ይላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

    የ10 ዓመቱ ገመቹ በደምቢዶሎ ጎዳናዎች ላይ ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በልጅ አእምሮው አንድ ቀን ከተማዋን ለቅቆ ለመሄድ ወሰነ።

    እናትየው ልጃቸው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ፍላጎት አንደነበረው ይነግራቸው እንደነበር በመግለጽ አዲስ አበባ እንደደረሰም በስልክ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    እናት ልጃቸው አዲስ አበባ ለመድረስ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ አንደነበር ሲነገራቸው “ፈጣሪ አተረፈልኝ አንጂ ምን እላለሁ። . . . ወደፊት ጥሩ ቦታ እንደሚደርስ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

    ገመቹ ለእናቱ ደውሎ ‘አትጨነቂ አዲስ አበባ ደርሻለሁ፤ የምትፈልጊኝ ከሆነ ፖሊስ ጣቢያ ታገኚኛለሽ’ እንዳላቸው ተናግረዋል።

    አዲስ አበባ ውስጥ እናቱን እና ታዳጊውን ለመደገፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ድጋፍ እየተሰበሰበ መሆኑ እየተነገረ ነው።

  16. የአውሮፓውያኑ አዲሱ ዓመት አከባበር በመላው ዓለም

    አዲሱ የአውሮፓውያኑ ዓመት 2026 በመላው ዓለም በድምቀት ተከብሯል።

    ከኬንያ መዲና ናይሮቢ እስከ አሜሪካዋ ግዙፏ ከተማ ኒው ዮርክ እንዲሁም ለንደን እና ሲድኒ አዲሱን ዓመት እኩል ለሊት ጠብቀው በድምቀት ተቀብለዋል።

    2026ን ቀድመው ከተቀበሉ ክፍለ ዓለማት መካከል የፓሲፊክ ውቅያኖስ ሀገራት እንዲሁም ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ ይጠቀሳሉ።

    በለንደን ቢግ ቤን የተሰኘው ታዋቂ ደወል አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ሲቃጭል ተሰምቷል። በቴምስ ወንዝ ዙሪያ ደግሞ 12 ሺህ ገደማ ርችቶች ተተኩሰዋል።

  17. አል ሻባብ ሶማሊያውያን በእስራኤል ላይ ጠመንጃ እንዲያነሱ ጥሪ አቀረበ

    ቴል-አቪቭ ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የነጻ አገርነት ዕውቅና በመቃወም እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል ሻብብ ሶማሊያውያን በእስራኤል ላይ ጠመንጃ እንዲያነሱ ጥሪ አቀረበ።

    የቡድኑ ቃል አቀባይ ባስተላለፈው በቪዲዮ በተቀረጸ መልዕክት ሶማሊያውያን አገራቸውን ከእስራኤል ለመከላከል ታጥቀው እንዲነሱ ጥሪ አስተላልፏል።

    የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሼክ አሊ ሞሐሙድ ራጌ ወይም አሊ ዳሂር ባቀረበው ጥሪ የሶማሊላንድ መሪዎችን "ከሃዲ" በማለት በሶማሊያ ሕዝብ ላይ "ቅኝ ግዛትን ጋብዘዋል" ሲል ከስሷል።

    "ማንኛውም የሠለጠነ እና መሳሪያ ያለው በተለይ ወጣቶች ካሉበት ቦታ ሆነው በእስራኤል ላይ ጦርነት መጀመር አለባቸው" በማለት አይሁዳውያንን ዒላማ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

    መሳሪያም ሆነ ሥልጠና ለሌላቸው ደግሞ ቡድኑ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ እንዲቀላቀሉት ጥሪውን አስተላልፏል።

    በበርካታ አገራት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከዓለም አቀፉ ቡድን አል ቃኢዳ ጋር ትስስር እንዳለው የሚነገርለት አል ሻባብ ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ የሶማሊያ እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ የሽብር ጥቃትን በመፈጸም ይታወቃል።

    የሶማሊያ መንግሥትን ለመጣል የሚዋጋው ቡድኑ ከአገሩ መንግሥት ባሻገር አሜሪካንን ጨምሮ በአጎራባች አገራት የሽብር ቡድን ተብሎ እየታደነ ያለ ነው።

    እስራኤል የሰጠችውን ዕውቅና የተቃወመው የአል ሻባብ ቃል አቀባይ የሶማሊላንድ ሕዝብ እስራኤል የሰጠችውን ዕውቅና እንዲቃወመውም ጥሪ አቅርቧል።

    ነገር ግን ከ30 ዓመታት በላይ ከሶማሊያ መንግሥት እራሷን ነጥላ ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ እስራኤል ባለፈው ሳምንት የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅናን መስጠቷን ተከትሎ በሀርጌሳ በርካታ ሕዝብ አደባባይ በመውጣት ደስታውን ሲገልጽ ነበር።

    በሌላ በኩል ደግሞ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ዕውቅናውን አጥብቆ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት መውሰዱ ይታወቃል።

    እንዲሁም ሶማሊያውያን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ባካሄዷቸው ሰልፎች የሶማሊላንድን የአገርነት ዕውቅና ተቃውመውታል።

  18. ህወሓት "የተፈናቃዮች ሞትን" በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት አጣሪ ቡድን እንዲያሰማራ ጠየቀ

    የአፍሪካ ኅብረት በትግራይ ጦርነት “ወቅት ከነበረው በበለጠ” ሁኔታ በታህሳስ ወር የተመዘገበውን “የተፈናቃዮች ሞት”፤ “የሚሰንድ የሐቅ አፈላላጊ ተልዕኮ” እንዲያሰማራ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠየቀ።

    በክልሉ በሚገኙ ተፈናቃዎች ላይ እየተከሰተ ያለው “የጀምላ ረሀብ” የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚጥስ እንደሆነም ገልጿል።

    ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሓት ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በጻፈው ደብዳቤ፤ በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

    በክልሉ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸው የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጠቀሰው ህወሓት፤ ክስተቱ የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመውን "የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚጥስ ነው" ሲል ከስሷል።

    ድርጅቱ በመጠለያ ካምፖቹ ውስጥ ያለው ሁኔታ በዚህ ወር ውስጥ መባባሱን እና ያለው ሁኔታ በትግራይ ውስጥ ጦርነቱ ከጀመረበት ወቅት ከነበረው የከፋ ሆኖ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል።

    ሕወሓት በደብዳቤው፤ የአፍሪካ ህብረት በታህሳስ ወር የታየውን የተፈናቃዮች ሞት “መባባስ፣ የአምስት ዓመት የሞት ቁጥር እና ስልታዊ የእርዳታ ዕቀባን የሚሰነድ የሐቅ አፈላላጊ ተልዕኮ” እንዲያሰማራ ጠይቋል። ተልዕኮው “በ60 ቀናት ውስጥ ሪፖርት” እንዲያቀርብም አሳስቧል።

    ሕጻፍ በሚባለው የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የተከሰተው የምግብ ችግርን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ በሰጠው መግለጫ እርዳታ ምግብ አቅርቦት እንዳልተቋረጠ መግለጹ ይታወሳል።

    በተጨማሪም የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተ/ማሪያም ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ህወሓት የእርዳታ አቅርቦትን እንደሚያደናቅፍ እና ለራሱ ጥቅም እንደሚያውል በመጥቀስ ከስሰዋል።

    ነገር ግን ህወሓት ለተፈናቃዮች የእርዳታ አቅርቦት ያለመቆራረጥ እየቀረበ ነው በማለት ያቀረበውን መረጃ ውድቅ አድርጎ፤ የፌዴራል መንግሥቱን እርዳታ በማደናቀፍ በአጸፋው ወንጅሏል።

    ህወሓት በደብዳቤው፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎችም አጋሮች ለተፈናቃዮች አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲፈቀድ እንዲጠይቁ እና በተከሰቱ የሰዎች ኅልፈት ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ በመጠየቅ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል።

  19. ዞህራን ማምዳኒ የኒው ዮርክ ከንቲባ ሆኖ በቁርዓን ቃለ መሃላ ፈጸመ

    አዲሱ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ በቁርዓን ቃለ-መሐል ፈፅሟል።

    ማምዳኒ በእስልምና ቅዱስ መፅሐፍ ቃለ-መሐላ የፈፀመ የመጀመሪያው የኒው ዮርክ ከንቲባ ሆኗል።

    የ34 ዓመቱ ዲሞክራት ከከተማ አስተዳደሩ ሕንፃ አቅራቢ በሚገኝ የባቡር ጣቢያ ውስጥ ነው እኩለ ለሊት እንዳለፈ ቃለ-መሐላ ፈፅሞ በይፋ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆነው።

    ማምዳኒ ከዚህ ቀደም መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ቃለ-መሐላ ከፈፀሙ ከንቲባዎች በተለየ ቁርዓንን በመጠቀም ቀዳሚው ሲሆን አልፎም የመጀመሪያው ደቡብ እስያዊ እና አፍሪካ የተወለደ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ይሆናል።

    አወዛጋቢው ሶሻል ዲሞክራት የግዙፏ ኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ለመሆን ዕጩ ሆኖ ሲቀርብ በመላው ሀገሪቱ መነጋጋሪያ ሆኖ ነበር።

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ማምዳኒ ዕጩ ሳለ መራጮች ድምፃቸውን እንዳይሰጡት በይፋ ቢጠይቁም ከተመረጠ በኋላ ወደ ዋይት ሐውስ ጠርተው እንዳናገሩት ይታወሳል።

  20. ኤርትራን ጨምሮ አሜሪካ የጣለችው የጉዞ ዕገዳ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል

    አሜሪካ ወደ አርባ የሚጠጉ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በሌሎችም ላይ ያሳለፈችው ሙሉ የቪዛ እና የጉዞ ዕገዳ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

    የአሜሪካ መንግሥት ከወራት በፊት ኤርትራን እና ሶማሊያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ዕገዳ የጣለው በአገራቱ ውስጥ ባለ ደካማ የዜጎች ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ እንዲሁም በርካቶች አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ለረጅም ጊዜ በመቆየት እና እዚያው በመቅረታች ነው።

    ይህ እርምጃ የአሜሪካንን ደኅንነት ለመጠበቅ መሆኑን የገለጸው ዋይት ሐውስ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት ወደ 40 የሚጠጉት ላይ እገዳ ተጥሏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይህ በመላው ዓለም በሚገኙ አገራት ላይ የተጣለው የቪዛ እና የጉዞ ዕገዳ አገራቱ አሳማኝ መሻሻል እስኪያሳዩ ድረስ በሥራ ላይ ይቆያል።

    አንዳንድ የአፍሪካ አገራት የአሜሪካ ውሳኔን በመቃወም ወደ አገራቸው በሚመጡ የአሜሪካ ዜጎች ላይ ተመሳሳይ ዕገዳን መጣላቸውን አሳውቀዋል።

    የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የሆኑት ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ አሜሪካዊያን ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የጉዞ ዕገዳ በመጣል የአፀፋ ምላሽ ሰጥተዋል።